ግመል-ጊመል-ገመል-ጀመል (ክፍል አንድ)
(አፈንዲ ሙተቂ)
—
የኢትኖግራፊ ፈረሳችን አንዳንዴ ከሰዎች ዓለም ይወጣል፤ ከዚህ ቀደም ወደ ጂንኒዎች ዓለም ሄደን ከዚያ ያገኘነውን ጨዋታ እያጫወትናችሁ በፍርሃት አርበድብደናችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ፈረሳችን ወደ እንስሳት ዓለም በመሸጋገር እንደርሱ ጋላቢ ከሆነው ተአምረኛው “ግመል” ጋር ተፋጧል፡፡
ፈረሱም ፈረስ ነው፡ ግመሉም ግመል
ግመል ግን ይበልጣል በረሃ “እሚሸቅል”
እውነት ነው! ፈረስ በፍጥነቱ አንጀት አርስ ነው፡፡ በእሽቅድምድምና በግልቢያ አንደኛ ነው፡፡ በድሮ ዘመን ጦርነት ሲካሄድም ይህ ቀረሽ የማይባል አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ የሰው ልጅ እንስሳትን አላምዶ መጠቀም ከጀመረበት ዘመን አንስቶ ለሰዎች የሰጠው አገልግሎት ቢመዘን ግን ከግመል አይበልጥም፡፡ ለዚህም ብዙ ማስረጃዎች አሉን፡፡ አሁን እነርሱን አናስቆጥራችሁም፡፡ ጊዜው ሲደርስ ማስረጃዎቹ ራሳቸው እየጮኹ ይናገራሉ፡፡ Let the facts speak themselves እንዲሉ ፈረንጆች!!
ይልቅስ የዛሬው ጉዞአችን በረሀ ለበረሀ ስለሚያዟዙረን ግመልን ራሱኑ መጓጓዣችን ብናደርገውስ?… ይገባዋል! ለበረሃ ሐሩር፣ ለአሸዋ ውሽንፍር የማይበገረው “ግመሌ” ነው፡፡ ስለዚህ ፈረሳችንን በቆላው መሬት ውስጥ ለገበሬዎች በአደራ ሰጥተናቸው በግመል ጀርባ እየጋለብን ስለተአምረኛው እንስሳ እንዲህ እናወጋችኋለን፡፡
*****
የእንስሳው ስም “ግመል” ነው ብለናል፡፡ ይህንን ስም ልብ ብላችኋልን?….! እንግዲህ ተአምሩ የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡ “ግመል” የአማርኛው ስሙ ነው፡፡ በትግርኛም “ግመል” ነው፡፡ በእብራይስጥ ደግሞ “ጊመል” ነው፡፡ በግዕዝ “ገመል” ተብሎ ይጠራል፡፡ ዐረብኛው “ጀመል” ይለዋል፡፡ በሀረሪ ቋንቋ “ጋሚላ” እንለዋለን፡፡ እነዚህ ቋንቋዎች በሙሉ ሴማዊ ናቸው፡፡ እንስሳው በነዚህ ቋንቋዎች በተመሳሳይ/ተቀራራቢ ስም የሚጠራው ቋንቋዎቹ ስሙን በመወራረሳቸው አይደለም፡፡ ስያሜው የሴም ቋንቋዎች መነሻ ነው ተብሎ ከሚታመነበት ግንደ ሴማዊ ቋንቋ (Proto-Semitic Language) ተነስቶ በያንዳንዱ ቋንቋ ውስጥ እየተላለፈ ወደዚህ ዘመን ስለደረሰ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ እንስሳው ራሱ ከሰው ልጅ ጋር የተላመደው የሴም ህዝቦች መነሻ ከሆነው መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ እንደሆነ ይጠቁመን ይሆን?..
