ድፍረት፡ በኢትዮጵያ የፊልም ጠለፋ፣
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
(ዘግይቶ የተተርጎመ )
በአንድ መንደር ውስጥ የምትገኝን ወጣት ልጃገረድ ጠልፎ በማግባት እና በአንድ ከተማ በሚኖር የፊልም ባለሙያ በሚደረግ የፊልም “ጠለፋ” መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? “ድፍረት” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የአማርኛ ትርጉም ሙሉ ፊልም ከሰውነት ውጭ፣ ኢሰብአዊ እና ኋላቀር በሆነ መልኩ በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚፈጸም ጎጂ ልማዳዊ የጠለፋ ድርጊት ወይም ደግሞ የልጅ ሙሽራዎች ጠለፋ ሲሆን ይህ ፊልም ሒሩት (ትዝታ ሀገሬ ከላይ ሰንዳንስ በሚለው ማስታወቂያ ላይ ፎቶግራፏ የሚታዬው) በምትባል ወጣት ልጃገረድ እውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ በመዘጋጀት ለዕይታ የበቃ ፊልም ነው፡፡ (“ድፍረት” የሚለው ቃል ብዙ ትርጉሞች ያሉት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ደፋርነት፣ ሴትን አስገድዶ መድፈር፣ በማህበረሰቡ ውስጥ እንድትዋረድ ማድረግ እና ተስፋዋን ማጨለም የሚሉትን ያካትታል፡፡) ይህ ድፍረት የተባለው ፊልም የተደረሰው ኢትዮጵያዊ የፊልም ባለሙያ በሆነው በዘረሰናይ ብርሀኔ መሀሪ ሲሆን የቅንብር ስራ በመስራት እና ለዕይታ እንዲበቃ የተደረገው በአንጌሊና ጆሊ ነው፡፡ ይህ “ድፍረት” የተባለው ተውኔት በሰንዳንስ የፊልም ክብረበዓል ላይ ቀርቦ የዓለም የሲኒማ የትወና ውድድር/World Cinema Dramatic Competition እና የበርሊን ዓለም አቀፍ የፊልም ክብረ በዓል/the Berlin International Film Festival በሁለቱም የ2014 የተመልካቾች ሽልማት/Audience Award አሸናፊ ሆኗል፡፡ ይህ ፊልም በዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ አካባቢዎች፣ በአውሮፓ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በእስራኤል እና በአውስትራሊያ ለእይታ በቅቷል፡፡ (የድፍረት ተውኔት ደራሲ ከሆነው ዘረሰናይ ጋር የተደረገውን አስደሳች የሆነ ውይይት እና ልዩ በሆኑት የኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች የቀረበውን ትችት ለማየት በዩቲዩብ/You Tube እዚህ ጋ ይጫኑ፡፡)
በፊልሙ ላይ እንደሚታዬው ድፍረት ከትምህርት ቤት ወደ መኖሪያ ቤቷ በመመለስ ላይ ባለች አንዲት ወጣት ልጃገረድ ላይ ከዕለታት በአንዱ ቀን ከመካከላቸው አንዱ ቀደም ሲል ልጅቷን ለማግባት ጥያቄ አቅርቦ ፈቃደኝነቷን ያላገኘው ሰው ጭምር ሆነው በሰባት መሳሪያ በታጠቁ ወንዶች ተጠልፋ መወሰዷን የሚተርክ ፊልም ነው፡፡ በዚያኑ ዕለት ምሽት በጎጆ ሳር ቤት ውስጥ ተዘግቶባት በግዳጅ እንድታገባው በሚፈልገው ጎረምሳ የግዳጅ የግብረ ስጋ ግንኙነት ተፈጸመባት፡፡ ሆኖም ግን በማግስቱ የጠላፊዋን ጠብመንጃ ከቤት ከግድግዳው ስር ከማዕዘኑ ስር አንስታ በመያዝ አምልጣ በምትሄድበት ጊዜ ሲከተላት በማስጠንቀቅ የማይመለስ መሆኑን ስተገነዘብ እራሷን ለማዳን ስትል ተኩሳ የገደለችው መሆኑን ያሳያል፡፡ ሒሩት የፈለገውን ያህል የግዳጅ ወሲብ ቢፈጸምባት እና ብትደበደብም የአካባቢው የፍትህ አካላት ነፍስ በማጥፋቷ ምክንያት በሞት እንድትቀጣ ብይን ሰጡ እናም ከእርሷ የጠለፋ የሞት ሰለባ ጋር አብራ ተቀበረች)፡፡ (ይኸ ኋላቀር የሆነ የጠለፋ ወንጀል ወይም ደግሞ በልጃገረዶች ላይ ጠለፋ እና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል መፈጸም እንዲሁም ያለዕድሜ ጋብቻ መፈጸም በቸልተኝነት በኢትዮጵያ ብቻ የተተወ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ይህ አስቀያሚ ድርጊት በብዙ የአፍሪካ አገሮችም ጭምር የሚተገበር ነው፡፡ (በዓለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ ያለዕድሜ ጋብቻ ከሚፈጸምባቸው 20 አገሮች መካከል 15ቱ የሚገኙት በአፍሪካ ውስጥ ነው፡፡) ለምንም የማትበገረዋ የህግ ባለሙያ እና የህግ አገልግሎት ድጋፍ የሚሰጠውን ቡድኗን አቋቁማ በመንቀሳቀስ ላይ የምትገኘው መዓዛ አሸናፊ (ሜሮን ጌትነት) የሒሩትን ጉዳይ ለመከላከል የህግ አገልግሎት በመስጠት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ድፍረት የተሰኘው ፊልም በኢትዮጵያ በዘመናዊው የህግ አገልግሎት እና በባህላዊው ኋላቀር ህግ መካከል ያለውን ውጥረት እና በኢትዮጵያ በተለያዩ የገጠር አካባቢዎች በሚኖሩ ሴቶች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጭቆና በግልጽ ያመላክታል፡፡
በየትኛውም መለኪያ ቢሆን ይህ ፊልም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለውን ገዥ አካል የፖለቲካ ሁኔታ ወይም ደግሞ በእርሱ ላይ የሚደረግን ትችት አያመላክትም፡፡ ፊልሙ ገዥውን አካል በጨረፍታ ለመጥረብ ወይም ደግሞ በመጥፎ ሁኔታ ላይ ያለ መሆኑን አያመላክትም፡፡ እንደ ሰንዳንስ የፊልም ክብረበዓል/Sundance Film Festival ዘገባ ከሆነ “ኢትዮጵያዊ ትውልድ ያለው ደራሲ እና ዳይሬክተር ዘረሰናይ ብርሀኔ መሀሪ ወደ እኩልነት መብት የሚያመጣውን በሀገሪቱ ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ችግር ለማስወገድ የሚያስችለውን የሽግግር ውስብስብ ሁኔታ ለማፋጠን እና ለማሳለጥ ድፍረትን የተላበሰው አዲሱ ወጣት ትውልድ ለጉዳዩ እራሱን ባለቤት በማድረግ እንዴት ማስወገድ እንደሚችል እጅግ በጣም ባማረ እና በተዋበ አቀራረብ ከሽኖ እና መጥኖ አቅርቦታል“ ብሎታል፡፡ እኛም ይደልዎ! ብለናል፡፡ በሁፊንግተን ፖስት ድረ ገጽ የተለቀቀውን ስንመለከት ሒሩት እና ጠበቃዋ መዓዛ አሸናፊ በጉዳዩ ላይ እንዴት እንደሄዱበት እና በኢትዮጵያ ጥንታዊ በሆነው የጠለፋ ጋብቻ ልምድ ላይ ተንሰራፍተው የሚገኙትን የህግ ተግዳሮቶች በማሸነፍ እንዴት ለስኬት እንደበቁ ያሳያል፡፡ በሒሩት ጉዳይ ላይ የተሰራው ፊልም ድፍረትን የተቀላቀለበት ጊዜ በመፍጠር በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ አዲስ እና የተሻለ ምዕራፍ ይከፍታል፡፡
የፊልም ባለሙያ የሆነው ዘረሰናይ ይህ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የፊልም ስራ ለምን ለበርካታ ወራት ለዕይታ እንዳይቀርብ ታግዶ እንደቆዬ እ.ኤ.አ ማርች 2014 ባደረገው ንግግሩ ምክንያቱን ጠቁሟል፡፡ ዘረሰናይ ከኢትዮጵያ በድፍረት ፊልም የዓለም ቁንጮ ይሆናል የሚል ግምት አለ፡፡ ሆኖም ግን ፊልሙ ገና ከመጀመሪያው ለዕይታ መቅረብ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በድንገት እና ሰፊ ዓለም አቀፋዊነት ሙገሳን በተላበሰ እና ፍጹም በሆነ መልኩ አድናቆትን ተችሮት ነበር፡፡ ዘረሰናይ ሁኔታውን እንዲህ በማለት ገልጾታል፣
