Letter to the former ETV ይድረስ ለቀድሞው ኢቲቪ – የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ ያለው ማን ነበር?
ለሶደሬ
ሰሞኑን አዲስ ስያሜ ይዘህ የወደፊት መለያዮን/ፈረንጆች ሎጎ ይሉታል/ ስሩልኝ፤ የጣቢዬንም መርህ /ሞቶ/ ሰይሙልኝ ብለህ ያስነገርከውን ማስታወቂያ ተመልክተናል፡፡ እርግጥ ነው ገና ስያሜህን ቀይረህ በኢቲቪ መስኮት ብቅ ባልክበት ሰሞን አንድ ጦማር በዚሁ ገፅ ላይ መፃፋችንን አትረሳውም፡፡‹ ለባለሙያዎች ውድድር ብታወጣ የተሻለ አዲስ ለዓይን ማራኪ መለያ ታገኛለህ› ብለን ያቀረብነው፡፡ ሀሳብ ብዙም ሳይቆይ ሰምተህ ወደ ጨረታ መሄድህ ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡
ውድ የቀድሞ ኢቲቪ
አዲሱን መለያህን በተመለከተ ከስምንት ሺህ በላይ ሰዎች ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር ተሳትፎ ማድረጋቸውን ነግረኸናል፡፡ጥሩ ነው፡፡ ስራውንም በራስህ ሳይሆን በባለሙያዎች አዋቅረህ ማስገምገምህንና የዩኒቨርሲቲው መምህራን የኮሚቴው አባላት እንደነበሩ ተመልክተናል፡፡ ነገር ግን ባለሙያ የተባሉት የዩኒቨርሲቲ መምህራን በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ናቸውን? ይህንን ጥያቄ የጠየቅነው ያለነገር አይደለም፡፡ አንተን እንዲያማክሩና ሙያዊ አስተያየት እንዲሰጡህ በጀት መድበህ የሰየምካቸው ‹ምሁራን› እንዴት ብለው ነው ሞቶህን በእንግሊዝኛ መርጠው የሰጡህ?!፡፡
ውድ የቀድሞ ኢቲቪ
ለመሆኑ ጣቢያህ ከ24 ሰዓታት ስርጭት ከ18 ሰዓታት በላይ የሚሆነውን ስርጭት የሚያቀርበው ለሀገር ውስጥ ተመልካችና ለኢትዮጵያውያን ሆኖ ሳለ ከቶ ለምንድነው ሞቶው በእንግሊዝኛ እንዲቀመጥ የተደረገው? በእንግሊዝኛ ማድረጉ ከዓለም አቀፍ አሰራር ጋር ያገናኛል ቢባል እንኳ በመጀመሪያ መፃፍ ያለበት የትኛው ነው? መቼም ሀገሪቱ በአፍሪካ ውስጥ የራሷ ቋንቋና ፊደል ያላት ብቸኛ ሀገር መሆኗን ላንተም ሆነ ለ‹ምሑራኑ› መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያውያን የሚኮሩበትና በቅኝ አለመገዛታችንን ከሚያውጁበት ቀሪ ቅርሶች መሃከል የቀረው ፊደላችን ነበር፡፡ታዲያ ይህንን ፊደላችንን ከቲቪ መስኮትህ ላይ በቅድሚያ እንዳይታይ መከልከልህ ምን ይባላል? ለመሆኑ ‹ጎረቤትህ የኤርትራ ቲቪ› ይህንን ፊደላችንን እንዴት አሽሞንሙኖና አሳምሮ እንደሚጠቀምበት ልብ ብለሃል? በእጅ የያዙት ወርቅ ሆኖ ይሆን ?…
ውድ የቀድሞ ኢቲቪ
እርግጥ ነው የሀገሪቱ የሥራ ቋንቋ አማርኛ እንደሆነ በግልፅ ተደንግጓል፡፡ ህገ መንግስቱን ማክበርም ሆነ ማስከበር አንተን አይመለከትም ማለት ነው?
