‘አንድነት’ ከሆያሆዬ ወጥቷል – አቅጣጫው ዴሞክራሲያዊ Dominant ፓርቲ መሆን ነው

(አሥራት አብርሃም – የአንድነት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ‹‹የአንድነት እስትራቴጂ ከሁሉም ይለያል!›› በሚል ርዕስ በፌስቡክ ገጹ ያተመው) በምርጫው እንደሚሳተፉ እርግጠኛ ሳይሆኑ የምርጫ ምልክት ከወሰዱ ፓርቲዎችና በሂደቱ በደመነፍስ ከገቡ ፓርቲዎች አንድነት በእርግጠኝነት የተሻለ አቅጣጫ ያስቀመጠ ፓርቲ ነው። የፖለቲካውን ምህዳር ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር በማስፋት በምርጫው ላይ በሙሉ ልብ ለመሳተፍ ወስኗልና። አንድነት በባዶ መሬት ህዝቡን ሳያደራጁ ህዝባዊ አመፅ ከሚጠሩትም በእጅጉ የተሻለ እቅድ ያለው ፓርቲ ነው! አሥር ሰው ይዞ ፓርቲ መመስረት ይቻል ይሆናል አሥር ሰው ይዞ ስርዓት መቀየር ግን የሚታሰብም፤ የሚቻልም አይደለም። ስለዚህ እስኪ በመጀመሪያ ህዝቡ ከጫፍ እስከጫፍ ይደራጅ፤ እስኪ በምርጫው ሂደት በንቃት እንዲሳተፍ እናድርገው፤ ከዚያ ባግባቡ የተደራጀ ህዝብ ምን ማድረግ እንደሚችል ለማየት ቀላል ነው የሚሆነው። መምረጥ የሚችል ዜጋ ሁሉ በትክክል የህዝብ ታዛቢዎች ይምረጥ፤ የምርጫ ካርድ በነቂስ ወጥቶ ይያዝ፤ እንደገናም በነቂስ ወጥቶ ይምረጥ ይህን ሁሉ ሂደት ከታለፈ በኋላ ምርጫው የሚዘረፍ ከሆነ ያኔ ይህ የተደራጀ ህዝብ ህዝባዊ እምቢተኝነት ለማካሄድ በቂ የሆነ ምክንያት ይኖረዋል። የአንድነት እቅድ ይሄ ነው፤ ሌላ እቅድ አለኝ የሚል ካለ መብቱ ነው፤ አንድነት በእኔ እቅድ አጨብጫቢ ሆኖ ይሰለፍ ማለት ግን ተገቢ አይደለም፤ ተቀባይነትም የለውም። አንድነት በመላ ሀገሪቱ ሰፊ መዋቅር ያለው፣ ስለአባላቱና ስለህዝቡ ሀላፊነት የሚሰማው ፓርቲ ንው። ከዚህም ባሻገር የነገው መንግስት መሆን የሚያስችለው ቁመናና ስብስብ ያለው ፓርቲ ነው። በዚህ ምክንያት በእርሱ ክብደት ድልድዩን አንቀጠቀጥነው ለማለት ለሚመኙ ሁሉ የሚመች ፓርቲ አይሆንም፤ ከሆያሆዬ ፖለቲካ ነጥሮ ከወጣም ቆይቷል። […]