አምርረን ለማስገደድ ዛሬም ቃላችንን እንጠብቅ ከአቢይ ኢትዮጵያዊ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ

ብዙ ሰዎች ፍቅርን እና ሰላምን ለያይተውት ማወቅ አይችሉም።የመፅሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ግን በሙሉ ከመንፈሳዊ ትምህርትነታቸው በላይ በተአማኒነት የሚታወቁት በአፈ-ታሪካዊነታቸው ሳይሆን፣የፍቅርን እና የሰላምን ትርጉም እንደባሕር ጥልቀት በዕውነተኛነት መረጃ በማስተማራቸው ነው። አይደለም የሰው ልጅ፣እንደምድረ-በዳዎች ሁሉ በውስጡ የጦርነት ሕይወት የሚ ኖ ርበት ባሕር እንኳ ሰላማዊ ነው ይባላል፤ዕውነቱ ግን በረሐዎችም ሆኑ ውቅያኖሶች መቼም ጊዜ ሰላማዊ ሊሆኑ አይችሉም።በሕዝባዊ መረጃነት የመፅሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ደግሞ ከግለሰብ ጀምሮ በሥም እየተጠቀሱ በጥንቃቄ ተመዝግበው የተጻፉና ሳይዛነፉ የቆዩ ናቸው።በተለይም በእኛ የ፳፻፯ /2015 ዓመተ-ምህረት የክርስቶስን ልደት የገና በዓል በምናከብርበት ሰሞን ሰላምን ሳይሆን ፍቅርን እናወቅ ዘንድ ለሰው ልጆች ሲሉ ውድ ሕይወታቸውን የሰጡትን በክብር ስናነሳ:- በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህኑ ለሰው ልጆች ነፃነት እና ፍቅር ሲሉ የደም-ዋጋ የሚከፍሉትን አግኝተው ለመግደል በሺህ የሚቆጠሩ ሕጻናትን የፈጁ የግብፁ ገዢ ፈርዖን እና የእስራኤሉ ገዥ ሄሮዱስ (ሁለት አንባገነን ገዢዎችን) አነሳስና አወዳደቅ ታሪክ ልናስታውስ ይገባናል ።

የመጀምሪያው የግብፁ ገዢ ፈርዖን ሲሆን፣ሙሴን በሕጻንነቱ ለመግደል ብሎ የፈፀመው የሕጻናት ግድያነው።ሁለተኛው ደግሞ የእስራኤሉ ገዥ ሄሮዱስ ክርስቶስን ሲወለድ ለመግደል ያሳረዳቸው ሕጻናት ናቸው።ያኔ የሁለቱም መንግስታት ገዥዎች የነበሩት ስልጣናቸውን ላለማጣ ገና የተወለዱ ሕጻንትን በአዋጅ አሳርደዋል፤ሆኖም ሁለቱንም የማይቀረው የሕዝብ አመፅ በትንቢት ጎርፍ አዋርዶ እስከዘላለሙ ላይመለሱ ተቀብረዋል።ዛሬ ሁለቱም ገዥዎች በዚያ ሰይጣናዊ ድርጊታቸው ይኮነናሉ፤ዛሬም ብቻ አይደለም፣ሁለቱም ገዥዎች ገና ወደፊትም በትውልድ እንደተረገሙ ይኖራሉ።በተለይም ሙሴንና ክርስቶስን ያነሳሁበት ዋናው ምክንያት፦ሙሴ እስራኤሎችን ስለነጻነታቸው ቀማኞችን እንዲዋጉ በምሳሌ ሲያስተምር ለምን እግዚአብሔር ሁሉንም እንዲሰጠን እንጠብቃለን ብሎ ሕዝቡን ለነጻነቱ እንዲነሳሳና ልቦና እንዲገዛ በማድረጉ፣ሕዝቡ በነጻነት ማሸነፉን ከመጽሐፍ ቅዱሳችን እናነባለን።እንዲሁም ክርስቶስ ደግሞ መለኮታዊና የፈጣሪነቱን ኃይል ሳይመካ በዳዮችን ግፍ እንዳይፈጽሙ ፊትለፊት ከመናገርም በላይ ራሱ በጅራፍ እየገረፈ ከቤተመቅደስ አስወጥቷቸዋል።ጠላቶቹ ይባስም ብለው የክርስቶስን በግፍ መታሰር ሕዝቡ እንዳያውቅ በሃሰት ችሎቱን በጨለማ እንዲታይ አድርገው ከሰሱት።የፈጸሙት ወንጀል አልበቃም ብሏቸው ባደባባይ አዋርደው ሰቅለውታል።ያንን ሁሉ ያደረገው ታዲያ ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ ለሰው ልጆች ፍቅር ብሎ ተሰቀለ እንጂ፤ተሸንፎ አይደለም።

