በኢትዮጵያ የባለዘውዶች የስልጣን ሽኩቻ የዥዋዥዌ ጨዋታ፣
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
(ዘግይቶ የተተረጎመ)
“የስልጣን ሽኩቻ ጨዋታ” (በዓለም ላይ ታዋቂነትን ካተረፈው እና ተከታታይነት ካለው የቴሌቪዥን ትረካ መጽሐፍ ተመሳሳይ ርዕስ የተወሰደ) የገዥው አካል ቤተሰቦች ለስልጣን ወንበራቸው ሲሉ መስመራቸውን በመለየት ዋናውን መንግስታዊ ዙፋን ለመውሰድ በማሰብ ኃይለኛ ግጭትን ይፈጥራሉ፡፡ የአገዛዙ ሰይጣናዊ ትርጉም ባላቸው እና ከተለመደው የሰው ልጅ አስተሳሰብ በተለየ መልኩ በቆሙ ፍጡሮች ለአደጋ ሰለባነት በተጋለጠ ጊዜ በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በኩል ስልጣን እወስዳለሁ አትወስድም በሚል የስልጣን ሽኩቻ አውዳሚነትን ሊያስከትል የሚችል ጦርነት ሊካሄድ ይችላል፡፡ በዚያ የትረካ መጽሐፍ ውስጥ ለስልጣን ወንበራቸው ሲፋለሙ ከነበሩት የስልጣን ተፋላሚዎች መካከል አንደኛው የሚከተለውን ምልከታ ያካሂዳል፣ “አብዛኞቹ ተራ የሆኑ ህዝቦች ዝናብ እንዲዘንብላቸው፣ ጤንነታቸው የተሟላ ልጆች እንዲኖሯቸው እና ምንም ዓይነት መጨረሻ የሌለው በህይወታቸው ሙሉ ታላቅ የደስታ ዘመን እንዲኖራቸው ነው ጸሎት የሚያደርጉት፡፡ እነዚሁ ተራ ህዝቦች በሰላም እስከኖሩ ድረስ ታላላቅ ንጉሶች እና ባለስልጣኖች ለስልጣን ወንበሮቻቸው ሲሉ የፈለገውን ያህል የስልጣን ሽኩቻ ትግል ቢያካሂዱ ደንታቸው አይደለም፣ በየትኛውም መልኩ ባለስልጣን አይደሉምና፡፡“ ሌላ ጌታ ባለስልጣን ደግሞ ሀዘን በተቀላቀለበት ድምጽ እንዲህ የሚል ጥያቄ ያነሳል፣ ”እናንተ በስልጣን ወንበር ላይ ያላችሁት ከፍተኛ ባለስልጣን ጌቶች የስልጣን ሽኩቻ የትግል ጨዋታ በምታካሂዱበት ጊዜ ለምንድን ነው አብዛኛውን ጊዜ ምንም የማያውቁት እና ከደሙ የሌሉበት ሰላማዊ ንጹሀን ሰዎች ያለሀበሳቸው የበለጠ የሚሰቃዩት?“
በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ተራው ብዙሀኑ ህዝብ አምላካቸው ዝናብ፣ ጤንነታቸው የተሟላ ልጆች እና ሰላም እንዲሰጣቸው ጸሎት እያደረጉ ባለበት ወቅት በስልጣን ሀራራ የናወዙት የገዥ መደብ አባላት ደግሞ ለዋናው የኢትዮጵያ የስልጣን ዙፋናቸው የስልጣን ሽኩቻ የሞት ሽረት ትግል በማድረግ የዥዋዥዌ የገመድ ጉተታ ጨዋታ በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ተራው ንጹሀን ዜጎች እንዲህ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፣ “ጅቦች እና ከርከሮዎች በተጣሉ ቁጥር ለምንድን ነው አብዛኛውን ጊዜ አጋዘኖች የሚሰቃዩት? አሁን በሚታዬው ሁኔታ ጥያቄ ሆኖ ሊቀርብ የሚችለው የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የወል የሆነውን የዙፋን ወንበር ለመንጠቅ እና እ.ኤ.አ በ2012 በነሀሴ ወር የሞተውን እና አሁን በህይወት የሌለውን የንጉስ መለስ ዜናዊን የአድራጊ የፈጣሪነት የዙፋን ወንበር በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የስልጣን ሽኩቻ ትግል በማድረግ ከእነዚህ ከሌሎች የጅብ ስብስብ መንጋዎች መካከል ፈልቅቆ በማውጣት በድል አድራጊነት ዙፋኑን ለግሉ ማድረግ የሚችለው ማን እንደሆነ ከመገንዘብ ላይ ነው፡፡“ የእኔ ጥያቄ በቀላሉ እንዲህ የሚል ነው፣ “በአሁኑ ጊዜ ከህወሀት የዙፋን ጀርባ ከተሰባሰቡት የስልጣን ናፋቂ ስብስብ ጅቦች መካከል ማን ነው በቀጣይነት የንጉስ መለስን የእስከህይወት ፍጻሜ የፈላጭ ቆራጭነት መቀመጫ የሆነችውን የዙፋን ወንበር ሊቀባ እና ሊቆጣጠር የሚችለው?“
የህወሀትን የዙፋን ወንበር ለመቆጣጠር የሚደረገው የትግል ምዕራፍ የመለስን ቤት በማፍረስ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ተጠናቀቀ፡፡ መለስ ለመጨረሻ ጊዜ በይፋ በህይወት የታዬው እ.ኤ.አ ጁን 19/2012 ሜክሲኮ ላይ የጂ20/G20 የመሪዎች ጉባኤ በተካሄደበት ዕለት ነው፡፡ በዚያ ስብሰባ ላይ መለስ በጣም የታመመ እና አካሉም በጣም የተዳከመ ሆኖ ታይቷል፡፡ ከዚያ ጉባኤ በኋላ መለስ ከዕይታ ተሰወረ፣ እናም ከዚያ በኋላ በይፋ በህይወት አልታዬም፡፡ የእርሱን በህይወት ማለፍ አስመልክቶ የገዥው አካል አመራሮች ድብቆች በመሆናቸው እና ለህዝብ ማሳውቅን ከመናቃቸው የተነሳ ሙጥጥ አድርገው ዓይናቸውን በጨው ታጥበው በህይወት እንዳለ በማስመሰል ጠንካራ የክህደት መግለጫዎችን ሲሰጡ የቆዩ ቢሆንም እውነታውን ፈልፍሎ በማውጣት አምባገነኑ መሪ በህይወት የሌለ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ ይፋ ያደረጉት በዋሺንግቶን ድሲ የሚገኘው አዲስ ድምፅ ራድዮና የኢትዮጵያ ሳቴላይት ቴሌቪዥን/ESAT ነበሩ፡፡ ያንን እንቆቅልሽ በማስመልከት “መለስ ከምድብ ስራው ላይ ተሰውሯልን?“ በሚል ርዕስ ትችቴ ጽፌ ማቅረቤ የሚታወስ ነው፡፡
የመለስን ከህዝብ ዕይታ መሰወር ለመደበቅ ሲደረግ የነበረውን የሰርከስ ተውኔት ተከትሎ በረከት ስምኦን (የዓዞ ባህሪን የተላበሰው እና ያሳዳም ሁሴን የካርቱን እረዳት ከነበረው “ኬሚካል (ወይም መቀደድ ይችላል) ዓሊ” ከተባለው ቀልደኛ ቃል አቀባይ አሜሪካ የኢራቅን የጦር ኃይል ድል አድርጋ ታንኮቿን እና ታላላቅ የወታደር መጫኛ ተሽከርካሪዎቿን ከባግዳድ ከተማ እምብርት ቦታ ላይ አቁማ ለቀጣይ ስራዎቿ የምታደርገውን በማሰላሰል ላይ እያለች ይህ እንደ አቡጀዲ የሚቀደድ ቀጣፊ የፕሬስ ጉባኤ በማዘጋጀት የአሜሪካንን የጦር ኃይል ድባቅ መትተው ድል እንዳደረጉት እና ጦሩ በመፍረክረክ እየጠፋ እንደሆነ አድርጎ የሀሰት መረጃ ሲያስተላለፍ ከነበረው ሰው መሳይ ሰው ጋር አንድ እና አንድ መሳ ለመሳ የሆነ ባለስልጣን) የተባለው የኮሙኒኬሸን ሚኒስትር ወደ መገናኛ ብዙሀን ቀርቦ ጉዳዩን በማጦዝ ወደ ከፍተኛ ደረጃ አደረሰው፡፡ ይህ ውሸትን በማነብነብ የሚኖር መንታ ምላስ ያለው በረከት ስምኦን የተባለ ሰው ገና ከመጀመሪያ ጀምሮ የመለስን የጤንነት ሁኔታ እና በዚያን ጊዜ መለስ ከህዝብ ዕይታ ለምን እንደተሰወረ እንዲሁም የት እንዳለ ሲጠየቅ ትክክለኛውን መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ያለመሆን፣ ሁልጊዜ አዎንታዊ ምለሽ ከመስጠት ይልቅ ተከላካይ እና አሉታዊ አስተሳሰብ ይዞ የመቅረብ እና ሁሉንም መረጃ የመደበቅ ባህሪ የተጠናወተው ሰው ነበር፣ አሁንም ነው፡፡ ያዲያቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይቀርም እንዲሉ፡፡ ይህ ሰው ስለመለስ ትንሽ የጤና መታወክ እንጅ በሽታው ምን እንደሆነ ሳይገልጽ እና የት ቦታም በመታከም ላይ እንዳለ በመደበቅ የውሸት በአጠቃላይ ቅጥፈት የተሞላበት የፕሬስ መግለጫ ሰጠ፡፡ ከዚህ አልፎ እንዲያውም መለስ ለበርካታ ዓመታት ያለምንም እረፍት ለህዝብ አገልግሎት ሲሰራ በመቆየቱ ለእረፍት እንደሄደ አድርጎ በመናገር ህዝብን ሽምጥጥ አድርጎ ዋሽቷል፡፡ በመቀጠልም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የስምኦንን ቅጥፈት እንዳለ በመድገም እንዲህ የሚል ተራ ውሸትን ለህዝብ አሰምቶ ነበር፣ “ምንም ዓይነት አሳሳቢ የሆነ ከባድ በሽታ የለባቸውም፡፡ በጣም ቀላል የሆነ ነገር ነው፡፡ እንደማኛውም ሰው ሁሉ ህክምና ማግኘት አለባቸው፣ እናም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ስራቸው ይመለሳሉ፡፡“
