The first female stage Actress, Artist Selamawit G. Selassie passed away በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ተዋናይት ወ/ሮ ሰላማዊት ገብረሥላሴ ማረፋቸው ተነገረ።

The first female stage Actress, Artist Selamawit G. selassie passed away .. በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ተዋናይት ወ/ሮ ሰላማዊት ገብረሥላሴ ማረፋቸው ተነገረ። ነፍስ ይማር ። ከአንድ ዓመት በፊት ድንቅ መጽሔት ከቤታቸው ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸው ነበር፣ እነሆ ለማስታወሻ ….

ሠላማዊት ገ/ሥላሴ – የመጀመሪያዋ የሴት አርቲስት (በጽጌ አይናለም የድንቅ መጽሔት ሪፖርተር ከአዲስ አበባ)
አብዛኛውን ጊዜ አስቸጋሪው ነገር ለአንድ ነገር የመጀመሪያ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ማህበረሰቡ ካወጣው የአኗኗር ይትባህል ወጥቶ “ያልተሰጠውን “ ስራ ለመስራት መመኮር የበለጠ ከባድ ይሆናል፡፡ ዛሬ የምናስተዋውቃችሁ እንግዳ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የሴት ተዋናይ የሆኑትን አርቲስት ሠላማዊት ገ/ስላሴን ነው፡፡ የ77 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት አርቲስት ሠላማዊት ዛሬም በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲያውም ላናግራቸው ቤታቸው በተገኘሁ ጊዜ ያለመነፅር እርዳታ መፅሐፍ ቅዱሳቸውን እያነበቡ ነበር ያገኘኋቸው!
በቅድሚያ እንዴት ወደ ኪነጥበብ ሙያ ሊገቡ እንደቻሉ ያጫወቱኝን ላካፍላችሁ፡፡
ወደዚህ ሙያ የገባሁት አስቤበት አይደለም፡፡ አንዲት ዘመናይ የምትባል ጓደኛ ነበረችኝ፡፡ ዘፈን ጭፈራ ትወዳለች፡፡ ታዲያ ያኔ አራዳ ጊዮርጊስ ቤቴክርስቲያን ፊት ለፊት የሚገኘው የድሮው ማዘጋጃ ቤት ሙዚቀኛ ለመቅጠር እንደሚፈልግ ትሰማና “ነይ የእጅ ስራ አሰልጥነው የሚቀጥሩ ሚሲዮናውያን ማስታቂያ አውጥተዋልና እንመዝገብ” ትልና ይዛኝ ትሄዳለች፡፡ እኔም እውነት መስሎኝ ተከትያት ሄድኩ፡፡ እዚያ ስደርስ በሹራብ መስሪያ ማሽን ፋንታ ፒያኖ፣ሳክስፎንና ቫዮሊን ተደርድሯል፡፡ ከሁሉ በላይ ያስደነገጠኝ ደግሞ እዚያ ያሉት በሙሉ ጎረምሶች መሆናቸው ነው፡፡ እነ ተስፋዬ ሳህሉ፣መኮንን አበበ፣አውላቸው ደጀኔ፣ተፈራ አቡነ ወልድ…ተኮልኩለውልሻል፡፡”እንዴ ከዚህ ሁሉ ጎረምሳ ጋር ምን ልሰራ ነው ያመጣሽኝ? “አልኩና ዘመናይ ላይ ጮህኩባት፡፡ እውነቱን ስትነግረኝ ትቻት ወደቤት ተመለስኩ፡፡ በኋላ ግን እንደምንም አባብላኝ በድምፅና በተውኔት ክፍል ተመዘገብኩ፡፡ የድምፅ ፈተና የፈተነኝ ተፈራ አቡነ ወልድ ነበር፡፡ የእሱን ፈተና አለፍኩ፡፡ በተውኔት ደግሞ የአፄ ቴዎድሮስን ሚስት ወ/ሮ ጥሩ ወርቅን ሆኜ እንድሰራ ነበር የተሠጠኝ፡፡ቃለ ተውኔቱን ብሸመድደውም እንዴት አድርጌ በወንዶቹ ፊት ልስራው? ያቺ እኔን ይዛ የሄደችው ጓደኛዬ ፈተናውን ስለወደቀች ብቸኛዋ ሴት እኔ ሆኛለሁ፡፡በወቅቱ የቲያትር ክፍሉ ኃላፊ የነበሩት አርመናዊው ካፒቴን ካንልቫንዲ ሁኔታዬን አይተው ሁላችንንም ሰብስበው እኔን አጠገባቸው አቆሙኝና “ትሰማላችሁ ይህቺ ልጅ ፈርታለች፣የፈራቸው ደግሞ እናተን ነው፤ስለዚህ ሁላችሁም እንደማትተናኮሏት ቃል ግቡልኝ”አሏቸው፡፡ ወንዶቹ በሙሉ “አንተናኮላትም!” አሉ፡፡ “እስኪ ማን ይሙት?” ሲሏቸው “ኃይለ ሥላሴ ይሙት” ብለው በመሃላ አረጋገጡና ልምምዴን በእነሱ ፊት ያለ ፍርሃት አቀረብኩ፡፡
ወንዶቹን ብለማመዳቸውም መድረክ ላይ ግን ለመውጣት ድፍረት ከየት ይምጣ! እኔ አልሆንልኝ ሲል ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ) ሸመደደውና ፂሙን ተላጭቶ፣ ጡት አበጅቶና ቀሚስ ለብሶ ተጫወተው፡፡ ያኔ እልህ ያዘኝ፡፡ እንዴት እኔ ሴቷ እያለሁ እሱ ይሰራል? አልኩና ለመጀመሪያ ጊዜ በ1938 ዓ.ም መድረክ ላይ ወጣሁ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ቲያትርን ያሳየነው በድሮው ሲኒማ ኢትዮጵያ ነበር፡፡ሙያውን ከሚወዱት አድናቆትንና ክብር ሳገኝ “እንዴት ሴት ልጅ አደባባይ ያውም ከወንድ እኩል” ከሚሉት ደግሞ ነቀፌታን ቢያከትልብኝም ተስፋ ሳልቆርጥ ገፋሁበት፡፡
ለአምስት አመታት ማዘጋጃ ቤት ከቆዩ በኋላ በ1944 ዓ.ም የሀገር ፍቅሩ ማቴዎስ በቀለ ከነ አውላቸው ደጀኔ ጋር አስኮብልሎ ወደ ሀረር ወሰዳቸው፡፡ በአጋጣሚ ሀረር ያረፉት በአክስታቸው ሆቴል ነበር፡፡ “የመጀመሪያው የቤተሰብ ፈተና በእሷ ተጀመረ” ይላሉ አርቲስት ሠላማዊት፡፡ “እንዴት በዘራችን የሌለውን እንደ ንጋቷ ከልካይ አዝማሪ ትሆኛለሽ?” ብላ ተቆጣችኝ፡፡ አርቲስት ሠላማዊት ያደጉት እኚሁ አክስታቸው ጋር ነው፡፡ ሆኖም ከአራተኛ ክፍል በላይ አላስተማሯቸውምና ቂም ይዘዋል፡፡ አጋጣሚው ደግሞ ቂማቸውን እንዲወጡ ረድቷቸዋል፡፡ “ታዲያ ያኔ አስተምሪኝ ያልኩሽ ለዚህ አልነበረም? አንቺ ግን የሆቴልሽ አሻሻጭ እንድሆን ነበር የፈለግሽው፡፡ ስለዚህ ተይኝ…” ብዬ ስጮህባት ተወችኝ” ሀረር ለአንድ ዓመት ከቆዩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡
በዳዊትና ኦርዮን፣አፄ ቴዎድሮስ፣ንግስተ ሳባ፣ስነስቅለት፣አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም፣አሸብር፣እኔና ክፋቴ፣የአዛውንቶች ክበብ…በተሰኙ ቲያትሮች ላይ የተወኑት አርቲስት ሠላማዊት ከለማ ገ/ሕይወት ጋር የሠርግ ዘፈኖችን የተጫወቱ ሲሆን ተወዛዋዥም ነበሩ፡፡ በ48 ዓመት የመድረክ ቆይታቸው ሩቅ ምስራቅ፣ሶቪየት ህብረት፣ሱዳንና ኡጋንዳ ሄደዋል፡፡ እስኪ በነዚህ ጊዜያት ካጋጠምዎት የማይረሱትን ያጫወቱን ብያቸው እንዲህ ነበር ያሉኝ፡፡