“የፊልም ስራውን ቆርጠን እና ቀጣጥለን የጨረስነው እ.ኤ.አ ጃንዋሪ 2014 ነበር፡፡ እናም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሰንዳንስ ተቀባይነትን አግኝተናል፡፡ ስለሆነም ሰንዳንስ መሄድ ነበረብን፡፡ ከዚያም ከአምስት ቀናት በኋላ በርሊን ውስጥ ነበር፡፡ በመሆኑም ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ በእርግጠኝነት ጊዜው አልነበረንም፡፡ ምክንያቱም ስርዓት እንዲይዝ ማድረግ ነበረብን… ስርዓት ሲባል የመክፈቻ ሂደትን መፈጸም፣ የስራው ዋና ባለቤትነትን ማረጋገጥ እና እውቅና መስጠት፣ ተዋናዮችን ማሳወቅ፣ ፊልሙ ለዚህ እንዲበቃ ድጋፍ ያደረጉትን እንዲታወቁ ማድረግ፣ በዚህ ፊልም ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ላሳዩት ሰዎች በምረቃ በዓሉ ላይ እንዲገኙ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ ፍላጎት ያሳዩትን በመለየት በብዙሀን መገናኛ ጥሪ ማስተላለፍ” ነበር፡፡
ዘረሰናይ ቃሉን አክብሮ ጸጥ በማለት እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 2014 ይከናወናል በሚል “የኢትዮጵያ የአሸናፊት ስርዓትን” ሲጠባበቅ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ባልጠበቀው መልኩ ጉዳት እንዲደርስበት ተደርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የወሮበላ ስብስብ ገዥ አካል ፊልሙ እንዳይታይ መሰረተቢስ ክልከላ እና የበቀል እርምጃ ይወስድብኛል የሚል እምነት አልነበረውም፣ እንዲያውም ጉዳዩን ቀለል አድርጎ ተመልክቶት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ጃንዋሪ 2014 የሰንዳንስ የፊልም ክብረ በዓል/Sundance Film Festival ዳይሬክተር ከሆኑት ከሮጀር ሮስ ዊሊያም ጋር በተደረገ ቃለ ምልልስ በድፍረት ፊልም አወዛጋቢነት ሁኔታ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ቢታይ ሊያሳግድ ይችል አይችል እንደሆነ ዘረሰናይ ተጠይቆ ነበር፡፡ ዘረሰናይ ሙሉ በሙሉ በእራሱ ላይ መተማመንን በተላበሰ ሁኔታ ምንም ዓይነት ችግር አይኖርም የሚል ምላሽ ነበር የሰጠው፡፡
ዊሊያም፡ በጣም አንገብጋቢ የሆነ ጉዳይ አለ (የህጻናት ሙሽራ ጠለፋዎቸ)፣ በጣም ውስብስብ የሆነ ጉዳይ፡፡ ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ አወዛጋቢ ነገር ሊሆን ይችላል፡፡
ዘረሰናይ፡ ይህ በእውኑ ዓለም የተፈጸመ እውነተኛ የሆነ ታሪክ ነው፣ እናም ስራ ላይ ህዝቦች ተሳትፈውበታል፣ ጉዳዩ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ እና በጋዜጦች ከተላለፈ በኋላም ድምጾቻቸውንም ሰጥተውበታል፡፡ ይህንን ፊልም እንደገና ህይወት ያለው ለማድረግ ከዚህ በኋላ የሚገጥም ችግር ይኖራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ እንዲያውም ይኸ ጉዳይ ለእኔ አሳሳቢዬ አይደለም፡፡ ይልቁንም ለእኔ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ ይቀርባል ብዬ የማስበው አንዱ እና ብቸኛው ጉዳይ እንዲሁም እኛንም በተወሰነ መልኩ ሊገዳደረን የሚችለው ጉዳይ በተለዬ የፊልም አሰራር አቀራረብ ተመልካቹን ህዝብ እንዴት ወደ ፊልሙ መሳብ እና ማሳተፍ እንደሚቻል ከማድረጉ ላይ ነው… ስለዚህ ጉዳይ ጥሩ ስሜት ይሰማኛል፡፡
ዘረሰናይ የዕኩይ ምግባር አፍላቂ የወሮበሎች ጭንቅላት ባለቤቶችን በውል የተገነዘበ እና ያጤነ አይመስልም፡፡ ዘረሰናይ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው የወሮበላ አገዛዝ በሀገር ፍቅር ስሜት ተነሳስቶ ይህ ፊልም ቢታይ ካለው ሀገራዊ ጠቀሜታ አንጻር ህዝቤን ሊያስተምር ይችላል በሚል ቀና መንፈስ በመመራት በሀገሪቱ ውስጥ እንዲታይ ይፈቅዳል የሚል የዋህ እምነት ነበረው፡፡ እጅግ በጣም ሲበዛ ተስፈኛ ነው፡፡ በመሆኑም ወጣቱ የፊልም ባለሙያ አዛውንት የሆኑትን የእስኮትላንድ ዜጋ የሮበርት በርንስን እንዲህ የሚለውን የጠበብትነት ስንኝ እንዲያሰላስል አስገድዶታል፣ “መሰረቱ በጥሩ ሁኔታ የተጣለ አጭር ልብወለድ/ሁልጊዜ መጥፎ ነገር ይገጥመዋል/እናም የተረፈን ነገር የለም የተረፈን ነገር ቢኖር ሀዘን እና ስቃይ ነው/ ደስታን ለተላበሰ ቃልኪዳን!“
እንደዚሁም ሁሉ ዘረሰናይ በመጋቢት ወር ቃልኪዳን ግብቶለት የነበረው እንዲሁም እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 4/2014 ለተመልካች እይታ እንዲቀርብ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው የድፍረት ፊልም ተጠባባቂ እና ዋና ተዋንያን እንደዚሁም ፊልሙን ለማየት በቦታው ተገኝተው የነበሩት ተመልካቾች ደስታ ወደ ሀዘን፣ ስቃይ እና ውርደት ተቀይሯል፡፡ በእርግጠኝነት ድፍረት በኢትዮጵ ያለው ገዥ አካል ምን ያህል ድፍረት የለሽ መሆኑን፣ ቦቅቧቃ ፈሪ እና እርባና የለሽ ለመሆኑ የመጨረሻ ማሳያ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ፊልሙ ለተመልካች ዕይታ ከመቅረቡ በፊት በዩቲዩብ ቪዲዮ እንደታዬው ሊታመን በማይልችል መልኩ ዘረሰናይ ግራ በተጋባ ሁኔታ፣ ውርደትን በተላበሰ መልኩ እና ደጋግሞ ይቅርታ በመጠዬቅ በአንድ እጁ ልጁን በመያዝ እና በሌላኛው እጁ የድምጽ ማጉያውን በመያዝ ከመድረክ ላይ ሆኖ ለታዳሚው የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጠ፡
የተከበራችሁ እንግዶች፣ አምባሳደሮች፣ ይህንን ፊልም እንድናቆም በፖሊስ ትዕዛዝ ተሰጥቶናል ምክንያቱም ከዚህ ጋር የተያዘ የፍርድ ቤት ጉዳይ አለ፡፡ ከዚህ በፊት የተነገረን ነገር የለም፡፡ የባህል ሚኒስቴር እናም መንግስት ስለዚህ ጉዳይ ያውቃል ማለት ነው፡፡ ይህንን ስንሰማ ለመጀመሪያ ጊዚያችን ነው፡፡ ግልጽ የሆነ ጥቃት ነው እየተፈጸመብን ያለው፡፡ ይህ ሁኔታ በመፈጠሩ በእውነቱ ከልብ አዝናለሁ እናም በሌላ ጊዜ እንደምንገናኝ ተስፋ አደርጋለሁ…
ፊልሙ ለእይታ ለመብቃት የሰከንዶቸ (የደቂቃም አይሞላም) ጊዜ ሲቀረው በጣም ድንገተኛ እና ህገወጥ በሆነ መልኩ ፊልሙ ለእይታ እንዳይቀርብ የታገደ መሆኑ በተመልካቹ ዘንድ ሲሰማ ተመልካቹ በመብረቅ የተመታ ያህል ባለበት ደርቆ ቀረ፡፡ ከአዳራሹ በጠርዝ በኩል ባለው ተመልካች ዘንድ ከፍተኛ በሆነ ጩኸት የታጀበ ትርምስ ተፈጠረ፡፡ እንዲሁም እልህ እና ንዴት በተቀላቀለበት መልኩ በዘረሰናይ ላይ የደረሰውን ሀዘን እና ውርደት በሚቃወም ስሜት ተመልካቹ ለእርሱ ያለውን ድጋፍ ገለጸ፡፡ ቆንጆዋ ወጣት የፊልም ተዋናይ ሜሮን ጌትነት በድንጋጤ በድን ሆና ትንፍሽ ሳትል ሄዳ ተቀመጠች፡፡ በግልጽ ሊታይ በሚችል መልኩ በድን ሆና እና ግራ ተጋባች፡፡ ከመድረኩ የሰማችው ነገር ሊታመን እንደማይችል ውሸት መሆኑን በመገመት ሃሳቧን ለማካፈል በሚል ሰው ለማግኘት በአይኗ ማማተር ጀመረች፡፡ ማንንም አላገኘችም እናም ከመጥፎ የሌሊት ቅዠቷ ጋር እንዳለች ያህል ቆጠረችው፡፡ በዚያ አስደንጋጭ የመድረክ ማሳሰቢያ ሁሉም በድን ሆኖ ደንግጧል፡፡ ከሜሮን በስተጀርባ በኩል ያሉ በጣም የተበሳጩ ሴቶች እንዲህ በማለት እርስ በእርሳቸው ጥያቄዎቸን መወራወር ጀመሩ፡፡
ለምን? እኮ ለምን? እንዲህ ያለ ድርጊት የሚሰራው ለምንድን ነው? ሜሮን ከተቀመጠችበት ቦታ ሆና በልማዳዊው የጸሎት አቀራረብ ዓይነት የማይሳነው አምላክ በዚህ አስደንጋጭ እና በሀገር ላይም ታላቅ ውርደትን ሊያስከትል በሚችል ሰይጣናዊ ድርጊት ላይ እጁን እንዲያስገባ እና ፍትህን በመስጠት ህዝቡን ከብስጭት ሀገሪቱን ከውርደት እንዲታደግ በሚማጸን መልኩ የእጅ መዳፎቿን ጠበቅ አድርጋ በመያዝ ወደ ላይ አንጋጠጠች፡፡ አንድ ማንንቱ በውል ያልታወቀ ሰው በዚህ አስደንጋጭ ሁኔታ ላይ ምን እንደሚሰማት ጥያቄ አቀረበላት፡፡ (አንድ ሰው ልቡ ከዓለም እይታ ላይ ተነቅሎ እንዲወገድ ከተደረገ በኋላ እንዴት ያለ ስሜት ሊሰማው ይችላል?)