በዚያው ዓመት ጁላይ 18/2012 የፈረንሳይ የዜና ወኪል/Agence France በርካታ የዲፕሎማት የመረጃ ምንጮችን በመጥቀስ እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፣ “መለስ ቤልጀም ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ በጣም አሳሳቢ በሆነ ደረጃ ላይ ነው ያለው፣ እናም ህይወቱ በአደገኛ ሁኔታ ላይ ነው ያለው፣ በህይወት የመትረፍ ዕድሉ የመነመነ ነው፡፡“ በዚያው ዓመት ኦገስት 1 በረከት ስምኦን እንዲህ ብሎ ነበር፣ “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤንነት በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ እየተሰጣቸው ያለው መድኃኒት እና እየወሰዱት ያለው እረፍት ጤንነታቸው እንዲሻሻል እያደረገ ነው፡፡ ከመቸውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት የጤንነታቸው ሁኔታ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡“ በዚህም አላበቃም እንዲህ የሚል ነገርም ጨምሮ ነበር፣ “የጤንነታቸው ሁኔታ ቀድሞ ወደነበረበት ደረጃ ተመልሷል፣ ምንም አዲስ ነገር የለም፣ እናም በቅርቡም አዲስ የሚመጣ ነገር አይኖርም፡፡“ ኦገስት 21 የተሰጠው መንግስታዊ መግለጫ ደግሞ መለስ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዬ መሆኑን አውጇል፡፡ እስከ አሁንም ድረስ የመለስ ሞት መንስኤ ምን እንደሆነ ሳይታወቅ በከባድ የመንግስት ጥበቃ ስር ሚስጥር ተደርጎ እንቆቅልሽ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ የዘውድ ንጉስነት የስልጣን ሽኩቻ ትግል ውስጥ ደግሞ መለስ “በቅርብ ቀን ውስጥ ወደ ስራቸው ይመለሳሉ” ብሎ የተናገረው ኃይለማርያም ደሳለኝ ሴፕቴምበር 15 የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ተሾመ፡፡ ኃይለማርያም በሌሎች የወያኔ ሰዎች ቁጥጥር እና ድጋፍ ስር በመሆን የመለስ ሙት መንፈስ አገልጋይ ሆኖ የታላቁን መሪያችንን ራዕይ ለማሳካት እያለ እንዲቀጥል ተደረገ፡፡ ከዚህ ውጭ በእራሱ ስብዕና እና ተነሳሽነት የሚያደርገው ብቻ ሳይሆን የሚያስበውም ቢሆን ቅንጣት ያህል ነገር የለውም፡፡ የእርሱ ሹመት በስውር የንጉስነት ዙፋኑን ለመንጠቅ ለሚቃብዙት (በመንግስት ላይ መንግስትን የሚያሾሩ) የስልጣን ስግብግቦች በእርሱ የሹመት ምርጫ ላይ ነውጥ ሊያመጡ ይችላሉ በሚል ስጋት በከፍተኛ ሚስጥር እና ድብቅነት ነው የተካሄደው፡፡ ጥቂት የህወሀት ንጉስ አንጋሾች በቀላሉ የጥቃት ሰለባ ለመሆን የሚችል ሞኝ፣ ብልህነት የጎደለው እና የታዘዘውን ያለምንም ማቅማማት አቤት ወዴት እያለ ለመፈጸም የሚችል ደካማ እና ድሁር አስተሳሰብ ያለው እንዲሁም የመለስን ሞት ተከትሎ ያለውን የሽግግር ወቅት እንደፈለጉ የሚያጦዙት በመፈለግ በቦታው ላይ ለማስመሰያነት የሚያገለግል አሻንጉሊት ሰው ለማስቀመጥ ሰምምነት አደረጉ፡፡ የህወሀት ወሮበላ ቡድን ሁሉንም ወታደራዊ፣ የፖሊስ እና የደህንነት ኃይል፣ የመንግስታዊ ቢሮክራሲውን እና የእነርሱ ጥገኛ ምሁር ተብዮዎች እና አቃጣሪ ደጋፊዎች የምጣኔ ሀብቱን ሙሉ በሙሉ አንቀው ተቆጣጥረው ባለበት ሁኔታ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጥሩ ሁኔታ ተጠፍጥፎ የተሰራ ትክክለኛ አሻንጉሊት ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር፡፡ እንደታሰበውም ሆኖ አግኝተውት እያገለገለ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 ይካሄዳል ተብሎ በሚደሰኩርለት የይስሙላ ምርጫ በሌላ እስከሚተካ ድረስ የህወሀት የስልጣን ነጣቂዎች እና ንጉስ አንጋሾች የእራሳቸውን ሰው ከመካከላቸው አንዱን አዘጋጅተው ለንግስና ዙፋኑ እስከሚያበቁ ድረስ ኃይለማርያም የማስተላለፊያ ቱቦ ሆኖ በፈቃደኝነት ሲያገለግል ይቆያል፡፡ የዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጭ እና አበዳሪ ድርጅቶች ፈጣን እና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲደረግ እና እነርሱም የተለመደውን ስራቸውን እና ንግዳቸውን ያለምን ችግር ማቀላጠፍ እንዲችሉ የኃይለማርያምን በአሻንጉሊትነት መሾም በደስታ ተቀብለውታል፡፡
የኃይለማርያም መመረጥ በአጭርም ሆነ በረዥም ጊዜ ሲታይ ተጨባጭነት ያለው ችግር የለውም፡፡ ነጻ የሆነ የእራሱ የፖለቲካ መሰረት የለውም ወይም ደግሞ ከቁጥር የሚገባ የፖለቲካ ዕይታ የለውም፡፡ ኃይለማርያም ደሳኝ የይስሙላ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣኑን ከተረከበ በኋላ እጅግ በጣም አጠራጣሪ በሆነ መልኩ ንጉስ አንጋሾችን በመገዳደር ያለመታዘዝነት ምልክቶችን ሊያሳይ ይችል ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ እንደ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እራሱ ነገሮችን ሲገነዝብ የለም አይሆንም እራሴ አስቤ እንድሰራ ዕድሉ ይሰጠኝ አለዚያ አሻፈረኝ እኔ አሻንጉሊት አይደለሁም ሊል ይችል እና በሌላ እነርሱ በሚፈልጉት አሻንጉሊት ሊተካ ይችል ይሆናል፡፡ ነገሮች ገፍተው ከመጡ በእርሱ ላይ አደጋን ሊያስከትል የሚችል ሸምቀቆ በአንገቱ ላይ እንዲገባ እንደተደረገ ኃይለማርያም አሳምሮ ያውቃል፡፡ በአንድ ወቅት ከእርሱ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር በነበረው እና “በሙስና” በመወንጀል ለ12 ዓመታት በእስር ቤት እንዲማቅቅ የተደረገውን የታምራት ላይኔን ሁኔታ በሚገባ ተገንዝቧል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ብልህነት የጎደላቸው እና ነገሮችን ከሁሉም አቅጣጫዎች መመልከት የተሳናቸው እንዲሁም ለማታለል ትንሽም እንኳ ማስመሰያነትን ለመጠቀም ማሰላሰል የማይችሉ የአስተሳሰብ ድሁርነት የተንሰራፋባቸው ቆምጨ የህወሀት ካድሬዎች የኃይለማርያምን ሹመት እንደመጥፎ አጋጣሚ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ ይህም ድርጊት ከቀድሞው ወታደራዊ መንግስት ጋር በጫካ የሽምቅ ውጊያ አሸንፈው በስንት መስዋዕትነት የተቀዳጁትን ድል ሌላ ሰው መስጠት አጠቃላይ ስልጣናቸውን አሳልፎ እንደመስጠት እና የተከፈለውንም መስዋዕትነት ትርጉም የሚያሳጣ እርባናየለሽ ተግባር ነው ብለው ያምናሉ፡፡ እስከ አሁንም ድረስ ሌት ከቀን በመቆጨት ላይ ይገኛሉ፡፡ በ1997 ዓ.