ትግራይ ትናፍቃለች!


ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
—–
 እውነቴን ነው፡፡ በእጅጉ ላያቸው ከምጓጓላቸው የሀገራችን አካባቢዎች አንዱ ትግራይ ነው፡፡ ሰሜናዊው የኢትዮጵያ ዋልታ! የውበትና የድምቀት መዘክር!
ትግራይ የመንግሥተ-አክሱም ሀገር! የሳባ ፊደል ጥንስስ! የግዕዝ ልሳን ውርስ! የዳማት ታሪክ መስተንክር! በአህጉረ አፍሪቃ የመጀመሪያው ሳንቲም የተወቀረበት የስልጣኔ ጥንስስ!
ትግራይ! የኤዛና ሀገር! የሳይዛና ሀገር! የካሌብ ሀገር! የአብርሃ ወአጽብሃ ሀገር! የአሕመድ አል-ነጃሺ ሀገር! የአንበሳ ውድም ሀገር! የአጼ ዮሐንስ አራተኛ ሀገር፣ የነገሥታት ዙፋን መቀመጫ!
ትግራይ የአሉላ ሀገር! የስሁል ሚካኤል ሀገር! የሰበጋዲስ ሀገር! የመንገሻ ዮሐንስ ሀገር! የበሻይ አውአሎም ሀገር! የቀዳማይ ወያኔ ሀገር! የኃየሎም አርአያ ሀገር! የሌሎችም ጀግኖችና አርበኞች መፍለቂያ!
ትግራይ የጥላሁን ግዛው ሀገር! የብርሃነ መስቀል ረዳ ሀገር! የዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ሀገር! የዘርዑ ክህሸን ሀገር! የብርሃነ እያሱ ሀገር! የፀሎተ ህዝቅያስ ሀገር! የዮሴፍ አዳነ ሀገር! የዶ/ር ንግስት አዳነ ሀገር! የመለስ ተክሌ ሀገር! የግደይ ገብረዋህድ ሀገር! የአረጋዊ በርሀ ሀገር! የመለስ ዜናዊ ሀገር! የአብረሃም ያየህ ሀገር! የገብረመድህን አርአያ ሀገር! የግደይ ዘርዓ ጽዮን ሀገር! የኦቦይ ስብሐት ነጋ ሀገር! የስዬ አብረሃ ሀገር! የገብሩ አስራት ሀገር! የዶ/ር ሀይሉ አርአያ ሀገር! የጓድ ፍስሐ ደስታ ሀገር! የልዑል መንገሻ ስዩም ሀገር! የአብረሃ ደስታ ሀገር! ሺ ምንተሺህ ቱባ ፖለቲከኞችንና የነጻነት ፋኖዎችን ያፈራ ምድር!
ትግራይ የገብረ-ህይወት ባይከዳኝ ሀገር! የጊላወርቅ ተስፋማሪያም ሀገር! የስብሐት ገብረ-እግዚአብሄር ሀገር! የተወልደብርሃን ገብረ-እግዚአብሄር ሀገር! የአምባሳደር ካሳ ገብረ-ህይወት ሀገር! የዶ/ር ወልዳይ አምሀ ሀገር! የዶ/ር አሰፋ መድኃኔ ሀገር! ወገን ያስከበሩ ጎምቶ ምሁራን የበቀሉበት ደብር!
ትግራይ የቅዱስ ያሬድ ሀገር! የፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብ ሀገር! የኪሮስ አለማየሁ ሀገር! የኪሮስ ሀይለሥላሴ ሀገር! የሶፊያ አፅብሃ ሀገር! የኢያሱ በርሀ ሀገር! የብርሃነ ሀይለ ሀገር! የአብረሃም ገብረ መድህን ሀገር! የባህታ ገብረ ህይወት ሀገር! የማህሌት ገብረገርግስ ሀገር! ጥበብን እየዳመጡ የፈተሉ ከያኒያን የተገኙበት የኪነት መዘክር!
