ማን አለ ዘንድሮ!

በዘውገ ፋንታ

አዋሽ ተሸሸገ
ኦሞ ሄደ ቢሉት
ተከዜ አረገ
ፀሐዩ በዝቶበት።
በሉ እንበል ዋይ ዋይ!
በሽሎ ይንከራተት፣
ካየለበት ሰማይ፣
ሸበሌም ይሸፍት፣
ይበል ይኖራል ወይ?
አምልጦ ሸሽቶ፣
ከወያኔ ጠፍቶ?
አባይ አታጣላን፣
ለገንዘብ ከሆነ፣
የሚበላ አንተን፣
ቀጭን ሰው መች ሆነ!
ባሮ ይህድ ዞሮ፣
ኦሞ ጠፋ ካሉት፣
ወይ ውሃ ዘንድሮ፣
ገባ ወይ ከመሬት?
አጣና ያንን ዘር፣
መበተኛም ምድር።

አሻፈረኝ ይበል፣
የከፋው ወንዝ ሁሉ፣
መሬት ጠፋ ሲባል፣
የት ይኬድ ይበሉ።
የት ገባ ክልሉ?
ጎንደር አትደሩ፣
ጎጃም ይጠብቃል፣
ከሄደ አፋሩ?
ወሎ የት ይገባል?
ሸዋ ተሸክሟል፣
ቀሎታል ወይ ምድሩ?
የሚጎርፈው በዝቷል፣
የማነው አገሩ፣
ድንጋይ ብቻ ቀርቷል፣
የታጨደው ሳሩ፣
የጠፋው ዛፍ ቅጠል፣
የት ላይ ነው? አብቅሏል።

ኤሊባቡር ገባሁ፣
በየት ነው ወለጋ፣
ሀረርጌን አየሁ።
ከፋን ሳላወጋ፣
ሲዳሞ ገባሁ
ባሌን ፍለጋ፣
አርሲን አልጣ፣
ገሙን ላይ ወርጄ፣
እኔ ልቀጣ፣
ሁሉን ወድጀ።
ተደራርቦ ይምጣ።
ጎፋውማ አገሬ፣
እሱነው ክብሬ።
ረግፎ ተረጭቶ ፈሶ፣
የከፋው የት ይግባ፣
ዛፉ ሁሉ ታርሶ!
እስከ አዲስ አበባ።
ድንጋዩ ለምልሞ፣
ማን ጥሬውን ዘራ፣
ይውጣ ይሂድ ደግሞ፣
ያቺም ኤርትራ፣
ትወሰድ ተሰፍራ፣
ከሆነች እንጀራ።
በቃህ ይብቃህ በሉኝ፣
ጠልቄ የማላውቅ፣
አንድ ፍሬ ልጅ ነኝ፣
እናት የምናፍቅ።
አላውቅም ንገሩኝ፣
እሱ ማን ይባላል?
መልኩ መቸ ጠፋኝ፣
አለወይ ክልል?
ምን አለው ከመሀል?
ይወሰድ ከቃየው፣
ድርቀቱን እያየ፣
ክልሉን ይጥገበው፣
ይመለስ ከቆየ፣
ሲሰራ የጠፋው።