ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት የዓለም ዋንጫ


ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ

——
   የክፍለ ሀገር ልጅ ነኝ (በአሁኑ አጠራር የ“ክልል” ልጅ ሆኛለሁ)፡፡ የክፍለ ሀገር ልጅ መሆኔም ብዙ ጥቅም አስገኝቶልኛል፡፡ የክፍለ ሀገር ልጅ መሆኔ ቅር የሚያሰኘኝ በአንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ይህም በልጅነቴ የዓለም ዋንጫን በቀጥታ ስርጭት ለማየት አለመታደሌ ነው፡፡ የዚህም ምክንያት ከተማችን በዚያ ዘመን የቴሌቪዥን ስርጭት ያልነበራት መሆኑ ነው፡፡ በዚያ ዘመን በሰፊው የሀረርጌ ክፍለ ሀገር ውስጥ ከሚገኙት ከተሞች መካከል ቴሌቪዥን የነበራቸው ሀረር፣ ድሬ ዳዋ እና ጅጅጋ ብቻ ናቸው (እነዚህኛዎቹ ክፍለ ሀገር አይባሉም ማለት ነው)፡፡ ዛሬ የሳተላይ ዲሽ እንዲህ በየገጠሩ መበተኑ ላይቀር የደርግ መንግሥት ከሳተላት ዲሽ የሚከፈለውን የቀረጥ ክፍያ ከጣሪያ በላይ እየሰቀለ እኛን በመበደሉ የስራውን ይስጠው እላለሁ (ለነገሩ የአሁኑ መንግሥትም ቢሆን ከጭሮ ከተማ በስተቀር ለሌሎቹ የምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች የቴሌቪዥን አንቴና አልተከለም፡፡ ኮንትሮባንድ ነው ቶሎ ከተፍ ብሎ ከልጓሙ የገላገለን!! እድሜ ለኮንትሮባንድ! እድሜ ለሀርቲሼክ መንገድ! እድሜ ለቶጎጫሌ መንገድ! ቂቂቂቂቂቂ)
    ——
   የዓለም ዋንጫ የሚባል የውድድር ዓይነት መኖሩን ያወቅኩት የማራዶና ስም በየልብሱ ላይ ታትሞ በመውጣቱ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ከላይ በገለጽኩት ምክንያት በልጅነት ዘመኔ የተካሄዱትን ሁለት የዓለም ዋንጫዎች በቀጥታ ስርጭት ለማየት አልታደልኩም፡፡ እነርሱም የአጣሊያው የዓለም ዋንጫ (1990) እና የአሜሪካው የዓለም ዋንጫ (1994) ናቸው፡፡ (ከዚያ በፊት የነበሩት ሁለት የዓለም ዋንጫዎች እኔ ከተወለድኩ በኋላ የተካሄዱ ቢሆኑም ዕድሜዬ ገና ስለነበረ እንዳለፉኝ አድርጌ አልቆጥራቸውም)፡፡
 
   ይሁን እንጂ ሁለቱንም የዓለም ዋንጫዎች ተከታትያቸኋለሁ፡፡ የቀጥታው ስርጭት ቢያመልጠኝም ጨዋታዎቹን በሁለት ቀናት ልዩነት በቪዲዮ ካሴት እናያቸው ነበር፡፡ ለዚህ የረዳችን የሁል ጊዜ መኩሪያችን የሆነችው ድሬ ዳዋ ናት፡፡ በዚህም መሰረት ዛሬ የተካሄደው ውድድር በድሬ ዳዋ በካሴት ይቀዳና በማግስቱ ወደ ገለምሶ ከች ይላል፡፡ እኛም በሚቀጥለው ቀን ሲቻል ወደ ሀብሮ አውራጃ አኢወማ መዝናኛ ማዕከል፣ ካልተቻለ ደግሞ “ፎቶ ማወርዲ” ከሚባለው ታዋቂ ፎቶ ቤት በመሄድ ጨዋታውን እየተስገበገብን እናየዋለን፡፡ በዚህ ዓይነት በውድድሩ ከተካሄዱት ጨዋታዎች መካከል ቢያንስ ግማሽ ያህል የሚሆኑትን አይቻለሁ፡፡ ድሬ ለዚህ ባለውለታችን ናት፡፡ ማን እንደ ድሬ!! (ቀሽቲ እኮ ናት)፡፡