ትግራይ! የአቡነ አረጋዊ ሀገር! የሼኽ ቡሽረል ከሪም ሙስጠፋ ሀገር! የአባ ገብረ መድህን ሀገር! የአባ ሳህለ ድንግል ሀገር! የአቡነ ማቲያስ ሀገር! እልፍ አዕላፍ የሃይማኖት ሊቃውንትና ሰባኪያን የወጡበት ምድር!
ትግራይ የምሩጽ ይፍጠር ሀገር! የወርቅነሽ ኪዳኔ ሀገር! የገብረ እግዚአብሄር ገብረማሪያም ሀገር! የገብረመድህን ሀይሌ ሀገር!  ድፍን ኢትዮጵያን ያስጠሩ ውድ ስፖርተኞች የተገኙበት ሰፈር!
ትግራይ የአባዲ ጸጋዬ ሀገር፣ የዳንኤል ግደይ ሀገር፣ የግርማ በርሀ ሀገር፣ የሙሐመድ አደም ሀገር፣ የአግዘው አደራ ሀገር፣ የአግዐዚ አምሃ ሀገር፣ የተወልደ መዝገቡ ሀገር፣ የቢነጋ ተወልደ ሀገር፣ በትምህርት ቆይታዬ የማውቃቸው የበርካታ ምርጥ ጨዋና ሰላማዊ ጓደኞቼ ሀገር!
            *****
      “የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም” ይባላል፡፡ እኔ ግን በዚህ አላምንም፡፡ የማያውቁትን ሀገር ያህል ለማየት የሚያጓጓ ነገር የለም፡፡ የሚያውቁትንማ ለምን ይጓጉለታል? ለማየት የሚናፍቀውስ የማያውቁት ሀገር ነው፡፡ ለምሳሌ እኛ ትግራይን በጽሑፍና በቪዲዮ ካልሆነ በስተቀር ለአንድም ቀን አይተናት አናውቅም፡፡ ይሁን እንጂ ስለርሷ ያነበብነውና የሰማነው ሁሉ ዘወትር እንድንናፍቃት እያደረገን ነው (“እኛ” እንደ ጃንሆይ የሀረር ልጅ ስለሆንን “እኛ” በማለታችን “ እናንተ እነማን ናችሁ?” የሚል ጥያቄ እንዳታነሱብን ከዚህ በፊት አስታውቀናችኋል)፡፡ መቼ እንደምናደርገው እርግጠኛ ሆነን መናገር ቢያስቸግረንም ትግራይን መጎብኘታችን አይቀሬ ነው፡፡ ዕድሜና ጤናውን አብዝቶ ይስጠንና!
            *****
    አምና ታዋቂው ሳክስፎኒስት ቴዎድሮስ ምትኩ ማረፉን ከዜና ማሰራጫዎች ሰምተን ነበር፡፡ እርሱን ለመዘከር በሚልም  ስራዎቹ በልዩ ልዩ ሬድዮ ጣቢያዎች ተዳስሰዋል፡፡ በተለይ በመሳሪያ ብቻ የተቀነባበረው ዝነኛ ካሴቱ በየጣቢያው እንደ ጉድ ተለቆለታል፡፡ ታዲያ ከነዚያ ስራዎች መካከል እጅግ ተደጋግመው የተሰሙት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከነርሱም አንዱ ቴዲ የባህታ ገብረ-ህይወትን ተወዳጅ የትግርኛ ዘፈን የተጫወተበት ሙዚቃው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክም የህዝብ ፍቅር እየተቸራቸው ከዘመን ዘመን ለመሻገር ከበቁ ዜማዎች አንዱ ይህ የባህታ ገ/ህይወት ዘፈን ነው፡፡
      እውነት ነው! “ባህታ” ሲባል በብዙዎቻችን አዕምሮ ከተፍ የሚሉት ሁለት ዜማዎች ናቸው፡፡ አንደኛው የአማርኛው “ካላጣሽው አካል” ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ይህ የትግርኛ ዜማ ነው፡፡ የዚያ ዜማ ግጥምም እንደሚከተለው ነው (በነገራችን ላይ ግጥሙን በብዕራችን እንድንጨብጥ የረዳን ሙስጠፋ ሙሐመድ የተባለው የትግራይ ጓደኛችን ነው፡፡ ምስጋና ይገባዋል)፡፡
ስቓይ ይከአልዩ (3)
ሁልጊዜ…
ናይ ፍቕሪ ስቓይ ግን ዘይ ይከአልዩ
ዝደለዮ ተዘይ ረኸበ
የአማርኛ ፍቺው እንደሚከተለው መሆኑም ተነግሮናል፡፡
ስቃይ ይቻላል!
