የገንዘብ አቅም የፈተነው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ማኅበር

ሪፖርተር

ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በዘመነ መንግሥታቸው ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡት እንደነበርና ለዚህም እውን መሆን ራሳቸው የትምህርት ሚኒስትር እንደነበሩ ይወሳል፡፡

9a680faba7b2bfcaf0440e05426f8e79_Lከሕይወታቸው ፍፃሜ በኋላም የእሳቸውን ጅማሬ ለማስቀጠል በስማቸው መታሰቢያ ማኅበር ተቋቁሟል፡፡ ማኅበሩም በሕይወት ዘመናቸው ትኩረት ይሰጡት ለነበረው የትምህርት ዘርፍ በተቻለ መጠን ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በተለያዩ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙና በአካዴሚክ ዕውቀታቸው በጣም ጠንካራ ሆነው በቤተሰብ የኢኮኖሚው አቅም ማነስ ሳቢያ ወደ ኋላ የቀሩ ችግረኛ ተማሪዎችን፣ መታሰቢያ ማኅበሩ በመርዳት ላይ ይገኛል፡፡ ማኅበሩ እያከናወነ ስላለው ተግባርና ያጋጠመውን ተግዳሮት በተመለከተ የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑትን ሊቀ ካህናት ዓባይነህ አበበን፣ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- መታሰቢያ ማኅበሩ ከተቋቋመበት ቀን አንስቶ እስካሁን ስንት ችግረኛ ተማሪዎችን እንደረዳና ድጋፉንም አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችለውን የገቢ ምንጭ ከመፍጠር አኳያ ያለውን እንቅስቃሴ ቢያስረዱን፡-

ሊቀ ካህናት ዓባይነህ፡– ማኅበሩ ድጋፉን የሚሰጠው በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ኮሚቴ በማቋቋምና በማስጠናት ነው፡፡ በዚህ መልኩ የሕግ ዕውቅና አግኝቶ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ከ300 በላይ ችግረኛ ተማሪዎችን እየረዳ ለቁም ነገር አብቅቷል፡፡ ይህም ማለት በሜድስን፣ በኢንጂነሪንግ፣ በኢኮኖሚክስ ወዘተ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀው ራሳቸውን ከድህነት በማውጣት በተማሩት የሙያ መስክ አገሪቱን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ሌሎቹም ከ100 በላይ የሚሆኑ ችግረኛ ተማሪዎች በትምህርት ላይ ይገኛሉ፡፡ የመታሰቢያ ማኅበሩ አጀማመር ብዙ ችግረኛ ተማሪዎች እንዲረዱ በማድረግ ላይ ያተኩር ነበር፡፡ ነገር ግን የገንዘብ አቅሙ ውስን በመሆኑ የፈለገውን ያህል ለመርዳት አልቻለም፡፡ በየጊዜው ከተለያዩ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ለመታሰቢያ ማኅበሩ የሚቀርብለት የተማሪ ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ መታሰቢያ ማኅበሩ በየጉባዔው ይህንን ጉዳይ ለአባላቱ በማስተዋወቅና ብዙ ድጋፍ ሊገኝ የሚችልበትን መንገድ ሁሉም ጥረት እንዲያደርግ ከማሳሰብ የቦዘነበት ጊዜ የለም፡፡ ከዚህ አንፃር አንዳንድ አባላት በአንድ ጊዜ ከአሥር ሺሕ እስከ 100 ሺሕ ብር ድረስ በማውጣት ሲንቀሳቀሱ ይታያል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በ2006 በጀት ዓመት አባላትና አባላት ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖችን በተለያዩ መድረኮች በማሰባሰብ ግንዛቤ የመስጠትና በዚህም ወርኃዊና ዓመታዊ ክፍያቸውን እንዲያዋጡ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በዚሁ መነሻ ከመድረክ በተገኘው አቅጣጫ መሠረት ቦርዱ ዕቅድ ነድፎ ሲሄድበት የቆየውን እንቅስቃሴ በማጠናከር ከተለያዩ ግለሰቦች ለመታሰቢያ ማኅበሩ ዓመታዊ ዕቅድ ማስፈጸሚያ የሚሆን ከምን ጊዜውም የተሻለ ገንዘብ ለማሰባሰብ ተችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- ለአገር በቀል ማኅበራት በወጣው አዋጅ መሠረት ማኅበሩ እንዴት እየተንቀሳቀሰ ነው?