——–                                          
     በቪዲዮ የምናየውን ጨዋታ ውጤት በቅድሚያ እናውቀዋለን፡፡ በዚያ ላይ ደምሴ ዳምጤ በአደገኛ ምላሱ እያጣፈጠ የሚሰራቸው ዘገባዎች አያመልጡንም፡፡ የአዲስ ዘመንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦችንም እንከታተላለን፡፡ በ1986 ደግሞ የግል ጋዜጦችም ተጀምረው ስለነበረ እየተሻማን እናነባቸው ነበር፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ቅድመ-መረጃ በቪዲዮ የተቀዳልንን ጨዋታ ጣዕም አያደፈርስብንም፡፡ እንዲያውም ደምሴ በዘገባው የጠቀሳቸውን ነጥቦች በጨዋታው ውስጥ ለመመልከት ስንል በከፍተኛ ተመስጦ ውስጥ እንገባለን፡፡
  ታዲያ ዘወትር የሚገርመኝ አንድ ነገር አለ፡፡ ያለፉትን አምስት የዓለም ዋንጫዎችን በቀጥታ ስርጭት ነው ያየኋቸው (እግር ኳስን በቀጥታ ማየት የጀመርኩት እንደኛ አቆጣጠር በ1988 በተካሄደው የEuro-96 ወቅት ነው፡፡) ቢሆንም እነዚህ በቀጥታ ስርጭት ያየኋቸው ጨዋታዎች ያኔ በቪዲዮ እየተቀዱ ከሁለት ቀናት በኋላ የምናያቸውን ጨዋታዎች ያህል አይጣፍጡኝም፡፡ ጎሉም ሆነ ጨዋታው፣ ተጫዋቹም ሆነ ቡድኖቹ፣ አሰልጣኙም ሆነ ዳኛው ያኔ በልብ ላይ ይቀራል፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን ሁሉም ነገር ተለውጧል፡፡ በተለይም ባለፉት ሁለት የዓለም ዋንጫዎች ካየኋቸው ክስተቶች አንዳቸውም በአዕምሮዬ ውስጥ የሉም፡፡ ውጤቱንም ብትጠይቁኝ ልነግራችሁ አልችልም (እ.ኤ.አ በ2006 በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ዚነዲን ዚዳን ካሳየው ጣፋጭ ፉት ቦልና በፍጻሜው ጨዋታ ማቴራዚን በቴስታ ደረቱ ላይ መቶት ከመጣሉ ውጪ ማለቴ ነው)፡፡
በዚህ ጽሑፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁትን የዓለም ዋንጫ አስቃኛችኋለሁ፡፡ የአሜሪካውን የዓለም ዋንጫ በሌላ ጽሐፍ እመጣበታለሁ፡፡
==== 14ኛው የዓለም ዋንጫ በኢጣሊያ (Italy-1990)===
በኢጣሊያ የተካሄደው 14ኛው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ኤክስፐርቶች በጣም አሰልቺ የተባለለት ነው፡፡ በያንዳንዱ ውድድር የገቡት ጎሎች በአማካይ ከሁለት አይበልጡም፡፡ ቢሆንም ግን ያኔ ሁሉም ነገር እየጣፈጠን ነው ያየነው፡፡ ለኛ አሰልቺና አስቀያሚ የሆነብን የመጨረሻው ጨዋታ ብቻ ነው፡፡ በዚያ ጨዋታ ዳኛው ብዙ ቢጫና ቀይ ካርዶችን ማሳየታቸው ሳያንሰን አጨቃጫቂ “ሪጎሬ” ሰጥተው የጨዋታውን ስሜት አበላሹብን፡፡
  በዚያ የዓለም ዋንጫ የተካሄዱትን ጨዋታዎች በተመለከተ ዝርዝር ዘገባውን ከኢንተርኔት ስለምታገኙት እዚያ ውስጥ አልገባም፡፡ እኔ እዚህ የማደርገው ከአዕምሮዬ ያልጠፉ ክስተቶችንና ስብዕናዎች ማሳወቅ ነው፡፡