ም በተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ ወያኔ በሀገሪቱ በጠቅላላው በቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ በዝረራ በተሸነፈበት ወቅት ቱባ ቱባ የወያኔ ካድሬዎች እና ባለስልጣኖች የቅንጅቱ ምሁራን በህዝብ ተመርጠው ስልጣን ለመያዝ እንደማይችሉ ያላቸውን ቁርጠኝነት በይፋ ግልጽ በማድረግ “ስንት ደም ተከፍሎበት የተገኘን ስልጣን አሁን ከረባቱን እያሳመረ ከልቡ ስልጣን ሊይዝ ይፈልጋል ወይ” ብለው የተናገሩትን ልብ ይሏል! የስልጣን ስግብግብነት፣ የህዝብን ሀብት ዘራፊነት፣ ህዝብን መጥላት፣ ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገር ህልውና ማጥፋት ወዘተ በሚሉ ነገሮች ላይ አሁን በህይወት ከሌለው ባሏ ከመለስ ጋር አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ያላት የቀድሞ ሚስቱ ተስፋ በቆረጠ ሁኔታ የባሏን ስራ እና ቦታ ትፈልጋለች፡፡ በባሏ የቀብር ስነስርዓት ላይ ያስተላለፈችውን መልዕክት በጥንቃቄ ለተመለከተ ሰው ሊረሳ የሚችል አይደለም፡፡ በአጭሩ እንዲህ ነበር ያለች፣ “ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን በመቆም የመለስን ዓላማዎች፣ ራዕይ፣ ዕቅዶች እና ስልቶች በተግባር እንዲረጋገጡ የበኩሌን ድርሻ አበረክታለሁ፡፡“ የድሮውን የሽምቅ ተዋጊ ምስል እና አመለካከት ለማንጸባረቅ ጠንካራ ፍላጎት እንዳላት ታስታውቃለች፡፡ በተግባር እንዲሆን የተደረገው ግን ያ እርሷ ስታራምድው የነበረው ህልሟ አይደለም፡፡ በተጠና እና በተደራጀ መልኩ በእባቦቹ የቤተመንግስት ሸፍጠኞች ተበልጣለች፣ ተታላለች፣ በመሰሪዎቹ አጭበርባሪ ስብስቦች ተንኮል ዘዴ በተመላበት መልኩ እንደትወገድ ተደርጋለች፡፡
ኃይለማርያም ደሳለኝን በአሻንጉሊትነት ጠቅላይ ሚንስትር ብሎ ማስቀመጡ ተራ የማታለል ሸፍጥ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ከዙፋኑ ጀርባ ደፈጣ አድርገው ስልጣን ለሌላ ከህወሀት ውጭ የተሰጠ ለማስመሰል ይህንን ድርጊት ማድረግ መቻላቸው ተራ የማታል ድርጊት ቢሆንም አንድ ቀልብን የሚስብ እርምጃ ነው፡፡ ይህ የተንኮል ሽረባ ከአንድ አናሳ የብሄረሰብ ጎሳ ቡድን የመጣ በመምረጥ ከማንኛውም ሊሰነዘርባቸው ከሚችል ትችት እራሳቸውን ለመከላከል የተጠቀሙበት እኩይ ምግባር እንጅ ከልብ አምነውበት ለሀገር እና ለወገን ታስቦ የዴሞክራሲንም መርህ አክበረው ከልብ ለመንቀሳቀስ እምነቱ ኖሯቸው አይደለም፡፡ “አማራዎች” ወይም “ኦሮሞዎች” (ጎሳን የሚገልጹትን ቃላት ሆን ብዬ በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ አስገብቻቸዋለሁ ምክንያቱም የኢትዮጵያን ህዝቦች ሰብአዊ ከመሆን አንጻር አንድ ነን ምንም ዓይነት ልዩነት የለም የሚል እምነት ያለኝ መሆኔን ግንዛቤ እንዲያዝልኝ ለመጠቆም ነው፡፡) የጎሳ ትምክህተኝነት ወይም ደግሞ ሌላ መጥፎ የተለያዩ ስሞችን ይሰጡናል በሚል ፍርሀት ስለኃይለማርያም የይስሙላ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መመረጥ ምንም ዓይነት ቅሬታ ማሰማት እንዳይችሉ ለማድረግ የተሸረበ ደባ ነው፡፡ ይህ እኩይ ድርጊት ታላቅ የማጭበርበር ክህሎት የተፈጸመበት በሀገር እና በህዝብ ላይ የተደረገ ደባ ነው፡፡
ያገኘኋቸውን እና የሰበሰብኳቸውን የሁለተኛ ደረጃ የመረጃ ምንጮች ዋቢ በማድረግ ባደረግሁት ግምገማ እና ድምዳሜ መሰረት የይስሙላ ዙፋን ንጉስ አንጋሾች ኃይለማርያምን የይስሙላ ጠቅላይ ሚኒስትር ለምን ማድረግ እንደፈለጉ ቀላል የሆነ ምክንያት አለ፡፡ በማንኛውም የክብር መለኪያ እና መስፈረት መሰረት የኃይለማርያም በይስሙላ ሹመቱ ወቅት በህወሀት የገና ዛፍ ላይ ደማቁ አምፖል አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን ኃይለማርያም ሳይጠሩት አቤት ሳይልኩት ወዴት የሚል ቅን ታዛዥ ሎሌ እና የመለስ ታማኝ ፈልፈል (መሬት የሚጭር ምስኪን ድሁር እና አውሬ) ነበር፡፡ ኃይለማርያምን ከዚህ ቀደም ባቀረብኩት ትችቴ “የይስሙላ” ወይም “እጁን፣ እግሩን፣ እራሱን እና ዋናውን አካሉን በገመድ ታስሮ እንደተፈለገው የሚጦዝ አሻንጉሊት“ ጠቅላይ ሚኒስትር ብዬው ነበር፡፡ ምናልባትም የመለስ ትሩፋት/Meles’ Legacy ከሚለው በአማርኛ በተዘጋጀው የኤርምያስ ለገሰ መጽሐፍ ውስጥ ከተቀናቃኞቿ አንዱ ስለሆነው ኃይለማርያም ደሳለኝ የመለስ ሚስት በቀጥታ የተናገረችውን እንዲህ የሚለው ጥቅስ የበለጠ ገላጭ ይሆናል፣ “ኃይለማርያም ምንም ዓይነት ሀሳብ ማመንጨት የማይችል ሰው ነው፡፡ እንዲተኛ ሲነገረው ይተኛል፡፡ እንዲነሳ ሲነገረው ይነሳል፡፡ በአጭሩ ኃይለማርያም የገደል ማሚቶ ወይም ደግሞ ማስተላለፊያ ቱቦ ነው፡፡“ በመሆኑም ባለፉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከይስሙላው የዙፋን ወንበር በስተጀርባ ሆነው በሀገር እና በህዝብ ላይ ደባ በመስራት ላይ ለሚገኙት የህወሀት ወሮበላ የማፊያ ቡድን መሰሪዎች ታማኝ ሎሌ እና ያሉትን እና የሞሉትን ብቻ የሚፈጽም የድሁር አስተሳሰብ ባለቤት መሆኑን በተግባር አስመስክሯል፡፡ በእርሱ የህወሀት አለቆች የተነገረውን እንደማይክራፎን (የድምጽ ማጉያ) እያጎላ እና እንደበቀቀን እየደጋገመ በመናገር ላይ ይገኛል፡፡ አሁን በህይወት የሌለውን አለቃውን ራዕይ ለማስፈጸም በሚል የጅምላ አካሄድ “የታላቁን መሪያችንን ራዕያቸውን ለማስፈጸም” የሚል ራዕይ የለሽ የሰው ራዕይ አስፈጸሚ ታዛዥ ሎሌ ሆኗል፡፡ በመጋዘን ውስጥ ባለ ከረሜላ እጅጉን እየተደሰተ እንዳለ ህጻን ዓይነት ስሜትን በማንጸባረቅ ለህወሀት የወሮበላ የማፊያ ቡድን ኃይሎች የህዝብ ግንኙነት ሚናን የሚጫወት ታዛዥ እና አገልጋይ ሎሌ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከዚህም በላይ በየዋህነት ምንም ሳያውቅ ለጨካኙ ገዥው አካል ታማኝ አሽከር በመሆን በሰው ልጆች ላይ ስቃይ እና መከራን እንዲያስፈጽም ተልዕኮ ተሰጥቶት ያንን ለማስፈጸም በመዳከር ላይ ይገኛል፡፡ ኃይለማርያም በአደባባይ በሚያደርጋቸው ንግግሮቹ እና በሚሰጣቸው ቃለመጠይቆቹ አደናጋሪ እና ግራ አጋቢ አናሳ ቢሮክራት ለመምሰል ችሏል፡፡ ነገሮችን በውል ሳይረዳ እና ሳያጤን፣ የሚናገራቸው ቃላት አንዳቸው ከሌላኛው ጋር ያላቸውን የትርጉም ልዩነት እና አንድነት ከግንዛቤ ሳያስገባ እና ተራ እና አስፈላጊ ያልሆኑ ንግግሮችን በማሰማት እና ተጨባጭነት የሌላቸውን አመክንዮዎች በማቅረብ የቡሽን ዓይነት ባህሪ በማራመድ ላይ ይገኛል፡፡
