ወንድ ሆኖ ሳለ የሴት ጾታ ነው ያለኝ በማለት ያጭበረበረው ወጣት በእስራትና በገንዘብ ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30፣ 2007 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ወንድ ሆኖ ሳለ የሴት ጾታ ነው ያለኝ በማለት ሴት የሚያስመስለውን አልባሳትና መዋቢያዎች ተጠቅሞ በማታለል በርከት ያለ ገንዘብ ለመውሰድ ሲሞክር የተያዘው የ17 ዓመቱ ወጣት በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ።

ሙሉቀን ተመስገን የተባለው ይህ ተከሳሽ ሴት ሊያስመስለው የሚችለውን ውጫዊ መለያዎችን በመጠቀምና ስሙን ቅድስት በማለት ነው ድርጊቱን የፈጸመው።

ተከሳሹ የግል ተበዳይ የሆነችውን ግለሰብ ከተዋወቀ በኋላ ነው ቤቷ በመመላለስ በርከት ያለ ገንዘብ ለመውሰድ የሞከረው።

ይሁን እንጂ ነሀሴ 8፣ 2006 ዓ.ም ሲመላለስ የተመለከቱት የአካባቢው ወጣቶች በመንገድ ዳር ቆሞ ሲፀዳዳ በመመልከታቸው ተጠርጣሪው እጅ ከፍንጅ ሊያዝ ችሏል።

በዚህም በፈጸመው የማታለል ወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ መሆኑን ያረጋገጠው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 17ኛ የወንጀል ችሎት በተከሰሰበት የክስ መዝገብ በሁለት ዓመት ጽኑ እስራትና 300 ብር የገንዘብ መቀጮ ያስተምረዋል ሲል ወስኖበታል።

በሀይለየሱስ ስዩም

Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።