·        አስደሳቹ መጽሐፍ  
በውድድሩ ዋዜማ በጣም ተወዳጅ የሆነ አንድ መጽሐፍ ታትሞ ነበር፡፡ ርዕሱ “እግር ኳስ፤ ፊፋ እና የዓለም ዋንጫ” ይሰኛል፡፡ በአማርኛ ቋንቋ በስፖርት ዙሪያ ከተዘጋጁ መጻሕፍት እንደርሱ የሚማርከኝ የለም፡፡ ያ መጽሐፍ በርካቶቻችን እግር ኳስን እንድንወደው አስተዋጽኦ ያደረገ ይመስለኛል፡፡ በዓለም ዋንጫውን በንቃት እንድንመለከት ያስቻሉን መረጃዎችንም ሰጥቶናል፡፡ ያንን መጽሐፍ ያዘጋጁት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የስፖርት አምድ አዘጋጆች የነበሩት ግርማ ሰይፉ እና ፋንታሁን ሀይሌ ናቸው፡፡
ታዲያ ያ መጽሐፍ በአንድ ነገር አቀዣብሮኛል፡፡ መጽሐፉ በዝርዝር የሚያወሳቸውን እውቅ ተጫዋቾች በዓለም ዋንጫው ላይ የማያቸው መስሎኝ በጉጉት ስጠብቃቸው ነበር፡፡ በተለይም በ13ኛው የዓለም ዋንጫ ወቅት የተጫወቱትን ተጫዋቾች በናፍቆት እየጠበቅኳቸው ነው ውድድሩ የተጀመረው፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ የውሃ ሽታ ሆነው ቀሩ፡፡ ጥቂቶቹ ብቻ (ማራዶና፣ ቡርቻጋ፣ ቫንባስተን፣ ሩድ ጉሌት፣ ካሬካ፣ ጋሪ ሊነከር፤ ጆን ባርነስ፣ ሎታር ማትያስ፣ ሩዲ ቮለር ) በውድድሩ ውስጥ ነበሩ፡፡ የብራዚሉን ፓውሎ ሮቤርቶ ፋልካኦን ደግሞ ለተጫዋችነት ስጠብቀው አሰልጣኝ ሆኖ አገኘሁት፡፡
·        የአጂፕ ኩባኒያ ውለታ፡
ጨዋታው በጣሊያን ሀገር የተካሄደ በመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ስርጭቱን ለማስተላለፍ ስፖንሰር የሆነው የኢጣሊያ ኩባኒያ የሆነው አንጋፋው ነዳጅ አቅራቢ “አጂፕ” ነው፡፡ ያኔ በየጨዋታው መሀል ሲነገር ከነበረው ማስታወቂያ እንደሰማሁት “አጂፕ” በኢትዮጵያ ውስጥ 120 የማደያ ጣቢያዎች ነበሩት፡፡ እስከ አሁን ድረስ ቢኖር ኖሮ 1200 ጣቢያዎች ሳይኖሩት ይቀራል?  
·        የካሜሩን ጉዞ

በዓለም ዋንጫው እጅግ ከፍተኛ ደስታ የፈጠረልን የካሜሩን አስደናቂ ጀብድ ነው፡፡ አርጀንቲናን፣ ሩማኒያንና ኮሎምቢያን ያሸነፈባቸው ጨዋታዎች ከማንም አዕምሮ ውስጥ አይጠፉም፡፡ ሮጀር ሚላ፣ ኦማም ቢይክ፣ ማካናኪ እና በረኛው ቶማስ ንኮኖ የዘወትር ትዝታዎቻችን ናቸው፡፡ ይሁንና ለዋንጫው በጉጉት ስንጠብቀው የነበረው ያ አስደሳች ቡድን በእንግሊዝ ጉድ ተሰራና ከመንገድ ላይ ቀረብን፡፡
ያ ጨዋታ ከፍተኛ የዳኛ ተጽእኖ የታየበት መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ ካሜሩን እንግሊዝን በሁለት ለአንድ እየመራ ወደ መጨረሻው ደረሰ፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ስምንት ደቂቃ ብቻ ሲቀረው ዳኛው የፍጹም ቅጣት ምት ለእንግሊዝ ሰጡ፡፡ በዚህም እኩል ሆኑ፡፡ በጭማሪው ሰዓትም ዳኛው በድጋሚ ለእንግሊዝ ሪጎሬ ሰጡና አፍሪቃዊያንን