ሜሮን በግልጽ በሚታይ መልኩ በተሰበረ ልብ ውስጥ ናት፡፡ ሆኖም ግን ጸጥታን የተጎናጸፈ እና ጀግንነትን የሚያንጸባርቅ ዓይነት ገጽታዋን ታሳያለች፡፡ ንዴቷን ድንጋጤዋን ለመደበቅ ትግል ስታደርግ በግልጽ ትታያለች፡፡ ከእንባዎቿ ጋር እፈሳለሁ አትፈሱም ተንቅንቅ ገጥመዋል፡፡ ሆኖም ግን በተሰበረ ልብ ውስጥ ያለች ብትመስልም እርሷ ግን በፍጹም የተሰበረ መንፈስ እና ልብ ውስጥ አይደለችም፡፡ በዚህ አስደንጋጭ ድርጊት ላይ ምን እንደተሰማት ጥያቄ ላቀረበላት ሰው ሙሉ በሙሉ በእራስ መተማመን ስሜት እና ክበርን በተላበሰ መልኩ እንዲህ በማለት የጀግና እና ስኬታማ ሴት ምላሽ መልሳለች፣ “የማውቀው ነገር የለም፡፡ ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ ምንም ዓይነት ነገር መናገር አልችልም፡፡ ምን እንደተደረገ የማውቀው ነገር የለም፡፡“ ከዚህ በኋላ የስቃይ/ግርፋት ሰለባ ከገራፊው ፊት እንደሚያደርገው ሁሉ ታጥፈው የነበሩ የጸሎት እጆቿን ከፈተቻቸው፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው በተረጋጋ መንፈስ ሜሮን ለጥያቄዎቹ ምላሽ እንድትሰጥ ለማሳመን ሞከረ፡፡ “ህዝቡ የፊልሙን መታዬት በከፍተኛ ጉጉት ይጠባበቅ ነበር፡፡ ህዝቡ ይህንን የተሰቀለ ስሜት ይዞ በጉጉት ለማየት ከመምጣቱ በፊት ማስቆም አትችሉም ነበርን?“ ሜሮን አሁንም ግረማ ሞገስን በተላበሰ መልኩ በተረጋጋ መንፈስ፣ ጭንቀትን ባስወገደ ሁኔታ እና በጥሩ አንደበት እንዲህ በማለት ምላሽ ሰጠች፣ “ልናገር የምችለው ምንም ነገር የለም፡፡ የትወና ሙያውን እንደ ሙያ ሊያከብሩ ይገባ ነበር፡፡ ይህ ተውኔት ለዕይታ እንዲቀርብ ዕቅድ ከመውጣቱ በፊት ሊያቆሙት እና ሊያግዱት ይችሉ ነበር፡፡ ወይም ደግሞ በተያዘለት ዕቅድ መሰረት ለዕይታ ከቀረበ በኋላ ሊያግዱት ይችሉ ነበር፡፡ በእውነት በዚህ ድርጊት በጣም አዝኛለሁ፡፡“ ሜሮን በእነዚህ ጥቂት፣ የተመጠኑ እና ውብ ቃላት የዚህን አውሬ የገዥ አካል ታሪክ ቁልጭ አድርጋ አሳይታለች፡፡ በእርሷ እስከዛሬ ድረስ እንደዚህ ባለ ሁኔታ ኮርቸባት አላውቅም ነበር!
የተጠሩ ተጋባዥ እንግዶች ሁሉ በጣሙን እንደሚበሳጩ ጥያቄ የለውም፡፡ በቪዲዮው ይታይ እንደነበረው የእያንዳንዱ ሰው ፊት የተለየ ስሜትን ያንጸባርቅ ነበር፡፡ የእያንዳንዱ ሰው ፊት ቁጣ፣ የታመቀ ግንፍልተኝነት፣ ፍጹም የሆነ ብስጭት፣ አጠቃላይ ሀዘን፣ ጽኑ የጥላቻ መንፈስ፣ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ውርደት፣ አጠቃላይ ንዴት፣ ህዝባዊ ውርደት፣ መቻቻል የሌለበት የክብር ገፈፋ እና ክብር የመንሳት፣ ሰብአዊነትን የመርገጥ ሁኔታ፣ በሰው ላይ አጠቃላይ እምነትን የማጣት ከባቢ አየር ይነበብበት ነበር፡፡ በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ ተመልካቹ ግልጽ በሆኑ ጉዳት የተሸነፈ ይመስል ነበር፡፡ ህዝቡ ግራ በተጋባ እና ደስታ በራቀው ሁኔታ እርስ በእርሱ ይንሾካሾክ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ በህንጻው ውስጥ ልጁን ይዞ በመቆም ተመልካቹን ከአቅም በላይ በሆነ መልኩ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ተውኔቱ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በመሰረዙ ተመልካቹን በተደጋጋሚ ይቅርታ ሲጠይቅ የነበረውን ዘረሰናይን ለማጽናናት ሲሞክሩ ተስተውለዋል፡፡ ከተመልካቹ መካከል አንዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በትወናው ዓለም ዕውቅናን ያተረፈችው አንጌሊና ጆሊ ባለችበት የትወና መድረክ እንዴት ተውኔቱን ለማገድ በኢትዮጵያ በኩል አንዲህ ዓይነት ዕገዳ ይንጸባረቃል በማለት ሌላኛውን ተመልካች ይጠይቃል፡፡ መልስ ሰጨው ግልጽ የሆነ ስሜትን በማንጸባረቅ እንዲህ የሚል ምላሽ ይሰጠዋል፣ “እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ከመስጠት እቆጠባለሁ፡፡“ ሌላ በግልጽ የተቆጣ ሰው ቃለመጠይቁን ላቀረበው ሰው እንዲህ የሚል ምላሽ ሲሰጥ ይደመጣል፣ “ጥሩ ነገር በሚኖርበት ጊዜ ምንጊዜም ደግሞ ያንን የሚያሰናክል መጥፎ ነገር አለ፣ እባክህን ተወኝ!“ ሌላኛው ንዴት ያቃጠለው ተመልካች ደግሞ እንዲህ የሚል አስተያዬት ሲሰጥ ነበር፣ “በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ ነው፣ ከዚህ በፊት እንደዚህ ያለ ነገር በፍጹም አይቸ አላውቅም ፡፡ በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ ነው፡፡ ምክንያቱ ምን አንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ለተዋንያኖቹ፣ ለተመልካቹ፣ በክብር ለተጠሩ ተጋዥ እንግዶች ታላቅ ሀዘን ነው፣ በጣም አሳዛኝ ድርጊት ነው፡፡ በጣም አዝናለሁ፡፡“ የቪዲዮ ቀረጻው እንደተጠናቀቀ በጣም ንዴት በግልጽ የሚታይባት ሴት ፈጠን ፈጠን ብላ ከአዳራሹ በመውጣት ቃለመጠይቅ የሚደረግለትን ሰው አሳድዳ በመያዝ ለመጠየቅ ስትሞክር “ተይኝ እባክሽ ተይኝ! ተይኝ እባክሽ ተይኝ!“ የሚል ምላሽ አግኝታለች፡፡
የውጭ የክብር እንግዶች፣ አምባሳደሮች እና የዲፕሎማት ሰዎች የላይኞቹን ከንፈሮቻቸውን እያስረዘሙ በሰልፍ ከተውኔት ቤት አዳራሹ ወጡ፡፡ የዲፕሎማት ሰዎች በእራሳቸው ስብዕና ላይ ውርደትን የሚያመጣ ነገር ሲያጋጥማቸው እንዴት አድርገው መወጣት እንዳለባቸው የእራሳቸው ልዩ አካሄድ አላቸው፡፡ ትከሻቸውን ነፋ፣ ከንፈሮቻቸውን ዘንጠል፣ አረማመዳቸውን ቀጥ ማድረግ እንዲሁም በእነርሱ ላይ ምንም ዓይነት ነገር የማይታይባቸው ለማስመሰል ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ምንም ነገር ያልተፈጸመ ለማስመሰል ይሞክራሉ፡፡ ያለው ገዥ አካል ታማኝ እንዳልሆነ በሚያሳይ መልኩ እያንዳንዱ/ዷ ኢትዮጵያዊ/ት በአምባገነኑ የገዥ አካል በየዕለቱ የሚያጋጥማቸውን አፈናና ስቃይ ትንሿን ጠብታ እንኳ በማየታቸው የእጃቸውን አግኝተዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ “ክቡራት እና ክቡራን እንግዶች ዴሞክራሲ እና ፍትህ ወዳልተረጋገጡባት የሰው ልጀች መብት እንደ ገና/ታህሳስ በርበሬ ወደሚደቆስባት ምስኪን ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደኳን በደህና መጣችሁ!“
ድፍረት የተሰኘው ተውኔት ለዕይታ እንዳይበቃ የታገደው ለምንድን ነው?
ድፍረት ለተመልካች ዕይታ እንዳይቀርብ የታገደበትን ምክንያት እገዳውን ካደረጉት የደናቁርት ስብስብ በስተቀር ማንም ቢሆን በእርግጠኝነት ሊያውቀው አይችልም፡፡ ይህንን ጉዳይ የበለጠ ግልጽ እናድርገው፡ ፊልሙ ቢያንስ ፖለቲካዊ አይደለም፡፡ ገዥውን አካል የሚተችም አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህ ፊልም የሚያሳዬን በጣም ኋላቀር የሆነውን የጠለፋ ጋብቻን እና የአስገድዶ መደፈርን አሮጌ ባህል በ21ኛው ክፍለ ዘመን መፈጸም እዳይኖርባቸው ለማስወገድ እንዲቻል ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ የሰንዳንስ ፊልም በዓል አዘጋጅ ቡድን ለማየት እንደሞከረው ኢትዮጵያ “እጅግ ባማረ ውበት፣ አገሪቱ ወደ እኩልነት ስርዓት የምታደርገውን ውስብስብ የሽግግር ሁኔታ“ ያመላክታል ነበር ያለው፡፡
ስለሆነም በተውኔቱ ላይ ያለው ሁኔታ ይህ ከሆነ ገዥው አካል ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት ከዝንጀሮው የይስሙላ ፍርድ ቤት የማሳገጃ ወረቀት በማውጣት ለዕይታ የሰከንዶች የጊዜ ርዝመት ቀርቶት የነበረውን ተውኔት እንዲታገድ ያደረገው በውስጡ ምን አለበት ብሎ ቢያስብ ነው? ይህንን ተውኔት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጥቂት ኢትዮጵያውያን/ት እና ለዲፕሎማት ሰዎች ማሳየት ምን ጉዳት ያመጣል ተብሎ ታስቦ ነው?
በማንኛውም ሚዛናዊ አስተሳሰብ ይህ ተውኔት ለገዥው አካል ባርኔጣ ማስጌጫ ላባ ሆኖ በታዬ ነበር፡፡ ድፍረት የተባለው ተውኔት ለገዥው አካል አመራሮች ጥሩ አጋጣሚን በመፍጠር የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሆነው ይህንን የህጻናት ሙሽራ፣ ጠለፋ እና ያለዕድሜ ጋብቻ ኋላቀር ተቋም ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ከአፍሪካም ለማስወገድ በነጭ ፈረስ ላይ ሆኖ በእነዚህ ኋላቀር ባህሎች ላይ ጦሩን ለመሰካት በተንቀሳቃሰ ነበር፡፡ ገዥው አካል የድፍረት ተውኔትን በብዙሀን መገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ይህንን ኋላቀር ልምድ ለማስወገድ እና በሴቶች ላይ የሚፈጸሙትን ጭቆናዎች ለማስወገድ፣ ለመቀስቀሻነት፣ ለማስተማሪያነት እና ህብረተሰቡን ለአዲስ ለውጥ ለማንቀሳቀስ ሊጠቀምበት ይችል ነበር፡፡ ገዥው አካል ይህንን ተውኔት ያለዕድሜ ጋብቻ እና የህጻናት ሙሽራነት ጉዳዮች ላይ የህዝባዊ ውይይት እና የክርክር መድረክ በመፍጠር ገዥው አካል ቁልፍ ሚና በመጫወት የድርጊት መርሀ ግብርን ማካሄድ ይችል ነበር፡፡ ይህ ተውኔት ለዕይታ ቢቀርብ ኖሮ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ሴቶች የጾታ አድልኦን እና የጾታ ጭቆናን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ላይ ከዓለም አቀፋ ማህበረሰብ የገንዘብ፣ የማቴሪል እና የሀሳብ ድጋፍ መገኘት በቻለ ነበር፡፡
እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ከመገረም የሚያስቆመኝ ነገር በፍጹም የለም! ይህንን ብቀላ፣ ኃላፊነት የጎደለው ስራ እና የገዥው አካል የወረደ ድርጊት በተመለከትሁ ጊዜ እውነታውን ለመናገር ከዚህ በታች ሊያጎነብሱ አይችሉም፡፡ ነገር ግን ከዚያ በታች ማጎንበስ ይኖርባቸዋል!
