ልጇን አንቃ ገድላ ለሦስት ቀናት የደበቀችው እናት በ18 ዓመት እሥራት ተቀጣች Mother sentenced to 18 years for strangling her own son to death, hiding his body for three days

በ  
የአንድ ዓመት ዕድሜ ያለውን ህፃን ልጇን ተሰድቤበታለሁ፤ ተዋርጄበታለሁ በሚል መነሻ በተኛበት አንቃ በመግደል ለሶስት ቀናት በሻንጣ ውስጥ እንዲቆይ ያደረገችው ተከሳሽ፤ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 20ኛ ወንጀል ችሎት ጥፋተኛ በመባሏ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ ማክሰኞ ህዳር 30 ቀን 2007 ዓ.ም ተፈረደባት።

የ18 ዓመት ዕድሜ ያላት ተከሳሿ አስቴር ሽፈራው ስትባል፤ የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ በክስ መዝገቡ እንደሚከተለው አትቷል። ተከሳሿ ሰውን ለመግደል በማሰብ ታህሳስ 10 ቀን 2005 ዓ.ም ከንጋቱ 12 ሰዓት ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው መንደር 8 ቀርሳ በሚባለው አካባቢ በቤት ሠራተኝነት በተቀጠረችበት የወ/ሮ ወርቄ መኮንን እና አቶ ለማ ዘውዴ ቤት በተሰጣት ሰርቪስ ክፍል ውስጥ የአንድ ዓመት ዕድሜ ያለውን ህፃን ልጇን ቤቢ ጌታቸውን ጨካኝነቷን በሚያሳይ ሁኔታ ገድላዋለች ይላል። ዐቃቤ ሕግ ስለግድያው አፈፃፀም ሲገልጽም፣ ተከሳሽ ህፃኑ በተኛበት ወቅት በእጇ አንቃ የገደለችው መሆኑን፤ እንዲሁም ድርጊቱን ከፈፀመች በኋላ ለሶስት ቀናት አስክሬኑን በማዳበሪያ ውስጥ ጠቅልላ በሻንጣ ያስቀመጠች በመሆኑ የህፃኑ አስክሬን በመሽተቱ ምክንያት ሊታወቅ መቻሉን በመጥቀስ የፈፀመችው ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ነው ሲል ያትታል።

ተከሳሿ የዐቃቤ ሕግን ክስ በሚገባ ልትከላከል ባለመቻሏ ፍርድ ቤቱ ህዳር 25 ቀን 2007 ዓ.ም ውሎው ጥፋተኛ ናት ሲል በይኗል። ዐቃቤ ሕግ በቅጣት አስተያየቱ ግለሰቧ በፈፀመችው ወንጀል ያልተፀፀተችና ጥፋቷንም አምና ይቅርታ ያልጠየቀች በመሆኑ በሞት እንድትቀጣ ጠይቋል።

     የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 20ኛው ወንጀል ችሎት በበኩሉ የቅጣቱን መነሻ ዕድሜ ልክ በማድረግ እና ተከሳሿ የወንጀል ሪከርድ የሌለባት እንዲሁም የኑሮ ደረጃዋ ዝቅተኛ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ ሲል ትናንት በዋለው ችሎቱ ፍርዱን አስተላልፏል።

ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜላችሁን አስመዘግቡ።