በጋራ ህዝቡን የምናታግልበትን መንገድ እንድንፈጥር ጥሪዬን አቀርባለሁ – (የሰማያዊ አመራር ኢያስፔድ ተስፋዬ)
(አቶ እያስፔድ ተስፋዬ የሰማያዊ ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚና የወጣቶች ክፍል ሃላፊ ናቸው። በቅርቡም ከሚሰሩበት መስሪያ ቤት/ባንክ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ምክንያት ተባረዋል። በነገረ ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ ጽሁፎችን የሚያቀርቡ ወጣት ፖለቲካኛ ናቸው። በጋራ ህዝቡን ማታገል እንደሚገባ በመገልጽ በተለትም ለሰማያዊና ለአንድነት ፓርቲ ጥሩ ያቀረቡበት ጽሁፍን ያንብቡ)
ለውጡ ይመጣል! ጥያቄው ግን ተዘጋጅተናል ወይ?
————————————————-
ስለ 1966ቱ ለውጥ ብዙ ተብሏል፡፡ በለውጡ ወቅት የነበሩትን ሰዎችም ሆነ ሌሎቹን የሚያስማማ አንድ ነገር ቢኖር የለውጡ ግብታዊነት እና ለውጡን ሊሸከም የሚችል ድርጅት በወቅቱ አለመኖሩ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ቆመን ለውጡ ገና ነው ብለን ብንዘናጋ እንደ ኃይሌ ፊዳ ልንሳሳት የምችልባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ይመስሉኛል (ሀይሌ ፊዳ ከብርሀነ መስቀል ጋር ባደረጉት ውይይት ለውጡ ገና ነው ብዙ አመታትንም ይፈልጋል ብሎ ነበረ)፡፡ ከዚያ ይልቅ ለውጡን ለመቀበል በሚያስችል ተክለ ሰውነት ላይ ለመገኘት ምን እናድርግ የሚለው ላይ መዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡
ብዙዎች በመኢሶን እና በኢህአፓ መካከል የነበረው ልዩነት ያለፈውን ትውልድ ዋጋ እንዳስከፈለው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ አንዳንዶች የሁለቱ ልዩነት የእናቸንፋለን እና የእናሸንፋለን የቃላት ጨዋታ ነበረ ሲሉ በሚያነሱት ሀሳብ ባልስማማም (ልዩነታቸው መሰረታዊ ነበር ብዬ ስለማምን) የሁለቱ ልዩነት ግን ትውልዱን ዋጋ ማስከፈሉን የማይቀበል ማንም ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡
ስለሁለቱ ልዩነት ሲነሳ ቢያንስ በሁለት ወቅቶች ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡
የመጀመሪያው ከለውጡ በፊት የነበረው እና ከለውጡም በኋላ እስከተወሰነ ድረስ አብሮ የዘለቀው የሁለቱ ፓርቲዎች የመደጋገፍ ጊዜ ነው፡፡ በአልጀርስ የነበረው የኢህአድ/ኢህአፓ መስራች ቡድን ከሀይሌ ፊዳው የመኢሶን መስራች ቡድን ጋር በአንዳንድ ነጥቦች ሳይስማሙ ቢለያዩም ልዩነታቸው ሰፊ የሚባል አልነበረም፡፡ ለዚህም ማሳያው የኢህአፓ ልሳን የነበረችው የዴሞክራሲያ የመጀመሪያ ዕትሞች እና የመኢሶን ልሳን የነበረችው የሰፊው ህዝብ ድምፅ ጋዜጣ የመጀመሪያ ዕትሞች በይዘት መመሳሰል እና በሀሳብ መደጋገፍ ነው፡፡ ይህ ሂደት እነ ሀይሌ ፊዳ ከውጪ ወደ ሀገር ቤት እስኪገቡ ድረስ የቀጠለ እንደነበርም ታሪክ መዝግቦ ያስቀመጠው ሀቅ ነው፡፡
ሁለተኛው ወቅት ደግሞ ለውጡ ከመጣ በኋላና እነ ሀይሌ ፊዳ ሀገር ቤት ከገቡ በኋላ ያለው እና በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ያለው ልዩነት መሰረታዊ እየሆነ የሄደበት እና በጣም የተለጠጠበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በመኢሶን እና በኢህአፓ አመራሮች መካከል ግንኑነት ለማድረግ የተሞከረ ቢሆንም (ለአብነትም ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ከዶ/ር ሀይሌ ፊዳ ጋር፤ ነገደ ጎበዜ ከአለማየሁ ሀይሌ(ደርግ ውስጥ ሰርጎ የገባ የኢህአፓ ሰው ነው ይባል ነበር) ጋር ተገናኝተው አውርተዋል) ከረፈደ በኋላ የተደረገ ውይይት በመሆኑ ያመጣው ለውጥ አልነበረም፡፡
በእኔ እይታ ለሁለቱ ድርጅቶች አለመስማማት አቢዩ ምክንያት ከለውጡ በኋላ ኢህአፓ ሰፊ ህዝባዊ መሰረት (ማስ ቤዝ) ማግኘቱ በመኢሶን በኩል ለደርግ ሂሳዊ ድጋፍ እየሰጡ መቀጠል ይሻላል ወደሚለው ሀሳብ እንዲሄዱ የገፋቸው ይመስለኛል፡፡ ከመነሻው የነበራቸውን አነስተኛ ልዩነት አጥብበው በጋራ ቢሄዱ ኖሮ አንዳቸው ተለይቶ ህዝባዊ መሰረት የሚገነባበት እና ሌላኛቸው ህዝባዊ መሰረት ለመያዝ ከወታደሩ ጋር የሚሰለፍበት ሁናቴ አይኖርም ነበር፡፡
ለማንኛውም ይህን ያነሳሁት በታሪኩ ላይ ለመነታረክ ሳይሆን ዛሬም ከታሪክ ሳንማር ያለፈውን ስሀተት እንዳንደግም ካለኝ ፍርሀት ነው፡፡
ዛሬ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም ሰማያዊ እና አንድነት በጋራ ሆነው ለሚመጣው ለውጥ ራሳቸውን ካላዘጋጁ በስተቀር ከለውጡ በኋላ ልዩነታቸውን አጥብበው ለውጡ ተፈጥሯዊ ይዘቱን ጠብቆ ለሀገር በሚጠቅም መልኩ ለማስቀጠል ይችላሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ ልዩነታቸውን አሁን ላይ ማጥበብ እና በጋራ መቆም ካልቻሉ ከለውጡ በኋላ እንደ ጠላት የሚተያዩበትም እድል እጅግ በጣም የሰፋ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ በተለይም ደግሞ ለውጡን ተከትሎ ከሁለት አንዳቸው ከፍ ያለ መስዋዕትነት የከፈሉ እንደሆነ፡፡
የተቃዋሚዎች በአንድ መቆም ለለውጡ ተዘጋጅቶ ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለውጡን ለማምጣትም የተሻለው እና አጭሩ መንገድ ነውና የየፓርቲዎቹ አመራሮች(በተለይም የሰማያዊ እና የአንድነት) ዛሬ ነገ ሳንል ቁጭ ብለን በመነጋገር ወደ አንድ የምንመጣበትን እና በጋራ ህዝቡን የምናታግልበትን መንገድ እንድንፈጥር ጥሪዬን አቀርባለሁ ፡፡