ቀልድን በተላበሰ እና ከእውነታው ጋር ተጻራሪ በሆነ መልኩ የህወሀት ንጉስ አንጋሾች የንጽህና መሀንዲስ/Sanitary engineer የሙያ ዘርፍ ባለቤት የሆነውን ኃይለማርያም ደሳለኝን መምረጥ ነበረባቸው የሚለው አባባል ሊያሳምን ይችላል፣ ለእኔም የገባኝ ሃሳብ ቢኖር ይኸው አባባል ነው፡፡ መለስ የሚባል ቀንዳም ሰይጣን ጥሎት ያለፈውን ሁሉንም ምስቅልቅለ ነገር፣ ሁሉንም ዓይነት ቆሻሻ እና ጥራጊ እንዲሁም የሰው እና ሌሎችን የደረቅ ቆሻሻዎችን ለማጽዳት የህወሀት ንጉስ አንጋሾች ከንጽህና መሀንዲስ/Sanitary engineer የሳይንስ የሙያ ዘርፍ የበለጠ ምን ሊመርጡ ኖሯል? (በተመሳሳይ መልኩ እንደ ንጽህና መሀንዲስ እና ከዚህ ጋርም ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆኑ አንጻር ኃይለማርያም ደሳለኝ ውጤታማ የሆነ የጎርፍ መቀልበሻ እና ማስወገጃ ስርዓት፣ እንዲሁም የቆሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃ እና በከተሞች አካባቢ የጎርፍ መከላከያ ስርዓት እና በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ደግሞ አስተማማኝ የሆነ የመጠጥ ውኃ አገልግሎት ማቅረብ ነበረበት ብዬ አምናለሁ፡፡)
ኃይለማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ በተሾመበት ጊዜ ቢያንስ ጥቂት ነገሮችን መለስ ሲያደርገው ከነበረው በተለዬ መልክ ይሰራል የሚል ተስፋ በመሰነቅ (የዋህ ብትሉኝም ትችላላችሁ ግድ የለኝም) እንዲህ የሚሉ አንዳንድ ምክሮችን ለመለገስ ሞክሬ ነበር፡፡
ኃይለማሪያም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታው ላይ መሾሙን ተከትሎ ወደ ቢሮው ገብቶ ስራ ሲጀምር ቀደም ሲል ከእርሱ በፊት የነበረው እና አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ በጥላቻ ኃይል የተሞላ እና ጠብየለሽ በዳቦ፣ ግትር እና እብሪተኛ ሳይሆን ከዘለፋና የብልግና የጋጠወጥነት ንግግሮች በመላቀቅ ለሰዎች ክብር መስጠት እና ትህትናን ማሳዬት እንዳለበት ብልህነት ያለው አካሄድ ይሄዳል የሚል እምነት እንደነበረኝ ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡ የውሸት ሙገሳ እየሰጡ ያልሆነ እና የእነርሱን እኩይ ድርጊት እንዲያስፈጽምላቸው ከሚፈልጉት አለቆቹ መጥፎ ስሜት በመላቀቅ ከእርሱ አስተሳሰብ በተጻራሪ መልክ ከቆሙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መቀራረብ እና አብሮ መስራት እንዳለበት ተስፋ እንዳለኝ አሳውቄ ነበር፡፡ ከእርሱ አስተሳሰብ እና ፕሮግራም ጋር ከማይስማሙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በግጭት እና ኃይልን በመጠቀም ሳይሆን በሰላማዊ እና እርቀሰላምን ባወረደ መልኩ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የበለጠ በመገንዘብ እና ተስፋቸውን በማጠናከር እንዲሁም ውኃ ቀጠነ በማለት ሌት ቀን እነርሱን ማውገዝ ሳይሆን በማበረታታት እና በሀገሪቱ ውስጥ የብዙሀን ፓርቲ ስርዓት እንዲመሰረት ጥረት ማድረግ እንዳለበት ለማሳሰብ ሞክሬ ነበር፡፡ እንደዚሁም ደግሞ በስልጣን ላይ ስልጣንን በመደረብ ከስልጣን ስካር ላይ በመላቀቅ፣ ፍጹም የሆነ እና በሙስና ተተብትቦ የተያዘን ፍጹማዊ ስልጣን በማስወገድ ጥበብን በተላበሰ መልኩ ፍትህን እና ተግባብቶ በመስራት ፍቅር ያለበትን አሰራር ማራመድ እንዳለበት ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ ኃይለማርያም ብዙ በማዳመጥ ሆኖም ግን ጥቂት በመደስኮር ለተቋማት፣ ለተቃዋሚዎች፣ እና ለስራ ባልደረቦቹ ክብር በመስጠት እንደ መለስ ሁሉ የማይፈጸሙ ብዙ የውሸት ቃልኪዳኖችን ከመደርደር ይልቅ ጥቂት ቃልኪዳኖችን በመግባት እና ብዙ ተግባራትን በመፈጸም ስኬታማ ስራ እንዲሰራ ተስፋ በማድረግ ምክር ለግሸ ነበር፡፡ በግልለሰብ ደረጃ ለሰብአዊ መብቶች መከበር ቅዱስነት እና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ያለኝን የማይናወጥ እምነት ይጋራል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ለእርሱ ስራ የተቃና መሆን ያለኝን ምኞትም እንዲህ በማለት ገልጨ ነበር፡ ከፊት ለፊቱ እረዥም እና ውጣ ውረድ የበዛበት ጠመዝማዛ እንዲሁም እሾህ እና እንቅፋት የተንሰራፋበት ጉዞ እንደሚጠብቀው፣ ከረዥሙ ጉዞ መጨረሻም በድል አድራጊነት ለመድረስ የሚችለው በቅን ልቦና ተቃዋሚዎችን እና የስራ ባልደሮቦቹን ከሸፍጥ በጸዳ መልኩ በማገዝ የማንዴላን የጉዞ አሻራ እንጅ የሌላ የማንንም በመከተል እንዳልሆነ አጽንኦ በመስጠት በማስገንዘብ መልካም የስራ ጊዜ በመመኘት ምክሬን ለማጠናቀቅ ሞክሬ ነበር፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም ምክሮች እና ምኞቶች የተምኔታዊ ኢትዮጵያዊ ባዶ ተስፋዎች መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ኃይለማርያም አንድ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆነ በኋላ እርሱ በእርግጠኝነት ኃይለማርያም ለመሆኑ ወይም ደግሞ የመለስ የሙት በድን ምስል መሆኑን በእርግጠኝነት ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ በግልጽ በሚታይ መልኩ የመለስ ማስመሰያ የሙት ምስል ሆኖ አረፈው፡፡ የእርሱን ንግግሮች ማዳመጥ ማለት መለስ በሙት መንፈስ መጥቶ የሚናገር ያህል ሆነው ይሰሙ ጀመር፡፡ በየጊዜው በሚያደርጋቸው ንግግሮች እና በሚሰጣቸው ቃለ መጠይቆች ከመለስ የሙት መንፈስ ጋር የሚደረግ ስብሰባ አስመሰለው፡፡ የመለስን ባህሪያት የብልግና ንግግሮችንም ሳይቀር እንዳሉ በመኮረጅ ሳይጨምር ሳይቀንስ ማነብነብ እና መንተባተብ ጀመረ፡፡ እንደ መለስ ሁሉ እራሱን በየሙያ ዘርፉ የጠለቀ እውቀት ያለው የሙያ ባለቤት እንደሆነ በማስመሰል ሳያውቅ አዋቂ ሆኖ ለመቅረብ መሞከሩን ተያያዘው፡፡ በህዝብ ግብር በሚተዳደር ብዙሀን መገናኛ የእብሪት ዲስኩር ማሰማቱን ስራዬ ብሎ ቀጠለበት፡፡ የሰውነቱ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በእብሪት ተሞልቶ የነበረውን አሁን በህይወት የሌለውን የመለስን ባዶ እብሪት እንዳለ የሚያሳዩ ሆነው ተቀመጡ፡፡ የእርሱ የመለስን የሙት መንፈስ ተከናንቦ የቀረበው ምስል እንዲህ በማለት በየዜና ማሰራጨዎች እንደ አቡጀዲ ይቀደድ ጀመር፣ “የታላቁን ባለራዕይ መሪያችንን ስራዎች እና ራዕያቸውን ለማስቀጠል በትጋት እንሰራለን…ምንጊዜም ለራዕያቸው በጽናት እቆማለሁ… ህዳሴ…“ እንደ መለስ ይራመዳል፣ እንደ መለስ ጉራ ይቸረችራል እናም እንደ መለስ የሚቆጠቁጥ እና ማቋረጫ የሌለው እርባናየለሽ ፍሬከርስኪ ንግግር ያደርጋል፡፡ ኃይለማርያም በእውነት መለስ ነውን?