እ.ኤ.አ ኤፕሪል 2014 የአፍሪካ ህብረት “ያለእድሜ ጋብቻን በአፍሪካ ለማስቀረት የአዲስ አበባ መግለጫን አጽድቋል፡፡“ እ.ኤ.አ በ2013 የውጭ ግንኙነቶች ምክር ቤት/Council on Foreign Relations የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ባጠናው ጥናት መሰረት በአፍሪካ ያለእድሜ ጋብቻ ከሚካሄድባቸው 10 የመጀመሪያ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ እንደዚሁም ደግሞ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል በአስር ዓመታት ጊዜ ውስጥ የጠለፋን የወንጀል ድርጊት እና ያለእድሜ ጋብቻን አጠፋለሁ በማለት አውጇል፡፡
የድፍረት ተውኔት ለዕይታ መቅረብ ለገዥው አካል የተበላሸውን ዓለም አቀፍ ገጽታውን እንዲያገግም በማድረግ ያልተጠበቀ የህዝብ ግንኙነት ስኬትን አስገኝቷል፡፡ ድፍረትን የእራሳቸው ማድረግ ይችሉ ነበር፡፡ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ይታዩበት ነበር፣ እናም የፕሬስ መግለጫ በመስጠት ተውኔቱን እንዴት አድርገው እንደሰሩት ኋላቀር የሆኑትን የጠለፋ ልምዶች፣ ያለእድሜ ጋብቻን እንዴት አድርገው ለማጥፋት ጥረት እያደረጉ እንዳሉ፣ ይህ ተውኔትም እነዚህን ኋላቀር ባህሎች ለማስወገድ እና ለማጥፋት ወደ ህብረተሰቡ ወርዶ ማህበረሰቡን እንዴት አድርጎ ሊያስተምር እንደሚችል በመግለጽ ለስኬታማነታቸው ዲስኩራቸውን በመንዛት ቡራ ከረዩ ማለት ይችሉ ነበር፡፡ ይህንን ተውኔት ከማገድ ይልቅ እንዲታይ ቢፈቅዱ ኖሮ አዎንታዊ የሆነ የፕሬስ ጥቅም እና መልካም ስምን ይጎናጸፉበት ነበር፡፡ ከእነዚህ ፍጡሮች ጋር ምን ነገር እንዳለ እኔ ሊገባኝ አልቻለም፡ በፍጹም፣ በፍጹም ይህን የመሰለ መልካም እድል ሊያጡት የሚገባ አልነበረም!
እውነታው ሲገለጥ ግን በኃይል አስገድዶ እና በጠለፋ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ልጃገረዶችን ጋብቻ እንዲፈጸምባቸው ማድረግ በሰዎች ላይ የሚፈጸም ኢሰብአዊ ወንጀል እና በበርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ላይ እገዳ የተጣለበት ጉዳይ ነው፡፡ (በዋሻው ሰው ዘመን ይደረግ እንደነበረው ሁሉ ሴቷን ጭንቅላቷን በመምታት ጽጉሯን ጨምድዶ በመያዝ መሳብ እና በፍጥነት ይዞ ወደ ዋሻው ውስጥ በመሄድ ሙሽራ ማድረግ እንደሚቻል ጠረጠርኩ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የቅሌት አካሄድ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በፍጹም ተቀባይነት እይኖረውም!) እ.ኤ.አ በ1948 የጸደቀው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ድንጋጌ አንቀጽ 16 ጋብቻን በማስመልከት እንዲህ ይላል፣ “ጋብቻ በሁለቱ ተፈላላጊ ጾታዎች ነጻ እና ሙሉ ፍላጎት ብቻ መፈጸም አለበት፡፡“ ወጣት ልጃገረዶች ህጋዊ ስምምነት ለማድረግ ችሎታው የላቸውም፡፡ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የህጻናት መብት ስምምነቶችን ጨምሮ (1989) እና በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ማናቸውም ዓይነት አድልኦዎችን የማስወገድ ስምምነት (1979) ያለእድሜ ጋብቻን እና ማንኛውንም ዓይነት በሴቶች ላይ የሚደረጉ ጭቆናዎችን ሁሉ ያወግዛል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ታዋቂው የተባበሩት መንግስታት አካል የሆነው እና በዓለም ላይ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እንዲስፋፋ እና እንዲጠናከር ኃላፊነት የተሰጠው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ጉባኤ የተለያዩ መንግስታት የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመንደፍ በከፍተኛ ሁኔታ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን የሚጎዱትን ያለእድሜ እና የጠለፋ ጋብቻን የሚያጠፉ ውሳኔዎችን እንዲያጸድቁ እና እነዚህን ኋላቀር ባህሎች እንዲያጠፉ በዓለም ላይ የመጀመሪያ የሆነውን የተባበሩት መንግስታት ውሳኔ አጸደቀ፡፡
ይህ የተጠላው የጠለፋ ኋላቀር ድርጊት፣ የህጻናት ሙሽሮች እና ያለእድሜ ጋብቻ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ እና በሌሎችም የዓለም ከፍሎች ሁሉ መወገዝ፣ መነቀል እና መወገድ አለበት፡፡ የዚህን ኋለቀር ባህል ከአንድ ሺ እና ከአስር ሺ ዓመታት ጀምሮ ሲተገበር የኖረ ነው በማለት አሁንም ቢሆን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ቢፈጸም ቸግር እንደሌለው ሊያሳምን የሚችል የባህል የመከራከሪያ ጭብጥ ከየአቅጣጨው ቢቀርብ ባይቀርብ ለእኔ ጉዳዬ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ መቆም አለበት፣ እናም በተገኘው እና ባስፈላጊው ሁኔታ ሁሉ ከምድረገጽ መወገድ አለበት!!!
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ፊልም ለሰብአዊ መብት መከበር ደንታ ከሌለው ከገዥው አካል ባህሪ አንጻር ሲታይ ተውኔቱን ያለምንም ዕገዳ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲታይ ቢደረግ ኖሮ ገዥው አካል ጥሩ የንግድ ሁኔታን ያመቻች ነበር በማለት የክርክር ጭብጤን አቀርባለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ገዥው አካል ለልመና፣ ለእርጥባን እና ለምጽዋት ያጎበደደ ፍጡር ነው፡፡ ይህንን ተውኔት ገዥው አካል ቢጠቀምበት ኖሮ በምን ዓይነት ሁኔታ የአሜሪካንን ልብ ያማልል እንደነበር እና የአውሮፓን መንግስታት ምጽዕዋት ለማግኘት እና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በህዝብ ስም የህጻናት ጋብቻን ለመዋጋት እና ለመዝረፍ እንዲሁም ለእነርሱ አገልጋይ እና አቀባይ ለሆኑት የይስሙላ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በመስጠት እንደገና በሌላኛው ኪሳቸው ወስደው በማጨቅ ወደ ውጭ ባንኮች በማዞር የእራሳቸውን የባንክ አካውንት ይከፍታሉ፡፡ ይህንን የመሰለ ትልቅ እድል እና በእጃቸው የገባውን ዶለር እንዴት ሊያጡት እንደቻሉ ለመገመት አልችልም! እንደገና በፍጹም ጥሩ ዕድልን የማግኘት ዕድልን በፍጹም ማጣት የለባቸውም!
የድፍረት ተውኔት ሊታገድ የቻለባቸው ሌሎቸ ምክንያቶች ይኖሩ ይሆን? ምናልባት ሊኖር ይችላል፡፡ ምናልባትም የድፍረት ተውኔት ሊታገድበት የቻለበት ምክንያት የገዥው አካል አመራሮች ይህንን ኋላቀር የሆነ የህጻናት ሙሽራ የጠለፋ ግብቻ ተውኔት ለዕይታ እንዲቀርብ መፍቀድ እራሳቸው ፈጥረናል የሚሉትን በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ያላቸውን ገጽታ ያበላሽብናል ከሚል እምነት የተነሳ ሊሆን ይችል ይሆን? በአፍሪካ አህጉር ታላቁን ግድብ እየገነባሁ ነው የሚል ገዥ አካል እንዴት የጠለፋ እና ያለእድሜ ጋብቻን ሊፈቅድ ይችላል? ባለፉት አስርት ዓመታት በየዓመቱ በ11 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገብኩ ነው ከሚል አካል ውስጥ (ታላቋ የቨርጅኒያ ከተማ ከሰባት ዓመታት ያላነሰ ጊዜ የወሰደባትን) እገነባለሁ ከሚል የገዥ አካል እንዴት ይህን ኋላቀር የሆነ የጠለፋ እና ያለእድሜ ጋብቻ ሊፈቅድ ይችላል? እንዴት ያለ በሀሳብ ፊኛ ላይ ተኝጠልጥሎ የሚጓዝ ምናባዊ መንግስት ነው እባካችሁ…?