የባሰ አሳረሩ፡፡ ተቃጠልን ነው የምላችሁ!! በጣም ሚያሳርረው ደግሞ እነዚያን ሁለት ከይሲ ጎሎች ያስቆጠረው ከላይ የጠቀስኩትን መጽሐፍ አንብቤ በጉጉት ስጠብቃቸው ከነበሩት ተጫዋቾች አንዱ የነበረው እንግሊዛዊው ጋሪ ሊነከር መሆኑ ነው (ጋሪ ሊነከር በሜክሲኮ በተካሄደው 13ኛው የዓለም ዋንጫ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ነው የጨረሰው)፡፡
   ለኳስ እንደዚያ የተናደድኩበት ጊዜ የለም፡፡ ከኔ በላይ ደግሞ ኳስ አፍቃሪው ኢትዮጵያዊ ህዝብ እርር ነው ያለው፡፡ ታዲያ ጨዋታውን በቪዲዮ ማየት እንደጀመርን (“ቪዲዮው ተቀድቶ የሚመጣልን የጨዋታው ውጤት ከታወቀ በኋላ ነው” ያልኳችሁን አትዘንጉ) ማን እንደፈጠረው የማይታወቅ ወሬ በከተማችን ተዛምቶ ነበር፡፡ “ዳኛው ተጽእኖ ያደረገ መሆኑ ስለተረጋገጠ ጨዋታው ይደገማል” የሚል፡፡ ይህ ወሬ እውነት ነው ብለን ስንጠብቅ ከሁለት ቀን በኋላ እንግሊዝ ከጀርመን ጋር ትጫወታለች ተብሎ ተነገረ፡፡ እንደገና እርር!! እንደገና መቃጠል!! ደግነቱ ጀርመንና ጣሊያን እንግሊዝን ቀጥተውልናል፡፡
·        የማይረሱ ጨዋታዎች
የዓለም ዋንጫው የግብ ድርቅ ስላጠቃው “ወዝ የለውም” ይባል እንጂ ዘወትር ከሰው ህሊና የማይጠፉ ምርጥ ጨዋታዎችንም አይተንበታል፡፡ አርጀንቲናና ሩማኒያ፣ ካሜሩንና ኮሎምቢያ፣ ጀርመንና ኮሎምቢያ፣ ኢጣሊያና ቼኮዝሎቫኪያ፣ ብራዚልና ስዊድን፤ አርጀንቲና እና ኢጣሊያ፣ ጀርመንና ሆላንድ፣ አየርላንድና ሩማኒያ በጣም ጥሩ ጨዋታ አሳይተውናል፡፡
·        እጅግ ምርጥ ጨዋታ
ከላይ ከጠቀስኳቸው ጨዋታዎች ይበልጥ ሁሉንም ሰው ቁጭ ብድግ ያደረገው የአርጀንቲናና ብራዚል ጨዋታ ይመስለኛል፡፡ ከምድቡ ሶስቱንም ጨዋታዎች በአሸናፊነት ያጠናቀቀው ብራዚል ካሜሩንን እንኳ ማሸነፍ ባቃተው የአርጀንቲና ቡድን ተረታ፡፡ ለዋንጫ የጠበቅነው ቡድን ስለነበረ ልባችን ነው የተቆረጠው፡፡
·         አስደሳች ተጫዋቾች
 የሩማኒያው ጆርጅ ሃጂ፣ የአርጀንቲናዎቹ ዲየጎ ማራዶና እና ክላውዶ ካኒንጃ፣ የካሜሩኖቹ ሮጀር ሚላ እና ማካናኒ፣ የብራዚሎቹ ካሬካ፣ አሊማው እና ሙለር፣ የኢጣሊያዎቹ ሳልቫቶሬ ሺላቺ እና ሮቤርቶ ባጂዮ፣ የቼኮዝሎቫኪያው ቶማስ ስኩራቪ፣ የስፔኑ ሚሼል፣ የእንግሊዞቹ ጋሪ ሊነከር እና ፖል ጋስኮኝ፣ የእንግሊዙ በረኛ ፒተር ሼልተን፣ የጀርመኖቹ ሎታር ማትያስ እና ሩዲ ቮለር በጣም ምርጥ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡  

·        የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች
በዚያ የዓለም ዋንጫ ላይ ካየኋቸው ተጫዋቾች መካከል ኮከብ ነው ብዬ የምመርጠው የኮሎምቢያውን ካርሎስ ቫልዴራማን ነው፤ በለው! በለው! አቤት ጨዋታ! አቤት ታክቲክ! አቤት አብዶ መስራት፣ ወይኔ! ወይኔ! (ወደዳችሁም ጠላችሁም ኳስ ድሮ ቀረ አቦ!)
