የሰሞኑ ሹክሹክታ – የቅዳሜ ማስታወሻ (Tesfaye Gebreab)
ከድሬዳዋ ተነስተው ኤርትራ ቀይ ባህር ዳርቻያረፉት የኢትዮጵያ ሄሊኮፕተሮች ጉዳይ ለወያኔ ራስ ምታት ሆኖበት ሰንብቶአል። ሄሊኮፕተር ይዘው ኤርትራ የገቡት ኢትዮጵያውያን የአየር ሃይል አብራሪዎች ማንነት እና በወያኔ ላይ ያላቸው ተቃውሞ ምን እንደሆነ ገና አልታወቀም። በተያያዘ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ከማንኛውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ሽባ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። አማራ እና ኦሮሞ የጦር አይሮፕላን አብራሪዎች ከስራ ውጭ ተደርገዋል። የትግራይ አብራሪዎችና ቴክኒሻኖች ደ’ሞ በጣት የሚቆጠሩ በመሆናቸው አየር ሃይልን በትግራይ ሰዎች ብቻ ለማንቀሳቀስ አልተቻለም። በተለይም ክኒሻኖች በአብዛኛው አማራና ኦሮሞዎች በመሆናቸው ወያኔ ችግር ውስጥ ወድቆአል። የፌክ ፌደራሊዝም ውጤት ይኸው ነው።
ኦቦ ሌንጮ ለታ ለቀጣዩ ምርጫ ወደ ፊንፊኔ ያቀናል ሲባል ተሰንብቶ ነበር። እምን እንደደረሰ አልተከታተልኩትም። ሌንጮ ጠቅልሎ ቢገባ ግን ወያኔ የሚጎዳ እንጂ የሚጠቀም አይመስለኝም። እንኳን ሌንጮ ገብቶ መረራ ጉዲና እንኳ እያዋዛ ፈተና ውስጥ ጨምሯቸዋል። በቀጣዩ ምርጫ በመጠኑም ቢሆን ወያኔን ሊፈታተን የሚችለው መረራ ጉዲና ነው። ስልጣን ይገለብጣል ተብሎ ባይታመንም ጥቂት የፓርላማ ወንበሮችን ያገኝ ይሆናል። ሌንጮ ተሳክቶለት ፊንፊኔ ገብቶ አስማተኛውን የኦነግ ባንዴራ ማውለብለብ ቢችል የምርጫ ሜዳውን ሞቅ ደመቅ ባደረገው። ወያኔም ቢጫ ወባ በሽታው በተቀሰቀሰበት ነበር። በነገራችን ላይ “ODF” የሚለው ምህፃረ ቃል Oromia Defence Force መስሎ ይሰማኛል።
አሜሪካኖች ህወሃትን እየደገፉ መሆኑ አይካድም። ህወሃትም ቢሆን ለአሜሪካ ብብቱን ከፍቶ ሰጥቶአቸዋል። አሜሪካኖች በህወሃት አመራር ባገኙት ጥቅም ደስተኛ ቢሆኑም፤የወያኔ ስርአት በስልጣን እንዲቆይ ይፈልጋሉ ማለት ግን አይደለም። “አናሳ ብሄረሰብ በስልጣን ላይ ሊቆይ ከሚችለው በላይ ገዝታችሁዋል። ከዚህ በላይ መሄድ አትችሉም። ችግር ሳይገጥማችሁ ቦታውን ብትለቁ ይሻላል።” ብለው ደጋግመው መክረዋቸዋል። ወያኔ የህዝብ ድጋፍ ስለሌለው አገሪቱን ገፍቶ ገፍቶ ገደል ይጨምራታል ብለው ሊሰጉ ይችላሉ። አሜሪካኖች እንደ ሰማያዊ ፓርቲ ያሉትን ከጀርባ ደጋግፈው ወደ ስልጣን ለማምጣት እንደሚፈልጉ ይታወቃል። ስለ ኦሮምያ ነፃነት የሚያስቡ ወጣቶችን ግን አሜሪካኖች በጣም ይፈሯቸዋል። “በኢትዮጵያ አንድነት” የሚያምን፣ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል ወጣት ኦሮሞ ለማግኘት መከራቸውን ሲያዩ ሰንብተዋል ይባላል። የሚሳካላቸው አይደለም። በርግጥ በመጪው ዘመን የኦሮሞን ህዝብ በትክክል የሚወክል ሃይል ወደ ስልጣን ካልመጣ የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ምእራባውያኑ አስጠንተው ደርሰውበታል። ያም ሆኖ ኦሮሞዎች ካላቸው አቅም አንድ አስረኛውን እንኳ እንዳልተጠቀሙ ይታመናል።
የአንድነት ሃይሎች የፖለቲካ አካሄድ ቀልድ ይመስለኛል። አንዳርጋቸው ፅጌ፣ “ነፃነትን የማያውቅ ነፃአውጪ” ብሎ ነበር። “አንድነትን የማያውቁ አንድነቶች” ከፕሮፓጋንዳ ባሻገር የትም መሄድ አልቻሉም። ኢትዮጵያዊነት ባለቤት አጥቶአል። ህይወቱን ቀርቶ እንቅልፉን የሚሰዋለት እያጣ ነው።ጠጋ ብሎ ላያቸው “አንድነቶች” በጎንደርና በጎጃም፤ በወሎና በመንዝ ተከፋፍለው ሲሻኮቱ ይገኛሉ። የጎንደር – ሸዋ ሽኩቻቸውን ሳይፈቱ ኦጋዴን ኢትዮጵያዊነትን እንዲዘምር ይመኛሉ። ብዙውን ጊዜ የአማራ ፖለቲከኞች፣ “ኦሮሞ ወንድሞቻችን” ማለት ያበዛሉ። በአማራ ፖለቲከኞች ዘንድ፣ “ግማሽ ኦሮሞ ነኝ” ማለት ፋሽን ሆኖአል። በአንፃሩ የኦሮሞ ፖለቲከኞች፣ “አማራወንድሞቻችን” የሚል አባባል ሲጠቀሙ ሰምቼ አላውቅም። አንደኛው ተለማማጭ የመሰለበት ምክንያቱ ምንድነው? ከልብ ስላልሆነ ይመስለኛል። “ወንድሞቻችን” የሚለው አባባል የለበጣ ነው።የኦሮሞን ህዝብ ስነልቦና “የቡርቃ ዝምታ” በተባለው መፅሃፌ ጥሩ አድርጌ በመግለፄ እኔ የአማራ ህዝብ ባለውለታ እንደሆንኩ ይሰማኛል። አሁንም አማራ ፖለቲከኛ ወንድሞቼን በግልፅ መምከር እፈልጋለሁ። ጊዜ እያመለጠ ነው። የአማራ ፖለቲከኞች ከሽማግሌ ኦሮሞዎች ጋር ዛሬውኑ ተግባብተው ለመስራት ካልሞከሩ በርግጥም ጊዜ እያመለጣቸው ነው። ሽማግሌዎቹ ቢያንስ በኢትዮጵያዊነት ስር ኖረዋል። ወደውም ሆነ ተገደው ለባንዴራው ዘምረዋል። አዲሱ የኦሮሞ ትውልድ ግን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለሙን ባንዴራ አጥብቆ ይጠላዋል። አማርኛን ይጠየፋል። ‘ኢትዮጵያዊ ነኝ’ ማለት አይፈልግም። የአንድነት ሃይሎች ዛሬውኑ መባነን አለባቸው። ዮሃንስ መጥምቁ፣ “ከኔ በሁዋላ የሚመጣው በእሳት ያጠምቃችሁዋል!” እንዳለው እየመጣ ያለው የኦሮሚያ አዲሱ ትውልድ ከአበሻ ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር ስለመቻሉ እጠራጠራለሁ።
