የሰማያዊ እና ኦህዴህ ሊቃነ-መናብርት ነገ ችሎት ይቀርባሉ

10422441_744706228944022_7803105229502393540_nህዳር 27 እና 28/2007 ዓ.ም በ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ተዘጋጅቶ በነበረው የአዳር ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ የቅስቀሳ በራሪ ወረቅት ሲበትን ለእስር የተዳረገው የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሲሳይ ዘርፉ በፌደራል አቃቤ ህግ ክስ ቀርቦበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታዬ ሲሆን በነገው ዕለት (ጥር 7/2007 ዓ.ም) የሰማያዊ እና የኦህዴህ ሊቃነ-መናብርት ለተከሳሽ ተከላካይ ምስክር ሆነው እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡

ተከሳሹ አቶ ሲሳይ ዘርፉ ‹‹…‹ነጻነት ለፍትሓዊ ምርጫ› ለመላው ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ሁሉ….ተብሎ የተጻፈበት በራሪ ወረቀቶች ለህብረተሰቡ ሲያከፋፍል እጅ ከፈንጅ በመያዙ በፈጸመው የሐሰት ወሬን በማውራት ህዝቡን ማነሳሳት ወንጀል…›› በሚል በፌደራል አቃቤ ህግ መከሰሱ ይታወሳል፡፡
አቶ ሲሳይ ባለፈው ታህሳስ 30 ቀን 2007 ዓ.ም የአቃቤ ህግ ሁለት ምስክሮች ቀርበው በተከሳሽ ላይ ‹‹ምስክርነት›› ሰጥተውበት ነበር፡፡ በዕለቱ ዳኛው በበራሪ ወረቀቱ ላይ የተጠቀሰውን ‹‹የኢህአዴግ መንግስት ያፍናል፣ ያጭበረብራል፣ ይገድላል…›› የሚለውን በመጥቀስ ድርጊቱ ወንጀል ስለሆነ ተከሳሹ መከላከል አለበት ሲል ወስኖ ነበር፡፡

ስለሆነም ተከሳሽ አቶ ሲሳይ ዘርፉ በነገው ዕለት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበርና ም/ሊቀመንበር የሆኑትን ኢ/ር ይልቃል ጌትነትና አቶ ስለሺ ፈይሳ እንዲሁም የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኦህዴህ) ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለን በመከላከያ ምስክርነት ይዞ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡

ተከሳሹ ከሰው ምስክርነት በተጨማሪ የተለያዩ ሰነዶችን በመከላከያ ማስረጃነት ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አቶ ሲሳይ ዘርፉ ለአዳር ሰልፉ ወረቀት በመበተን ላይ እያለ በፖሊስ ተይዞ ‹‹የሐሰት ወሬን በማውራት ህዝቡን ማነሳሳት ወንጀል›› ተከሶ እስካሁን እስር ቤት ላይ ሲሆን በአዳር ሰልፉ ወቅት ድበደባ ተፈጽሞባቸውና አቶ ሲሳይ ከተከሰሰበት ወንጀል ከፍ ባለው ‹‹ህገ መንግስቱን በመናድ›› ተወንጅለው የነበሩት የ9ኙ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት በታሰሩ በ6ኛ ቀን መፈታታቸው ይታወሳል፡፡

ነገረ ኢትዮጵያ / Negere Ethiopia