አንድ ጊዜ ለአዲስ ዓመት ሶቭዬት ህብረት ነበርን፡፡ ጨዋታችንን አሳይተን ከጨረስን በኋላ አብረውን ከነበሩት አንዱ አሁን በሕይወት የለም ይሄን የሶቭየት ቮድካ ሲጨልጥ ያመሽና ሞቅ ሲለው እንደአገሩ መስሎት አንዷን አስተናጋጅ ይጎሽማል፡፡ አጅሪት መጥረጊያዋን ላጥ አድርጋ ኮሪደር ለኮሪደር አሯሯጠችዋ! እኛ ክፍላችን ገብተናል፡፡ ግርግሩን ሰምተን ስንወጣ እሱ ነፍስ ይዞት ይሮጣል፡፡ በኋላ ቡድኑን ይመሩ የነበሩት አቶ ብርሃኑ እንደምንም ብለው አስጥለውት ገብቶ ተኛ፡፡
ሱዳን ደግሞ የሆንኩትን ልንገርሽ ሁልጊዜ የትም ስንሄድ “ያገኛችሁትን ብሉ” እንባላለን፡፡ እኔ ግን አክራሪ ቢጤ ስለሆንኩ የሱዳኖቹን ምግብ ለመብላት አንጀቴ ተቆለፈ፡፡ ምግብ ትቼ ውሃ ብቻ ስጠጣ ቆይቼ ታመምኩና ሆስፒታል ተወሰድኩ፡፡ ሐኪሙ ምግብ ካለመብላት የመጣ ድካም ነው አለና ቫይታሚን ወጋኝ፡፡ ቫይታሚኑ አለርጂ ሆኖብኝ ፊቴን አያሳብጠውም! ሌላ ጭንቀት ፊቴ አብጦ እንዴት መድረክ ላይ እወጣለሁ፡፡ አለቃችን “በይ እንደምንም በይና ስራሽን ቀጥይ” ብለው ተቆጡኝና ዓሣ አስጠብሰው አመጡልኝ፡፡ ለካ በአገራቸው ዓሣ ከእነ አንጀቱ ነው የሚጠብሱት፡፡ ገና ነካ ሳደርገው አንጀቱ አይወጣልሽም! አዬ የኔ ነገር አበቃለት፡፡ እዛው ሱዳን ገጠር ዘፈን ለማሳየት ስንሄድ ምግብ በቡድን ተይዟል፡፡ ለኔ በአጋጣሚ ዳቦ እና የተቀቀለ እንቁላል ደረሰኝ፡፡ እንቁላሉን ልጬ ከፈት ሳደርገው ውስጡ ምን አገኝልሻለሁ? ጫጩት! ጫጩቱን ዳቦ ውስጥ ከተትኩኝና ዛፍ ላይ ሰቅየው ኮካዬን ብቻ ጠጥቼ ጉዞ ቀጠልን፡፡ ስንመለስ አብረውኝ የነበሩት ጓደኞቼ “እስኪ የሰላም ጫጩት አድጋ እንደሆን እንያት” እያሉ ሲያሾፉብኝ ቆዩ፡፡
ካላበዛሁብሽ እዚህ ከገጠመኝ ሁለቱን ልንገርሽ፡፡ “አሉላ አባነጋ” ትያትር ላይ የአፄ ዮሐንስን ጠላ ቤት አብርኸትን ሆኜ ነው የምጫወተው፡፡ ታሪኩ ላይ አሉላ እና ደበብ ይጣላሉ፡፡ እኔ የደደብ ወዳጅ ነኝ፡፡ ታዲያ አሉላ ደበብን ሲመታው እኔ አሉላን በዋንጫ እመታዋለሁ ታዲያልሽ አንድ ቀን ይህን ክፍል ስንጫወት አሉላን በዋንጫ እመታለሁ ስል ያደረኩት ነጠላጫማ ያንሸራትተኝና ሽው ብዬ ወደቅሁልሽ፡፡ ጣውላው ቻይናዎች ለሚያሳዩት ትርዒት እንዲመች ተብሎ እስከሚያበራ ተወልውሎልሻል፡፡ እኔ ስወድቅ ተመልካቹ አክት ያደረኩ መስሎት ከዳር እስከ ዳር ሆ! ብሎ ሳቀ፡፡ እኔ በድንጋጤ ከምኔው እንደተነሳሁ ሳላውቅ ጨዋታዬን ቀጥያለሁ፡፡ አብረውኝ የሚሰሩት የተጎዳው መስሏቸው ደንግጠዋል፡፡ ስጨርስ ያበጠ እጄን በበረዶ አሽቼ አዳንኩት እልሻለሁ፡፡
ሌላ ግዜ ደግሞ ኦሮምኛ ልንጨፍር ነው፡፡ ወንድና ሴት ሆነን ነው የምንጨፍረው፡፡ የኔ አጫፋሪ ረስቶት እዛው መድረክ ኋላ ቀርቷል፡፡ ባይ ብቻዬን ነኝ፡፡ ከዚያ እየጨፈርኩ ወደ ኋላ ሄጄ ያንን ልበ ቢስ አጫፋሪዬን ይዤ ወደ መድረክ መጣሁ፡፡ አሁንም ተመልካቹ አዲስ ስልት መስሎት አጨበጨብልኝ!