ገና በመጀመሪያው ዓመት የቢሮ ስራ ሲጀምር ኃይለማርያም ያደረገው ልብ ሰባሪ ንግግር እና የመለስን ራዕይ እንደሚያሳካ እና የመለስን ህዳሴ ለማስቀጠል ስለመለስ የውሰጥ አስተሳሰብ ተጨባጭነት በሌለው መልኩ ምንም ዓይነት ነገር ሳያውቅ እና ዓላማውን በውል ሳይረዳ ራዕያቸውን ለማሳካት በማለት ሮቦት መሳይ አሰልች የሆነ ንግግር ነበር ያደረገው፡፡ ኃይለማርያም ስለመለስ ውስጣዊ ባህሪ እና እያራመደ ስላለው ፍላጎት ምንም ዓይነት ግንዛቤ ሳይኖረው (ወይም እያወቀ ሆን ብሎ) ራዕያቸውን ለማስቀጠል በማለት ሌት ከቀን በህልሙም በእዉኑም ያወራል፡፡ እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 2012 “ኢትዮጵያ፡ ትክክለኛ መሻሻሎችን የምታሳይበት ጊዜ አሁን ነው“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችቴ መለስ ይፋ በሆነ መልኩ እንደተናገረው የእርሱ ትሩፋት ቀጣይነት እና ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚ ልማት በማስመዝገብ ኢትዮጵያን ከድህነት አራንቋ መንጥቆ ማውጣት ብቻ አይደለም፣ ሆኖም ግን ስለመልካም አስተዳደር እና ዴሞክራሲ ወሳኝነት ያላቸው መሻሻሎችን ለማድረግ ተናግሮ ነበር፡፡ ኃይለማርያም የእርሱን የፖለቲካ ሀሁ አስቆጣሪ፣ መምህር እና አለቃ በውል የተገነዘበ ቢሆን ኖሮ እና በይስሙላ የመለስን ትውስታ እያነሳ የግብር ይውጣ ፍሬ ከርስኪ ንግግር ከማድረግ ይልቅ በመልካም አስተዳደር እና በዴሞክራሲ ተግባራት ላይ ወሳኝ የሆኑ ስራዎችን በመስራት የአለቃውን ራዕይ እና ትሩፋት ለማስቀጠል ቁጥር አንድ ስራ ባደረገ ነበር፡፡ እነዚህ መሻሻሎች የፖለቲካ እስረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመፍታት፣ የጸ ሽብር ህጉን፣ ቀያጅ የሆነውን የበጎ አድራጎት እና ማህበራት አዋጅን እና ሌሎችን ጨቋኝ ህጎች እና ደንቦች በመሻር የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ይጀምር ነበር፡፡ ኃይለማርያም መለስ ታምራዊ ኃይል የነበረው ሆኖም ግን የሞተ ቅዱስ የእምነት ሰው እንደሆነ አድርጎ ያወራል (ወይም ደግሞ እንዲያወራ ተነግሮታል)፡፡
ኃይለማርያም ባሳለፋቸው ሁለት የጠቅላይ ሚኒስትርነት የስራ ዓመታት ውስጥ አስደንጋጭ እና አሳፋሪ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥበቃ እና የህግ የበላይነት ውጤትን አስመዝግቧል፡፡ የኃይለማርያምን ስለህግ የበላይነት መረጋገጥ ግንዛቤ የማጣት ጥልቅ የሆነ ድንቁርና ይልቅ በውል ላልተገነዘቡት እና ለእራስ እንኳን ደስ ያለህ ዓይነት በቪርጂኒያ እየተገነባ ላለው ቀላል የባቡር ሀዲድ በላይ ምስክርነት ሊኖር አይችልም፡፡ በቅርቡ በቪዲዮ በተቀረጸ ቃለ መጠይቅ ኃይለማርያም እንዲህ ብሎ ነበር፣
ትናንትና የቨሪጅኒያን አገረ ገዥ አገኘኋቸው፡፡ ከሰባት ዓመታት በፊት እዚህ ስጎበኛቸው በነበረበት ጊዜ የቀላል ባቡር ግንባታ ስራቸውን ጀምረው ነበር፡፡ የቀላል ባቡር የግንበታ ስራ በ7 ዓመታት ዘግይቷል፡፡ ለምን የዚህን ያህል ጊዜ እንደዘገዬ ጠይቂያቸው ነበር፡፡ አገረ ገዥው የነገሩኝ ነገር ቢኖር የኢንሹራንስ፣ የንብረት ጉዳዮች፣ ይኸ ገዳይ፣ ያ ጉዳይ፡፡ ለዚህም ነው ይህን ያህል ጊዜ ሊወስድ የቻለው፡፡ አገረ ገዥው ሁለተኛውን የግንባታ ምዕራፍ እያሰቡ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ እስከ አሁን ድረስ 42 ኪሎ ሜትሮችን አጠናቅቀናል (በአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ግንባታ ፕሮጀክት)፡፡ በ3 ዓመታት ጊዜ ውስጥ እናጠናቅቀዋለን፡፡ እዚህ በትልቋ ሀገር ቨርጅኒያ 7 ዓመታትን ወስዶባቸዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው አገራችን የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ ነው፡፡
ቃሎችን መስማቱ እጅግ በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡ እንዲህ የሚለው የጎቴ ብልህነት የተቀላቀለበት የቃላት አጠቃቀም እንዴት ያለ እውነታን ያመላክታል፣ “ድንቁርናን በተግባር ከማየት የበለጠ የሚያስፈራ ነገር የለም፡፡“ ኃይለማርያም የቀላል ባበቡር ስራውን በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ከትልቋ ሀገር ከቨርጂኒያ የበለጠ መስራት ይችሉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ምስኪኖቹ እና ደሀዎቹ ቪርጅናውያን/ት በጣም ጥቂት የሆኑ ማይሎችን ለማጠናቀቅ 7 ዓመታት ፈጅቶባቸዋል፡፡ ስለ ቀላል ባቡር ግንባታ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ለሚኖር ሰው አንድ ወይም ሁለት ነገሮችን ለማስተማር ኩራት ይሰማው ነበር! (በቻይና ኩባንያ በመገንባት ላይ ያለው የባቄላ ቅርጽ ያለው የግንባታ ስራው በምን ያህል ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ጊዜ የሚያወጣው ይሆናል፡፡ የመጨረሻዋን አንድ ዶላር በመጀመሪያው ከባድ ዝናብ ለማስቀመጥ ፈቃደኛ ነኝ፡፡
በእርግጥ ኃይለማርያም በአሜሪካ ሁሉም መሬት ሙሉ በሙሉ እራሱን መንግስት በማስመሰል በህዝብ ጫንቃ ላይ ተቀምጦ በማተራመስ ላይ ባለ አምባገነን መንግስት ወይም በጫካ ዘራፊ የወሮበላ ቡድን ያልተያዘ ለመሆኑ ባይተዋር ነው፡፡ የግል ንብረትን ለህዝብ ጥቅም ለመውሰድ የተደነገገው አምስተኛው የዩናይትድ ስቴትስ ህገመንግስት ማሻሻያ የመንግስትን ስልጣን እንደሚገድብ እና ለህዝብ ጥቅም ሲባል የግል ንበረትን ለመውሰድም አስፋለጊ ሆኖ ሲገኝ ተገቢ የሆነ ካሳ እንደሚከፈል እና ንበረቱ ስለሚወሰድበት ጉዳይ ለህዝብ ግልጽ እንደሚደረግ ስለሚደነግገው አንቀጽ ኃይለማርያም ምንም ሀሳብ የለውም፡፡ ኃይለማርያም በድንቁርና ለማሰብ እና ለመቀበል ያልፈለገው ነገር ቢኖር በቪርጂኒያ የኢንሹራንስ እና የንብረት ጉዳዮች በጣም ውስብስብ እና በርካታ የሆኑ የግል ባለሀብቱን የሚያስተናግዱ የህግ ማዕቀፍ እንዳሉት እና የተወሳሰበ የፍርድ ቤት እና የህገመንግስት ጉዳዮች ያሉት መሆኑን ለመገንዘብ አለመቻሉ ነው፡፡ የባቡር ግንባታ ስራውን ለማካሄድ የህግ ማዕቀፉን ተከትሎ በመስራት እና ባለመስራት ጉዳይ ባለው ሁኔታ በአካባቢው ባለስልጣናት እና በፌዴራል መንግስቱ መካከል ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡ ከባቡር ግንባታ ስራው ጋር በተያያዘ መልኩ በአካባቢያዊ እና በፌዴራል መንግሰቱ መካከል እንዲሁም የማዘጋጃ ቤቶች ስልጣን እና ተግባር ምን መሆን እንዳለበት ሊያመላክቱ የሚያስችሉ በጣም አስቸጋሪ የሆኑ የህገ መንግስት ጉዳዮች ነበሩ፡፡ የስራውን አካሄድ ለማውገዝ፣ የተሰጠው ካሳ ፍትሀዊ ስለመሆኑ እና አለመሆኑ እና ሌሎች አንገብጋቢ በሆኑ የአካሄድ ስርዓቶች ላይ በጣም ረዥም እና የተንዛዛዛ የመሆን ችግሮች ነበሩ፡፡
