ሕዝብን ያላስከተለ ትግል ዉጤት አያመጣም – ግርማ ካሳ
ሕዝብን ያላስከተለ ትግል ዉጤት አያመጣም – ግርማ ካሳ
“ምርጫው ላይ ለመሳተፍ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠናል።በምርጫው ልንሳተፍም ሆነ ላንሳተፍ ውሳኔ የምናሳልፈው እኛ ሳንሆን ሂደቱ ነው” ብለዋል። " እኛ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጥነው ምርጫ ላይ ሳይሆን የምርጫ ሂደቱ ላይ ነው” ሲሉ ደግሞ አቶ ግርማ በቀለ የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ፀኃፊ፣ ቀደም ሲል ለምርጫው ቅድመ ሁኔታ አላቀመጥንም የሚለው ለማሻሻል ሞክረዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የትብብሩ አመራሮች መልስ ለመስጠት የተቸገሩ፣ እርስ በርሳቸዉም አንድ አቋም ያልያዙ መሰለኝ። አቶ ዮናትን ቅድመ ሁኔታ ለምርጫው አስቀምጥናል እያሉ፣ የትብብሩ ዋና ጸሃፊ ለምርጫው ቅድመ ሁኔታ አላስቀመጥንም የሚሉ ከሆነ የቱ ነው ትክክለኛ የትብብሩ አቋም ? ? ? አቶ ዮናትን ወይስ አቶ ግርማ በቀለ ያሉት። በዚህ ጥያቄ ላይ "Honesty is the best policy" ይላሉ ፈረንጆች። ሰማያዊም ሆነ ትብብር በዚህ ረገድ አቋማችሁን በግልጽ ማስቀመጥ አለባችሁ። መቃረን የለባችሁም።
ሌላው ወደ ምርጫ ለመግባት ሂደቱ ይወስነዋል ይላሉ አቶ ዮናታን። ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል። አንዱ ቅድመ ሁኔታ ይመስለኛል የምርጫ ቦርድ ነጻ መሆን አለበት የሚል ነው። በዚህ ረገድ አሁን ባለው ሁኔታ ገዢው ፓርቲ ፈቀቅ ያለበት ሁኔታ የለም። ካልተገደደ በቀር አሁን ያለው ምርጫ ቦርድ ነው የሚቀጥለው።
ትዝ ይለኛል ከምርጫ ቦርድ ሰብሰባ ሰማያዎች ረግጠው ወጥተው ነበር …ምርጫ ቦርድ ግን ኢግኖር ነው ያደረጋቸው። ስራዉንም ቀጥሏል። የአንድ ወር መርሃ ግብር ብለዉም ከፖሊሶች ጋር ተጋጩ፥ ብዙዎች ለሁለት ሶስት ቀናት ታሰሩ። አሁንም ምንም ለዉጥ የለም በምርጫ ቦርድ አካባቢ።
ሁለት ሶስት መቶ ሰዎች ይዞ ሰልፍ መዉጣት አገዛዙን አያስገድድም። ይልቅ መቶ ሺሆች፣ ሚሊዮን ሕዝብ እንዲወጣና ለመብቱ እንዲጮህ ነው ማድረግ የሚያስፈለገው። ለዚህም በጋራና በትብብር መስራት ያስፈልጋል። ጠንካራ ከሚባሉ ድርጅቶች ጋር ከነ አንድነት፣ መድረክ ጋር አብራችሁ ሰላማዊ ሰልፎችን ሰማያዎች ቢጠሩ፣ አብረው መሰረታዊ የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን ቢያነሱ ብስለትና እውቀት ባለበት መልኩ ቢንቀሳቀሱ፣ ትልቅ ቫይብሬሽን መፍጠር ይቻል ነበር።
እርግጥ ነው እዚህ በዉጭ ያሉ እንዳንድ ጽንፈኞቹ ከረን አፌር ክፍል ያሉ ሰማያዎችን ፣ ሆይ ሆይ እያሏቸው ነው። ምናልባት ሁለት፣ ሶስት ቀናት በመታሰራችሁ "ጀግኖች፣ አንበሶች" ሲሏቸው፣ ያለ እነርሱ ሰው የሌለ ሊመስላቸው ይችላል።