ድፍረት የተባለው ተውኔት ለምን እንደታገደ የግሌ አመለካከት፣
የቱንም ያህል ዋጋ ይኑረው አይኑረው ድፍረት የተባለው ተውኔት የታገደበት ምክንያት በእራሴ አመለካከት በጣም ቀላል የሆነ ምክንያት ነው፡፡ በውጫዊ መልኩ በግርድፉ ሲታይ ይህ የጠለፋ ጋብቻ ላይ የሚያጠነጥነው ተውኔት ለዕይታ ሊቀርብ በሰከንዶች የሚቆጠር ጊዜ ሲቀረው እንዳይታይ መከልከል ማለት እራሳቸው አድራጊ ፈጣሪ ጌቶች መሆናቸውን ለሌሎች ሰዎች ለማሳየት ነው፡፡ እነርሱ በእራሳቸው ትዕዛዝ ማድረግ የሚፈልጉትን ሁሉ ማድረግ እንደሚችሉ በግልጽ ለማሳየት ነው፡፡ ጉዳዩን ጠለቅ አድርገን ስናስበው በእርግጥ ከሁኔታው ለመገንዘብ እንደሚቻለው ድፍረት የተባለው ተውኔት አንጀታቸውን በልቶታል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ድፍረት የተባለው ተውኔት በአጠቃላይ ስለኢትዮጵያ ነው የሚተርከው (ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ላይ ትኩረት ተደርጓል)፡፡ እናም ይህ ተውኔት የውበታዊ ኪነ ጥበብን የተላበሰ እና ለኢትዮጵያ ታላቅ ክብርን የሚሰጥ ተውኔት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ዘረሰናይ ብርሀኔ መሀሪ ይህንን ድፍረት የተባለውን ተውኔት በሚያዘጋጅበት ወቅት ኢትዮጵያዊ የመሆንን እውነታ (የመሆንን እውነታ የሚለውን ቃል አስምሩበት) በሚገባ አንጸባርቋል፡፡ እያንዳንዱን የተውኔቱን ጽሁፍ ያነበበ ሁሉ የፊልም ባለሙያው በዚህ ስራ ላይ የጠለቀ ችሎታ እና ልዩ ተሰጥኦ ያለው ኢትዮጵያዊ የፊልም ባለሙያ እንደሆነ በግልጽ ያመላክታል፡፡ በተውኔቱ ላያ ዘረሰናይ የእርሱን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እህቶቹን ህይወት የሚያጨልመውን ኋላቀር ጎጅ ተቋም ለማጥፋት በሙሉ ልቡ እና አቅሙ የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ እውነታው ግን ኢትዮጵያ የምትለዋ ቃል በገዥው አካል አመራሮች ላይ ሊቆጣጠሩት የማይችሉትን መንፈራገጥ ታጭርባቸዋለች (የነብሳቸው በሽታ) በጥቂት ሰዎች ላይ ጥላቻን ትፈጥራለች፡፡
በጣም ግልጽ በመሆኔ ይቅርታ እንድታደርጉልኝ እጠይቃለሁ! ዘረሰናይ ጠባብ የሆነ የጎሳ ፖለቲካን እና ዕኩይ ምግባርን ሊያራምድ የሚችል ተውኔት ቢሰራ ኖሮ ገዥው አካል ይህንን የተውኔት ባለሙያ አንበሳ አድርጎ ያሞካሸው ነበር፡፡ እንዲያውም ገዥው አካል በየቀበሌው እና በየአካባቢው የሚኖሩትን ሰዎች በግዳጅ እንዲወጡ እያደረገ በግድ እንዲመለከቱት ያደርግ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ድፍረት የተባለው ተውኔት ስለፖለቲካ አንዳችም የሚለው ነገር የለውም፡፡ ይልቁንም ሙሉ በሙሉ ስለሰብአዊ መብት ሁኔታ ነው የሚተርከው እና ለማሳየት የሚሞክረው፡፡ እንዲያውም ይህ ተውኔት የሚያጠነጥነው የማህበረሰቡን ባህል እና ልማድ መተግበር በሚል ሽፋን በመንደር ወሮበሎች የአስግድዶ መደፈር ወንጀል የሚፈጸምባቸውን ወጣት ሴቶች ሰብአዊ መብት ለማስከበር የተዘጋጀ ተውኔት ነው፡፡ እንደዚሁም ሴቶች እንደ ሴት መብታቸው እንዲጠበቅ ለማስቻል የተዘጋጀ ተውኔት ነው፡፡ ተውኔቱ በልማድ ሰበብ የህጻናት አስገድዶ መደፈርን እና ያለ እድሜ ጋብቻን ለማጋለጥ የተዘጋጀ ነው፡፡ እንግዲህ የድፍረት ተውኔት ማለት ስለእነዚህ ጉዳዮች ሁሉ ማለት ነው አንጅ የተንኮል ፋብሪካዎች እና አፈቀላጤዎች እንደሚሉት ሌላ ምንም ዓይነት ተልኮ የለውም፡፡
በቀጣዮቹ አስርት ዓመታት ዘረሰናይ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ጭምር በጣም የተከበረ እና ታዋቂ የተውኔት ባለሙያ ይሆናል ብዬ አገምታለሁ፡፡ ድፍረት የተባለውን ተውኔት በማዘጋጀት እንደዚህ ያለ ድፍረትን የተላበሰ ወኔ በማሳየቱ እኮራበታለሁ፡፡
በዜጎቹ ላይ ክፋትን መስራት የሚያረካው አገዛዝ፡ የህዝቦች ስቃይ፣ መከራ እና መጥፎ ዕድል የጮቤ የሚያስረግጠው ገዥ አካል፣
ገዥው አካል ድፍረት የተባለውን ተውኔት ለዕይታ ለመቅረብ በሰከንዶች የሚቆጠር ጊዜ ሲቀረው ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዳይታይ ያገደበት የእራሱ የሆነ የስነ ልቦናዊ ምክንያት አለው፡፡ ይህም ምክንያት “የክፋት እርካታ” ይባላል፡፡ ይህ ቃል ከጀርመን ቋንቋ ወደ እንግሊዝኛ እንዲተረጎም በማድረግ በሌሎች ዜጎች ላይ ስቃይ፣ መከራ እና መጥፎ ዕድል ሲያጋጥም በከፍተኛ ደረጃ እርካታን የሚያገኝ የሚል ትርጉም ይዞ ይገኛል፡፡ የክፋት እርካታ መሰሪዎች ሰቃይን፣ መከራን እና በሌሎች ሰዎች ላይ መጥፎ ዕድልን በማድረስ እርካታን እና ደስታን በማግኘት የእራሳቸውን ነብስ የሚያስደስቱ ዕኩይ ፍጡሮች ናቸው፡፡ በእንደዚህ ያለ በሰዎች ላይ ክፋትን በመስራት እርካታ የሚያገኙ ሰዎች በሌሎች ሰዎች ላይ የሚደርሱ ስቃዮች፣ ሀዘኖች እና መከፋቶች አነርሱን ከምንም በላይ ያስደስታቸዋል፡፡ የሌሎች ሰዎች ስቃይ እርካታን ይፈጥርላቸዋል፣ የሌሎች መከራን መቀበል ለእነርሱ ፍጹም እርካታን ያጎናጽፍላቸዋል፣ ሙሉ ደስተኞችም እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡
እስቲ ይህንን ነገር አስቡት፡ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል አመራሮች በመጀመሪያ ደረጃ ድፍረት የተሰኘውን ተውኔት በፊልም እንዳይቀረጽ ማገድ ነበረባቸው፡፡ ለህዝቡ በማስታወቂያ እንዳይነገር እና በሀገር ደረጃም ውይይት እንዳይደረግበት ማድረግ ነበረባቸው፡፡ ዘረሰናይ ይህንን ተውኔት ለህዝብ ዕይታ ለማቅረብ ገና ለባህል ሚኒስቴር የፈቃድ ጥያቄ ሲያቀርብ መከልከል ነበረባቸው፡፡ ቀደም ሲል ይህ ተውኔት ለዕይታ እንደማይቀርብ ለዘረሰናይ በግልጽ በመንገር ኋላ ብዙ ልፋት እና ጉልበት ካፈሰሰበት በኋላ በማገዳቸው እንዳይበሳጭ ማድረግ ነበረባቸው፡፡ አይደለም! አይደለም! በፍጹም አይደለም! ተውኔቱ ለህዝብ ዕይታ በሰከንዶች (አይደለም በደቂቃ) የጊዜ ርዝመት ሲቀረው ማገድ አለባቸው፡፡ ለምን? ምክንያቱም ተውኔቱ ውጤታማ እንዲሆን እና በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ ሆኖ ዓላማውን እንዲያሳካ ጥረት ያደረጉ ተዋንያኖች፣ አዘጋጆች እና ዳይሬክተሮች ሲሰቃዩ እና ሲያዝኑ ማየት ለእነዚህ የዕኩይ ምግባር አራማጆች ህሊና ታላቅ እርካታ ነው፡፡ የገዥው አካል አመራሮች የተውኔት አዘጋጁ በታዋቂ ኢትዮጵያውያን/ት እና በዓለም አቀፍ ዲፕሎማት የተውኔቱ ተመልካቾች ፊት ሲበሳጭ፣ ሲያዝን እና ሲዋረድ ማየት ከምንም በላይ ያረካቸዋል፡፡ ሜሮን ስትዋረድ እና እንባዋን ስትፈነጥቅ ማየት የደስታቸው ምንጭ ይሆናል፡፡ የተውኔቱ ተመልካች ተውኔቱን ለማየት በደስታ ተውጦ በነበረው ስሜቱ ላይ ውኃ በመቸለስ ስነልቦናዊ ጫና በመፍጠር ደስታውን መደቆስ ከምንም በላይ ያስደስታቸዋል፡፡ ያ ነው እንግዲህ በኢትዮጵያ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ የሚገኘው ገዥ አካል አመራሮች እኩይ የመንፈስ እርካታ እና ፈንጠዝያ!
