የሚያስመርሩኝ የአማራ ልሂቃንና ያስመረረኝ አስተሳሰባቸው
(በአማን ነጸረ) ሁለት ጽንፍ የያዙ ኃይላት ያገሪቱን የፖለቲካ መድረክ ተቆጣጠረዋል–ያንድነት ኃይላት ነን ባዮችና ብሔረሰባውያን!! 2ቱም የየራሳቸው በጎ ጎን እና ለሀሳባቸው አሳማኝ ምክንያቶች እንዳላቸው እረዳለሁ፡፡ሆኖም በጎ በጎውን ላቆየውና የሚያሥከፋኝን ልናገር፡፡ያደፋፈረኝ የልሂቃኑን የብሔር መነሻ ከአመለካከታቸው ለማስተሳሰር የደፈረው የዶ/ር መረራ መጽሐፍ ነው፡፡ 1– ትናንት የተፈጸሙ በደሎችን ሽምጥጥ አድርገው ይክዳሉ ወይም ያለባብሳሉ፡፡ “እኔ አልጨቆንኩህም ሥርዓቱ ነው” ማለት አንድ ነገር ነው፡፡ነገር ግን ተጨቆንኩ ብሎ ያመነን ማኅበረሰብ–ያውም ስለጭቆናው ከአያት ቅድመ – አያቱ ብቻ ሳይሆን ከበዙ የአማርኛ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ሊረዳ የሚችልን ፊደል የቆጠረ ትውልድ ስለ አንተ አለመጨቆን ታሪክ እጽፍልሀለሁ ማለት ግብዝነት ነው!! “ነገሥታቱ እናንተን ብቻ ሳይሆን እኛንም ጨቁነዋል” የሚለው መከራከሪያ እኔ ራሴ ብዙ ጊዜ ብጠቀምበትም በኢ/ያ የጭቆና ትረካ አቀራረቡ ትክክል አልሆንልህ ይለኛል፡፡ምክንያቱም የአንድ ብሔር የራስ በተባለ ሰው (ብሔር) መንገላታትና ከራስ ውጭ ባለ ሰው(ብሔር) መንገላታት ያለው ትርጉም ይለያያል፡፡ለምሳሌ፡- የአጼ ቴዎድሮስ የሸዋን መሳፍንት እጅ መቁረጥ እና የአጼ ምኒልክ የኤርትራውያንን ምርኮኞች እጅና እግር መቁረጥ ታሪኩን እንደሚዳኘው ሰው የብሔር ማንነት ትርጉሙ ሊለያይ እንደሚችል መረዳት አለብን፡፡የምኒልክ ንጉሥ ተ/ሃይማኖትን እምባቦ ላይ መውጋት ራሱን እንደ ምኒልክ ልጅ ለሚቆጥረው የዛሬ ዘመን የጎጃም ልሂቅ ምንም ላይመስለው ይችላል፤ለወላይታው ልሂቅ ግን የምኒልክ ጦናን መውጋት የአባት ተግባር ሳይሆን በማንነት ላይ የተቃጣ የጎረቤት ትንኮሳ ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡የምኒልክ የደቡብ ሕዝቦችን የማስገበር ሂደት አፈጻጸሙ ታይቶ “ባልተወለደ አንጀቱ…” ቢባል አይግረመን፡፡ “እኔ ስላልተሰማኝ ለምን ይሰማችኋል??” አንበል!!በቃ!! የተሰማው የተሰማውን በተሰማው መጠን ይናገር!!ድርጊቱን እስካመንን ድረስ ቢያንስ […]