ቫልዴራማ ኳስ ሲይዝ አስማት በሉት! ሜዳው ጠቦት ይሸከረክርበታል፡፡ በተለይም የጀርመን ተጫዋቾችን እያጥበረበረ ሲያታልላቸው ሁኔታው ሁሉ ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ሆኖባቸው ነበር፡፡ የካሜሩን ቡድንም ኮሎምቢያን አሸንፎ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ የቻለው በረኛው ቀሽም በመሆኑ እንጂ በኮሎምቢያ ቡድን ድክመት አይደለም፡፡ ቫልዴራማ በዚያ ጨዋታም ላይ ኮከብ ሆኖ ነበር የዋለው፡፡ ቫልዴራማ እ.ኤ.አ. በ1987 የላቲን አሜሪካ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጦ ነበር (በ1986 ኮከብ የሆነውን ማራዶናን በልጦ ማለት ነው)፡፡
·        ምርጥ ወጣት ተጫዋቾች
በዚያን ጊዜ ለጨዋታው ልጅ እግር ከሆኑት መካከል በጣም ያስደሰቱኝ ሁለት ወጣቶች ናቸው፡፡ አንደኛው የስዊድኑ ቶማስ ብሮሊን ነው፡፡ ቡድኑ ሁሉንም ጨዋታዎች ተሸንፎ ከምድቡ ቢባረርም ብሮሊን በአጨዋወቱ ማንንም ነበር ያስደሰተው፡፡ ደግሞም በብራዚል ላይ አንድ ግብ አስቆጥራል (ብሮሊን በቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ሶስተኛ ኮከብ ሆኗል)፡፡
   ሌላኛው የኢጣሊያው ሮቤርቶ ባጅዮ ነው፡፡ ሮቤ ለኢጣሊያ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር አያያዙ አደገኛ መሆኑን አስመሰክሯል፡፡ እነዚህ ሁለት ተጫዋቾች በኢጣሊያው “ሴሪ አ” ተገናኝተው ምርጥ ፉት ቦል አሳይተውናል፡፡
·        የማይረሱ ተጫዋቾች
1.      ሬኔ ሂጉታ፡
የኮሎምቢያ በረኛ ነው፡፡ በሁኔታዎቹ ሁሉ እብድ በሉት፡፡ ኳስ በእግሩ እንጂ በእጁ ለመያዝ ይጠየፋል፡፡ ሲያቀብል በእግር! ሲቀበልም በእግር! በዚያ ሁኔታው ኮሎምቢያ ለሁለተኛው ዙር ማለፉ አስደናቂ ነበር፡፡ የሂጉታን እብደት ያጠናው የካሜሩኑ ሮጀር ሚላ ግን ሳያስበው ጉድ ሰራው፡፡ አቤት የያኔው የአፍሪካ ደስታ! አቤት የሚላ ዳንስ!! (አቤት የደምሴ ዳምጤ አዘጋገብ)!
2.     የአርጀንቲናው በረኛ፡
ስሙን ዘንግቼዋለሁ፡፡ ሁለተኛ በረኛ ሆኖ ነበር ወደ ኢጣሊያ የሄደው፡፡ ነገር ግን ዋናው በረኛ ከሶቪየት ህብረት ጋር በተደረገው ጨዋታ በመጎዳቱ እርሱን ተክቶ ወደ ጨዋታው ገባ፡፡ ከዚያ በኋላ ማን ይቻለው!!? በተለይም ኢጣሊያ በደጋፊዎቿ ፊት ተጫውታ በመለያ ምቶች በአርጀንቲና ስትሸነፍ የበረኛው አስተዋጽኦ ሌላ ነው፡፡ (ያኔ የውድድሩ ኮከብ በረኛ ምርጫ ባይደረግም ከሁሉም የሚበልጠው እርሱ ይመስለኛል)፡፡   
·        ምርጥ ግብ አዳኞች
1.      ቶማስ ስኩራቪ (ቼኮዝሎቫኪያ)፡
በሁለተኛው ዙር በኮስታሪካ ላይ የሰራውን ሀትሪክን ጨምሮ አምስት ጎሎችን ነው ያስቆጠረው፡፡ ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረው ቼኮዝሎቫኪያ አሜሪካን 5-1 ባሸነፈችበት ጨዋታ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ቼኮዝሎቫኪያ አሜሪካን ማሸነፏ ሶሻሊዝም በኢምፔሪያሊዝም ላይ የተጎናጸፈው ድል ተደርጎ ስለተወሰደ የአውራጃችን አኢወማ መሪዎች ከደስታ ብዛት ማበድ ነው የቀራቸው (ትልቋ ሶቪየት ህብረት በአርጀንቲና መሸነፏን ያልሰሙ ይመስል ጉራው ሌላ ነበረ)፡፡
