Ethiopia broadcasting authority undecided on whether to issue permit for private TV station ለግሉ ዘርፍ ቴሌቪዥን ቻናል የመስጠት ጉዳይ አልተወሰነም

ተጻፈ በ  

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን በተያዘው የበጀት ዓመት 15 አዳዲስ የቴሌቪዥን ቻናሎችን ለተጠቃሚዎች የማስተላለፍ ዕቅድ ቢኖረውም ለግሉ ዘርፍ መስጠቱን አላረጋገጠም፡፡

በአሁኑ ወቅት በብሔራዊ ደረጃ ካለው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቻናል በተጨማሪ 15 አዳዲስ ቻናሎችን፣ እንዲሁም ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚደረገው ሽግግር እየተጠናቀቀ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

በአምስት ዓመቱ የዕድገትና  ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የቴሌቪዥን ቻናሎች ለግል ዘርፍ የመስጠት ሐሳብ እንደሌለ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በግልጽ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን በሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ለግል ዘርፍ የቴሌቪዥን ቻናሎችን የመስጠት ሐሳብ አለ ወይ? ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ልዑል ሲመልሱ በጉዳዩ ላይ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን እነዚህን ጥያቄዎች የሚመልስ ጥናት እያካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ከጥናቱ በፊት የሚወሰነውን ውሳኔ ማወቅ እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡ 

ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን የተቋቋመበት አዋጅ ለግል ዘርፍ የቴሌቪዥን ፍሪኩዌንሲ መስጠት የሚፈቅድ ቢሆንም፣ ላለፉት 15 ዓመታት ይህንን ተግባራዊ ሳያደርግ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ቻናል በተጨማሪ 15 የቴሌቪዥን ፍሪኩዌንሲዎች ለመስጠት አቅዷል፡፡ የዚህ ፍሪኩዌንሲ ዋነኛ ተጠቃሚዎች ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ሲሆኑ፣ ለእነዚሁ አካላት 12 ፍሪኩዌንስ ይሰጣቸዋል፡፡ ቀሪዎቹን ፍሪኩዌንሶች ለምን ጠቀሜታ እንደሚውሉ አልታወቀም፡፡ 

በዚህ የበጀት ዓመት የቴሌቪዥን ፍሪኩዌንሲዎች ጥቅም ላይ ላይ ለማዋል በቅርቡ የመቀበያ መሣሪያዎች ግዥ ሊፈጸም እንደሆነ ታውቋል፡፡ አቶ ልዑል እንዳሉት አዳዲሶቹ ፍሪኩዌንሲዎች የሚስተናገዱባቸው መቀበያዎች ግዥ እንዴት  እንደሚፈጸም እየተካሄደ ያለው ጥናት ሲጠናቀቅ የሚወሰን ይሆናል፡፡ መቀበያ መሣሪያዎቹን በአገር ውስጥ ለመገጣጠም መታሰቡንም አቶ ልዑል ገልጸው፣ መሣሪያዎቹን የሚያቀርቡ ኩባንያዎችን ለመለየት በቅርቡ ጨረታ እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡

 በአገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ቻናሎች እንዲኖሩ የሚያደርገው ሥራ በብሔራዊ ደረጃ በተቋቋመ ኮሚቴ የሚመራ ሲሆን፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ኮሚቴውን እየመሩ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ ይህ ብሔራዊ ኮሚቴ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ፕሮጀክቱን አጠናቆ አየር ላይ የማዋል ዕቅድ መያዙ ታውቋል፡፡

ከእነዚህ 15 ቻናሎች ውስጥ 12 ያህሉን ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ይረከቡታል ተብሏል፡፡ በቀሪዎቹ ላይ እስካሁን ውሳኔ አልተሰጠም፡፡ አንድ የቴሌቪዥን ቻናል 24 ሰዓታት ስለሚኖሩት በበቂ ሁኔታ የሚተላለፉ ፕሮግራሞች ሊኖሩ ይገባል፡፡ የቻናል ተጠቃሚ ክልሎችን ባለሥልጣኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ማነጋገሩ ታውቋል፡፡ የቻናል ባለቤት የሚሆኑት አካላት ከወዲሁ ባለሙያዎችን እያዘጋጁና ፕሮግራሞችን እየቀረፁ መዘጋጀት እንዳለባቸው አቶ ልዑል አሳስበዋል፡፡ 

ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜላችሁን አስመዘግቡ።