ሁልጊዜ…
የፍቅር ስቃይ ግን አይቻልም
የሚሻውን ካላገኘ በቀር
  ከትግራይ ከያኒያን ብዙ ትዝታ የጣሉብኝ ግን ሶስት ሰዎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ኪሮስ አለማየሁ ነው፡፡ የትግርኛ ዜማን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ከርሱ ይመስለኛል፡፡ በተለይ “እንጓይ ፍስስ” ከልቡ መስተፋቅራዊ ውበት የነገሠበት ስራ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በድሮው ጊዜ ዘፋኙ የሚዘፍነው ስለደስታ ይመስለኝ ነበር፡፡ የዜማው መልዕክት እኔ ከጠበቅኩት ተቃራኒ እንደሆነ የተረዳሁት አሁን በቅርቡ ነው፡፡ “እንጓይ ፍስስ” ሲባል “የአጥንቴ መቅኒ ይፍሰስ” ማለት እንደሆነ ያስረዳን የሽረ ተወላጅ የሆነው ወዳጃችን ሙስጠፋ ሙሐመድ ነው፡፡
     ሁለተኛው አርቲስት አንድ ግለሰብ አይደለም፡፡ እኔ እንደ አንድ ሰው ያየኋቸው ሁለት ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱም በቴሌቪዥን አልፎ አልፎ የምናያቸው ዝነኛው ባለ ከበሮ ሽማግሌ እና ስሟን ለጊዜው መለየት ያቃተን ወጣቷ የከበሮ ተጫዋች ናቸው፡፡ እነዚህን አርቲስቶች ያየሁበት አጋጣሚ ራሱ ለየት ያለ ትዝታ ጥሎብኛል፡፡
      ዘመኑ እንደ ኢትዮጵያው አቆጣጠር በ1980 ነው፡፡ በጊዜው ዝነኛ የነበረው የትግራይ ክፍለ ሀገር የኪነት ቡድን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወረ ዝግጅቱን ሲያቀርብ የኛዋ ገለምሶም በረከቱ ደርሶአት ነበር (በዘመኑ ገለምሶ የሐብሮ አውራጃ ዋና ከተማ ሰለነበረች አዋሽን የተሻገረ ሁሉም ኪነት እኛ ዘንድ ይመጣ ነበር)፡፡ ታዲያ ድሮ በምንሰማው የትግርኛ ዘፈን ውስጥ ከበሮው “ግድፍ! ግድፍ! ግድፍ!” እያለ ማስገምገሙን እንጂ እንዴት ይመታ እንደነበረ ምንም መረጃ አልነበረንም፡፡ የትግራይ ኪነት ወደኛ ሲመጣ ግን ተአምረኛው ሽማግሌና ወጣቷ ተጫዋች የከበሮውን አስደናቂ ትርኢት በዐይናችን እንድናየው አደረጉን፡፡ በዚያች ምሽት ሽማግሌው ወደ ላይ “ዝል..ዝል…” እያሉ  ከበሮውን ይደፍቃሉ፡፡ ወጣቷም እየተሸከረከረችና ሹሩባዋን እያሰናሰለች ከበሮውን ታተረማምሰዋለች፡፡ በተለይ የወጣቷ እንደ እንዝርት መሽከርከር ቢያስደንቀን ብዙዎቻችን ፊልም የምናይ እንጂ እውነት አልመስልህ ብሎን ነበር፡፡