ሊቀ ካህናት ዓባይነህ፡– የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር አገር በቀል የበጐ አድራጐት ማኅበር ነው፡፡ መንግሥት ባወጣው አዋጅ መሠረት አገር በቀል ማኅበራት ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ የሚፈልጉትን ሙአለ ነዋይ ማግኘት የሚችሉት ከአገር ውስጥ 90 በመቶ ሆኖ ከውጭ አሥር በመቶ እንዲሆን በሕግ ተደንግጓል፡፡ የአገር ውስጥ ምንጭ የተለያዩ ስብሰባዎችን፣ የእራትና የምሳ ፕሮግራሞችን፣ እንዲሁም በትላልቅ ድርጅቶችና ባለሀብቶች ዙሪያ ተዘዋውሮ ድጋፍ በመጠየቅ በሚገኝ ዕርዳታ የሚሠራ ነው፡፡ ሁለተኛውና አሥር በመቶ ከውጭ ድጋፍ የሚገኘው የፕሮጀክት ፕሮፖዛል በማዘጋጀትና ፈንድ በመጠየቅ ነው፡፡ እነዚህን ሁለት ዓበይት ጉዳዮች አሟጥጦ ለመጠቀም ቦርዱና ማኔጅመንቱ የተቻላቸውን ያህል ጥረት በማድረግ ከአገር ውስጥ ለሰው ኃይል አስተዳደር መምሪያ ዝግጅትና ድረ ገጽ ማሠሪያ 25,000 ብር፤ እንዲሁም ጽሕፈት ቤቱን በሰው ኃይል ለማጠናከር እንዲቻል የፕሮጀክት ፕሮፖዛል አዘጋጅቶ ለክርስቲያን በጐ አድራጐትና ልማት ማኅበራት ኅብረት በማቅረብ ለሁለቱ ፕሮጀክቶች በድምሩ 121,000 ብር ማግኘት ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል የሥራ አመራር ቦርድ የአጭር ጊዜ ዕቅድ በመንደፍ በአገር ውስጥና በውጭ የተሟላ ድጋፍ ማግኘት እንድንችል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አበረታች ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የገንዘብ አጠቃቀማችሁ በምን መልኩ እየተከናወነ ነው ማለት ይቻላል?

ሊቀ ካህናት ዓባይነህ፡– በአንድ ከፍተኛ ተቋም ውስጥ ቅድሚያና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የገንዘብ አጠባበቅና አጠቃቀም ደረጃውን በጠበቀና በሙያው በሠለጠነ የሰው ኃይል እንዲመራ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ በኩል መታሰቢያ ማኅበሩ ብርቱ ጥንቃቄ በማድረግ ሙያና ክህሎት ባላቸው ሠራተኞች እንዲመራ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት በ2006 በጀት ዓመት የመታሰቢያ ማኅበሩ ከልዩ ልዩ ገቢ 1,339,267 ከ 49 ሳንቲም አግኝቷል፡፡ ከዚህም ውስጥ ለዓላማ ማስፈጸሚያና ለሌሎች ተግባራት ማከናወኛ 392,066 ብር ከ14 ሳንቲም ወጪ ሆኗል፡፡ ለ2007 በጀት ዓመት ደግሞ በዕቅድ ለተያዙት ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ የሚሆን 376,380 ብር፣ ለ100 ተማሪዎች አበልና ትራንስፖት 120 ሺሕ ብር በድምሩ 496,380 ብር ተፈቅዷል፡፡

ሪፖርተር፡- መታሰቢያ ማኅበሩ በሚያካሂደው እንቅስቃሴ ዙሪያ ያጋጠሙ ችግሮችን ቢያብራሩልን?