  ፖለቲካው ሌላ ነው፡፡ ቶማስ ስኩራቪ ግን ያለምንም ማጋነን ነፍስ የሆነ ተጫዋች ነበረ፡፡ ጎል ለማግባት የተፈጠረ አጥቂ ነው፡፡ ይሁንና ከዚያ የዓለም ዋንጫ በኋላ በድጋሚ አላየሁትም (እነ ጆርጅ ሃጂንና ካርሎስ ቫልዴራማን ግን በድጋሚ ለማየት ችለናል)፡፡
2.     ሚሼል (ስፔን)
በጣም ጎበዝ አጥቂ ነበር፡፡ በምድብ ማጣሪያው በደቡብ ኮሪያ ላይ ሀትሪክ ሰርቷል፡፡ በቤልጅግም ላይ አንድ ግብ አስቆጥሯል፡፡
3.     ካሬካ  እና ሙለር (ብራዚል)፡
 አቤት ጨዋታ! አቤት ፍጥነት!! አቤት ዳንስ! በህይወቴ ካየኋቸው አስደሳች ተጫዋቾች መካከል ናቸው፡፡ ሁለቱም በጥምረት የሚያጠቁ ሲሆን ብራዚል ያስቆጠረቻቸውን አራት ግቦች ያገቡት እነርሱ ናቸው፡፡
    ካሬካ በስዊዲን  ላይ ሁለት ጎሎችን ካስቆጠረ በኋላ በቢጫ ማሊያው የደነሰው “ሳንባ” ዳንስ መቼም ቢሆን የሚረሳኝ አይሆንም፡፡ አስራ አንድ ቀጥሩ ሙለርም በኮስታሪካና በስኮትላንድ ላይ አንዳንድ ግቦችን አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ ሁለተኛው ዙር አሸጋግሮታል፡፡
4.     ሮጀር ሚላ (ካሜሩን)፡
 ዓለም በሙሉ ነበር የተደነቀበት፡፡ በዓለም ዋንጫ በ38 ዓመቱ ተሰልፎ ከአዕምሮ የማይጠፉ ግቦችን ለማስቆጠር የቻለ ሰው እርሱ ብቻ ይመስለኛል (ይህ ሪከርድ ከአራት ዓመት በኋላ በራሱ ተሰብሯል)፡፡ የሚደንቀው ነገር ሮጀር ሚላ ግቦቹን ያገባው ከእረፍት በኋላ ተቀይሮ እየገባ ነው፡፡ በሩማኒያ እና ኮሎምቢያ ላይ ሁለት ሁለት ጎሎችን ካስቆጠረ በኋላ የደነሰው ዳንስ የሁሉም አፍሪቃዊ ትዝታ ነው (ደምሴ ዳምጤ ጨዋታዎቹን ሲዘግባቸው አፍ ያስከፍት ነበር)፡፡ ታዲያ እስከ አሁን ድረስ ያልገባኝ ነገር ሰውዬው ሮጀር ሚላ ሆኖ ቴሌቭዥኑ “ሚለር” (Miller) እያለ የሚጠራው መሆኑ ነው፡፡
5.     ሳልቫቶሬ ሺላቺ (ኢጣሊያ)
አስገራሚ ብቻ ሳይሆን የዘረኝነትን መጋረጃ የደመሰሰ ተጫዋች ነው፡፡ በሲሲሊ ደሴት ላይ ከምትገኘው የፓሌርሞ ከተማ ተወልዶ የሀብታሞቹን የሰሜን ኢጣሊያ ልጆች ለመብለጥ የቻለ ነው፡፡ ከሰሜናዊ ኢጣሊያ ከተሞች (ሚላን፣ ቶሪኖ፣ ሮማ፣ ፍሎሬንስ፣ ቬኒስ፣ ወዘተ…) የተገኙ ሰዎች በነርሱ እይታ “ደሀ” የሚባሉትን የሲሲሊና የሳርዲኒያ ሰዎችን ያለ ልክ ይንቋቸዋል፡፡ በሁሉም ነገር አንደኛ እኛ ነን ይላሉ፡፡ ሺላቺ ግን ሳይወዱት በግድ ወደ ውስጣቸው እንዲመለከቱ አደረጋቸው፡፡
  
  ይህ ተጫዋች ኢጣሊያ ባደረገቻቸው ሰባት ግጥሚያዎች ላይ ስድስት ግብ አስቆጥሯል፡፡ በዚህም የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን የወርቅ ጫማ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይሁንና ከውድድሩ በኋላ በኢጣሊያ ውስጥ በዘላቂነት ሊጫወት አልቻለም፡፡ ለረጅም ጊዜ ከኢጣሊያ ተሰዶ ለጃፓን ቡድኖች ይጫወት እንደበረ አውቃለሁ፡፡ አሁን ምን ላይ እንደደረሰ አላውቅም፡፡
  
·        የማይረሱ ጎሎች
1.      ከሮጀር ሚላ ጎሎች መካከል በሬኔ ሂጉታ ላይ ያስቆጠራት ሁለተኛዋ ጎል በዓለም የፉትቦል ተመልካቾች ዘንድ ዘወትር የምትታወስ ትመስለኛለች፡፡
2.     የቼኮዝሎቫኪያው ቶማስ ስኩራቪ በኮስታሪካ ላይ ያስቆጠራቸው ሶስት ጎሎችም አይረሱም፡፡
3.     የአርጀንቲናው ክላውዶ ካኒንጃ ብራዚልን ከጨዋታ ውጪ ያደረገችውን ጎል አስቆጥሮ ስንቱን አስለቀሰ?… ወይኔ ብራዚል! እንደዚያ ምርጥ ጨዋታ እየተጫወተ በመንገድ ላይ ቀረብን!
