በገርጂ የኮንዶሚኒየም ህንፃ የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል Condominium in Addis is in danger of collapse, visible cracks on the wall

በቦሌ ክፍለከተማ ገርጂ ቁጥር አንድ ኮንደሚንየም ተብሎ በሚጠራው በብሎክ ሃያ አንድ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች የኮንደሚንየም ቤቱ በላያችን ላይ ሊፈርስ ነው አሉ። በዚሁ ሳይት የሚገኘው ብሎክ ሃያ አንድ ቤት ግርግዳው ከመሰረቱ እስከጣራው ድረስ እየተሰነጣጠቀ መሆኑን የተመለከትን ሲሆን ነዋሪዎቹም የግርግዳው የስንጥቆቹ ክፍተቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መሄዱን ገልፀውልናል።

ከዚህም በተጨማሪ ህንፃው ከቁመናው የመዛባት ባህሪ እየታየበት ስለሄደ ነዋሪዎቹ የቤቶቻቸው መዝጊያዎች ሳይቀሩ እየተዛነፉ ለመክፈትና ለመዝጋት በመቸገራቸው በየጊዜው እያሰቆረጡ ቁመታቸውን ለማስተካከል መገደዳቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልፀዋል። በቦታው ተገኝተን መረዳት እንደቻልነው የብሎኩ ነዋሪዎች ቤት ከውስጥም ከውጪም በከፍተኛ ደረጃ የመሰንጠቅ ችግር የገጠመው ሲሆን ስንጥቆቸም በሁሉም የብሎኩ ነዋሪዎች ቤቶች የመስፋት ሁኔታ ይታይባቸዋል።

በዚሁ ብሎክ በቤት ቁጥር አምስት ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ብርቄ መንግስቱ ቤቱን በ1997 ዓ.ም መረከባቸውን አስታውሰው፤ ይሁንና ቤቱ መሰነጣጠቅ ከጀመረ አመታት የተቆጠረ ቢሆንም ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ ግን እየተባባሰ መሄዱን ገልፀውልናል። የሳቸው ቤት ምድር ቤት ሲሆን ከላይ ያሉትን ፎቆች የተሸከመ በመሆኑ የቤቱ የመሰነጣጠቅ ክፍተት ከሌሎቹ ከላይ ካሉት ፎቆች የሰፋ መሆኑን ተመልክተናል።

የቤቶቹ የመሰነጣጠቅ ክፍተት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መሄዱን ነዋሪዎቹ የገለፁልን ሲሆን እኛም በቦታው ተገኝተን መመልከት እንደቻልነው የስንጥቆቹ ክፍተቶች ከላይኞቹ ፎቆች ወደ ወደታችኞቹ ፎቆች ሲወርዱ የመስፋት ሁኔታ ይታይባቸዋል።

እንደነዋሪዎቹ ገለፃ ህንፃው ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደታች ዝቅ የማለት ሁኔታም ይታይበታል። ወይዘሮ ብርቄ የወጥቤታቸው የእቃ ማስቀመጫ ካቢኔት ሳይቀር በቤቱ ግርግዳ እየተገፋ እቃቸውን ለማስቀመጥ እሰከመቸገር የደረሱ መሆኑን ለመመልከት ችለናል። በዚሁ ብሎክ የቤት ቁጥር አራት ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ትግስት አዲሱ ህንፃው መጀመሪያ የመሰንጣጠቅ በህሪን ሲያሳይ ቀለል ያለ ችግር ነው በሚል እሳቤ የተወሰነ እድሳት አከናውኖ በቀላል ጥገና ችግሩን ለመፍታት ታስቦ የነበረ ቢሆንም ይሁንና በሂደት ሲታይ ግን ህንፃው ከላይ እስከታች የመሰነጣጠቅ ባህሪን በማሳየቱ ዘለቄታዊ መፍትሄን ለማገኘት ለተለያዩ የመንግስት አካላት ሪፖርት ሲደረግ የቆየ መሆኑን ገፀውልናል።

በዚሁ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን የሳይቱን ነዋሪዎች ማህበር ተወካዮች ለማነጋገርም ጥረት አድርገናል። ጉዳዩን በተመለከተ በፅህፈትቤታቸው ማብራሪያ የሰጡን የማህበሩ የጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ ሻምበል ባሻ ግዛቸው ታረቀኝ በቤቱ ላይ ለተፈጠረው ችግር ዋነኛው መንስኤ በሳይቱ አካባቢ ያለው ዋና መንገድ መሆኑን ይገልፃሉ።