ይኸ ጉዳይ ያ ጉዳይ በማለት ኃይለማርያም የማይቀበላቸው ጉዳዮች በ19ኛው ክፍለ ዘመን መሬትን የማግኘት ፖለቲካ እና የባቡር ሀዲዶች የነበራቸው የመሬት ባለቤትነት መብት ሙሉ በሙሉ የባለቤትነት ወይም ደግሞ በከፊል የባለቤትነት መብትን ከማግኘት አንጻር እንዲሁም የባቡር ፉርጎዎችን ከሚጭኑት ከባድ የጭነት መኪናዎች ጋር በተያያዘ መልኩ የነበረውን ስምምነት ሊገነዘብ አይችልም፡፡ ለኃይለማርያም በዩናይትድ ስቴትስ ያሉ የአካባቢ መንግስታት መሬትን ከዜጎች በቀጭን የወረቀት ትዕዛዝ፣ ወይም ደግሞ በቢሮክሮቶቹ የዘፈቀደ ትዕዛዝ በቀጥታ በመንጠቅ ለእነርሱ አፋሽአጎንባሽ አሽከሮች፣ የቤተሰብ አባላት፣ ለካድሬዎች እና ለፖለቲካ ካድሬዎቻቸው መስጠት ሊመስለው ይችላል፡፡ ኃይለማርያም በአሜሪካ የከፍተኛ ትምህርት ተከታትሏል የሚል ወሬ አለ ሆኖም ግን ስለአሜሪካ ፖለቲካ እና የህገመንግስት ሂደት በጣም ቀላል የሆነውን ክፍል እንኳ መገንዘብ ያለመቻሉ ሲታሰብ እጅግ በጣም ከማሳዘን እና ከማስደንገጥ የበለጥ ምንም ሊባል አይችለም፡፡ ቢሆን ግን አሁን ቢሆን ክፍት የሆነ አዕምሮ እና ቅንነቱ ካለ ለመማር ጊዜ አልረፈደም፡፡ የንብረት ባለቤትነት መብቶች በአሜሪካ እጅግ በጣም የተከበሩ ናቸው፡፡ እነዚህ መብቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ህግ በመጣስ በዘፈቀደ በፌዴራል መንግስት እንዳይነጠቁ በአምስተኛው የህግ ማሻሻያ ተካትቶ ጥበቃ ተደርጎለታል፣ እንዲሁም የአካባቢ መንግስታት ተመሳሳይ ድርጊትን እንዳይፈጽሙ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ አራተኛው የህገ መንግስት ማሻሻያ ሰነድ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጀምሮ ኃይለማርያም የተሳሳተ እና የውሸት እምነትን ማራመድ ይዟል፡፡ ይህንን በማስመልከት የአፍሪካ ዘጋቢ እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቧል፣ “በአሁኑ ወቅት ማንም ቢሆን ስለኢትዮጵያ ተሀድሶ ነው እየተናገረ ያለው፡፡“ እርግጥ ነው ማንም ቢሆን እየተናገረ ያለው ስለኢትዮጵያ ነው፡፡ ይህም ንግግር እያጠነጠነ ያለው ስለኢትዮጵያ ህዳሴ ሳይሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ስለመጣው የፕሬስ ነጻነት እጦት እና በምርመራ የቁጥጥር መዳፍ ስር መዋል፣ በንጹሀን ኢትዮጵያውያን/ት ላይ እየተደረገ ያለው የጅምላ ግድያ ወንጀሎች፣ በህግ አልባነት የዜጎችን የምርጫ ድምጾች ሲዘርፉ ስለመኖር እና አሁንም በያዝነው ዓመት ስለሚካሄደው የይስሙላ ምርጫ ገዥው አካል ዓይኑን በጨው በመታጠብ እንደተለመደው ለመዝረፍ ተዘጋጅቶ እንደተቀመጠ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ተንሰራፍቶ ስለሚገኘው ሙስና እና በንጹሀን ዜጎች ላይ በየጊዜው ስለሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ረገጣ ነው፡፡
ኃይለማርያም በመለስ የቀብር ስነስርዓት ላይ በመገኘት የተናገረውን ያንን እጅግ በጣም የሚያበሳጭ የሆነ የፍብረካ ንግግር አሁንም በመድገም ላይ ነው፡፡ ውሸትን መደረት የማያልቅበቱ ኃይለማርያም አሁንም እንዲህ ይላል፣ “ታላቁ መሪያችን መለስ ዜናዊ ባለፉት ስምንት ዓመታት በተግባር ለታዩት ተጨባጭነት ያላቸው የባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ ያደረጉ የሀገራችን ህዳሴ ዋና ቀያሽ መሀንዲስ ነበሩ“ ይኸ ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት እየተባለ በውሸት የሚደሰኮረው ነገር ተራ ቅጥፈት መሆኑን “የመለስ ዜናዊ የውሸት ኢኮኖሚክስ” በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁትን ትችት ያነበበ ማንም ሰው ይገነዘበዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ (ምናልባትም ኃይለማርያም ማንበብ አይወድም ይመስለኛል፣ በተለይም “ረዥም” ትንተና ይዘው የሚቀርቡ ትችቶችን)፡፡
በሶስተኛው ምዕራፍ የንጉስ አንጋሾች የዙፋን ሽኩቻ የዥዋዥዌ ጨዋታ ኃይለማርያም የይስሙላ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኗል፡፡ ኃይለማርያም በምስራቅ ኬፕ ኩኑ ላይ በኔልሰን ማንዴላ የቀብር ስነስርዓት ላይ በመገኘት በተግባር ያልተገለጸ እና አሁንም የማይገለጽ ባዶ ድንፋታ እንዲህ በማለት አሰምቷል፣ “ለፍትህ መርሆዎች ተግባራዊነት በጽናት የምንቆም ከሆነ ለነጻነት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሰው ልጆች ክብር የምንቆረቆር ከሆነ የፈለገውን ያህል መሰናክሎች ቢደረደሩብንም እንኳ በጭራቃዊነት ላይ ድልን እንቀዳጃለን”፡፡ ተግባር እና ዲስኩር አራንባ እና ቆቦ! በኃይለማርያም የወያኔ የጠቅላይ ሚኒስትርነት የዙፋን ዘመን ነገሮች ሁሉ እየተበላሹ የቁልቁለት መንገዱ ፈጣን በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ በእርሱ የአገዛዝ ዘመን በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በዘፈቀደ እየተያዙ በየማጎሪያ እስር ቤቱ እየተጋዙ በመማቀቅ ላይ መገኘታቸው እንደፍትህ ተቆጥሮ በኢትዮጵያ ጭራቃዊነት የለም፡፡ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ የእድሜ ገደባቸው በ20ዎቹ የሆኑ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች በፌስ ቡክ እና በሌሎች የማህበራዊ ድረ ገጽ መገናኛዎች ሀሳባቸውን በመግለጻቸው እና በመጻፋቸው ብቻ ተወንጅለው አሸባሪ የሚል ታፔላ ከጀርባቸው ተለጥፎ በቀጥጥር ስር ውለው ወደ ዘብጥያ ተወርውረዋል፡፡ በዚህ ወር ስድስት ታዋቂ የሆኑ ነጻ የህትመት ውጤቶች ማለትም አፍሮ ታይምስ፣ አዲስ ጉዳይ፣ እንቁ፣ ፋክት፣ ጃኖ እና ሎሚ በዘፈቀደ በማን አለብኝነት እንዲዘጉ በማድረግ ከስራ ውጭ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ በደርዘኖች የሚቆጠሩ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል ሌሎች ደግሞ ከእናት ሀገራቸው እንዲሰደዱ ተደርገዋል፡፡
በደርዘኖች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ምርጥ እና የብሩህ አዕምሮ ባለቤት የሆኑት ነጻ ጋዜጠኞች ከሰብአዊነት በወረደ መልኩ በመላ ሀገሪቱ ባሉ እስር ቤቶች ታጉሮባቸው በመማቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ ኃይለማርያም ዓለም አቀፋዊ የአፈና እና የጠለፋዎች ወንጀሎችን ለመፈጸም ብቁ ከሚያደርጉት የማፊያ ተቋማት ውስጥ የስልጠና ጊዜውን አጠናቅቆ ተመርቋል፡፡ የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ቡደን የሆነውን የግንቦት ሰባት ንቅናቄ የፍትህ፣ የነጻነት እና የዴሞክራሲ ዋና ጸሐፊ የነበሩትን አንዳርጋቸው ጽጌን የጠለፋ እኩይ ምግባር ለማስፈጸም ለወያኔ የወሮበላ አፋኝ ቡድን ትዕዛዝ በመስጠት የመን ላይ ተግባራዊ እንዲሆን አድርጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ2014 የኦክስፎርድ የድህነት እና የሰብአዊ ልማት ተነሳሽነት/Oxford Poverty and Human Development Initiative (OPHDI) ቀደም ሲል ደግሞ በየዓመቱ ዘገባ የሚያወጣው የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የድህነት መለኪያ/United Nations Development Program Poverty Index የተባሉት ታዋቂ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ባወጧቸው ዘገባዎች መሰረት ኢትዮጵያ ከዓለም በድህነት ከመጨረሻዎቹ ደኃ ሀገሮች በተከታታይ ለአራት ዓመታት በሁተኛነት ደረጃ ላይ ሆና ትገኛለች፡፡ ሀገራችን ይህን በመሰለ አሳፋሪ የውርደት ማጥ ውስጥ ተዘፍቃ በመንፈራገጥ ላይ በምትገኝበት አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ኃይለማርያም ከጌቶቹ በሚወረወርለት ፍርፋሪ ቀፈቱን አሳብጦ “በአሁኑ ወቅት ማንም ቢሆን ስለኢትዮጵያ ተሀድሶ ነው እየተናገረ ያለው“ በማለት እየዘመረ በመደነስ ላይ ይገኛል፡፡ የምን ህዳሴ? ውሻ በበላበት ይጮሀል እንዲሉ፡፡
የህወሀት የዙፋን ስልጣን ሽኩቻ ዥዋዥዌ የመጨረሻ ጨዋታ፣