4.     የኮሎምቢያው ፍሬዲ ሪንኮን በጀርመን ላይ ያስቆጠራት ግብ ፈጽሞ አትረሳም፡፡ ያ ጨዋታ ግብ አልባ ሆኖ ወደ መጠናቀቁ ሲቃረብ ጀርመኖች በ88ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ጎል አገቡ፡፡ በዚህም ኮሎምቢያ ያለቀለት መሰለ፡፡ ከዓለም ዋንጫ ሊባረር የሚባረርበት ጊዜ ቀረበ፡፡ ነገር ግን ካርሎስ ቫልዴራማ ብልሃቱን አምጥቶ ያገኛትን ኳስ አስተካክሎ ለፍሬዲ ሬንኮን አቀበለ፡፡ ሬንኮንም የአቻነቷን ጎል አስቆጠረ፡፡ ኮሎምቢያም በአንደኛው ዙር ከመባረር ተርፋ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈች፡፡
·        ኮከብ አሰልጣኝ
የጀርመኑ ፍራንዝ ቤከንባወር ኮከብ አሰልጣኝ ሆኖ መመረጡ ትክክል ይመስለኛል፡፡ ቡድኑ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ለዋንጫ ደርሶለታልና፡፡ እኛም ጀግናውን ቤከንባወርን በተጫዋችነት ዘመኑ ለማየት ባይቻለንም በአሰልጣኝነቱ በማየታችን እድለኞች ነን፡፡
·       የማይረሳው አሰልጣኝ
የአርጀንቲና አሰልጣኝ ካርሎስ ቢላርዶን ማንም የሚረሳው አይመስለኝም፡፡ ቢላርዶ ከሌሎቹ አሰልጣኞች የሚለይበት ነገር አሰልጣኞች ከሚቀመጡበት ወንበር ላይ በመነሳት ወደ ሜዳው እየሄደ ለተጫዋቾቹ እየጮኸ ምክር ቢጤ የሚለግስ መሆኑ ነው፡፡ ያኔ በተመለከትኳቸው ጨዋታዎች ሁሉ አሰልጣኞች ከወንበራቸው ሲነሱ አላየኋቸውም፡፡ ካርሎስ ቢላርዶ ግን ከተጫዋቾቹ እኩል ነበር የሚንቀሳቀሰው፡፡
በቀጣዮቹ የዓለም ዋንጫዎች ግን ያ ልማድ ተቀየረ፡፡ ሁሉም አሰልጣኝ ከወንበር እየተነሳ የሚመክር በመሆኑ ወንበር ላይ ተቀምጦ ጨዋታውን የሚያይ አሰልጣኝ ጠፋ (እኔ እንደታዘብኩት ከዚያ ወዲህ ካየኋቸው አሰልጣኞች መካከል ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ የተለየ እንቅስቃሴ የማያሳዩት የሞሮኮ ቡድንን ለረጅም ጊዜ ሲያሰልጥኑ የነበሩት ሄንሪ ሚሼል እና በ2002 የኮሪያ-ጃፓን የዓለም ዋንጫ ሴኔጋልን ያሰለጠኑት ብሩኖ ሚትሱ ናቸው፡፡ ( ሄንሪ ሚሼል ቁጭ ብሎ ማስቲካውን ያኝካል፤ ጎል ከገባበት ግን ይናደድና ሲጋራውን ያቀጣጥላል፤ ብሩኖ ሚትሱ ደግሞ እጆቻቸውን በማጣመር ይቆሙና ይተክዛሉ)፡፡  
·        የጨዋታው ማስታወሻ