በርካታ ተጨባጭነት ያላቸው ጥናቶች እንዳረጋገጡት ከፍተኛ የሆነ የእራስ መተማመን እና የደህንነት ስሜት ካላቸው ሰዎች ይልቅ በእራሳቸው ላይ መተማመን የማያሳዩ እና ከፍተኛ የሆነ የምቀኝነት፣ የጥላቻ እና የበታችነት ስሜትን የሚያንጸባርቁ ሰዎች በሌሎች ሰዎች ስቃይ ላይ የበለጠ እርካታን የሚጎናጸፉ መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡ (ቫን ዲክ የተባሉት ጸሀፊ ያዘጋጁትን “በእራስ መተማመን፣ ግለሰባዊ ጽናት እና በሰዎች ስቃይ መደሰት“ የሚለውን መጽሀፍ ይመልከቱ)፡፡ የአምባገነኖች ስነልቦናዊ ባህሪዎች በሚል ባዘጋጀኋቸው የእራሴ ጥናቶች ላይ መደምደሚያ ለመስጠት እንደሞከርኩት አምባገነናዊ እኩይ ምግባሮችን የሚተገብሩ አምባገነኖች የስነ አዕምሮ በሽታዎች ሰለባዎች ናቸው፡፡ እናም ዘራፊነትን የሚፈጽሙ አምባገነኖች ነብሶቻቸው ሊድን በማይችል እና በፍጥነት እየተስፋፋ በሚሄድ የጥላቻ የካንሰር በሽታ የተለከፉ እኩይ ፍጡሮች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰዎች ስቃይ ላይ እርካታን የሚያገኙ ሰዎች የመንፈስ በሽተኞች ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምንም ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ ለሰው ልጆች ሰብአዊ መብቶች ቅንጣት ያህል ደንታ የላቸውም፡፡ እነርሱ እራሳቸው ብቻ ሰዎች ናቸው ለስሙም ቢሆን፡፡ ከህይወት ጋር ቅርኝት ያለውን ማንኛውንም ነገር ሁሉ እና ህይወትን ትርጉም የሚሰጠው ምን እንደሆነ ፍጹም በሆነ መልኩ እረስተውታል፡፡ መጥፎ የሆነ የጥላቻ መንፈስን ተሸክመው ባዶ እና እርባናየለሽ ህይወታቸውን በመግፋት እንደ ሙት መንፈስ ይዞራሉ፡፡ የሙሉነት ስሜት የሚሰማቸው፣ ደስታ እና እርካታን የሚጎናጸፉበት ብቸኛው መንገድ ሌሎችን ሰዎች በማሰቃዬት እና ፍዳ በማሳዬት ብቻ ነው፡፡ የእነርሱ ደህንነት የሚወሰነው በጥላቻ የተሞላ ኃይልን በመጠቀም ብቻ ነው፡፡ እነዚህ የእኩይ ምግባር አራማጆች ለእነርሱ ደስታ እና እርካታን የሚያገኙት ሌሎች ሰዎች ደህንታቸው ሲቃወስ እና በፍርህት እየራዱ ሲኖሩ ማዬት ነው፡፡ መሰረታዊ የሆኑ የሰው ልጆችን ሀሳብን የማካፈል፣ መግባባት እና ሌሎችን የመርዳት ዝንባሌ ወይም ደግሞ ፍቅርን ማሳዬት በመሳሰሉ ክቡር የሰው ልጅ ባህሪያት ላይ በተጻራሪ መልኩ እነዚህ የእኩይ ምግባር አራማጆች እና የአዕምሮ በሽተኞች ጥልቅ የሆነ ጥላቻ ያላቸው እና እንደዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ለሰው ልጅ በጎ ባህሪያት ተሞክሮ እና ችሎታው የሌላቸው መሰሪዎች ናቸው፡፡ በቀላሉ አነጋገር በእነርሱ ወጣት ዜጎች በሚያድርጉት ኪነታዊ ውበት ስኬት ምክንያት በኢትዮጵያውያን/ት እና በውጭ አገር ዜጎች ምስጋና፣ እውቅና እና አድናቆት ሲቸራቸው ማየት ያስጠላቸዋል፣ ያቅለሸልሻቸዋልም፡፡ እነዚህ ፍጡሮች በአጠቃላይ መልኩ በጭፍን ጥላቻ የተሞሉ ናቸው፡፡ ወጣቶቹ በትንሽ እርካታ የሚደሰቱበትን እነርሱ ግን ስር በሰደደ እና መጠነ ሰፊ በሆነ የጥላቻ የድብርት ባህር ውስጥ ገብተው ይንቦጫረቃሉ፡፡ አንድ ሰው ከተመረጠ፣ የእራስ መተማመን ስሜትን ካዳበረ፣ ተወዳጅ ከሆነ ወይም ደግሞ ታላቅ ክብርን የሚጎናጸፍ ከሆነ እነርሱ የተጠሉ፣ የተናቁ፣ የተወገዙ እና የተወገዱ መስሎ ይታያቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል አመራሮች በእራሳቸው ዙሪያ በእንደዚህ ያሉ ዕኩይ ኃይሎች ተከበው የሚገኙ ሲሆን በእነርሱ ህልው መሆን የአቶሚክ ቅንጣቷ እንኳ ሳትቀር ትበታተናለች የሚል መሰሪ እምነት አላቸው! እኔ ስለእነርሱ አዝናለሁ!!!
የጭራቃዊነት ችግር በኢትዮጵያ፣
ባለፉት በርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ወስጥ ስላሉት የጭራቃዊነት ችግሮች በርካታ ትችቶችን ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡ “በኢትዮጵያ የጭራቃዊነት የተስፋ ማቆጥቆጥ” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት ላይ በስልጣን ላይ ባሉ ኃይሎች አማካይነት በተራው እና በጣም ተራ በሆነው ህብረተሰብ ላይ የሚፈጸሙ የጭራቃዊነት የአዙሪት ድርጊቶችን ለማስገንዘብ ጥረት አድርጊያለሁ፡፡ በዚያ የክርክር ጭብጤ ላይ የገዥው አካል አመራሮች እንደሚያታልሉ፣ ዘረፋ እንደሚያካሂዱ፣ እንደሚሰርቁ እና ያለምንም የህግ ተጠያቂነት ንጹሀን ዜጎችን እንደሚገድሉ ምክንያቱም በምድር ላይ እነርሱን ለህግ ተጠያቂ የሚያደርግ ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል እንደሌለ አድርገው ስለሚቆጥሩ በማለት ለማስገንዘብ ሞክሪያለሁ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ በተራ ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን የጭራቃዊነት ድርጊት ከዳር ቆመው ጸጥ በማለት እየተመለከቱ ምንም ዓይነት ተቃውሞም ሆነ ድርጊቱን ለማስቆም እርምጃ በማይወስዱ ሰዎች ላይ ያለኝን ጭንቀት ገልጨ ነበር፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ጥሩ ጥሩ ወንዶች እና ሴቶች በአንድ ላይ ቆመው ለምን ለመብቶቻቸው እንደማይታገሉ እና ከዚያ ይልቅ በፍርሀት ቆፈን ውስጥ ተወሽቀው ለምን ተደብቀው እንሚገኙ እና ለምን ሽባ ሆኑ? የሚል ጥያቄ አንስቼ ለማስገንዘብ ሞክሪያለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለምን ያስመስላሉ እናም በእርግጠኝነት ጭራቃዊነት የለምን ወይም ደግሞ እንደተመልካቹ ነውን? ምን ዓይነት ጭራቃዊነት ቢፈጸም ነው ማየት የተሳናቸውን፣ በጸጥታ የተቀመጡትን እና መስማት የማይችሉትን ብዙሀን ህዝቦች ሊያስተሳስር እና ሊያነሳሳ የሚችለው? ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዲህ የሚል ትምህርት አስተምረው አልፈዋል፣ “ጭራቃዊነትን በጸጋ የሚቀበል ማንም ቢሆን ጭራቃዊነቱን ከሚፈጽሙት መሰሪዎች እኩይ ምግባር ጋር እኩል እንደተሰለፈ ይቆጠራል፡፡ ጭራቃዊነትን ያለምንም ተቃውሞ የሚቀበል በእርግጠኝነት ከተግባሩ ጋር እንደተባበረ ይቆጠራል፡፡“
“ኢትዮጵያ፡ ከጭራቃዊነት እብሪት በላይ” በሚል ርዕሰ ባዘጋጀሁት ትችት በኢትዮጵያ በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጦ የሚገኘው ገዥ አካል እየፈጸመ ያለውን የፖለቲካ ደባ ለመግለጽ ሞክሪያለሁ፡፡ በክርክር ጭብጤ የገዥው አካል አመራሮች እየተስፋፋ በመጣው የልብ እና የአዕምሮ እብሪት መታበይ እየተሰቃዩ መሆናቸውን ገልጨ ነበር፡፡ እነዚሁ በእብሪት የመወጠር ድርጊቶች የእራሳቸው የሆኑ ባህሪያት እንዳሏቸው ሀሳብ አቅርቤ ነበር፡፡ እነዚህ እብሪተኞች በማንም የማይነኩ እና በማንም ዘንድ ተጠያቂ ሊሆኑ የማይችሉ አድርገው እራሳቸውን ይቆጥራሉ፡፡ እነዚህ መሰሪ ሰዎች በማህበረሰቡ ውስጥ የሞራል ኃላፊነት ወይም ደግሞ የሰው ህሊና እንዳይኖሯቸው ሊከለክሏቸው የሚችሉ እንደ በጨካኝነት፣ በኃይለኝነት፣ በጸረ ሰውነት እና ባህሪያት የተጆቦኑ ግላዊ ተፈጥሮዎች አሏቸው፡፡ ለእርሱ የእነርሱን እብሪቶች ሊያስታግስ የሚችል ምንም ዓይነት ህግ የለም ምክንያቱም የእነርሱ ቃላት እና ድርጊቶቻቸው በእራሳቸው ህጎች ናቸው፡፡ ከሞራል ንቅዘት ማዕድ ላይ በመመገብ (የፈለጉትን ትክክል ወይም ስህተት ቢሉም) እነዚህ ሰዎች የሰዎችን ክብር ለማሳነስ፣ ለማዋረድ፣ ለመዘለፍ፣ ለእራስ ብቻ ክብር በመስጠት እና ግላዊ የስልጣን ስግብግብነትን በማራመድ ምንም ዓይነት ተከላካይ የሌላቸውን እረዳት የለሾች ለማሰቃየት እና ከሰብአዊነት በወረደ መልኩ መከራ ለማሳየት ጥልቅ በሆነ የስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ተዘፍቀው የሚገኙ ከንቱ ፍጡሮች ናቸው፡፡ እረዳት እና ተከላካይ የሌላቸውን የእነርሱ የግፍ ሰለባዎች ክብር ዝቅ ባደረጉ እና ባዋረዱ ቁጥር ጠቅላይ ኃያልነት፣ የበላይነት እና እራስን ብቻ እውነት አድርጎ የማቅረብ ከእውነታው ተጻራሪ በሆነ መልኩ ደስታዎችን ያጎናጽፋቸዋል፡፡ በእብሪት ለተሞሉ ጭራቆች ለህይወት ትርጉም መስጠት እና ነገሮችን በምን ዓይነት መልኩ መስራት እንደሚያስፈልግ ማሰብ ምንም ዓይነት አስፈላጊ ያልሆነ ደንታቢስነት መለያ ባህሪዎች ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል በወጣት ኢትዮጵያውያን/ት ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና በከያኒያን ላይ የከፈተው ጦርነት፣
ድርጊቶችን እና ነገሮችን ሁሉ ሁልጊዜ በተናጠል ብቻ ማየት የለብንም፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል የኢትዮጵያን ምርጥ እና የባለብሩህ አዕምሮ ባለቤት የሆኑትን ወጣት ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እና የሲቪክ ማህበረሰብ ወትዋቾችን ስም የማጥፋት እና ተደጋጋሚ የሆነ የአቅም ማዳከም ዕኩይ ምግባራትን ሲፈጽምባቸው ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ብርቱካን ሚደቅሳ የምትባል ወጣት ሴት የፖለቲካ መሪ ነበረቻት፡፡ ብርቱካን የዚህ ዓይነት አርዓያነት ያለው ተግባር በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ወጣቶች በተለይም ደግሞ ለወጣት ሴቶች መሰረት የሚሆን አስገራሚ ተግባርን አሳይታለች! መለስ ዜናዊ እራሱ የእርሷን እስራት በትዕዛዝ ተፈጻሚ እንዲሆን አድርጎ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለብርቱካን መፈታት ጉዳይ እንዲህ የሚል የእብሪት ዲስኩር አደረገ፣ “የእርሷ ጉዳይ የተዘጋ ጉዳይ ነው፣ አራት ነጥብ“ ምን ዓይነት የእራስ ነብይነት ነው ለመለስ!