በዘመናችንም የማይቀረውን የሕዝብ አመፅ ለማስቀረት የዘመኑ አምባ ገነኖችም ለሥጋዊ የሥልጣን ፍላጎታቸው በየአገሩ የተለያዩ ግድያዎችን በድብቅ እና በአደባባይ ሲፈጽሙ ምን እየከፈሉ እንደሆነ ዓለም ያውቃቸዋልና አልመለስበትም።ምክንያቱም ባለሥልጣናት እየሰሙ እንዳልሰሙ፤እያዩ እንዳላዩ በመሆናቸው ነው።በአገራችንም የኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ከገዥዎቻችን አንጻር ስናይ፦”በስምምነት እንነጋገር ሲባል፤”ማን ተጣላና?”ይላሉ፤ በሰላምና በፍቅር ሲጠየቁ ከአገር ቤት ውጭ በስደት ላይ ባለነው ሳይቀር በአፈ-አቃቤዎቻቸው(ቲፎዞዎች)አማካኝነት የሌለ ዕውነት እየፈበረኩ በየቤተክርስቲያኖቻችንና በሕዝብ ተቋሞቻችን ውስጥ ውሸት እያስወሩ ሕዝቡን በማጋጨት ላይ ይገኛሉ።ከነዚህም አንዱ በ”ኤሮፕ”ባለነው “ዩኬ” ባለነው ስደተኞች ላይ ነው።
በ”ዩናትድ ኪንግደም” ስደት ላይ ያለን፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ስለርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያንን የሁለት ዓመታት ችግር ሰፋ አድርገን ማየት ያስፈልገናል።ለምን ቢባል የተከሰተው ችግር የኢትዮጵያ ዖርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን፦በኢትዮጵያዊነት ላይ ያነጣጠረ የዘመናት ችግር በመሆኑ ነው።እናም ችግራችን በኢትዮጵያዊነት ምክንያት መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን ሥጋዊም ነው።ስለዚህ የተፈጠረው ሰላም የፍቅር ባለመሆኑ +ከመለያየት እንዲያወጣን እና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ነፃነት በአንድነት ሆነን ይህን የጉጅሌ ቡድንን አምርረን በማስገደድ ወደ ፍትህ እንዲቀርብ ለማድረግ በዝርዝር እንመልከተው።
እንደመግቢያ፦መንደርደሪያ ርዕሰ-ጉዳዮች፤

*መጀመሪያ ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።፩ኛ የዮሐንስ መልእክት ፬፥፰
በመቀጠልም ይህንኑ የፍቅርን ምንነት ዮሐንስ በተግባር ሲገልጸው ምን ብሏል።
*ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ።፩ኛ የዮሐንስ መልእክት ፫፡፲፰
በማስከተልም ዮሐንስ ለምን በተግባር እንጂ በአፍ ብቻ ልንዋደድ አይገባም አለ?
ጠቢቡ ሰለሞንም አስቀድሞ ብሎታልና ነው።
*ውሸተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አሰጸያፊ ነው እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው።መጽሐፈ ምሳሌ ፲፪፥፳፪
አዎ እውነትን ማድረግ እንጂ ማውራት ብቻ አይደለም እና ምን እንድናድርግ ?
*ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና።ወደ ቲቶ ፩፥፱
የታመነውን ቃል እንፈፅምስ ዘንድ የምንፀናበት ቃሉስ ምንድነው?ከቅዱሱ መጽሐፍ ስንመልከት የገላትያን ሰዎች መልሱን ይሰጡናል፦
*ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው።ወደ ገላትያ ሰዎች ፭፥፲፬
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኛቸው መልካም ነገሮች ሁሉ በፍቅር ይጠቃለላሉ።

*በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ።፩ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ፲፫፥ ፩
ለመሆኑ እነዚህን የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ማንሳት ለምን አስፈለገ?ምክንያቱም የምንነጋገርባቸው ጉዳዮች መፈሳዊ ሥራዎችን ለመፈፀም እንዲረዱን እና ሕሊናችንን በይቅርታ ለፍቅር እንድናስገዛ የመጽሐፍ ቅዱሳችንን በማጣቀስ እንድንረዳዳ ነው።በመሠረቱ ለአንድ አገር የፖለቲካ ሥራ ወይም በቀላል አቀራረብ(ሕዝብን የማስተዳደር ሳይንስ የማይቀር)ዋናው አስፈላጊ እና ሥጋዊ ኃላፊነት ነው።መንፈሳዊ ሕይወታችንን ለመጠበቅ አገር አያስፈልግም የሚሉት እነሱነታቸውን በሌሎች ትከሻ ላይ በማኖር በዚህች ምድር የምር ኖረው የማያውቁ ናቸው።እናም በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ በሚያግባቡን ላይ ተስማምተን በሚያለያዩን ደግሞ ለአለመነጋገር በመወሰን ሐገር የጋራ ሐይማኖት የግል መሆኑን አምኖ በመቀበል ለአገር አንድነት መቀራረብ ብልህነት ነው።የወያኔን አገር አፍራሽነት እያወቅን ሕገ-ወጥ ጳጳስ ቢቀመጥም እንኳ የካህናቱን ኃላፊነት***( ወደ ሮሜ ሰዎች ፰ ፥ ፴፫ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው?)***ለየራሳቸው እንዲነጋገሩና እኛ ምዕመናን ግን ጉጅሌው አንድነታችንን እንዳያደፈርስ ከፖለቲካ አመለካከት እና ከባዶ ቃላት ባሻገር ለኢትዮጵያዊነት የየራሳችንን ጥበብ መዘርጋት ይጠበቅብናል።

በዚህም መሠረት መንፈሳዊ እና ሥጋዊ ትግላችን ሳይቋረጥ በርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ዖርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ላይ የደረሰብን መዓት እና አስተዳደራዊ-ችግሮቹ[ያለፉትን የመከራ ጊዜዎች አያድርገውና]ከሰላሟ በስተቀር እስከዛሬም ድረስ ችግሯ ክገረገራዋ ተገፍትሮ አልወጣም።ይልቅስ በሁሉም ምእመናን መሐከል ሆኖ በለሆሳስ እየተወራ ቅዱስ ደጃፏ ላይ ብቻ ቀርቷል።