የዓለም ዋንጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ብሄራዊ ሎተሪ ውድድሩን አጠቃልሎ የሚዘግብ ፖስተር በማሳተም አስደሰተን፡፡ የፖስተሩ አብዛኛው ክፍል ለሩብ ፍጻሜ የደረሱትን ስምንት ቡድኖችና የውድድሩ ቅመሞች የነበሩትን ምርጥ ተጫዋቾች በፎቶግራፍ ያሳያል፡፡ ከታች ደግሞ በውድድሩ የተከናወኑ ጨዋታዎች ውጤት በሰንጠረዥ ተጠቃልሎ ቀርቧል፡፡ ብሄራዊ ሎተሪ ፖስተሩን በነጻ ለማሰራጨት ያዘጋጀው ይመስለኛል፡፡ ይሁን እንጂ ለማንም ሰው በነጻ ሲሰጥ አላየሁም፡፡ ሁሉም ሰው በብር እየገዛው ነው በቤቱ ሲለጥፈው የነበረው፡፡ ያ ልምድ በቀጣዩ የዓለም ዋንጫም ተደግሟል፡፡ በዚህ ዘመን ያለው አሰራር ግን ሌላ ነው፡፡ የውድድሩን ፕሮግራሞች ለማሳየት በሚል ከጨዋታው በፊት የተዘጋጁ እንጂ የዓለም ዋንጫ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚዘጋጅ የማስታወሻ ፖስተር አላየሁም፡፡
==== የልጅነት ተስፋና ቅሬታ===
ያ የዓለም ዋንጫው በደስታ ቢያልቅልንም ከፍተኛ ቅሬታም ጥሎብናል፡፡ ለምን መሰላችሁ? ማይክል ጃክሰን የትሪለር አልበምን በለቀቀ ጊዜ ፋሽን የሆኑ አልባሳት በሙሉ በርሱ ስም ተሰይመው ነበር፡፡ በሜክሲኮ በተካሄደው 13ኛው የዓለም ዋንጫ ማግስት ደግሞ ማራዶና በዓለም ዙሪያ ዝነኛ ሆነ፡፡ በመሆኑም የልብስና የጫማ ውጤቶች በሙሉ በርሱ ስም እየተሰየሙ ሀገሩን አጥለቅልቁት፡፡፡ ፋሽን ነው የተባለ ቱታ፣ ፒጃማ፣ ስኔከር ጫማ፣ ሸሚዝ፣ ጂንስ ሱሪ… የሁሉም መጠሪያ “ማራዶና” ሆነ (አልፎ አልፎ ግን Zicco እና Azzaro በሚሉ ስሞች የተሰየሙ ሸሚዞች ነበሩ)፡፡ በተጨማሪም በውድድሩ ላይ የተካፈለውን የእያንዳንዱን ተጫዋች ፎቶ ግራፍ የያዘ ማስቲካ መጥቶ ነበር፡፡
እኔ ባየሁት የ14ኛው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ማግስትም ተመሳሳይ ነገር የሚከሰት መስሎኝ ነበር፡፡ ከምንወዳቸው ተጫዋቾች በአንዱ ስም የተሰየመ ፋሽን ሸሚዝና በቪዲዮ ያየናቸውን የነ ቫልደራማንና የጆርጅ ሃጂን ፎቶግራፎች የያዙ ማስቲካዎችን በተስፋ ስንጠብቅ ቀናት አለፉ፡፡ ወራት አለፉ፡፡ ስድስት ወር ሆነ፡፡ ስምንት ወር አለፈው፡፡ ተስፋችን ሳይሟላልን እንዲሁ ስንብሰለሰል ጭራሽ የደርግ መንግሥት ወደቀ፡፡
  በህይወቴ ከሚቆጩኝ ነገሮች መካከል አንዱ ያ የልጅነት ተስፋዬ ሳይሟላልኝ መቅረቱ ነው፡፡ “ድርቅ የመታው የዓለም ዋንጫ” የተባለው ይህ ሁሉ ተደምሮ ይሆን እንዴ? መጠርጠር ነው፡፡
——-
አፈንዲ ሙተቂ
ሚያዚያ 16/2006
በሸገር ተጻፈ፡፡