የመለስ አገዛዝ የቴዎድሮስ ካሳሁንን (ቴዲ አፍሮ፣ በእርሱ የትውልድ ዘመን ካሉ ኢትዮጵያውያን/ት ወጣቶች መካከል በከያኒነቱ ታዋቂ የሆነው) ሰውን በመኪና ገጭቶ በማምለጥ በሚል ወንጀል የሸፍጥ ክስ በመመስረት ለእስር እንዲዳረግ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ቴዲ ስለ ፍቅር፣ ስምምነት፣ ሰለእውነት፣ ስለዕርቅ እና ስለኢትዮጵያውያን/ት ሁሉ ህብረት ብቻ አስፈላጊ እንደሆነ በመገንዘብ የሚዘምር ከያኒ ነው፡፡ ስለእርሱ ተከታታይነት ያላቸው የሀሰት ውንጀላዎችን በመፈብረክ በእነርሱ የጥላቻ ቀለም እንዲቀባ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት አድርገዋል፡፡ ፍቅር ምንጊዜም ያንጸባርቃል፣ እንደዚሁም ሁሉ ቴዲ፡፡
የኢትዮጵያ ወጣት የብሩህ አዕምሮ ባለቤት የሆነውን የህግ ባለሙያ እና በወንጀል ምርመራ የህግ ሙያ ታዋቂ የሆነውን አንዷለም አራጌን አሰሩት፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 ተደረገ በተባለው የይስሙላ ሀገር አቀፍ ምርጫ አንድነት ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ የተሰኘውን የተቃዋሚ የፖለቲከ ፓርቲ በመወክል በቴሌቪዥን ቀርቦ ሲያደርግ የነበረው የምርጫ ክርክር ዳህራ በኢትዮጵያ ታሪክ በመጭው ትውልድም ሲታወስ ይኖራል፡፡
የማይናወጥ እና የጸና እምነት ያለውን ማንኛውንም ታላቅ የሆነ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ሽልማት አሸናፊ የሆነውን እውቅ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን አሰሩት፡፡ የነጻው ፕሬስ ታሪክ ሲጻፍ በመጽሀፉ የፊት ለፊት የመጀመሪያ ገጽ ሽፋን ላይ የእስክንድር ፎቶግራፍ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም፡፡
በርካታ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ሽልማቶችን አሸናፊ የሆነችውን ወጣቷን ሴት ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙን አሰሯት፡፡ ርዕዮት በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባውን ግድብ አስመልክቶ ወይም ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በሌላ ስያሜ ቢጠሩትም የመለስ ዜናዊን ቅጥፈት ለመጋፈጥ ጽናቱ አላት፡፡ ለእስክንድር ነጋ እንዳደረጉት ሁሉ ርዕዮትም ይቅርታ ጠይቃ ከማጎሪያው እስር ቤት እንድትወጣ ጠየቋት፡፡ እንደ አስክንድር ሁሉ ርዕዮትም ይህንን ጥያቄ ውድቅ አደረገችው፡፡
ወጣት ዉብሸት ታዬ እንዲታሰር እና ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን/ት ጋዜጠኞች ደግሞ ከሀገር እንዲሰደዱ አደረጉ፡፡
የኃይማኖት ነጻነት እንዲከበር በሰላማዊ መንገድ ሲናገር የነበረውን እና መንግስት በኃይማኖት ጉዳዮች ላይ ጣልቃ እንዳይገባ በጽናት ሲታገል የነበረውን ወጣቱን ኢትዮጵያዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አቡባከር አህመድን አሰሩት፡፡
የኢትዮጵያን ወጣት የአካዳሚክ ምሁር እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆነውን በቀለ ገርባን “የኢትዮጵያን መንግስት በሸፍጥ በኃይል ለመገልበጥ” በሚል የሀሰት ውንጀላ ክስ በመመስረት አሰሩት፡፡
የድፍረት ተውኔት ተዋንያን እና አዘጋጆች ቀጣዩ የእስራት ሰለባ ሊሆኑ ይችሉ ይሆን? የኢትዮጵያ የፍልም ስራ ባለሙያዎች የሆኑት ዘረሰናይ ብርሀኔ፣ ሜሮን ጌትነት፣ ትዝታ ሀገሬ እና ከዚያም አልፎ የአሜሪካ የፊልም ባለሙያ የሆነችውን አንጌሊና ጆሊን በአሁኑ ወቅት በጸረ ሽብር ህጉ የሽብር ድርጊትን የሚቀሰቅስ ተውኔት በመስራት በማለት ወደ ዘብጥያ ያወርዷቸው ይሆን? ነው ወይስ ደግሞ እነዚህን ወጣት ከያንያን እናንተን እዚህ አንፈልጋችሁም፣ ስለዚህ “ከአገር ለቃችሁ ውጡ” ወይም ተሰደዱ የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ታስቦ ይሆን?
ኪነ ጥበብ ህይወትን ነው የሚያመሳስለው?
በኢትዮጵያ ያለው የወሮበላ ቡድን ድፍረት የተባለውን ተውኔት በመጥለፍ ለተመልካች ዕይታ እንዳይቀርብ ያደረገው ጠለፋ ወጣት ልጃገረዶችን በጠለፋ ወስደው በግዳጅ ጋብቻ ለመፈጸም ከተሰማሩት የመንደር ወሮበላዎች ድርጊት የተለየ አይደለም፡፡ የድፍረት ተውኔት ለህዝብ እይታ እንዳይቀርብ የከለከለው ገዥው አካል በሰዎች ሀዘን እና ስቃይ ላይ እርካታን በማግኘት በፈጸመው ዕኩይ ድርጊት የህግ የበላይነትን ጥሷል፡፡ የህንንም አሳፋሪ ድርጊት በመፈጸሙ ገዥው አካል ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት የሚለውን እራሱ የደነገገውን ህገመንግስታዊ መብት እንዳለ በመደፍጠጥ ለበርካታ ዓመታት ጭራቁ አካል እያልኩ ስገልጸው የቆየሁትን በሚገባ አረጋግጧል፡፡ በውሸት ሳቅ እንደ ጅብ የሚያሽካኩት የገዥው አካል ደናቁርት ያልተገነዘቡት ነገር ቢኖር አንድን ተውኔት ለተመልካች እንዳይቀርብ ባገዱት ቁጥር የዚያ ተውኔት ሚስጥራዊነት የመቅረት እና ታዋቂነቱ እየጎላ የሚሄድ መሆኑን ነው፡፡ በዓለም ላይ ያለ የተውኔት ታሪክ እንደሚያሳየው በመንግስታት ተጽዕኖ የሚታገዱ ተውኔቶች በአጭር ጊዜ እና የመጨረሻ ታዋቂነትን እንዲጎናጸፉ ያደርጋቸዋል፡፡ በበርካታ አገሮች ተውኔቶች ዘለፋን የሚያስተናግዱ ሲሆኑ፣ ወይም ደግሞ የፖለቲካ አመራሮችን የሚተቹ ሲሆኑ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸውን ቡድኖች የሚፈጥሩ ሲሆን፣ ወሮበሎችን የሚያሞካሽ ሲሆን እና ሌሎች ወንጀሎችን እና ሰይጣናዊ ተግባራትን የሚያስፋፋ ሲሆን፣ ወይም ደግሞ በስዕል የኃይል ድርጊትን ወይም ሌሎች ነገሮችን የሚያደፋፍር ሆኖ ሲገኝ ለተመልካች እይታ ከመቅረብ ይታገዳል፡፡ በመጨረሻም የእገዳው ድርጊት በእራሱ ተዘጋጅቶ የነበረውን ተውኔት የበለጠ ታዋቂነት እዲኖረው ያደርጋል፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በጣም አወዛጋቢ የሆነው ተውኔት በርካታ ገንዘብ ከሚከፈልባቸው ተውኔቶች መካከል ዋናው ነው! በማንኛውም ምክንያት ይሁን ገዥው አካል በሚቀርበው ተውኔት ላይ ደስተኛ ካልሆነ በጠቅላላው ዝም ብሎ ትኩረት ሳይሰጥ መተው ነበረበት፡፡ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ወስጥ እየከሰመ በመሄድ ከዚያ በኋላ ይረሳ እና እነርሱም ወደተለመደው ስራቸው መግባት ይችሉ ነበር፡፡ ምስጋና ለገዥው አካል ይሁን እና በአሁኑ ጊዜ ድፍረት ዓለም አቀፋዊ ትኩሳት ሆኗል! (የእኔ ግላዊ ምስጋናም እዚህ ላይ መታከሉ ልብ ይባልልኝ!)