  በኮንደሚንየሙ ሳይቱ አካባቢ ወደ የረር መገናኛ የሚወስደውን መንገድ በዩኒቲ ዪኒቨርስቲና ኮሪያ ሆስፒታል በኩል ወደ ዋናው የገርጂ መብራት ሀይል መንገድ የሚያገናኝ ጥርጊያ መንገድ አለ። በአካባቢው ፋብሪካዎች ከመኖራቸውም በተጨማሪ የገርጂ አርባ ስልሳ የቤት ግንባታን ጨምሮ የበርካታ ህንፃዎች ግንባታ በአካባቢው ስለሚከናወን ገልባጭ መኪናዎች እንደዚሁም ከባድ የኮንስትራክሽን ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙት ይሄንኑ የጥርጊያ መንገድ ነው።

ከሻምበል ባሻ ግዛቸው ገለፃም ሆነ ከነዋሪዎቹ ማብራሪያ መረዳት እንደቻልነው መንገዱ ለከባድ ተሸከርካሪዎች አገልግሎት መፈቀዱ በመኪኖቹ ምልልስ ምክንያት በአካባቢው የኮንደሚኒየም ቤቶች ላይ ከባድ መናጋትን እየፈጠረ ነው። መኪኖቹ በሚያልፉበት ወቅት በብሎኮቹ ላይ ንቅናቄን በመፍጠር ግርግዳ ላይ የተሰቀለን እቃ ሳይቀር የሚጥል ንዝረት መኖሩን ነዋሪዎቹ ገልፀውልናል። ብሎክ ኤ እና ቢ በሚል ሁለት የተያያዙ ህንፃዎችን የያዘው ይኸው ህንፃ እያንዳንዳቸው ሃያ ቤተሰብን በጠቅላላ አርባ አባወራን የያዙ መሆኑ ታውቋል። በአንደኛው ህንፃ ላይ የደረሰው መናጋትና መሰነጣጠቅ ወደ ሁለተኛውም ህንፃ ጭምር እየተዛመተ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልፀውልናል። ነዋሪዎቹ የህንፃው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሄዱ በላያቸው ላይ ሳይፈርስ የሚመለከተው የመንግስት አካል መፍትሄ እዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።

ማህበሩ መንገዱን በተመለከተ ለአዲሰ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በፃፈው ደብዳቤ በመንገዱ በቀን ከአንድ ሺ በላይ ከቀላል እስከባድ መኪኖች የሚመላለሱብት መሆኑን ይገልፃል። የማህበሩ ኮሚቴ በብሎክ ሃያ አንድ ላይ የደሰረው አይነት መሰነጣጠቅ በሌሎቹ ብሎኮች ላይም ጭምር እንዳይደርስ ለመከላከል በማሰብ መንገዱን ከባድ መኪኖች ሊያልፉ በማይችሉበት መልኩ በእንጨት ጊዜያዊ መከላከያ ቢሰራም በቦሌ ክፍለከተማ በወረዳ አስራአንድ የስራ ኃላፊዎች አማካኝነት ማገጃው እንዲነሳ የተደረገ መሆኑን ሻምበል ባሻ ግዛቸው ገልፀውልናል።

ከዚህም በተጨማሪ በመኪኖቹ ምልልሰና በነፋስ በሚፈጠረው የመንገዱ አቧራ ነዋሪዎቹ ልብስ ማስጣት፣ እንደዚሁም በሮቻቸውንና መስኮቶቻቸውን ሳይቀር እንደልብ መክፈት ያልቻሉ መሆናቸውን አመልክተዋል። ይሄንኑ ጉዳይ በተመለከተ የሳይቱ ማህበር ኮሚቴ ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሁለት ጊዜ ደብዳቤ የፃፈ መሆኑን መረዳት ችለናል። የመጀመሪያው ደብዳቤ ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም በደብዳቤ ቁጥር01/ኮ/503/06 በቀጥታ ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የተፃፈ ነው። ደብዳቤው በአካባቢው በሚያልፉ ከባድ የኮንስትራክሽንና የጭነት ተሽከርካሪዎች ኮንደሚኒየም ቤቶቹ ላይ የንቅናቄ ብሎም የመሰነጣጠቀቅ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ይገልፃል። ተሸከርካሪዎቹ የሚያስነሱት አቧራም ለሳይቱ ነዋሪዎች አስቸጋሪ እየሆነ መሄዱን በመግለፅ መንገዱ እንዲሰራ ብሎም ለኮንደሚንየም ቤቶቹ ደህንነት ሲባል በመንገዱ መግቢያና መውጫ ላይ የከባድ ጭነት ተሸከርካሪ ማገጃ ምልከት እንዲተከል ይጠይቃል።

ሻምበል ባሻ ግዛቸው ጥያቄውን ተከትሎ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን መንገዱን በ2007 በጀት ዓመት ግንባታውን ለማከናወን ቃል ገብቶ የነበረ መሆኑን ይገልፃሉ። ደብዳቤው በጥር ወር ከተፃፈ በኋላ በዚያው ዓመት ክረምት በጣለ ከባድ ዝናብ የመንገዱ ጎርፍ በብሎክ አስራዘጠኝ ምድር ቤት የመኖሪያ ቤቶችን በማጥለቅለቅ በነዋሪዎቹ ንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሰበት ሁኔታ እንደነበር ሻምበል ባሻ ግዛቸው አስታውሰዋል።

