ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ አገዱ

  • በአድባራት አለቆች ላይ የተላለፈው ውሳኔ ‹‹ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ነው›› /ፓትርያርኩ/
  • ‹‹ቤተ ክርስቲያናችን በቂ ሕገጋት አሏት፤ ማእከሉ ተጠብቆ ሊሠራባቸው ይገባል፤›› /ሲኖዶስ/
  • ልዩ እና አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ስለ መጥራት ምክክር መደረጉ ተጠቁሟል

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፫ ቁጥር ፯፻፸፱፤ ታኅሣሥ ፲፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

addis admasየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ‹‹በቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ቤተ ክርስቲያን ዕውቅና በሰጠችው ማኅበር ላይ ተገቢ ያልኾነ ቃል ተናግረዋል›› ባላቸው በአንዳንድ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራት አስተዳዳሪዎች ላይ ያሳለፈው ውሳኔ አፈጻጸም ‹‹ሕገ መንግሥቱንና ሰብአዊ መብትን የሚፃረር ነው›› በሚል በፓትርያርኩ መታገዱ ተገለጸ፡፡

ፓትርያርኩ ኅዳር 30 ቀን በቁጥር ል/ጽ/126/300/2007 ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ ‹‹አፈጻጸሙ እንዲቆይ›› በማለት ያገዱት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና በጠቅላይ ቤተ ክህነት በተካሔዱ ጉባኤዎች÷ ‹‹ተገቢ ያልኾነ ቃል ተናግረዋል፤ ይህም አነጋገር ጉባኤውን ቅር አሰኝቷል፤›› ያላቸው የአድባራት አስተዳዳሪዎች በጠቅላይ ቤተ ክህነት በኩል ቀርበው ቀኖናዊ ምክርና ተግሣጽ እንዲሰጣቸው በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ያሳለፈው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በመንበረ ፓትርያርክና በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሾች በተካሔዱት ስብሰባዎች የቀረቡት ሐሳቦች ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱን መልካም አስተዳደርና ወቅታዊ ችግሮች›› የተመለከቱ የጉባኤተኞች አስተያየቶችና ሐሳቦች እንደነበሩ ያስታወሱት ፓትርያርኩ፣ በአጀንዳውና በተከፈተው ውይይት ተሰብሳቢዎቹ ሐሳባቸውንና አስተያየታቸውን በግልጽ መናገራቸውና ከዚኽ በመነሣት አሉ ተብለው የታመነባቸው ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ ‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃም ኾነ በሀገራችን ለሕዝብ የተፈቀደ ዴሞክራሲያዊ መብት መኾኑ የሚያጠያይቅ አይኾንም›› ብለዋል፡፡ በስብሰባዎቹ ሐሳባቸውንና አስተያየታቸውን በግልጽ ያቀረቡ ሰዎችን መገሠጽና መውቀስም ‹‹ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ይመስላል›› ሲሉ ነው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ አፈጻጸም እንዲቆይ ያስታወቁት፡፡

ጉባኤዎቹ በቤተ ክርስቲያን ጠሪነት የተካሔዱ እንደነበሩና ተሰብሳቢዎቹም የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት፣ አገልጋዮችና ሠራተኞች መኾናቸውን ፓትርያርኩ ጠቅሰው÷ የጎደለው እንዲሟላ የጠመመው እንዲቃና ያላቸውን አስተያየት በማቅረባቸው ተግሣጽና ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ቅዱስ ሲኖዶሱ ያሳለፈው ውሳኔ ‹‹የስብስባ ነፃነትንና መብትን ነፍጎ ሐቁ እንዳይነገር›› የሚከለክልና ውጤቱም‹ጊዜ ያለፈበትን አፈና በማንገሥ ችግሮች ካሉበት ተባብሰው እንዲቀጥሉ ማድረግ ነው›› ሲሉ ብለዋል፡፡ በውይይቱ ወቅት ‹‹የዳኅፀ ልሳን ወለምታ አጋጥሞም ከኾነ በወቅቱ ማብራሪያና ማስተካከያ ይሰጥበታል እንጂ እንደ ከባድ ጥፋት ተቆጥሮ ሰዎች ሊገሠጹበትና ሊወቀሱበት አይገባም፤ ሕግም አይፈቅድም፤›› ሲሉ ገልጸዋል – በደብዳቤአቸው፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ‹‹ተገቢ ያልኾነ ቃል ተናግረዋል›› ያላቸው አንዳንድ የአድባራት አስተዳዳሪዎች በጠቅላይ ቤተ ክህነት በኩል ቀርበው ቀኖናዊ ምክርና ተግሣጽ እንዲሰጣቸው ያሳለፈው ውሳኔ ‹‹ሕግንና ሰብአዊ መብትን የሚፃረር›› ብቻ ሳይኾን ‹‹ትልቁን ጉባኤ በታሪክና በሕግ ዐዋቂዎች ዘንድ ግምት ውስጥ የሚጥለው እንዳይኾን›› አስጠንቅቀው፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ዳግመኛ በጥልቀትና ከሕግ አንጻር ፈትሾ ሊያጤነው ስለሚገባ አፈጻጸሙ እንዲቆይ እንዲደረግ ለመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ በምልዓተ ጉባኤ ስብሰባው ውሳኔውን ያሳለፈው በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ እንደኾነ ውሳኔው የሰፈረበትና በቁጥር 83/187/2007 በቀን 8/3/2007 ዓ.ም. ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በተጻፈ ሸኚ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የተላከው የጥቅምት 21 ቀን ቃለ ጉባኤው ያስረዳል፡፡ በጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የሚመራው ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በዚኹ መነሻነት ውሳኔው ተግባራዊ እንዲደረግ በቁጥር 1374/11/19/2007 በቀን 18/3/2007 ዓ.ም. በአድራሻ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ቢያስታውቅም አፈጻጸሙ በፓትርያርኩ መታገዱ ታውቋል፡፡ በቃለ ጉባኤው የሰፈረው የምልዓተ ጉባኤው ውሳኔ ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው፤

ቤተ ክርስቲያናችን በቂ ሕገጋት አሏት፡፡ እነዚኽ ሕገጋት ማእከሉ ተጠብቆ ሊሠራባቸው ይገባል በማለት ጉባኤው በሰፊው ተወያይቶ፣ በቃለ ዐዋዲው ሕግና ደንብ መሠረት በደረጃው ማለትም ውሳኔ የተሰጠው ከኾነ በይግባኝ ታይቶ መምጣትና ይህን ተከትሎ መሥራት እንዳለበት አምኖበታል፡፡ እንዲኹም ቀደም ሲል በጠቅላይ ቤተ ክህነትም ኾነ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተደረጉ ጉባኤያት አንዳንድ የደብር አስተዳዳሪዎች ተገቢ ያልኾነ ቃል ስለተናገሩና ይህ አነጋገር ጉባኤውን ቅር ያሰኘው በመኾኑ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በኩል ቀርበው ቀኖናዊ ምክርና ተግሣጽ እንዲሰጣቸው ሲል ምልአተ ጉባኤው በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኗል፡፡

‹‹ተገቢ ያልኾነ ቃል ተናግረዋል›› የተባሉት የአድባራት አስተዳዳሪዎች በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚገኙና የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ቢኾንም ከማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን መዋቅር ኹሉ የበላይ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ የወጡ ሕጎችን፣ የተላለፉ መመሪያዎችንና የተሰጡ ውሳኔዎችን ለሚመለከታቸው አካላት በፊርማቸው ከማስተላለፍ ጀምሮ በተግባር ላይ መዋላቸውን የመከታተልና የመቆጣጠር ሓላፊነቶች ያሉባቸው በመኾኑ ቅ/ሲኖዶሱ በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ ያሳለፈውን ውሳኔ አፈጻጸም የማገድ ሥልጣን እንደሌላቸው ተገልጧል፡፡ እንደ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ድንጋጌ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጽ/ቤት ተጠሪነት ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በመኾኑም የቅዱስ ሲኖዶሱን መመሪያዎችና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕገጋት መፈጸምና ማስፈጸም እንደሚጠበቅበት ተመልክቷል፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ በራስዋ ሕግና ሥርዐት የምትመራበት የበላይ ሕግ÷ ሕገ ቤተ ክርስቲያን እንደኾነና በሕጉ መሠረት የምታስተዳድራቸውን ካህናትና ምእመናን የምትቆጣጠርበት፣ ለሚፈጸሙ ጥፋቶችና በደሎችም የቅጣትና የእርምት ርምጃ የምትወስድበት ደረጃውን የተከተለ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ የዳኝነት ሥልጣን እንዳላት ተጠቅሷል፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ የዳኝነት ሥልጣንም በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወሰኑ ውሳኔዎች የመጨረሻ ውሳኔዎች እንደኾኑ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ሰፍሯል፡፡ በፓትርያርኩ ደብዳቤ ‹ ‹በቤተ ክርስቲያን ጠሪነት የተሰበሰቡ ናቸው› በተባሉት ጉባኤያት የቀረቡት ሐሳቦችና አስተያየቶች በቃለ ዐዋዲው ሕግና ደንብ መሠረት ደረጃቸውን ጠብቀው ያልቀረቡ መኾናቸውን የተቸው የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔም ‹‹ቤተ ክርስቲያናችን በቂ ሕገጋት አሏት፤ እነዚኽ ሕገጋት ማእከሉ ተጠብቆ ሊሠራባቸው ይገባል፤›› በማለት አሳስቧል፡፡

የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ የማስፈጸምና አፈጻጸሙን የመከታተል ሓላፊነት ያለባቸው ብፁዕ ዋና ጸሐፊው፣ ፓትርያርኩ አፈጻጸሙ እንዲቆይ ያስታወቁበት ደብዳቤ በጽ/ቤቱ በኩል በግልባጭ የደረሳቸው ሲኾን በቋሚ ሲኖዶስ አባላትና በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድም በፓትርያርኩ የሕገ ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ጉዳይ ልዩ እና አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ስለመጥራት ምክክር መደረጉ ተጠቁሟል፡፡

corrupts and day light robbersለቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ መነሻ ከኾኑት ጉባኤያት በተለይም መስከረም ፳፯ ቀን ‹‹የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ አስተሳሰብ ማበልጸግ›› በሚል ርእስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዳራሽ በፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ የተመራውና የአድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች የተካፈሉበት ስብሰባ ተጠቅሷል፡፡ ተሰባሳቢዎቹ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ጠቃሚ ነው ብላ ላመነችበት አገልግሎቱ ዕውቅና ሰጥታ በተለያዩ አግባቦች የምትቆጣጠረውን ማኅበር÷ ‹‹ፈጣሪ የለም ይላል፤ አሸባሪና አክራሪ ነው፤›› እያሉ ከዓለም የአቀፍ ጽንፈኞች ጋራ እያስተካከሉ መወንጀላቸው አግባብነት እንደሌለው፤ የማኅበሩ አባላት የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ ኹለንተናዊ አገልግሎቱም ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ እንደኾነ አረጋግጦ ሊያሠራው በሚያስችል ሕግ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ቅዱስ ሲኖዶሱ በውሳኔው አስታውቋል፡፡

ውይይቱ በሒደቱ ከተያዘለት ርእስ በጠበበና ይልቁንም በማኅበረ ቅዱሳን ላይ አነጣጥረው ይሰነዘሩ በነበሩ አስተያየቶች የተመላ እንደነበር የሚገልጹ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ የመድረኩ አያያዝ አስቀድሞ ለተቆረጠ አጀንዳ ሕጋዊ ልባስ ለመስጠትና በአድማው ለተለዩ ሰዎች የተወሰነ እንጂ ፓትርያርኩ እንዳሉት ሐቁ የተገለጸበትና ነፃ እንዳልነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ቆራጣ ደብዳቤ ይበቃዋል፤ ከመንግሥት ጋራ በመተባበር እስከ ጫፍ አድርሱልን፤ በቶሎ ቁረጡት›› ማለት፤ ሊቃነ ጳጳሳቱንም ‹‹ከፈለጉ ቆባቸውን አስቀምጠው ወደዚያው ይግቡ›› እያሉ ማቃለላቸውና መዝለፋቸውስ በምን መመዘኛ ነው ዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግሥታዊ የሚኾነው በማለት ተሳታፊዎቹ ይጠይቃሉ፡፡

ፓትርያርኩ በተሾሙበት ቀን በፈጸሙት ቃለ መሐላ የኹሉም አባት(አበ ብዙኃን) ኾነው ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ጠብቀው ያለአድልዎ መምራት ሲገባቸው፣ ‹‹ቅዱስ ሲኖዶሱን ቅር የሚያሰኝ ያልተገባ ቃል ተናግረዋል›› የተባሉት የአድባራት አስተዳዳሪዎች ቀኖናዊ ምክርና ተግሣጽ እንዲሰጣቸው ምልዓተ ጉባኤው በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ያሳለፈውን ውሳኔ አፈጻጸም በሌላቸው ሥልጣን ማገዳቸው÷ በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ አመራር፣ በካህናቱና በምእመናኑ ዘንድ መንፈሳዊ አባትነታቸውንና ታማኝነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባው እንደሚኾን አሳስበዋል፡፡

ፓትርያርኩ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን በመጣስና የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሥልጣን በመፃረር የውሳኔውን አፈጻጸም ያገዱበት ደብዳቤpat ab mathias banned holy synod decision pat ab mathias banned holy synod decision02