በስልጣን አምላኪዎቹ የህወሀት የዙፋን ስልጣን ሽኩቻ ዥዋዥዌ የመጨረሻ ጨዋታ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ፡ “የ2015ን የይስሙላ ምርጫ ተከትሎ የይስሙላ ዙፋኑ ንጉስ ሊሆን የሚችለው ማን ነው?” የሚለው ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ በማስመልከት “በ2015 በኢትዮጵያ ምርጫ እና ቅርጫ“ በሚል ርዕስ ባዘጋጀሁት ትንታኔዬ በአጠቃላይ በጉዳዩ ላይ ያለኝን ሀሳብ ለአንባቢዎች ማካፈሌ የሚታወስ ነው፡፡ “ምርጫ” የሚለው ቃል እውነታውን የማይወክል ቅጽል ስም ወይም ደግሞ ሌላ ማሳሳቻ ስም ነው፡፡ ይልቁንም የታዕይታ ምርጫ፣ ወይም የምርጫ ጨዋታ የሚሉት ሀረጎች በተሻለ መልኩ ይገልጹታል፡፡ በ2015 የሚደረገው የይስሙላ ምርጫ ውጤት አስቀድሞ የታወቀ የተበላ ዕቁብ ነው፡፡ ይልቁንም ብቸኛው መጠየቅ ያለበት ጥያቄ የማሸነፊያ ህዳጉ እ.ኤ.አ በ2010 በተካሄደው የታዕይታ የምርጫ ውጤት ከነበረው ከ99.6 በመቶ ይበልጣልን የሚለው ነው፡፡ መለስ የእርሱ ፓርቲ ከ99.6 በመቶ ባነሰ ውጤት የሚያሸንፍ ከሆነ ከመቃብር ሆኖ ይገለባበጣል፡፡
በመጨረሻው የዙፋን ስልጣን ሽኩቻ ጨዋታ ኃይለማርያም ተባራሪ እና ወደ ቆሻሻ ቅርጫት የሚጣል የተቀደደ እና የተበላሸ የካርታ መጫወጫ ካርድ ነው፡፡ ለእነርሱ በጊዜው የተከበረ ነው፡፡ በዓላማ ማስፈጸሚያነት ተጠቅመውበታልና፡፡ ሆኖም ግን የዙፋን ስልጣን ሽኩቻ ተፋላሚዎች በርካታ ችግሮች አሉባቸው፡፡ የመለስ አቻ ሊሆን የሚችል መለስን የሚተካ ሰው የት አለ? በዙፋን ስልጣን ሽኩቻ ተፋላሚዎች ግንዛቤ አንድ መለስ ዜናዊ ብቻ- ብቁ ጭንቅላት፣ ጉልበተኛ ጡንቻማ እና ስመ ታዋቂ ከወዴት ሊገኝ? ከእነርሱ ትንሹ አምላክ (መለስ) ውጭ ምንም ነገር የሌላቸው ባዶዎች ናቸው፡፡ አንድ ዓይናው የዙፋን ንጉስ ሲወገድ በዚህች ምድር ላይ እራሳቸውን ዓይን የሌላቸው ስብስቦች ሆነው አገኙት፡፡ በአሁኑ ጊዜ በጨለማ ውስጥ ገብተው በመደናበር ላይ ሲሆኑ ከጨለማው እንዴት እና በየት በኩል መውጣት እንዳለባቸው የማያውቁ የደናቁርት ስብሰቦች ናቸው፡፡
የህወሀት የዙፋን ስልጣን ሽኩቻ ተፋላሚዎች በስልጣን እንደመዥገር ተጣብቀው ለመቆየት እንደ መለስ ያለ በሸፍጥ የተሞላ ሰው ጤፉ የሆነ የለየለት አምባገነን እና አጭበርባሪ ያስፈልጋቸዋል፡፡ መለስ ስለህወሀት አመጣጥ እና ምንነት የሚያውቅ ልዩ የሆነ ምልክታቸው ነው፡፡ መለስ የወደፊቱን መተንበይ የሚችል እንዲሁም እያቆጠቆጡ የሚመጡበትን የተቃዋሚ ኃይሎች በማስታገስ ተመጣጣኝ ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ በማድረግ ማለትም ተቃዋሚዎችን በማስፈራራት፣ ጉቦ ወይም መሸንገያ ነገር በመስጠት፣ ከህግ አግባብ ውጭ በማሰቃየት እና በይስሙላው ፍርድ ቤት በተንዛዛ ቀጠሮ በማመላለስ ሞራላቸው እንዲነካ በማድረግ ከወያኔዎቹ መካከል የሚስተካከለው የማይገኝ ጎበዝ አጭበርባሪ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር እንዴት መያዝ እንዳለበት በሚገባ ያውቃል፡፡ በሁላቸውም ዘንድ ንጽህና የሚባል ነገር እንደሌለ አሳምሮ ያውቃል፡፡ ከዚህም በላይ ሁሉም በርካሽ ዋጋ ሊገዙ እና ሊሸጡ እንደሚችሉ በሚገባ ያውቃል፡፡ ከኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የዘረፉትን ገንዘብ ለመቁጠር እና ባግበሰበሱት ሀብት ላይ ለመዋኘት 10 እርምጃዎች ወደ ኋላ ሲንጠራሩ መለስ ግን በ5 እርምጃዎች ወደፊት በመወንጨፍ ቀድሟቸው ይገኛል፡፡ በመጨረሻው የስልጣን ሽኩቻ ጨዋታ ከመለስ ህይወት ማለፍ በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ በድብቅ ከዙፋኑ ጀርባ አሸምቆ ያለው ስውር ስልጣን ፈላጊ ቡድን እንዲህ የሚለውን የሌቦችን ተቃርኖ ያመላክታል፡ ሌቦች ሲሰርቁ አይጣሉም፣ ጠብ የሚመጣው የዘረፉትን ለመካፈል በአንድ ላይ ሲቀመጡ ነው፡፡ ከዙፋን ስልጣን ሽኩቻው ሌባ ደናቁርት መካከል የትኛው ሌባ ነው የሚቀጥለው የዙፋን ንጉስ ሊሆን የሚችለው?!
የወባ ትንኝ ተመራማሪ የሆነውን ቴዎድሮስ አድኃኖምን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት በሾሙበት ጊዜ እ.ኤ.አ በ2015 በሚደረገው የይስሙላ ምርጫ የሹምሽር ድልድል እርሱን በኃይለማርያም የይስሙላ ወንበር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ለማስቀመጥ እንዲመቻቸው ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ያመላክታል፡፡ ምንም ዓይነት የዲፕሎማትነት ስልጠና ወይም ልምድ ሳይኖረው ከፍተኛ የዲፕሎማትነት የስራ ቦታ በሆነው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ማስቀመጥ የሚቻለው በኢትዮጵያ ብቻ ነው፡፡ (በእንደዚህ ያለ የነቀዘ ስርዓት ውስጥ አድሎአዊነት፣ ቡድናዊነት እና ቤተሰባዊነት የገዥው አካል ዋና መገለጫ ይሆናል፡፡) ቴዎድሮስን የፈለጉበት ዋናው ምክንያት እስከ ምርጫው ድረስ በህዝብ ዘንድ እንዲታይ እና ዓለም አቀፋዊ ልምዶችንም ሲያይ እንዲቆይ እንዲሁም የውስጥ ተቃዋሚዎችን በሂደት ለማረጋጋት እና በመጨረሻም ተቀባይነት እንዲኖረው በማለማመድ አፋቸውን ለማስያዝ ነው፡፡ በ2015 በሚደረገው የይስሙላ ምርጫ ስልጣን ከንጽህና መሀንዲሱ ወደ ወባትንኝ ተመራማሪው ሲሸጋገር በዙፋን ስልጣን ሽኩቻ ቡድኑ አማካይነት እስኪሸጋገር ዝም ብለን ነው የምንጠብቀው?
አድኃኖም ለውጭ ጉዳይም ሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚያበቃው አንዳችም ነገር የለውም፡፡ የዘር ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ባለፈው ዓመት ህዳር ወር የኢትዮጵያ ዜጎች በሳውዲ አረቢያ በተለያዩ ስራዎች እና በስደተኛ መጠለያዎች ላይ የነበሩ ወገኖቻችን የሰሩበትን የጉልበት ዋጋዎቻቸውን በኃይል እየተነጠቁ ሰብአዊነት በጎደለው መልኩ ስቃይ እና ግድያ እየተፈጸመባቸው ሲባረሩ በነበረበት ጊዜ የሰጠው መልስ አሳፋሪ፣ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ለስራው እና ለወንበሩ ብቃት የሌለው እና ሊታመን የማይችል እንቆቅልሽ ነው ተብሎ ብቻ ሊታለፍ የማይችል ሳይሆን በምንም ዓይነት መልኩ ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ እነከተማ ይፍሩን እና እነ አክሊሉ ሀበተወልድን የመሳሰሉ ምጡቅ የዲፕሎማት ሰዎች ያፈራች ሀገር እንዴት አሁን ጃርት አብቅላ በእነርሱ ወንበር ላይ እንደ አድኃኖም እና ኃይለማርያም ያሉትን ከሙያውም ሆነ ከልምዱ ጋር የማይተዋወቁትን ብቃት የለሾች ልታስቀምጥ ትዘጋጃለች? “ከኢትዮጵያ እሳት ወደ ሳውዲ አረቢያ የመጥበሻ እረመጥ” በሚል ርዕስ ባዘጋጀሁት ትችቴ ላይ በሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን/ት ላይ የደረሰው ግፍ በጣም እንዳስገረመው እና እንዲህ ዓይነት ነገርም ይፈጸማል የሚል ግምት እንዳልነበረው ሲናገር በመስማቴ የተሰማኝን ቁጭት ገልጨ ነበር፡፡ እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድኃኖም በዜጎቹ ላይ ሊደርስ ስለሚችል አደጋ ሊገምት የማይችል የሙያ ብቃት የለሽ ነው፡፡ እንደዚሁም ዜጎቼ በሳውዲ አረቢያ ፖሊስ በኃይል ወይም በሌላ በገፍ ቢባረሩ በምን ዓይነት መልክ ጉዳት ሳይደርስባቸው እና ሀገሬም ውርደት ውስጥ ሳትገባ መቋቋም እችላለሁ የሚለውን ማገናዘብ እና ዝግጅት ማድረግን አያውቅም፡፡ በሳውዲ አረቢያ ገዥ አካል የዜጎችን ማስወጣት ፖሊሲ ተከትሎ ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ ቢያንስ የስድስት ወራት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ነበር፡፡ አድኃኖም ግን በብቃት ማጣት እና በግድየለሽነት ምክንያቶች በወገኖቻችን ላይ ያን የመሰለ ለመናገር የሚዘገንን ድርጊት እንዲፈጸምባቸው አድርጓል፡፡ (ከሳውዲ አረቢያ ዘመናዊ ባርነት በግፍ የሰሩበትን ተነጥቀው እና ከሞቱት በተጨማሪ አካለ ጎደሎ ሆነው በሺዎች ለሚቆጠሩ ለተባረሩት ወገኖቻችን በነአድኃኖም በኩል የተደረገው ነገር እጅግ በጣም አናሳ ነው፡፡) እኔን የበለጠ ያበሳጨኝ እንዲህ የሚለው የአድኃኖም ቆጥቋጭ መግለጫ ነው፣ “ኢትዮጵያ የሳውዲ ባለስልጣኖች ስለሰጡት ውሳኔ እና ስለህገወጥ ሰዎች ዝውውር መመለስ ጉዳይ ስላወጡት መመሪያ ኢትዮጵያ ታከብራለች“ በእርግጠኝነት እንዲህ ነው ያለው!!!