በሚገባ! የሰው ልጅን የስልጣኔ ታሪክ ያጠኑ ምሁራን እንደሚመሰክሩት ግመልን ለመጀመሪያ ጊዜ ያላመዱት የሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች ናቸው፡፡ በመሆኑም በአንዳንድ ቋንቋዎች (ኦሮምኛ፣ ሶማሊኛ ወዘተ…) እንስሳው የተለየ ስያሜ ቢኖረውም በዛሬው ዘመን አብዛኛው የዓለም ህዝብ ግመልን የሚጠራው ከሴማዊ ቋንቋዎች የወረሰውን ቃል በ“ማንሻፈፍ” (corrupt በማድረግ) ነው፡፡ ለምሳሌ እንግሊዛዊያን “ካሜል” ይሉታል፡፡ በጀርመንም “ካሜል” ይባላል፡፡ በፈረንሳይኛ፣ በስጳኝ፣ በጣሊያንኛና በሌሎችም የአውሮጳ ቋንቋዎች በተቀራራቢ ስም ይጠራል፡፡ እነዚህ ቋንቋዎች ቃሉን የወረሱት ከላቲን ነው፡፡ ላቲንም ከግሪክ ነው የወረሰው፡፡ ግሪክ ደግሞ በጥንቱ ዘመን በሶሪያና በፍልስጥኤም የብዙ ህዝቦች መግባቢያ ከነበረው የአረማይስጥ ቋንቋ ነው የወሰደው፡፡
ታዲያ ዛሬ ከምንጽፍባቸው ፊደላት መካከል አንዱ በዚህ እንስሳ ስም የተሰየመ መሆኑን የምታውቁት ስንቶቻችሁ ናችሁ?… በሮማዊያንም ሆነ በሳባ፣ በዐረብም ሆነ በግሪክ ፊደላት የምትጠቀሙት ሁሉ ከምትጽፉባቸው ፊደላት መካከል አንዱ በዚህ እንስሳ ስም የተሰየመ መሆኑን ተገንዘቡት፡፡ እንዴት ማለት “አሪፍ” ነገር ነው፡፡
“ሀረር ጌይ” በተሰኘው መጽሐፌ ለማስረዳት እንደሞከርኩት በዓለም ላይ ከሚሰራባቸው የፊደል ገበታዎች መካከል በጣም የሚበዙት ከአንድ ምንጭ ነው የተቀዱት፡፡ የሮማ ፊደል፣ የግሪክ ፊደል፣ የሳባ (ግዕዝ) ፊደል፣ የዐረቢያ ፊደል፣ የቄርሎሳዊያን (የሩሲያ) ፊደል እና የሳንስክሪት (ህንድ) ፊደል ምንጫቸው አንድ ነው፡፡ እርሱም የጥንቱ የፊንቃዊያን (Phoenicians) የፊደል ገበታ ነው፡፡ እነኚያ ፊንቃዊያን የመጻፊያ ፊደላትን ሲፈጥሩ እያንዳንዱን ፊደል በቅርብ በሚያውቋቸው ፍጥረታትና የሰው ልጅ የስራ ውጤቶች ነው የሰየሙት፡፡ ለምሳሌ “አሌፍ” ሲባል “በሬ” ማለት ነው፡፡ “ቤት” ደግሞ መጠለያችን የሆነው “ቤት” ነው፡፡ “ጊመል” ሲባል “ግመል” ነው፡፡ “ዳሌጥ” ደግሞ የቤት መግቢያ ምድራክ ነው፡፡ “ሚም” የሚፈስ ውሃ ማለት ነው፡፡ “ኑን” አሳ ማለት ነው፡፡ “ዐይን” ዐይን ነው፡፡ ወዘተ….
