የአቡነ መቃርዮስ የገና በዓል መልዕክት
በሕጋዊው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስ የአውስትራልያና የኢየሩሳሌም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ መቃርዮስ የልደት በዓልን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል። አቡነ መቃሪዮስ በዚሁ መልዕክታቸው ነጻነቱን አጥቶ በእስር ቤት እየተሰቃየ በየአደባባዩ እየተገደለና ከክብሩ እየተዋረደ ያለውን ኢትዮጵያዊውን ወገናችንን ማስታወስ እንዳለብን ተማፅነው፣ በቅርቡ በባህር ዳር ከተማ ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ “ጥምቀተ ባህር አይሸጥም አይለወጥም የታቦት ማረፊያችንንም አሳልፈን አንሰጥም” በማለታቸው በአደባባይ በጥይት ለገደላቸው ወጣቶች የኢትዮጵያ አምላክ ልዑል እግዚአብሔር እረፍተ ነፍስ ይስጥልን ብለዋል። ቤተሰቦቻቸውንም በዚህ የሰላምና የመጽናናት በዓል በቅዱስ መንፈሱ እንዲያጽናናልን እንጸልያለን ብለዋል። በደብረ ማርቆስና በአካባቢው በህጻናት፣ ተማሪዎችና በነዋሪዎች ላይ የሚደርሰው ድብደባና አፈሳ፤ በመፈጸም ላይ መሆኑንና በሌሎችም ልዩ ልዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚደርሰው ማፈናቀል ስውር ግድያና እስራት ለሀገራችንና ለቤተክርስቲያናችን በአጠቃላይ ለህዝባችን ታላቅ ሀዘንና ፈተና መሆኑ ከሁላችንም የተሰወረ አለመሆኑን አመልክተዋል።
ከዚህም አያያዘው ወያኔ በውጭ ሀገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ተባብሮ ሥራ እንዳይሠራና ለወገኑ እንዳይደርስ እርስ በርስ በመለያየት እንዲጣላና ሰላም እንዳይኖረው በክፍለ ሀገር፤ በዘርና በጎሳ በመበታተን ቤተክርስቲያኑን እንዳይሠራ ጠንካራ የኢትዮጵያውያን ማኅበር እንዳይኖር አንዱ የሌላውን ስም እንዲያጠፋው የውሸትና የፈጠራ ወሬን በመንዛት በስውር ወኪሎቹ የጥፋት ሥራውን እያከናወነ እንደሚገኝ አጋልጠዋል። አቡነ መቃርዮስ ያስተላለፉትን መልዕክት ሙሉ ቃል ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ። የአቡነ መቃሪዮስ የልደት በዓል መልዕክት