የሲዳማ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ‹‹ማደራጀት ህገ ወጥ ነው›› ተብሎ ታሰረ

Semayawi Partyየሲዳማ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የሆነው አቶ አንተነህ አሰፋ ‹‹ማደራጀት ህገ ወጥ ነው፣ ፓርቲያችሁ ወጣቶችን እየመለመለ ወዳልሆነ አቅጣጫ እየወሰደ ነው›› በሚል መታሰሩን የዞኑ የሰማያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ደም መላሽ አበራ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ አንተነህ አሰፋ በትናንትናው ዕለት ከምሽሩ 12 አካባቢ በፖሊስ ተይዞ አዋሳ ከተማ ውስጥ ሀይቅ ዳር ፖሊስ ጣቢያ የታሰረ ሲሆን ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ የሚሰራው ስራ ህገ ወጥ ነው፡፡ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ነውጥ ለማምራት እየጣረ ነው፡፡ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ከሚያደርገው ሰማያዊ ፓርቲ መውጣት አለብህ፡፡›› የሚል ማስፈራሪያ እየደረሰበት እንደሆነ ተገልጾአል፡፡

ፖሊስ የሌሎቹን የፓርቲው የሲዳማ ዞን አመራሮች ቤትም እያፈላለገ እንደሆነ የገለጹት ሰብሳቢው ፖሊስና ደህንነቶች አመራሮቹንና አባላትን በማዋከብና በማሰር በህጋዊ መንገድ የሚደርጉትን የማረዳጀት ስራ ለማስቆም ከዚህም አልፎ ከሰላማዊ ትግሉ እንዲያፈነግጡ ጥረት እያደረገ ነው ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም የፖሊስ ወከባና እስር በህጋዊ መንገድ እያከናወኑ ያለው የፓርቲያቸው ስራ እንደማያደናቅፋቸውና ደህንነትና ፖሊሶቹ እንደሚያስቡት ከሰላማዊ ትግሉ እንደማያፈገፍጉ አቶ ደም መላሽ አክለው ገልጸዋል፡፡