የፊንቃዊያኑን ፊደል እንደ መነሻ በማድረግ የተፈጠሩት ልዩ ልዩ የፊደል ገበታዎች ሆሄያትን ያስቀመጡበት ቅደም ተከተል፣ የፊደላቱ ቅርጽና የመጠሪያ ስማቸው በዘመናት ሂደት ተለውጧል፡፡ ነገር ግን ወደ ኦሪጂናሌ አቀማመጣቸው ስንመልሳቸው ሁሉም ከአንድ ምንጭ የተነሱ መሆናቸውን በቀላሉ ማስተዋል ይቻላል፡፡ በዚህ መሰረት የዐረብኛ የፊደል ገበታ “አብጀድ” በተሰኘው ጥንታዊ አሰላለፉ ሲቀመጥ “ጂም” የሚባለው ሶስተኛ ፊደል በጥንቱ የፊንቂ ገበታ ላይ ከነበረው “ጊመል” የተገኘ መሆኑን ያዙልኝ፡፡ የኛው የሳባ ፊደል ገበታ በ“አቡጊዳ” ተራው ሲቀመጥ “ጊ” ከጥንቱ “ጊመል” የተገኘ መሆኑን እወቁልኝ፡፡ የእብራይስጡ “ጊመል”ም እንደዚያው፡፡ የግሪካዊያኑ “ጋማ”ም እንደዚያው፡፡ የእንግሊዝኛው (የ“ሮማ”ው) “ጂ”ም እንደዚያው…. ወዘተ….፡፡ እነዚህ ፊደላት ሁሉ አጠራራቸው ቢለያይም የፊንቃዊያኑን “ጊመል” መነሻ በማድረግ የተቀረጹ ናቸው፡፡ “ጊመል” ደግሞ የኛው “ግመል” ነው፡፡ ተአምረኛው እንስሳ!!
*****
አላህ በቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡፡
“ወደ ግመል አይመለከቱምን? እንዴት እንደተፈጠረች”
(አል-ጋሺያህ-17)
ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ያለው ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ›ወ) እስልምናን ማስተማር ሲጀምሩ “ፈጣሪ የለም” ብለው በማስተባበል በተቃውሞ ለተነሱባቸው ሰዎች ነው፡፡ እነዚያ ሰዎች በንዳዱ ከታወቀው የዐረቢያ በረሃ ነው የተገኙት፡፡ በዚያ በረሃ ከምንም በላይ ዋጋ ያለው እንስሳ ግመል ነው፡፡ ግመሉ በአስቸጋሪው በረሃ እየኖረ በሚሰጠው አገልግሎት የሰዎች ኑሮ የተቃና እንዲሆን አድርጓል፡፡ እናም የቅዱስ ቁርኣን መልዕክት “እነዚያ ‘ፈጣሪን አናውቅም’ ባዮች የዚህን ድንቅዬ እንስሳ ባህሪ በማየት ብቻ የፈጣሪ መኖር በተከሰተላቸው ነበር” የሚል ነው፡፡
እውነት ነው!! የበረሃው ሙቀት የቱንም ያህል ቢጨምር ግመሉ የመቋቋም ብቃት አለው፡፡ ግራር በቀል ከሆኑት የአዳማና የሀርዲም ቆላዎች አንስቶ እስከ ሰሜን አፍሪቃው የሰሐራ በረሃ እና የአፋር የዳሎል ስምጥ ቦታ ባሉት ሞቃት የዓለማችን ክልሎች ሁሉ የመኖር ብቃት አለው፡፡ ሌላው ቀርቶ ለርሱ የሚስማማ መኖ ካገኘ በደጋማ አካባቢዎችም (ውርጭ በሌለባቸው ማለቴ ነው) መኖር ይችላል፡፡