የገዥው አካል የጫካ እና የደፈጣ አስተሳሰብ፣
በኢትዮጰያ ያሉ የገዥው አካል አመራሮች ወደ ጫካው እና የድብብቆሽ ህይወታቸው በመመለስ እና እራሳቸውን ብቻ ከመስማት ውጭ ምንም ዓይነት የሌላ ወገንን ሀሳብ ለመስማትም ሆነ ለማስተናገድ ፍላጎትም ሆነ ችሎታ የሌላቸው መሆናቸውን አምናለሁ፡፡ የጫካ አስተሳሰብ እጅግ በጣም እራስን ከትችት የመከላከል እና ከሌሎች አካላት በተከታታይ የሚወረወሩባቸውን ትችቶች እጅግ በጣም በተጋገነነ መልኩ የውሸት የአጻፋ ምላሾችን በመስጠት ተጠምዶ የመኖር አስተሳሰብን ያራምዳሉ፡፡ የድብብቆሽ አስተሳሰብ የሰለባነት እና የመከላከል የጋራ አስተሳሰብ ነው፣ አንዱ በሌላው በተከታታይነት የሚጠቃበት፣ የሚጨቆንበት ወይም ደግሞ ከሌላው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አሉታዊ እይታ የጋራ አስተሳብ የወጣ ተደርጎ የሚወሰድበት አካሄድ ነው፡፡
እውነታው ግን የገዥው አካል አመራሮች የሚኖሩት ታላቅ በሆነችው በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን ያንኑ የጫካ አስተሳሰባቸውን እንደያዙ እና በመተግበር ላይ ናቸው፡፡ ግልጽ ለማድረግ ወሮበሎችን ከጫካ ውስጥ ማስወጣት ይቻላል ሆኖም ግን ጫካውን ከወሮበሎች ውስጥ ማስወጣት አይቻልም፡፡ በገዥው አካል ላይ ያለው ትልቁ እና ቁልፉ ችግር ይኸ ነው፡፡ ከዚያ ከጫካ አስተሳሰብ ውስጥ በመውጣት ለማደግ ስብዕናቸው አይፈቅድላቸውም፡፡ ከመንግስት ክፍያ እየተከፈላቸው ከሚጽፉት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚወጡት ጥቂት መገናኛ ብዙሀን ላይ ከሚወጣው በስተቀር ገዥው አካል ሁልጊዜ እንደተደበደበ ነው፡፡ ገዥው አካል ሁልጊዜ እና በማያቋርጥ መልኩ ከዓለም አቀፍ የመገናኛ አውታሮች መራራ የሆነ ትችት ይቀበላሉ፡፡ በየሳምንቱ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና የፕሬስ ድርጅቶች ውግዘት ይደርስባቸዋል፡፡ በየቀኑ በኢትዮጵያውያን/ት ዲያስፖራዎች ተቃውሞ ይቀጠቀጣሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የስልታዊ አካሄድ ለውጥ በማድረግ በሰለጠነ መልኩ በጠረጴዛ ዙሪያ ነገሮችን መፍታት ሲያቅታቸው ወደ ዱሮው የጫካ ዘመን የአውሪያዊ የድርጊት አስተሳሰባቸው ተመልሰዋል፡፡ እርግጥ ነው አንድ ጥንታዊ አባባል እንደሚጠቁመው “መዶሻ በእጅህ ላይ ከያዝክ ሁሉም ነገር ምስማር ይመስልሀል“ ነው ነገሩ፡፡ በጫካ ውስጥ የምትኖር ከሆነ እና ሁሉንም ነገር በደብቅ እና በሚስጥር አስተሳሰብ የምትመራ ከሆነ እንዲሁም የሚሰማው እና የሚያዳምጠው የእራሱን የገደል ማሚቶ ብቻ ከሆነ ሁሉም ነገር ጠላት ይመስለዋል፡፡ የሚፈለፈሉ ጫጩቶችን ወዲያውኑ መደፍጠጥ!
ወጣት ኢትዮጵያውያን/ት በገዛ ሀገራቸው ተዋርደዋል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግን ተከብረዋል፣
በአሁኑ ጊዜ ስለኢትዮጵያ ወጣቶች አሳዛኙ ጉዳይ ምርጦቹ እና የብሩህ አዕምሮ ባለቤት የሆኑት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ ተብለው ሽልማቶችን እና እውቅናን ሲጎናጸፉ በእራሳቸው ሀገር ውስጥ ግን ውርደትን እና አለመከበርን በመቀበል ላይ ይገኛሉ፡፡ ወጣት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እና የኪነ ጥበብ ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ይከበራሉ ሆኖም ግን በእራሳቸው ሀገር ይዋረዳሉ፣ ወንጀለኛ ይደረጋሉ፣ ሀሳቦቻቸው ይመረመራሉ እንዲሁም በየእስር ቤቱ ይታጎራሉ፡፡ ገዥው አካል እነዚህን የብሩህ አዕምሮ ባለቤት የሆኑትን ወጣቶች እንደ ቆሻሻ ይቆጥራቸዋል፡፡ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ እየተናገርሁ ያለሁት እነዚህን ትንታግ ወጣቶች ላለማደፋፈር እና ስብዕናቸው እንዲጎዳ ለማድረግ አይደለም፡፡ ለመሆኑ በእንደዚህ ያለ የበከተ እና የወረደ እንደ ጅብ መንጋ እያሽካካ የሚኖር የደናቁርት ስብስብ እነርሱን አመሰገናቸው አላመሰገናቸው እውቅና ሰጣቸው አልሰጣቸው ምን ሊፈይድላቸው?
ለአንጌላ ጆሊ እና ለብራድ ፒት ልዩ ምስጋና እና ጥልቅ ይቅርታ፣
አንጌላ ጆሊ እና ብራድ ፒት የኢትዮጵያ ልዩ ወዳጆች ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ የህጻናት ሞግዚት (የዛህራ፣ የ9 ዓመት ልጅ) ሆነው የእኛን ዜጋ መርዳታቸው ብቻ አይደለም፣ ሆኖም ግን ኤች አይቪ ኤይድስን እና የሳንባ ነቀርሳን በሀገራችን ለመዋጋት የሚያስችል የ2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እርዳታ ሰጥተዋል፡፡ እብሪኞቹ እና በኃይል ጡንቻቸው የሚያምኑት ወገኖቻችን እንዲህ የሚለውን ቅዱስ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ወስደው እና በአዕምሯቸው አዋህደው እንዲተገብሩት እጠይቃለሁ፣ “የሚያደርጉትን አያውቁም እና ይቅር በላቸው፡፡“ ወ/ሮ አንጌላ ጆሊን ስላላት መልካም አስተሳሰብ እና ምግባር ልባዊ የሆነ ምሰጋናዬን አቀርበለሁ፡፡ እ.ኤ.አ ፌብሯሪ 2014 በተካሄደው ዓለም አቀፍ የድፍረት ተውኔት አሸናፊነት በዓል ላይ ወ/ሮ አንጌላ በቦታው ተገኝታ ስለጀግና ግለሰቦች እና የህዝቡን ንቃተ ህሊና ለማነሳሳት ስላደረጉት ድፍረት ዘላለማዊ እውነታ ያላትን ጽኑ እምነት እንዲህ በማለት ገልጻለች፣
ይህ ተውኔት በኢትዮጵያ ውስጥ ኪነጥበብን ለማሳደግ ጠንካራ ሁኔታን የፈጠረ ነው፡፡ እንደዚህ ያለውን የፈጠራ ኪናዊ ውበት የተላበሰውን እጅግ ያማረ ጠቃሚ ታሪክ ማየት በእራሱ አስደሳች ነገር ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያን የባህል ሀብታምነት እና የአካባቢውን ባህል በማክበር ረገድ የህግ አገልግሎቱ እድገት የሚያሳዬውን ሁኔታ በግልጽ ያመላክታል፡፡ ይህ ታሪክ የኢትዮጵያን የወደፊት ትውልድ እና የሌሎችን አገሮች የህግ ጥበቃ ሳይደረግ እነርሱን እና አካላቸውን መደበቂያ በማሳጣት ለቁጥር በሚያዳግቱ ልጃገረዶች ላይ የሚፈጸመውን አስነዋሪ ድርጊት ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ደፋር ግለሰቦች እንዴት እድርገው የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ለመለወጥ እየታገሉ እንዳሉ የሚያሳይ ተስፋ የሚሰጥ እና አበረታታች ሁኔታ ነው፡፡
ድፍረት በአንድ የእራሷን ክበር ለማስከበር ስትታገል በነበረች አንዲት ደፋር ልጃገረድ፣ የዚህች ልጃገረድ ጠበቃ የሆነችዋን እና የሴቶችን ኢሰብአዊነት ድርጊት ለማስቆም በጽናት የቆመችዋን የህግ ባሉሙያ ወጣት፣ የአንድ ወጣት የኢትዮጵያ የተውኔት ባለሙያ እና ዓለምን ስለኢትዮጵያ ሴቶች ኢሰብአዊነት ድርጊት ሁኔታ ለማስተማር እንዲሁም ሌሎችን በርካታ የኢትዮጵያ ተዋንያን፣ ዳይሬክተሮችን እና ሌሎች የቴክኒክ ባለሙያዎችን አካትቶ የያዘ ነው፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ/ት ሁሉ በእነዚህ ጀግና የጥበብ ሰዎች ሊኮራ እና ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል!
“ጥቂት የሆኑ ሃሳባውያን እና በጽናት የቆሙ ዜጎች ዓለምን መለወጥ ይችላሉ፡፡ በእርግጥም እስከ አሁን ድረስ ያለው ነገር ይኸው ብቻ ነው“ ማርጋሬት ሚድ፡ ስለሰው ዘር አመጣጥ ታሪክ የሚያጠና ሳይንስ ባለሙያ ፣
=============
ድህረ ጽሁፍ፡ የድፍረት ተውኔትን ለማየት የመጡ የዲፕሎማት ሰዎች፣ አምባሳደሮች፣ እና ሌሎች ታዋቂ ሰዎች ጠቃሚ ትምህርት እንደተማሩ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አንዱ “የድፍረት” የአማርኛ ትርጉሙ ግንፍልተኛ ደፋር፣ ለሰዎች ክብር የማይሰጥ፣ እብሪተኛ እና ንቀትን የሚያሳይ ማለት ነው፡፡ ይህ ተውኔት ለዕይታ ለመቅረብ የሰከንዶች ያህል ጊዜ ሲቀረው የገዥው አካል የወጣውን ፕሮግራም አስሰርዞ ተውኔቱ እንዳይታይ ማገዱ በውጭ የዲፕሎማት ማህበረሰቡ ላይ ያለውን ንቀት እና ዘለፋ ያሳያል፡፡
የተጨናገፈውን የድፍረት ተውኔት የተመለከቱትን የአሜሪካ እና የአውሮፓ ማህበረሰብ የዲፕሎማት አባላት በየዓመቱ በሚደረግ ዓመታዊ እርዳታ በቢሊዮን የሚቆጠረውን ዶላር ለምትረዱት የእጃችሁን ዋጋ አገኛችሁ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ለማድረግ የምትችሉት ትንሹ ነገር አለ ቢባል ጠንካራ የሆነ ማስጠንቀቂያ ማውጣት ነው፡ ውሻ የሚመግበውን እጅ መንከስ የለበትም፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ህዳር 8 ቀን 2007 ዓ.ም