ሊቀ ካህናት ዓባይነህ፡- በእንቅስቃሴያችን ውስጥ ጐላ ያለውን ሥፍራ ይዞ እየተሄደበት ያለው የነፃ ትምህርቱ ዘርፍ ነው፡፡ ይኼኛው ዘርፍ ከመንግሥት አስተዳደር እስከ ክልል አስተዳደር ድረስ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የድጋፍ እንቅስቃሴ እንደመሆኑ መጠን ዩኒቨርሲቲዎቹ በየጊዜው ሊረዱ የሚገቡ ተማሪዎችን ቁጥር ለይቶ በማሳወቅ ረገድ የሚታየው የጊዜ መዘግየትና ይኼው ከተከናወነ በኋላ ደግሞ ዕድሉን ላገኙ ተማሪዎች የሚላከውን ገንዘብ ለዕድለኛ ተማሪዎች አድርሶ ማስረጃዎችን በጊዜ ያለመላክ ጐልተው ከሚታዩ ችግሮች ዋናው ነው፡፡ የመታሰቢያ ማኅበሩ የሚጠቀምበት ኪራይ ቤት እጅግ ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ አስፈላጊውን መረጃም ሆነ አገልግሎት ለመስጠት የማይቻልበት ደረጃ ላይ መሆኑም ተጠቃሽ ችግር ነው፡፡ ስኮላርሺፕ ከምንሰጣቸው ተማሪዎች ጋር በቅርብ ተገናኝቶ ለመወያየትና ስለግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር ዓላማ ለማስረዳት የሰው ኃይል ሆነ የገንዘብ እጥረት መኖሩ አንዱ ችግር ነው፡፡ ሌላው ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ሥራ ዓለም የሚገቡ የስኮላርሺፕ ተጠቃሚዎች ከማኅበሩ ጋር የሚኖራቸውን ትስስር ሳይቋረጥ እንዳለ ማስቀጠል የሚቻልበት ሁኔታ መመሥረት አለመቻል እንደ ችግር ሊታይ ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ ለወደፊቱ እንደ መፍትሔ ሊያገለግል ይችላል ተብሎ ተስፋ የተደረገበት የመታሰቢያ ማኅበሩ ድረ ገጽ ሥራ ሲጠናቀቅ ለትስስሩ መዳበር በመፍትሔ አማራጭነት ያገለግላል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- መታሰቢያ ማኅበሩ በደርግ የተወረሱት የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጐ አድራጐት ድርጅት ንብረቶች እንዲመለሱለት የጠየቀው ከምን ደረሰ? 

ሊቀ ካህናት ዓባይነህ፡– ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በዘመነ መንግሥታቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጠቀሜታ ይውል ዘንድ የተለያዩ በጐ አድራጐት ድርጅቶችን በማቋቋምና ቀጣይነት ያለው የገቢ ምንጭ በመፍጠር ሲታደጉ መቆየታቸው እሙን ነው፡፡ ሆኖም በወደቀው የደርግ መንግሥት ስለተወረሱ ቀጣይነት ያለው ሕዝባዊና አገራዊ ጠቀሜታቸው ተቋርጧል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ በጐ ሥራ መቀጠል አለበት በሚል መንፈስ፣ በስማቸው በተቋቋመው መታሰቢያ ማኅበር ስም የተወረሱ ድርጅቶች እንዲመለሱልንና ለሕዝብ ጠቀሜታ እንድናውላቸው የሚል ጥያቄ ለመንግሥት አቅርበን ምላሽ ማግኘት እንችል ዘንድ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ እናገኛለን፡፡ ምላሽ በሚገኝበት ወቅት ከቤት ኪራይ ነፃ እንሆናለን፡፡ ከቤት ኪራይ ነፃ ስንሆን ደግሞ ለዚሁ እናውለው የነበረውን ገንዘብ ለትምህርት ዘርፍ እናውለዋለን ብለን እንገምታለን፡፡ ጥያቄውንም ያቀረብነው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ሲሆን፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስም ከጐናችን በመቆም ብዙ ድጋፍ አድርገውልናል፡፡ ለመንግሥትም አሳስበውልናል፡፡ አሁንም ባሉበት ሁኔታ ብርቱ ድጋፍ እያደረጉልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጥያቄው የሚሳካ ይመስሎታል?