     ዘፋኙ ጨዋታውን ሲያበቃ ህዝቡ “ይደገም… ይደገም.. ይደገም… “ እያለ በጋለ ጭብጨባ ጥያቄውን አቀረበ፡፡ ይሁንና ካባ የለበሰው የመድረኩ መሪ “ክቡራንና ክቡራት ወገኖቼ! ይደገም ያላችሁበት ምክንያት ገብቶኛል፡፡ በከበሮው ትርዒት የተማረካችሁ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ የትግራይ ጨዋታ በአብዛኛው እንዲህ ዓይነት ነው፡፡ እኛም ይዘናቸው በመጣነው ዘፈኖች በሚበዙት ላይ ሁለቱ ተጫዋቾች እየገቡ ከበሮአቸውን ይጫወታሉ፡፡ ስለዚህ የቅድሙን ጨዋታ ከምንደግም ትርኢቱን በሌላ ጨዋታ ላይ ብታዩት ይሻላል” አለንና ጥያቄአችንን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መለሰልን (የመድረኩ መሪ በዚያች ምሽት ባየነው ድራማ ውስጥ አሉላ አባነጋን ሆኖ ተውኗል)፡፡ በእውነትም እርሱ እንዳለው ሁለቱ አርቲስቶች በየጨዋታዎቹ ጣልቃ እየገቡ ህዝቡን ሲያስደንቁ አምሽተዋል፡፡ ካደግኩኝ በኋላ ያንን የከበሮ ትርዒት በሌሎች አጋጣሚዎች አይቻለሁ፡፡ የያኔው ግን ምን ጊዜም ቢሆን ከአዕምሮዬ አይጠፋም፡፡ የሚገርመኝ ነገር በዚያ ቡድን ውስጥ ታዋቂዋ አርቲስት ሶፊያ አጽብሃ እንደነበረችበት ከአስር ዓመታት በኋላ ማወቄ ነው፡፡ የትግራይ ወዳጆቼ በቁምጣ የምትዘፍነው እርሷ ናት አሉኝ፡፡
   ሶስተኛው ትዝተኛ አርቲስት ብርሃነ ሀይለ ነው፡፡ ብርሃነ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ “ሸው በሊ ብለነይ” እያለ ሲጫወት “እንዴት የሚያምር ዘፈን ነው” በማለት በተመስጦ ነበር የሰማሁት፡፡ በወቅቱ ዘፈኑ ትግርኛ ይመስለኝ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን የትግርኛ፣ ቢለን እና ትግረ ቋንቋዎች ቅልቅል መሆኑን ነው የተረዳሁት፡፡ ብርሀነ እንዲህ ነበር ያለው፡፡
ሸው በሊ ብለነይ ብለነይ
ዝለሊ ብለነይ ብለነይ
አሊሊ ብለነይ ብለነይ
አቲ ጓል ከረነይ ብለነይ
ትርጉሙ እንዲህ ይመስለኛል፡፡
ጨፍሪ አንቺ ብለን ሆይ
ዝለሊ አንቺ ብለን
እልል በይ አንቺ ብለን
አንቺ የከረን ልጅ የብለን፡፡
     ቢለን ኤርትራ ውስጥ የሚኖር ብሄረሰብ ነው፡፡ ብርሀነ የቢለን ቆንጆ ወጣትን እያሰበ ነው ይህንን የተጫወተው፡፡ ዜማው የተዜመው በሰሜንና ምዕራብ ኤርትራ በሚኖሩት የትግረ ህዝቦች ምት ነው (የሙዚቃው beat ሬጌ ቢመስልም ከሬጌ ለየት ይላል)፡፡ ብርሃነ ዘፈኑን በዚያ ዘመን ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ቢጫወተውም ለዛሬም ቢሆን ይሰራል፡፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ መለያየት መቼም ቢሆን የህዝቦቻችንን ታሪካዊና ባህላዊ ቁርኝት የሚፍቅ አይሆንም፡፡ 
            *****