በረሃው እንደ እሳት የሚፋጀው ቀን ቀን ነው፡፡ ሌሊት ላይ በተቃራኒው ብርዱ አይቻልም፡፡ ሙቀቱ በጣም ወርዶ “ደብረ ብርሃን ነው ያለሁት እንዴ?” ከሚያሰኝበት ደረጃ ይደርሳል፡፡ ሌሎች እንስሳት ለእንዲህ ዓይነቱ የአየር ለውጥ የተመቹ አይደሉም፡፡ ግመል ግን ሁሉንም ሳይቸገር ይቋቋማል፡፡
ግመል ለምግቡም ቢሆን አይቸገርም፡፡ ዝናብ በተከታታይ ዓመታት ቢጠፋ እንኳ “መኖ ካላመጣህ” በማለት ባለቤቱን አያስጨንቀውም፡፡ ያገኘውን ዛፍና ቁጥቋጦ እየቀነጠበ ህይወቱን ማቆየት ይችልበታል፡፡ ለህይወቱ የሚያሰጋ በሽታም እምብዛም አያጋጥመውም፡፡ እርሱን የሚገድለው ወይ እርጅና ነው፣ ወይ የአንበሳ መንጋ ነው፡፡
አዎን! ግመል የሚበላውንና የሚጠጣውን አጥቶ ሞተ ሲባል ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅ!…! ግመል ከብትና ፍየል አይደለም፡፡ ምንም ነገር ሳይቀምስ ለብዙ ቀናት መቆየት ይችላል፡፡ ውሃ ሳይጠጣም ለሁለት ወር ያህል መቆየት ይችላል፡፡ ውሃ ከአካባቢው ጭራሹኑ ከጠፋ ባለቤቱን ራሱ እየመራው ውሃው ከሚገኝበት ስፍራ ይወስደዋል፡፡ ውሃውን ሲያገኝ ደግሞ አጠጣጡ ለጉድ ነው!! አንድ የፍየል መንጋ የሚያጠግበውን አሊያም አምስት በሬዎች የማይጨርሱትን ውሃ በአንድ ጊዜ ዥው አድርጎ መጠጣት ይችላል፡፡ ሆኖም ኢኮኖሚ የማያውቅ አይምሰላችሁ! ግመል እንዲህ የሚጠጣው በቂ ውሃ ባለበት አካባቢ ነው፡፡ ለምሳሌ የከረዩና የአፋር አርብቶ አደሮች ወደ አዋሽ ወንዝ እየመሩ ሲወስዱት ከወንዙ ውሃ እስኪበቃው ድረስ ይጎነጫል፡፡ ትንሽዬ የውሃ ጉድጓድ (ኤላ) ብቻ ባለበት ጭው ያለ በረሃ ግን ባለቤቶቹ በኦኮሌ እየጨለፉ የሰጡትን ብቻ ይጠጣና ያችኑ አብቃቅቶ ለወር ያህል ይቆያል፡፡
የግመል ዋነኛው ተአምር “ሻኛው” ነው፡፡ እጅግ የደለበ የቅባት ስብስብ!! የሰውነቱ ስብና ሞራ በዚያ ላይ ነው የሚሰባሰበው፡፡ ምግብ ባጣ ጊዜ፣ አሊያም ውሃ በጠፋ ጊዜ በሻኛው ከተጠራቀመው ቅባት እየቆነጠረ እንደምግብ ይጠቀምበታል፡፡ ውሃውንም ከርሱ ያገኛል፡፡ አስቸጋሪ በሆነው የበረሃ ክልል ለመኖር የቻለውም ፈጣሪ “ሻኛ” የሚባለውን ድልብ ስለፈጠረለት ነው፡፡ ከሻኛው ጋር ሻኛውን እያቀለጠ የሚጠቀምበትንም ችሎታ ፈጥሮለታል፡፡ ታዲያ ይህ ችሎታ የተሰጠው ለርሱ ብቻ እንደሆነ ልብ በሉ!! ሻኛ ያላቸው ሌሎች እንስሳት በሙሉ ሻኛቸውን እያቀለጡ እንደ ምግብ ሊጠቀሙበት አይችሉም፡፡ ግመል ብቻ ነው ይህንን ማድረግ የሚችለው፡፡ የፈጣሪ ተአምር!!
(ይቀጥላል)
—-
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 19/2006