      የማህበሩ ኮሚቴ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በሁለት ሺ ሰባት በጀት አመት ግንባታውን ለማከናወን በገባው ቃል መሰረት የመንገዶቹን ግንባታ ያከናውናል ብሎ ሲጠባበቅ ቢቆይም ግንባታው ሳይጀመር ሩብ አመቱ በማለፉ በህዳር ወር 2007 ዓ.ም በድጋሚ ለባለስልጣን መስሪያቤቱ ደብዳቤ የፃፈ መሆኑን ከቀሪው ግልባጭ ደብዳቤ ተመልክተናል። ሆኖም በበጀት አመቱ አጋማሽ ላይም ቢሆን በአካባቢው ምንም አይነት የመንገድ ግንባታን አልተመለከትንም።

በህንፃው ላይ ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ ጉዳዩን ወደ ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አምርተን ነበር። በዚሁ ዙሪያ በቀጥታ ይመለከታቸዋል የተባሉትን በሚኒሰቴር መስሪያቤቱ የቤቶች ህንፃ ዲይዛይን ዝግጅትና ትግበራ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሪት ደስታ ሸዋሞላ አግኝተን አነጋግረናቸዋለን። ወይዘሪት ደስታ ህንፃው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን ገልፀው፤ በህንፃው ላይ የሚገኙት ነዋሪዎች የችግሩን አሳሳቢነት በመጥቀስ ለከተማ ልማት ቤቶችና ለኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ሀይሌ በመስከረም ወር 2007 ዓ.ም ደብዳቤ የፃፉ መሆኑን ገልፀውልናል። ይሁንና ሚኒስትሩ ከስልጠናዎች ጋር በተያያዘ የተጣበበ ጊዜ ላይ ስለነበሩ ደብዳቤውን በህዳር ወር ተመልክተው በሚኒስትሩ መስሪያ ቤት ስር ላለው የመኖሪያ ቤቶች ልማት ቢሮ እንደመሩት ወይዘሪት ደስታ ገልፀውልናል።

ደብዳቤው ከተመራ በኋላም የተፈጠረው ችግር የዲዛይን ችግር ሊሆን ይችላል በሚል በሳቸው የሚመራው የቤቶች ህንፃ ዲዛይን ዝግጅትና ትግበራ መምሪያ ከፕሮጀክት ግንባታ ክትትል መምሪያ ጋር በመተባበር ባለሙያዎች ተወጣጥተው ወደቦታው መሄዳቸውን አመልክተዋል። እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ባለሙያዎች በቦታው በመገኘት ምርመራ ያደረጉ መሆኑን የገለፁልን ኃላፊዋ፤ በተደረገው ምርመራም በህንፃው ላይ የታዩት ችግሮች መለየታቸውን ነግረውናል። መንስኤው የአፈር ችግር፣ እንዲሁም የህንፃው መሰረትም እንደአንድ መንስኤ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢው ከባድ ተሸከርካሪዎች በብዛት ስለሚመላለሱ አንዱ ምክንያትም ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ኃላፊዋ ጠቁመዋል። በተጨማሪም ባለሙያዎች በቦታው ተገኝተው ባደረጉት ምርመራ በአንዱ የህንፃው ክፍል ነዋሪዎች ግርግዳው ተነስቶ ከበረንዳው ጋር የመቀላቀል ስራ የተሰራ በመሆኑና ይህም እንደችግር የሚታይ እንደሆነ አመልክተዋል። የውጪኛው ግርግዳ ከክፍል መለያነት ባለፈ ከኮለኑ ጋር ሆኖ የቤቱን ክብደት ስለሚሸከም ለህንፃው መናጋት አንዱ ምክንያት እንደሚሆን ሀላፊዋ ጨምረው አመልክተዋል። የባለሙያዎቹ ቡድን የራሱን ምርመራ አጠናቆ ሪፖርት እንዳደረገም የከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ሀይሌ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመጥቀስ ለአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት አስቸኳይ ደብዳቤ መፃፋቸውን ወይዘሪት ደስታ አረጋግጠዋል። ቤቱ ከመሰረቱ ጀምሮ እስከ ጣሪያው ድረስ የመናጋትና የመሰነጣጠቅ ችግር ስለታየበት የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ደብዳቤው ለአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ፅህፈትቤት ከተፃፈም በኋላ በሂደቱና በቀጣይ በሚኖረው ውጤት ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የራሱን ክትትል የሚያደርግ መሆኑን ጨምረው ገልፀውልናል። ከመንገዱ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፈቃደ ሀይሌን ለማናገር በተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም።

Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።