ሊቀ ካህናት ዓባይነህ፡- ይሳካል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካና ለዓለም ያበረከቱት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ አፍሪካውያን ለእሳቸው ያላቸው ፍቅርና አክብሮት ለየት ያለ ነው፡፡ እንደውም በስማቸው አንድ መታሰቢያ አለመቆሙ አፍሪካውያን በየጊዜው በቁጭት የሚያነሱት ጉዳይ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ለቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከሕይወት ዘመናቸው ፍፃሜ በኋላ ምን ሠሩ? ምን አደረጉ? እያሉ በጉጉት የሚጠበቅ አጀንዳ ሆኗል፡፡ ይኼም ጉዳዩ በመንግሥት በኩል ቶሎ እልባት ያገኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ እንዲመለሰለት የጠየቀው ‹ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በጐ አድራጐት ድርጅት ያቋቋማቸውን የገቢ ምንጮች በሙሉ ነው? ወይስ የተወሰነውን ነው?

ሊቀ ካህናት ዓባይነህ፡– እኛ የጠየቅነው ሁሉንም ሳይሆን ከግዮን ሆቴል በታች ያለው የቀድሞ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የነበረበትንና አሁን የሀድያ ሱፐር ማርኬት ያለበትን ሕንፃ ብቻ ነው፡፡ በቀድሞ ሥርዓት ተወርሰው የነበሩ ንብረቶች ለበጐ አድራጐት ድርጅቶቻቸው ተመልሰዋል፡፡ አለአግባብ የተወረሰባቸው የግለሰቦች ንብረትም መንግሥት ባቋቋመው ግብረ ኃይል እየተጠና እንዲመለስላቸው የተደረጉ አሉ፡፡ የመታሰቢያ ማኅበሩም ጥያቄ ከዚህ ውጭ አይደለም፡፡ መንግሥት ከሕግ አኳያም ሆነ ከሌሎች አዋጆች ጋር አገናዝቦ አይገባም ብሎ ይወስናል ብለን አንጠብቅም፡፡ መንግሥት እንደውም የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ ያደርጋል ብለን የምንጠብቀው ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ሲንቀሳቀስ የሚስተዋለው በአገር ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ዳያስፖራውን ሊያቅፍ አልቻለም ይባላል፡- 

ሊቀ ካህናት ዓባይነህ፡- ቦርዱ በዚህ ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ በሰፊው ከተወያየ በኋላ በክቡር ልጅ ሚካኤል መንገሻ ሥዩም የሚመራ ቡድን በአውሮፓና በአሜሪካ እየተንቀሳቀሰ አባላትን የማሰባሰብና ማኅበሩንም በየአገሩ የማጠናከር ሥራ እንዲያካሂድ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ቡድኑም በቅርቡ ሥራውን  ይጀምራል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ይህ እውን ከሆነ የብዙ ተማሪዎች ስኮላርሺፕ ጥያቄ ይፈታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በአገር ውስጥ ደግሞ ዶ/ር ዳዊት ዘውዴና ልዑል በዕደ ማርያም መኰንን ማኅበሩን የማጠናከር ሥራ በስፋት እንዲሄዱበት ቦርዱ ከስምምነት ላይ ደርሷል፡፡