ሐቁ ይ-ሰ-መ-ር-ልኝ እና መራራ በመሆኑ «ሐቁ»፤ዕውነቱ ማለትም አይደለም፤ አዎ!ሐቁ፦ግን ከነዚህ ዕውነታ ውጭ ነው።ይኸውም ችግሮቹ ድምፅ የላቸውም እንጂ ዛሬም አሉ፤እንደውም የእያንዳንዱን ምዕመን እና ካህናት ቤቶች እያንኳኩ ገብትው የአንድነት እና የሐገር ፍቅራችንን ሸርሽረው በሶስት ቦታዎች ሰንጥቀውታል። በቤተመቅደሱ ውስጥ፣በድንኳኗ እና በየቤታችን ሸንሽኖን አስቀርቶናል።በጣም የምታሳዝነው ትንሿ ነፃነታችን፣ የዜግነት እና የሰብዓዊ መብታችን መሠረት የሆነችው«ሐይማኖት የግል፣ሐገር የጋራ ነው፤»የምትለዋ ብሂል ናት።እናም«ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የሕይወት መመሪያነቷ ብቻ ከጥንት ጀምሮ በንብረትነቷ ታውቆ»መርህ ሆና ለዘመናት የኖረችው፣ ዛሬ በግለሰቦች የግል ፖለቲካ አመለካከት ብቻ ከየምዕመናኑ ላይ ከስደት ሕይወታችን ተፈንቅላ በራሳችን ስደተኞች መሰረቋ ነው።ሐቁን መቶ በመቶ ጙሊህ አድርገን እና በጥንቃቄ ተጠግተን ብንመረምረው ሌቦቹ በሁለቱም ጎራዎች አሉ።ማለትም በድንኳኗ እና በቤተ-ክሲያን ውስጥ ባሉት የፍቅር ልብ በሌላቸው የሰውን ሥጋ በለበሱ ሰዎች ላይ ሰይጣናዊ መንፈሱ ሰርፆ ሲጠናወታቸው በተግባራቸው እንረዳለን።ለዚህም መረጃዬ ሁለቱንም ጎራዎችን የሚቀርቡ ምዕመናኖች እና ራሴም በየአጋጣሚዎቹ ባረጋገጥኳቸው ነው።በነገራችን ላይ ወደተሳሳተ አቅጣጫ(ኃይል)ከመጓዙ በፊት እርቁን ከመንፈሳዊ አባቶች ጋር ለማካሄድ ከፍተኛ ጥረት አድርገናል፤የካህናትን እና የምሁራንን ጥረት ሳይጨምር።ዛሬማ በሁለት መንፈሳዊ ጓደኞች በነበሩ ከፍተኛ ቀሳውስት አዝማችነት የሚመራ መንፈሳዊ ጦርነት እስኪመስል የፖለቲካ ልዩነት ሽፋንም ባልተገባ መንገድ አግኝቷል፤አሳዛኝ የስደተኞች መንፈሳዊ ታሪክ ነው።

በመግቢያዬ ላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት መዓቱ(የአጸያፊ ቃላቱ ስድ ስድቦች እና የመለኮታዊ ትዕዛዛትን ድፍረቱ[ከእነ ጫማቸው በመግባት መረገሙ]) ተወግዷል።ለዚሁም ለሚደረገው ሕጋዊ ከለላ በየጊዜው በሌለ ገንዘብ አላስፈላጊ ወጪ እየተደረገ ቤተክርስቲያኗ ለጥበቃ እንድትከፍል ተገዳለች።አሉ የሚባሉት ችግሮችም መልካቸውን ቀይረው በገሃድ በማይታየው ፍጹም በተሳሳተ የፖለቲካ አመለካከት ለመተካት ይዘቱን በውሸት እና በሰናፍጭ ዕውነት ቋጥሮ ውስጥ ውስጡን ይንዶቃዶቃል።በቀላል አቀራረብ እና በአጭር ተምሳሌት ስናስቀምጠው የንብረትነት ፍለጋው እና በቤተክርስቲያኗ ሥም ሊገኙ የሚችሉትን ጥቅሞች በምዕመናኑ እንዳይታወቅ መፈለግ የትም አያደርስም።ይልቅስ የሚያሳዝነን በቤተክርስቲያኗ ጥላ ሥር ስንቶቹን የጉጅሌ ሰለባዎችን ለመርዳት የተመኘንላቸው በጎ አድራጎቶች ከንቱ መቅረታቸው ነው።