አርቲስት ሰላማዊት በሕይወታቸውም ሆነ በሙያቸው ብዙ አሳዛኝ ነገሮች ገጥመዋቸዋል፡፡ “በሕይወቴ ከባዱ ነገር ከሶስቱ ልጆቼ ሁለቱ በሞት ማጣቴ ነው” ይላሉ በሃዘን ስሜት ፡፡ በሙያቸው ደግሞ ምክንያቱን በማያውቁት ሁኔታ ለዘጠኝ አመታት በወር 50ብር ብቻ እየተሰጣቸው ቤታቸው እንዲቀመጡ ተደርገዋል፡፡
አርቲስት ሰላማዊትን ከሁሉም በላይ የሚያስደስታቸው “እንዴት ሴት ልጅ አደባባይ ትወጣለች” የሚለው እሳቤ ተለውጦ ማየታቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ “ብቻዬን እተውንበት በነበረው መድረክ ላይ መተወን ብቻ ሳይሆን ራሳቸው ትያትር የሚፅፉ፣ የሚያዘጋጁ፣ የሚተረጉሙ ሴቶችን ሳይ እንዴት እንደሰታለሁ መሰለሽ! በእኛ ጊዜ እኮ በምናጠናው ተውኔት ላይ እንኳን ሀሳብ መስጠት አንችልም ነበር፡፡ “ደግሞ አንቺ ምን ታውቂያለሽ” ስለምንባል በሰው ፊት ላለማፈር ዝም ነው የምንለው፡፡ ይሄ ሁሉ ቀርቶ በመመልከቴ ራሴን እንደ እድለኛ እቆጥረዋለሁ፡፡ ለኔ ከሚሊዮን ብር የሚበልጥ ነገር ነው፡፡ እንኳንም ያኔ ደፍሬ ወጣሁ እላለሁ፡፡”
በሚያሳዩት ድንቅ አተዋወን ከቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ እጅ የተለያዩ ሽልማቶችን የተቀበሉት አርቲስት ሰላማዊት ዛሬ በወር በሚያገኙዋት 296 ብር የጡረታ አበል ከአጎታቸው ጋር ይኖራሉ፡፡” ረዳት ሳያስፈልገኝ ምግቤን አብስዬ፣ ልብሴን አጥቤና ቤቴን አፅድቼ እየኖርኩ ነው፡፡” የሚሉት የ77 ዓመቷ አርቲስት ካዛንችስ መተባበር ሆቴል አካባቢ ነው የሚኖሩት፡፡ እንደው ትዝ ብሎዎት ሊጠይቋቸው ከሄዱ እኔን እንዳገጠሙኝ በረንዳቸው ላይ ያለ መነፅር መፅሐፍ ቅዱሳቸውን እያነበቡ ያገኟቸው ይሆናል፡፡

[ዛሬ ንጋት ላይ ግን ማረፋቸው ተሰምቷል፣ ወ/ሮ ሰላማዊት የአንድ ወንድና የአንዲት ሴት ልጆች እናት ነበሩ]

Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።