ሆኖም ግን እዚህ በዉጭ ያሉ ጽንፈኖች ችግር ዉስጥ ነው ሰማያዎዎችን የሚከቷችሁ። አዎ ከዉጭ ድጋፍ ማግኘት ጥሩ ነው። ዉጭ ያለው ወገን የትግሉም አካል ነው። ሆኖም ዉጭ ያለው ማህበረሰብ የሚፈልገውን ሳይሆን በአገር ቤት ያለው ሕዝብ የሚፈለገውን በማዳመጥ ነው መንቀሳቀስ የሚገባው። የሰላማዊ ትግል የራሱ የሆነ ሰራዊት አለው። እርሱም ሕዝብ ነው። ሕዝብን ያላሰለፈና ያላንቀሳቀሰ ትግል ዋጋ አይኖረዉም።
አንድ ነገር ብዬህ ላቁም። ከአንድ አመት በፊት ሰማያዊ ሰልፍ ሲጠራ ወደ 70 ሺህ ሕዝብ ተገኝቶ ነበር። ከሶስት ወራት በኋላ ሰልፍ አንድነት ሲጠራ አብረው አእንዲያደረጉ ትልቅ ተማጽኖ ቢቀርብላቸውም፣ እምቢ ብለው፣ ተሽቀዳድመው ሰልፍ ጠሩ። ሰልፉ ጃን ሜዳ ነበር ግን መስቀል አደባባይ መሄድ አለብን ሲሉ ከፖሊስ ጋር ዉዝግብ ፈጠሩ። ጥቂት ፖሊሶች አፈኗችሁ።
ስድስት ወራት በኋላ፣ ሚያዚያ ላይ አንድነት ሰልፍ ጠርቶ ከአስተዳደሩ ጋር እየተነጋገረ ባለበት ጊዜ ፣ እንደ ጎህ ዝንብ ጣልቃ ገብተው፣ ሰልፍ ጠሩ። ለአንድነት አይሆንም በተባለ ቀን፣ እውቅና አገኙ። ለሰልፉም ቅስቀሳ አደረጉ። የተገኘላችሁ ሰው ሶስት መቶ አካባቢ ብቻ ነበር። ከሰባ ሺህ ወደ ሶስት መቶ መዉረድ ማለት ትልቅ የፖለቲካ ኪሳራ ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ የሰማያዊን ስትራቴጂ እንደማያደገፍ ሰልፉ ላይ ባለመገኘት ገለጸ።
ለምንድን ነው ይሄ የሆነው ብለው መጠየቅ አልቻሉም። አሁን በአንድ ወር መርሃ ግብር እንቅስቃሴያቸውም የተለየ ነገር አላየንም። እንደ ኢሳት ባሉ ሜዲያዎች ሁሉ ሳይቀር ለሌለ ማንም ድርጅት ያልተደረገ ትልቅ ቅስቀሳ ተደረገላቸው። በሶሻል ሜዲያዉም እንደዚሁም። ከአምስት ሚሊዮን የአዲስ አበባ ህዝብ፣ መቶ አይሞላም የወጣላቸው። ለምን የአዲስ አበባ ህዝብ ጥሪያቸዉን ሰምቶ እንቅስቃሴያቸዉን አልተቀላቀለም ? ይሄ መመለስ ያለበት መሰረታዊ ጥያቄ ነው።
ገዢው ፓርቲን ማስገደድ የሚቻለው ህዝቡ በነቂስ ሲወጣ ብቻ ነው። ሰማያዊቾ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ የነበረባቸው ሕዝቡ እንዲወጣ ማድረግ የሚቻልበትን ስትራቴጂ በመንደፍ ላይ መሆን ነበረበት። ደግሜ እላለሁ ….ሰማያዊች የያዙት መስመር በጣም አደገኛና ትግሉን የሚጎዳ ነው። አላስፈላጊ ኮንፍሮንቴሽን አስወግደው፣ ሕዝቡን በማደራጀት ላይ፣ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር አብሮ በመስራት ላይ ቢያተኩሩ ጥሩ የሚሆን ይመስለኛል። አለበለዚያ የሁለተኛ መርሃ ግብር ብለዉም የሚያወጡት ከአንደኛው የሚለይ አይሆንም።
የአንድነት ፓርቲ በፖለቲካ ፕሮግራም ተመሳሳይነት ካላቸው ጋር ፣ ሰማያዊን ጨምሮ፣ ያለ አንዳንች ቅድመ ሁኔታ በጋራ ለመስራት ዝግጁ እንደሆነ እየገለጸ ነው። ሆኖም የሰማያዊ አመራሮች ከአንድነት ጋር ለመስራት አለርጂክ ለምን እንደሆነባቸው ደጋፊዎቻቸው መጠየቅ ያለባቸው መስለኝ።