በሎንዶን የምንኖር ኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነት ተከታዮች የሆንን ሁሉ እኔም ሆንኩ ባለቤቴ ለቤተክርስቲያናችን ከአሥራ አምስት ዓመታት በላይ ላበረከትነው መባም ሆነ ዛቲ የምንጠብቀው ተመላሽ የኔነት ንብረት በፍፁም ከቤተ ክርስቲያናችን የለንም፤ሊኖረንም አይገባም።የይገባናል ጥያቄ ካነሳን ግን ጉዳዩ መንፈሳዊ ሳይሆን፤ሠለጠንን እንደሚሉት የክርስቲያን ድርጅቶች ማሕበር ወደ ሥጋዊነት ያደላና ክርስቲያናዊነት ስላልገባን ወደ ተሳሳተ የገደል ሕይወት ውስጥ የሚጨምረን ይሆናል።ከዚህ ሐቅ በመነሳት ነው የጋራ ችግራችን የሆነውን አለመግባባት በጥንቃቄ የምንመለከተው።

፩ኛ/የአስተዳደራዊ ይዘቱን መቀየር፤ወሳኙስ ማነው? ጠቅላላ ጉባኤው።፪ኛ/የአስተዳዳሪውን ማንሳት በውሳኔ የሚተካው ማነው?ጠቅላላ ጉባኤው። ፫ኛ/የመተዳደሪያ ደንቡን ለማሻሻል የሚወስነው የሚያሻሽለውስ ማነው ?ጠቅላላ ጉባኤው። እነዚህ መጠይቆች እና መፍትሔዎቻቸው ናቸው እንዳይፈፀሙ ቤተክርስቲያናችንን የሰው ሰይጣን የሚያምሳት።ታዲያ ለነዚህ ችግሮቻችን እና መፍትሔዎች ለማግኘት ለምን ጠቅላላ ጉባኤው አይጠራም?ብዙዎች ምዕመናን እና ቀሳውስት ያመኑበት ሁኔታ፦ ለመረጃው “በጣም ዘግይተናል የሚል ነው፤ ምክንያቱም ችግሩ ከጠቅላላ ጉባኤው አቅም በላይ ሆኖ በሕግ ፊት ተይዟልና አሁን ሊነሳ የሚገባ ጉዳይ አይደለም፤”ይሉናል።በኅላፊነት ላይ የተቀመጠው የሰበካ ጉባኤም ጠቅላላ ጉባኤውን እንዳይሰበሰብ የሚከለክለው ችግር ሳይታወቅ ወይም በተቃዋሚነትም ያለው ጠቅላላ ጉባኤው እንዳይጠራ የሚፈልግበት ምክንያት እንደተዳፈነ ሆኖ ለምዕመናኑ እና ለካህናቱ በእንቆቅልሽ ምናውቅልሽ ዝምታ በተለያዩ የተስፋ ሰበቦች ጊዜውን እያስታከኩት ይገኛል።መነገር የነበረበት ሁሉ ተነግሯል፤መባል ያለበት ሁሉ ተብሏል፤ የቤተክርስቲያን አባቶች አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል፤ሆኖም ውጤት እስካላመጣ ድረስ በቂ አይደለም ልንል እንችላለን።ሆኖም ምክንያቱንና ሰበቡን ለያይተን በጥንቃቄ እስካላወቅን ድረስ ከችግራችን አንወጣም፤እየሆነ ያለውም ይሄው ነው።

በጣም የሚመስለው ግን ይህ አይደለም፤የሚመስለው ግን የወያኔ ገዥ ቡድንን የሚቃወሙ ድንኳን ውስጥ የተወረወሩ ናቸው።በመቅደሱ ውስጥ ከታቦቷ ጋር ያሉት ደግሞ የገዥውን ቡድን ደጋፊዎች ተደርጎ ለማስመሰል ተቀምጧል።የስናፍጭ ቅንጣት ዕውነትነቱ ግን በአባ ማትያስና በመቅደሱ ውስጥ ባሉት፤በአባ መርቆርዮስ ድንኳኑ ውስጥ ባሉት መቀበል አለመቀበል ልዩነት ላይ የተመሰረተ ነው።”እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው?”