የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሔሊኮፕተር ተጠልፎ አሰብ ማረፉ ተረጋገጠ

(ቃለየሱስ በቀለ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል ንብረት የሆነ ተዋጊ ሔሊኮፕተር ባለፈው ዓርብ ተጠልፎ ኤርትራ ግዛት አሰብ ማረፉ ተረጋገጠ፡፡ የዘወትር የበረራ ልምምድ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሩሲያ ሠራሽ ኤምአይ 35 ተዋጊ ሔሊኮፕተር ይዞ ወደ ኤርትራ የኮበለለው ዋና አብራሪ ሻምበል ሳሙኤል ግደይ፣ ይህንን ዓይነት ተግባር ይፈጽማል ብለው እንደማያስቡ ባልደረቦቹ ገልጸዋል፡፡ ከሻምበል ሳሙኤል ጋር በኢትዮጵያ አየር ኃይል አብረው የሠለጠኑና የሠሩ የሥራ ባልደረቦቹ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ግለሰቡ መልካም ባህሪ ያለውና በፖለቲካ አቋሙ ገለልተኛ የሚባል ነው፡፡ ‹‹እጅግ በጣም ጥሩ ሰው ነው፡፡ የመንግሥት ተቃዋሚ አልነበረም፡፡ ራሱን ከፖለቲካ ጉዳዮች የሚያገል፣ ሥራውን ብቻ የሚሠራና ልጆቹን በኃላፊነት የሚያሳድግ ሰው ነበር፤›› ብለው በድርጊቱ ግራ መጋባታቸውን ገልጸዋል፡፡ አክለውም በትንሽ ነገር የሚከፋና የሚደሰት፣ በቅጽበት የሚለዋወጥ ባህሪ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በግል ሕይወቱም የሚበሳጭበት ጉዳይ እንደነበርና አልፎ አልፎም በዚሁ ጉዳይ ይደበት እንደነበር አልሸሸጉም፡፡ ሻምበል ሳሙኤል ለሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ አየር ኃይል የገባው በ1994 ዓ.ም. ሲሆን፣ የቅጥር ውል የፈረመው በታህሳስ ወር 1995 ዓ.ም. ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ለ12 ዓመታት አገልግሏል፡፡ በ2003 ዓ.ም. የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ወደ ዳርፉር ሱዳን ያሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል አባል በመሆን ለአንድ ዓመት ያህል እንዳገለገለና በዚያም ተልዕኮ ዳጐስ ያለ ዶላር ይዞ መመለሱን ባልደረቦቹ ተናግረዋል፡፡ ሻምበል ሳሙኤል ተወልዶ ያደገው በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ መሆኑን፣ ወላጆቹ የመቀሌ ነዋሪ መሆናቸውን ባለቤቱና ሁለት ልጆቹ ቢሾፍቱ እንደሚኖሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡  ባለፈው ዓርብ ማለዳ ከረዳት አብራሪው መቶ አለቃ ቢልልኝ ደሳለኝና የበረራ ቴክኒሺያን […]