ይድረስ ለቀድሞው ኢቲቪ
ወይስ እንደ ብሔራዊ ጣቢያነትህ ምንግዜም የሀገሪቱን የስራ ቋንቋ የግድ መጀመሪያ መፃፍ እንዳለብህ መንገር ሃምሳ ዓመቱን ለማክበር ሽር ጉድ እያለ ካለ ከእንዳንተ አይነት ‹ጎልማሳ› አይጠበቅም፡፡ልጆቻችንም ዘወትር በየትምህርት ቤቱ ‹ድንጋይ መወርወርና አማርኛ መናገር ያስቀጣል› እየተባሉ በቋንቋቸው እንዲያፍሩ የሚደረጉበትን አካሄድ የሚያግዝ መንገድ መከተልህ ምነው ? ያሰኛል፡፡ በመሆኑም ቢያንስ መግባቢያችን ሙሉ ለሙሉ አማ- እንግሊዝኛ ከመሆኑ በፊት አንድ ብትለው ይበጃል እንላለን፡፡
ውድ የቀድሞ ኢቲቪ
ለመሆኑ የመረጥከውና ለህዝብ ምርጫ ያቀረብከው ሞቶ ምን ያህል ከፖሊቲካዊ አስተሳሰብ የፀዳ ነው? የሚለውን አስተያየት እዚህ ላይ ለመስጠት አንፈልግም፡፡ ምክንያቱም ቃሉ ራሱ ስሜቱንና ምንነቱን ይናገራልና፡፡በመሰረቱ አንተ ከሰየምካቸው ‹ምሑራን ›የተሻለ እውቀት ባይኖረንም አንድ ሞቶ /መርህ/ሲወጣም ሆነ ሲሰየም የጣቢያውን የወደፊት ዓላማና ግብ የሚያንፀባርቅና በጊዜ ሂደት የማይቀየር ሊሆን የሚገባው ይመስለናል፡፡ ከመጣው ስርዓት ጋር የሚቀያየር ሞቶ ማስቀመጥ የጣቢያውን የተአማኒነት ደረጃ እንደሚያወርደው አይጠፋህም፡፡ ታዲያ ይህ ሞቶ የሚወጣውና የሚያገለግለው ህዳሴው እስከሚረጋገጥ ድረስ ብቻ ነው ወይስ ከህዳሴውም በኋላ ይቀጥላል? ከህዳሴው በኋላ ትርጉም ይኖረዋል? አይመስለንም፡፡ጣቢያው በእስካሁን አካሄዱ በህዝብ ዘንድ ያጣውን የተአማኒነት ችግርስ አዲሱ ሞቶ ማስተካከልና ማረም አልነበረበትም? ህንፃዎችንና መኖሪያ ቤቶችን ከዲሽ ወረርሽኝ የሚከላከል ሞቶ ከወዴት ይገኛል?
ውድ የቀድሞ ኢቲቪ
ለመሆኑ የተመረጡት ሞቶዎች አንድ ራዲዮንና ቴሌቪዥንን በበላይነት ከሚመራና ከሚያስተዳድር ጣቢያ ጋር ያላቸው ቁርኝት ምን ያህል ነው? ሁኔታው እጅግ አናሳ መሆኑን ያሳያል፡፡ አሁን ለምርጫ የቀረቡት ሞቶዎች እኮ የሬዲዮ እንጂ የቴሌቪዝን ሞቶ የመሆን አቅማቸው ደካማ ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡ ለምሳሌ የህዳሴው ድምፅ/The voice of Renascence /የብዝሃነት ድምፅና/ The voice of Diversity / እና የሁለቱ ጥምረት ውጤት የሆነው የህዳሴውና የብዛሃነት ድምፅ/ The voice of Renascence and Diversity / የሚሉት ሞቶዎች ትኩረታቸው ድምፅ ላይ በመሆኑ
የኢትዮጵያ ሬዲዮ መለያ ብቻ ከመሆን አይዘሉም፡፡ የቴሌቪዥን ቴሌክኖሎጂ ከሬዲዮ የሚለየው ድምፅ ላይ ብቻ ሳይሆን ምስልንም የሚያካትት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ማንም ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው ግን ለመጀመሪያ ጊዜ እነዚህን ሞቶዎች ሲሰማ የሬዲዮ ሞቶ መሆናቸውን ሊጠራጠር አይችልም፡፡
ውድ የቀድሞ ኢቲቪ
ለመሆኑ ስምህን ወደ ኮርፖሬሽን ስትቀይር የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ኮርፖሬሽን ለማለት ምነው አልደፈርክም? ሬዲዮና ቴሌቪዥን የተለመዱ ቃላት መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ‹ብሮድካስት› ብለህ ከሰየምከው የእንግሊዝኛ ቃል ይቀላል፡፡ በተለይም ፊደል ላልቆጠሩ ወገኖቻችን ‹ብሮድካስት› የሚለው ቃል የውጪ ድርጅት መለያ አድርገው ቢገምቱ ጥፋት የለባቸውም፡፡ የቋንቋ ምሑራን በዚህ ጉዳይ ላይ እንዴት አስተያየት ሳይሰጡበት እንዳለፉ ግራ ያጋባል፡፡ እርግጥ ነው የድርጅትህ ስያሜ የፀደቀው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ የቋንቋ ባለሙያ እጥረት ያለው አንተ ጋር ብቻ ሳይሆን እዚያም አካባቢ እንደሆነ አንድ ማሳያ ይመስለናል፡፡
ውድ የቀድሞ ኢቲቪ
የአንድ ቴሌቪዥን ሎጎም ሆነ ሞቶ ሀገርን የሚያስተዋውቅና የሀገርን ገፅታ የሚገነባ መሆኑ ካልተዘነጋ በስተቀር ብዙዎቹ ይህንኑ ስሜት ሲያንፀባርቁ ይታያል፡፡ አንዳንዶቹ ድርጅቶች የሀገር ቤት ቋንቋና ፊደልን በአግባቡ የሚያስተዋውቁበት መንገድ በስፋት ይታያል፡፡ የሌሎች ድርጅቶችን መለያ ትተን ካንተ ስራ ጋር ተቀራራቢ ስራ የሚሰሩት ራዲዮ ፋናና ሸገር ሬዲዮ ሎጓቸውን እንዴት በአማርኛና በእንግሊዝኛ አሰርተው እንደሚጠቀሙ ምናልባት ካላየኸው በዚህ አጋጣሚ ልንጠቁምህ ይገባል፡፡ የሀገሪቱን የቱሪዝም ሃብት የማስተዋወቅና የቱሪስት ፍሰቱን በማብዛት በ2012 ዓ.ም ከአፍሪካ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየሰራሁ ነው የሚለው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ምነው ነገሩን ችላ አለው?
ውድ የቀድሞ ኢቲቪ
ለመሆኑ የድሮ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የድሮው ሎጎ ባለበት ቢቀጥል ምን ይመስልሃል? የድሮው ሎጎ ላለፉት 50 ዓመታት በየዕለቱ ይታይ የነበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የቴሌቪዥን ተመለካች ህሊና ውስጥ አሁንም አለ ለማለት እንደፍራለን፡፡ በተለይም ድሮ በአባባ ተስፋዬ ተረቶች ያደግን ልጆች የአባባ ተስፋዬ ተረት ከመጀመሩ በፊት ቴሌቪዥኑ ፊት ተደርድረን ስንጠብቃቸው የቲቪውን ስርጭት መጀመር የሚያበስረን ይህ የድሮው አንቴና የተሸከመ ጎጆ ቤት ነበር፡፡በነገርህ ላይ በዚህ ዓመት 50ኛ ዓመትህን ለማክበር ተፍ ተፍ እያልክ እንደሆነ ሰምተናልና ይህንን የድሮ ሞቶ የሰራውን ሰው ፈልገህ ብታስተዋውቀን ከዚህ አለፍ ሲልም ያለፈው 50 ዓመታት ባለ ታሪክ በመሆኑ ብትሸልመው ደስ ይለናል፡፡ የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ ያለው ማን ነበር?
ውድ የቀድሞ ኢቲቪ
በል ቻዎ…ቁ
With our e-mail alerts, you will get everything from breaking news about Ethiopia to the days most popular videos, drama, health tips and stories sent straight to your inbox. Sign up for Email alerts