ወደ ሮሜ ሰዎች ፰ ፥ ፴፫:: ከዚህ ሐቅ ውጭ አጋዚን በመደገፍ ባለመደገፍ ላይ የተመሠረት አይደለም። ሐይማኖት የግል መሆኑን ሐገር የጋራ እንደሆነ ያልተቀበለ ስለርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ዖርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ባያወራ ብዙ ስህተቶች ከመስራት ይታቀባል።እንዲሁም አቅሌሲያ የሚባለውን የወጣቶች ክርስቲያናዊ ስብስብ አቅለ-ቢስ ብሎ መሳደብ፤አሊያም ከመከራ ተርፈው ለስደት የተዳረጉትን ወጣቶች በጅምላ የወያኔ ቡችሎች ብሎ መሰየም፤ኢትዮጵያ እየተመላለሱ ተቃዋሚ ነን በማለት መሹለክለክ፤አሊያም የአንድ መነኩሴና ካህናትን ሥም እየጠሩ ለስድብ መረባረብ ለችግሩ መድሃኒት ከመፈለግ ይልቅ ቁስሉን ማባባስ፣የመንፈሳዊ ሕይወትን ለማዳበር ከሚደክሙ ሁሉ አይጠበቅም።የጉዥሌው ቡድን ግን የሚፈልገው ይሄንኑ ነውና በተዘዋዋሪ በመረጃ የሚረዱት እንዳሉ ሆኖ ከገዥነቱ ቦታው እስከሚዘረጠጥ አንድነታችንን ለማስጠበቅ አንዲት ምርጫ ብቻ ናት የቀረችን።ሐይማኖት የግል ሐገር የጋራ እንደሆነ አምነን ባለን ልዩነት ብቻ እንደኢትዮጵያዊነታችን በጋራ ለመቆም ፍቅርን መቀበል።ይህም ጉጅሌው በኢትዮጵያዊነት ላይ ያነጣጠራቸውን ተንኮሎች (የኦርቶድክስን የማፍረስን ጨምሮ)እንደምንዋጋው አርቅቀን የማየታችን ምርጫ ብልህነታችንን ያረጋግጥልናል።አሁን ጉጅሌዎች እያደረጉ ያሉት ግን በልዩነቶቻችን ውስጥ ገብተው ዋናውን አጀንዳ፦«ለነፃነት መቆምን» መበታተን ነው።መፍትሔው ደግሞ ታቦታችን ባለበት ደጃፍ በጸሎት እና በጾም እየታገዝን ሰይጣንን በጾምና በጸሎት መታገል ነው፤ቤተክርስቲያኗ ውስጥ ገብተን እንዳንጸልይ የሚከለክለን ሕግ የለምና።ልባችን ግን ደንድኖ እያየን እንዳላየን እየሰማን እንዳልሰማን መሆኑ ከታሪክ ተጠያቂነት ሆነ ከሕሊና ዳኝነት ነፃ እንድንሆን አይረዳንም።

ለማጠቃለል፦ኢትዮጵያ አገራችንን ለመጠበቅ እኛ ኢትዮጵያውያን በአካል ያለነው ሌሎች ዜጋዎች የማይሸከሙልን እኛ ዜጋዎቿ ብቻ በነፍስ-ወከፍ ሥጋዊ (ሕዝባዊ፣ፖለቲካዊ፣አስተዳደራዊ) ሃላፊነት አለብን።ይህንን የንፍስ-ወከፍ ሥጋችንን ከእርኩሰ-መናፍስት መሰልጠኛነት ለማዳን ደግሞ መንፈሳዊ የሚያስፈለገን:- ሰላም ሳይሆን በፍቅር የተቋጠረ አንድነት ነው።ይህንን ለመድረግ ደግሞ እንኳን በስደት ላይ በአገራችንም ለማድረግ ሁሉንም እግዚአብሔር ሰጥቶናል።ሰይጣን እና ተከታዮቹ ግን አይደለም ባገራችን ኢትዮጵያ ብቻ በባዕድ አገሮች እንኳ ሳይቀር ሊነፍጉን በመንግሥት ስም እያሳደዱን ሊያጠፉን እንደባቢሎን ግንብ እንዳንግባባ አድርገውናል፤ዛሬም ምርጫው የኛው ነው።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤አሜን።