የኢህአዴግ መንገድና የኤዲፐስ መንገድ -ስለሺ ሐጎስ
አንዳንዶች ከማይቀረው ዕጣ ፈንታቸው አይናቸውን ጨፍነው ይሸሻሉ፤
የሚሸሹበት መንገድ ግን ወደማይቀረው ዕጣ ፈንታቸው በፍጥነት ያደርሳቸዋል፡፡
ሰሞኑን ኢህአዴግ በምርጫ ቦርድ በኩል የያዘውን ዘመቻ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ዘመቻው አንድነትን፣ መኢአድንና ሰማያዊ ፓርቲን ከምርጫ 2007 ሜዳ ገፍቶ ማስወጣት ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በኢህአዴግ ጥቁር መዝገብ ላይ የሰፈሩበት ምክኒያት ደግሞ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በምርጫ 2007 ኢህአዴግ የሚያጭበረብርበትን መንገድ ዘግተው ከፍ ባለ ድርጅታዊ ጥንካሬና በቁርጠኛ አመራር የኢህአዴግን መጨረሻ ለማወጅ ስለተነሱ ነው፡፡ ኢህአዴግ የሚሸሸው በ2007 ሊገጥመው የሚችለውን የሽንፈት ዕጣ ፈንታ እንደሆነ ተግባሩ ያሳብቅበታል፡፡ ሽሽቱ የኤዲፐስ አይነት ስለሆነ ከዕጣ ፈንታው ሊያመልጥ ግን አይችልም፡፡

ኤዲፐስ፣ በግሪክ አፈታሪክ ውስጥ ያለ ገጸ-ባህሪ ነው፡፡ አባቱ የቲብዝ ንጉስ ነበር፡፡ እናትና አባቱ የልጃቸውን ዕጣ ፈንታ (አባቱን የሚገድል እናቱን የሚያገባ ልጅ እንደወለዱ) ቴረሲያስ ከሚባል አንድ ነብይ ሰምተው ስለነበር እያዘኑ እንዲሞት ይፈርዱበታል፡፡ እናም ለእረኛቸው ግደል ብለው ሰጡት፡፡ እረኛው አልጨከነም፡፡ ለሌላ አሳዳጊ ሰጠው፡፡ ኤዲፐስ ከንጉስ ቤት እንዲገደል ወጥቶ በሌላ ንጉስ ቤት አደገ፡፡ እውነተና እናትና አባቱን ሳያውቅ ጎረመሰ፡፡ ባንድ ክፉ ቀን አንድ ነቢይ የራሱን ዕጣ ፈንታ “አባትህን ትገላለህ እናትህን ታገባለህ” ሲል አረዳው፡፡ ኤዲፐስም አወጣ አወረደና አባቴን ገድዬ እናቴን ከማገባ ብሎ ሰረገላውን አሰናድቶ ፈረሱን መጭ እያለ ከሀገር ለመጥፋት በረረ፡፡ የሚሄደው ሀገር ወደ ቲብዝ ነበር፡፡ ቲብዝ ያለው ንጉስ አባቱ መሆኑን ግን አያውቅም ነበር፡፡ መስቀለኛ መንገድ ላይ ከአባቱ ጋር ተገናኘ፡፡ አሳልፈኝ አላሳልፍም በሚል የክብር ጥያቄ ጠብ ገጠሙ፡፡ ኤዲፐስ አባቱን ገደለው፡፡ ቲብዝ ያለ ንጉስ ቀረች፡፡ ኤዲፐስ የአባቱን ሚስት አግብቶ በቲብዝ ላይ ነገሰ፡፡
የኤዲፐስ ታሪክ ባጭሩ ይሄ ነው፡፡ ኤዲፐስ ከዕጣፈንታው አይኑን ጨፍኖ ሸሸ፡፡ የሸሸበት መንገድ ግን ወደማይቀረው ዕጣ ፈንታው በፍጥነት አደረሰው፡፡
ኢህአዴግም የኤዲፐስን መንገድ የመረጠ ይመስላል፡፡ በ2007 ምርጫ ከማይቀረው የሽንፈት ዕጣ ፈንታው አይኑን ጨፍኖ እየሸሸ ነው፡፡ የሚሸሽበት መንገድ ግን ወደ ማይቀረው ዕጣ ፈንታው በፍጥነት እያደረሰው እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው፡፡
አንድነት ገና ከጠዋቱ ምርጫው ላይ ያለውን አቋምና ስትራቴጂ ግልጽ አድርጓል፡፡ “ምርጫ ውስጥ እንገባለን፣ አንድነት እንዲመረጥ እንቀሰቅሳለን፣ የህዝብን አሸናፊነት ኢህአዴግ በማጭበርበር ቀለብሳለሁ ካለ ደግሞ አስጨናቂ በሆነ ህዝባዊ እምቢተኝነት የህዝብን ድምጽ ለማስከበር የተቀናጀና ቁርጠኛ አመራር እንሰጣለን፡፡” ብሏል፡፡ ይህ አቋም አሁንም ያለ ነው፡፡ ኢህአዴግ ከምርጫው በፊት ማጭበርበር ውስጥ ከገባ ውድቀቱም ከምርጫው በፊት ይሆናል፡፡ ሽሽቱ እጣፈንታውን ቢያፈጥነው እንጂ ከሽንፈት አያስመልጠውም፡፡
ቺርስ! ለነገው ብሩህ ቀናችን፡፡