በሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃና ፍትሀዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን እናደርጋለን! – ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

ፓርቲያችን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ አንድነት ፓርቲ ከአሁን በፊት ቀደም ብሎ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት በሚል ሰፊ የሆነ ህዝባዊ ንቅናቄ ማድረጉ የሚታወቅ ነው። በመቀጠል ደግሞ የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባለቤትነትና የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች የሚሉ ዘመቻዎች በተከታታይ አካሄዷል። የዚህ ዘመቻ የመጨረሻው ምዕራፍ የሆነው የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃና ፍትሀዊ ምርጫ በዚሁ እጅግ የተሳካ ጉባኤ ባካሄድንበት ማግስት የሚካሄድ በመሆኑ ፓርቲያችን ባሁኑ ሰዓት ያለበትን የከፍታ ደረጃ በትክክል የሚያሳይ ነው።

ይሄ ዘመቻ በተለያዩ የሀገራችን ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች በማድረግ የሚካሄድ ሲሆን በሶሻል ሚዲያና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን በኩልም ሰፊ ቅስቀሳና ህዝባዊ ንቅናቄ ለመፍጠር እቅድ ተይዟል። የዚህ ዘመቻ ዋና ዓላማ ዜጎች በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ላይ በሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ በምርጫው አሸናፊ ሆኖ በመውጣት የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን ማደረግ ነው። አንድነት በሰላማዊ መንገድ የስልጣን ሽግግር ለማምጣት ላቀደው ዋነኛ የትግል ምዕራፍ በሀገራን እውነተኛ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልጉ ዜጎች ሁሉ ፓርቲውን በአባልነትና በደጋፊነት በመቀላቀል የለውጡ አካል እንዲሆኑ የሚያደርግ ተደራጅ 2007 ለለውጥ የሚል ሰፊ የማደራጀትና የቅስቀሳ ዘመቻ ለማካሄድ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ጨርሰዋል።

አንድነት ወደ ምርጫው ለመግባት ሲወስን የፖለቲካ ምህዳሩ ፍፁም ከመጥበቡም ባሻገር ወደ መዘጋት የተቃረበ መሆኑ ይረዳል። ምርጫ ቦርድም ሁሉ እንደሚያውቀው ነፃና ገለልተኛ ነው ብሎ አያምንም። ነገር ግን ለውጥ ፈላጊው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎኑ እንዲሰለፍ በማድርግ፤ በዚሁ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃና ፍትሀዊ ምርጫ ህዝባዊ ንቅናቄ አማካኝነት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ህዝቡ በአጠቃላይ በምርጫው ሂደት ላይ ሙሉ ለሙሉ ተሳታፊ እንዲሆን፤ በነቂስ ወጥቶ ካርድ እንዲወስድ፣ እንዲመርጥና ድምፁን እንዳይቀማ ተደራጅቶ እንዲጠብቅ በማድረግ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ የሚያደርገው እስትራቴጂ አውጥቶ እየሰራ ነው የሚገኘው። አንድነት ከዚህ የተሻለ የሰላማዊ ትግል አማራጭ አሁን ባለው የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የለም ብሎ ያምናል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝብ ከፓርቲያችን ጎን በመቆም በዘንድሮው 2007 ዓ.ም. በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ የኢህአዴግ መጨረሻ እንዲሆን ተግቶ እንዲንቀሳቀስና እንዲደራጅ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ነፃነታችንን እናስከብር!

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
ታህሣሥ 7/2ዐዐ7 ዓ.ም10153833_587630041337455_4078181881316786241_n

905888_388429767988047_2591897697800020709_o
አዲስ አበባ