እኔ በግሌ በዚህ የዙፋን ስልጣን ሽኩቻ ወንበር ላይ ቢያስቀምጡት የሚያመጣው ለውጥ የለውም፡፡ ኃይለማርያምን በአድኃኖም ወይም ደግሞ በሌላ መተካት ጉልቻ ቢቀየር ወጥ አያጣፍጥም ከሚለው ያለፈ የሚፈይደው እንዳችም ነገር የለም፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ማለት እንደሚወዱት “አሳማን የከንፈር ቀለም በመቀባት ለማሳመር ይሞከር ይሆናል፣ ሆኖም ግን በዕለቱ መጨረሻ ያው አሳማ ነው፡፡” እንደዚሁም ሁሉ አንድን ዘራፊ ወንበዴ እና ሌባ በማስቀመጥ ጥሩ ስም፣ ቆንጆ ቦርሳ በመስጠት በዙፋኑ ላይ ብታስቀምጠው በዕለቱ መጨረሻ ያው ዘራፊ ወንበዴ እና ሌባ ነው በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ የምታገኘው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የዘራፊዎችን አስተዳደር በምርጫ ቀለም ቀባብተህ ምርጫ ነው ብለህ ብታቀርበው በዕለቱ መጨረሻ ላይ ያው የዘራፊዎች አስተዳደር ነው የምታገኘው! የ2015 ምርጫ በኢትዮጵያ መልካም አስተዳደርን፣ የሰብአዊ መብቶችን መከበርን ወይም ደግሞ የህግ የበላይነት በኢትዮጵያ እንዲረጋገጥ የሚያስችል ስርዓትን የሚያመጣ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከዝንብ ማር አይቆረጥምና!
በሌላ ነጥብ ስመለከተው ጀን ፓውል “ምንም ዓይነት መውጫ የለም” በማለት እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የህወሀት የዙፋን ስልጣን ሽኩቻ ተፋላሚ እና በጥላቻ የተሞሉት ቡድኖች እና አስመሳዮች በመኖር እና ባለመኖር መካከል ባለ የሞት ሽረት የህልውና ትግል ላይ ይገኛሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ገሀነምን ፈጥረዋል፡፡ እናም ለፈጠሩት ገሀነም ዘብ በመቆም በዘላቂነት እንዲቀጥል ይፈልጋሉ፡፡ እውነታው ሲታይ ግን የእነርሱ የፖለቲካ ኃይል እና የዘረፉት ከንቱ ሀብት ትርጉምየለሽ እንደሆነ በጥልቅ ከልባቸው ያውቃሉ ምክንያቱም በአጠቃላይ እና ፍጹም በሆነ መልኩ በኢትዮጵያ ሰፊው ህዝብ እንደተጠሉ ያውቃሉ፡፡ ህዝቡ በጣም ርካሽ በሆነ ውርደት ውስጥ እንደወሸቃቸው አሳምረው ያውቃሉ፡፡ በቅርቡ በሁለት ቁንጮ የሆኑ የገዥው አካል ባለስልጣኖች በኦዲዮ የድምጽ መቅረጫ ተቀርጾ በድረ ገጽ የተለቀቀው ሲታይ እነዚህ ባለስልጣኖች እነርሱው መርጠው እና እድገት እንዲያገኙ በማድረግ ጥሩ ዕድሎችን እንደሰጧቸው እና አብረዋቸው የሀገርን ሀብት ሲዘርፉ በቆዩት ግብረ አበሮቻቸው ለምን እንደተከዱ የሚያትተውን ቪዲዮ ብቻ ማዳመጥ ይበቃል፡፡ ከዚህ በኋላ እራሳቸውን ጨምሮ ማንንም ሊያምኑ እንደማይችሉ አውቀዋል፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሁሉ ሲያሰለጥኗቸው የቆዩት አብዛኞቹ ካድሬዎች ሳይቀሩ ሁኔታዎች ሲመቻቹላቸው ካባህር ውስጥ እንዳይወጡ አድርገው ሊያሰምጧቸው እንደማይችሉ እና ጉድጓግ ከመማስ እንደማይመለሱ ተገንዝበዋል፡፡ የመለስ ትሩፋት የሚለው “የኤርሚያስ ለገሰ መጽሐፍ“ በዋናነት የሚያሳይ አንድ ማስረጃ ነው፡፡ ያ መጽሐፍ ስለሙስና፣ ስለአቅም እጦት እና ስለሸፍጠኞች እና አስመሳዮች እርባናየለሽነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ ለዘውድ ስልጣን ሽኩቻ ተፋላሚዎች እጅግ የሚቆጠቁጥ እና ሊቋቋሙት የማይችሉት ታላቅ ኪሳራ ሆኖባቸዋል፡፡ ሚስጥራቸው እና የሚፈጽሙት ደባም ተዘክዝኮባቸዋል፡፡ (ኤርሚያስ ለገሰ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የገዥው አካል ሚኒስትር ዴኤታ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በመኖር ላይ ይገኛል፡፡) ይህ መጽሐፍ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ በህወሀት ንጉስ አንጋሾች እና እነርሱ እየተጠመቁ እያገለገሏቸው ባሉ የሌሎች ብሄሮች ካድሬዎች መካከል በሚደረገው ፍትጊያ ማርገቢያ በማድረግ በሀገሪቱ ውስጥ የብዙኃን ፓርቲ ስርዓት ያለ ለማስመሰል እያደረጉት ያለውን የሸፍጥ ስራ ግልጽ አድርጎ ያሳያል፡፡ የኤርሚያስ መጽሐፍ ቁንጮ በሆኑት በዙፋን ስልጣን ሽኩቻ ተፋላሚዎች እና አስመሳዮች መካከል በአዲስ ልብስ ተጀቡነው ሌላ ንጉስ ሊሆኑ እንደሚፈልጉ በግልጽ ጠቁሟማል፡፡ እንደ ኤርሚያስ መረጃ ከሆነ የገዥው አካል ቁንጮ እና ቱባ የሆኑት ባለስልጣኖች (ከሶስተኛ ደረጃ የትምህርት ማስረጃ ያገኙት፣ የውሸት ዲፕሎማ እየቀፈቀፉ በገንዘብ ለሚገዟቸው ዲፕሎማዎች እና በተጭበረበረ እና ታማዕኒነት በሌለው የፒኤች ዲ ዲግሪ አላቸው በሚባሉት አጭበርባሪ ሸፍጠኞች) እንደ ኢትዮጵያ ውስብስብ የሆነች አገር ይቅርና ይህንን የተተበተበ የውሾች የቢሮክራሲያቸውን እንኳ መምራት አይችሉም፡፡ እነርሱ ያሉት ገንዘብ ለመመንተፍ ብቻ ነው፡፡ ያንን መንትፈው መሮጥ ብቻ ነው ዋናው ተልኳቸው፡፡
በአንድ ወቅት ኢትዮጵያን ለሺህ ዘመናት ቀጥቅጦ ሲገዛ የነበር የብረት ዙፋን ነበር፡፡ የዚያ መንግስት ንጉሶች የትውልድ መብት እና የመግዛት መንፈሳዊ ኃይል አለን ይሉ ነበር፡፡ ያ ዙፋን በመጨረሻ በጥቂት ወራት ውስጥ ላይመለስ በኖ ጠፋ፡፡ በአሁኑ ወቅት የህወሀት የዘውድ ስልጣን ሽኩቻ ተፋላሚዎች ኢትዮጵያን ቀጥቅጦ ለመግዛት የትውልድ መብት እንዳላቸው እምነት አላቸው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን በመያዝ አድሜ ዘመናቸውን ሁሉ ለመግዛት ሽር ጉድ በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡ የእነርሱ የዘውድ ስልጣን ሽኩቻ ተፋላሚዎች ስልጣን ከመቶ ዓመት በላይ እንደሚዘልቅ በድፍረት ይናገራሉ፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እኛን ለማስገንዘብ እንደሚሞክሩት በጠብመንጃ አፈሙዝ እገዛ የዘውድ ስልጣን ዙፋን የመሰረቱ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ ማንም ቢሆን በድምጽ መስጫ ወረቀት ሊያገኘው አይችልም!
“ነጻነት ከጨቋኞች በነጻ በፍጹም አይገኝም፣ በተጨቋኞች መጠየቅ አለበት” ማርቲን ሉተር ኪንግ
=========
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ህዳር 14 ቀን 2007 ዓ.ም