በላስቤጋስ፣ ኔቫዳ የሚገኘው የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ችግሮች
ለሕጋዊው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስ
ኦክላንድ፣ ካሊፎርኒያ
“እናንተ የሰው ልጆች፣ እስከ መቼ ድረስ ልባችሁን ታከብዳላችሁ ? ከንቱ ነገርን ለምን ትወዳላችሁ ? ሐሰትንም ለምን ትሻላችሁ ? እግዚአብሔር በጽድቁ እንደተመሰገነ እወቁ።” መዝ 4 ቁጥር 2-3
በላስቤጋስ፣ ኔቫዳ የሚገኘው የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ስር እንደሚተዳደር ይታወቃል። ሆኖም ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተክርስቲያኒቷ የመደባቸው አቡነ ዩሴፍ በቤተክርስቲያናችንና በምዕመናን ላይ ከፍተኛ በደል እየፈጸሙብን ይገኛሉ።
በቅርቡ የስራ ዘመኑ የተጠናቀቀውን የቤተክርስቲያናችን የሰበካ ጉባዔ (የአስተዳደር ቦርድ) የሚተኩ አዲስ አባላት ምርጫ ተካሂዷል። በዚህ ምርጫ ላይ ምዕመናን “ያገለግሉናል፣ ይሰሩልናል” ብለው ከመረጧቸውን አባላት መካካል አቡነ ዮሴፍ የማይፈልጓቸው በመገኘታቸው ምክንያት እራሳቸውን ባለመግዛት ጭምትነት የጎደለው ከአንድ ጳጳስ የማይጠበቅ “ጳጳስ እንዲህ ነው እንዴ?” የሚያሰኙ ንግግሮችን በአውደ ምሕረት ላይ አድርገው ምዕመናንን በእጅጉ አሳዝነዋል፣ አንገትም አስደፍተዋል። ከዚህም በፊት በሌሎች ጊዜዎችም አቡነ ዮሴፍ ለአንደበታቸው ልጓም እንደሚያስፈልጋቸው ስንታዘብበት የነበሩበት በርካታ አጋጣሚዎችን እናስታውሳለን።
ከዚህም በተጨማሪ እጅግ ከፍተኛ ክብር ያለውን የጳጳስነት ሥልጣናቸውንና ኃላፊነታቸውን በማራከስና በማውረድ የደሞዝና የጤና ኢንሹራንስ ጥቅማ ጥቅሞች ካልተደረገልኝ ጭራሹንም “የምትሰጡኝ $1,000 ምንም ዋጋ ስለማይሰጠኝ ቤተክርስቲያኑን እዘጋዋለሁ” ማለታቸው የቀደሙት አባቶቻችን በጸሎት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ይተጉ ስለነበሩ እንኳን ለራሳቸው ይቅርና ለሕዝብ ጤንነትና ምህረት ያስገኙ የነበሩ መሆኑን በቁጭት እንድናስታውስ አድርጎናል። የእኝስ የጉድ ነው! መንፈሳዊው አገልግሎትና ካልሆነላቸው አባ ዮሴፍ ከቤተክርስቲያን እርቀው በንግድ መስክ መተዳደር ሳይሻላቸው ስለማይቀር ሕዝቡን ማንገላታት ትተው ሳይመሽ የንግዱን መላ ቢዘይዱ ቤተክርስቲያንን ከማሳዘን ሳይሻል ይቀራል?
ከዚህ ቀደም በዋሽንግተን ዲሲ ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል መንበር ፓትርያርክ በአውደ ምህረት ላይ የሰበካ ጉባኤው አባላትን እንደ “ጋዳፊ ትወርዳላችሁ” በማለት ምዕመናን የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት በነበረው በሊቢያው ሞአመር ጋዳፊ መሰየማቸው ሲኖዶሱ ለገጠመው ችግር ዋናው አብይ ጉዳይ እንደነበር ይታወሳል። አባቶች ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ለእንዲህ አይነቱ ጸረ ቤተክርስቲያን ንግግር ቅዱስ ሲኖዶሱ በጊዜው የእርምት እርምጃ ባለመውሰዱና ሆያሆዬ የሚሉት በመብዛታቸው ለአሁኑ የአባ ዮሴፍ ችግርና ከቦታ ወደ ቦታ እየተሯሯጡ ለሚበጠብጡ ጥቂት መነኩሴዎችና ሰባኪወንጌላዊያን የቁልቁለትመንገድ ከፍቶላቸዋል።
በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶሱ ይህንን ጉዳይና በምንኩስንና ስም ከኪሳቸው በማያወጡት ገንዘብ ከአገር ወደ አገር በነጻ የአውሮፕላን ትኬት እየተሽሞነሞኑ ለህዝብ ሸክም ሆነው ህጋዊውን ሲኖዶስና ምዕመናኑን በማወክ በአንዳንድ አባቶች ላይ የሃሰት ክስ እንዲወረወር በማድረግ የሚንቀሳቀሱና እራሳቸውንም ለጵጵስና ያዘጋጁትን አደብ እንዲያስገዛልን እንማጸናለን። እነዚህ ከሕገ ቤተክርስቲያን የወጡ አይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ የሚሉና የሚያምታቱ ለሲኖዶሱም ለምዕመናኑም ግራ ያጋቡ ስመ መነኩሴ የቤተክርሲቲያን በታኞችን እየተመለከትን ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት ወደፊት የምንመጣበት ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶሱ እራሱን እንዲመረምርና ቢቻልም እርምትና አግባብ ያለው አስተዳደራዊ እርምጃ ዝውውርን ጭምር እንዲደረግ እያሳሳብን የላስቬጋሱ አባ ዮሴፍ ጉዳይ በአስቸኳይ እርማት እንዲደረግበት በትህትና እንጠይቃለን። ላስቬጋስ ውስጥ በሚገኘው የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ለሚደርሰው ማናቸው ችግር በሙሉ ተጠያቁው እራሳቸው አቡነ ዮሴፍ መሆናቸውን ቅዱስ ሲኖዶሱ ያውቅልን ዘንድ በታላቅ ትህትና እንጠይቃለን።
ቤተክርስቲያናችንን እግዚያብሔር ይጠብቅልን!
ከተቆርቋሪ ምዕመናን