    የትግራይ ሙዚቃ በጣም ደስ ይላል፡፡ በደንብ ቀርባችሁ ካጣጣማችሁት ልብን በሐሴት ይሞላል፡፡ አርቲስቶቹ ከልቡ ሲያቀናብሩት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከልቡ ይፈነድቅበታል፡፡ እንደምሳሌም ኪሮስ አለማየሁንና በቅርቡ ውጤታማ ለመሆን የበቁትን  አብረሃም ገብረ መድህንን እና ማህሌት ገብረ ገርግስን መጥቀስ ይቻላል፡፡
      
የትግራይ ሙዚቃ እንደ አብዛኛው የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ሙዚቃ በባለ አምስት ቁልፍ መደብ ላይ የተመሰረተ ( based on pentatonic scale) ነው፡፡ ቅኝቱን በትክክል መግለጽ ይከብደኛል፡፡ ሆኖም በትግራይ ምድር ቢያንስ ሶስት ዓይነት ምቶች እንዳሉ ማንም በቀላሉ አይቶ ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡  አንደኛው ምት ብዙዎቻችን የምናውቀውና “ግድፍ…ግድፍ…” እያለ በሚደለቀው የከበሮ ጉምጉምታ የሚቀናጀው ነው፡፡ ይህ ምት ሁለት ጫፎች እንዳሉት ልብ በሉ፤ ዘፈኑ ሲጀምር ከበሮው “ግድፍ…ግድፍ..” ብቻ ነው የሚለው፤ ወደ ማብቂያው አካባቢ ግን “ግድፍድፍ….ግድፍድፍ….” እያለ በሀይለኛ ድምጸት የሚወርድ ድለቃ ነው የምትሰሙት፤ የእስክስታው ዘውግም ከከበሮው ምት ጋር ይቀየራል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ዘገም እያለ የሚሄደውና ከብዙ የአማርኛ ምቶች ጋር የሚመሳሰለው ነው፡፡ እንደምሳሌም ኪሮስ አለማየሁ “አወይ ላሌ ላሌ… ላሌዋ” እያለ የዘፈነበትን ዜማ መጥቀስ ይቻላል (የዚህ ምት መነሻው የተምቤን አውራጃ ነው ሲባል የሰማሁ ይመስለኛል)፡፡ ሶስተኛው በራያ አዘቦና በአንዳንድ የእንደርታ አካባቢዎች የሚዘወተረው የ“ላሌ ጉማ..” ምት ነው፡፡ ይህኛው ምት ከሌሎቹ ፈጠን ይላል፡፡ በትግራይ ምድር እነዚህ ሶስት ምቶች መኖራቸው የተረጋገጠ ነው፡፡ ሌሎች ምቶች መኖራቸውን ብጠረጥርም እርግጠኛ ስላልሆንኩ ነው ያልጻፍኳቸው፡፡
             *****
   ከላይ እንደገለጽነው ትግራይ በጉብኝት ሊስታችን ውስጥ አለች፡፡ በመሆኑም ሁኔታዎች ሲመቻቹ ያንን ተናፋቂ መሬት ማየታችን አይቀርም (ሰፖንሰር ከተገኘ ግን ዛሬም ጎብኝተነው እዚያ ያለውን በረከት ልንጽፍላችሁ እንችላለን….… ግብዣ ተገኝቶ ነው እንዴ? ሆሆይይ!!)፡፡ እናንተም ምኞቴ እንዲሳካልኝ “ዱዓ” አድርጉልኝ እስቲ (ይሄ ምኞት የሚሉት ነገር እንዳይገድለኝ ብቻ)፡፡ 
—–
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 19/2006