ግመል-ጊመል-ገመል-ጀመል (ክፍል ሁለት)
ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
—
ዛሬም በበረሃውና በቆላው ክልል የምናደርገውን የኢትኖግራፊ ጉዞ ቀጥለናል፡፡ የተአምረኛውን እንስሳ አስገራሚ ባህሪዎችና ታሪካዊ ገድሎች የተቻለንን ያህል እንጨዋወታለን፡፡
*****
ግመል ያመነዥካል፡፡ ነገር ግን ከሌሎች አመንዣኪ የቤት እንስሳት በብዙ መልኩ ይለያል፡፡ ለምሳሌ የግመል የእግር መዳፍ እንደሌሎች እንስሳት ለሁለት የተከፈለ ቢሆንም በእግሩ ላይ ሽኮና የለውም፡፡ በሽኮናው ፋንታ ሁለቱ የመዳፉ ክፍሎች ጠንከር ባለ ቆዳ የተሸፈነ ነው፡፡ በመዳፉ ላይ ያለው ቆዳ በጉዞ ወቅት ይዘረጋል፡፡ በመሆኑም በጸሐይ ሙቀት የሚግለው የበረሃ አሸዋ እግሩን እያቃጠለ አያሰቃየውም፡፡ በተጨማሪም ቆዳው የበረሃ አሸዋና ኮረኮንች በመዳፉ ውስጥ እንዳይገባበት ይከላከልለታል፡፡
በግመል ዐይን ላይ ያለው ድርብ ሽፋን በበረሃ ውሽንፍርና ማዕበል የሚበተነው አሸዋ በዐይኖቹ ውስጥ እንዳይገባበት ይከላከላል፡፡ በደረቱ ላይ ያለው ወፍራም ፍርምባ መሰል አካል እና በጉልበቶቹ ላይ ያሉት ጠንካራ የቆዳ ሽፋኖች ግመሉ በሚተኛበት ወቅት አሸዋው እንዳያቃጥለው ይረዱታል፡፡ ታዲያ እንስሳው በብርድ ወራትም በቆፈን እንዳይጠቃ የሚረዳው ጸጉር በተፈጥሮ ተሰጥቶታል፡፡ ብርዱ እየበረታ ሲመጣ ጸጉሩ በጣም ያድጋል፡፡ ብርዱ ካለፈ በኋላ ግን ጸጉሩ ወይ በባለቤቶቹ ይቆረጣል፤ አሊያም በሙቀት ሀይል እየተቀረፈ ይወድቃል፡፡
“እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ” ሲባል ሰምታችኋል አይደለም… አዎን! ግመል ሽንቱን ወደ ኋላ ነው የሚለቀው፡፡ ፋንድያውንም ወደ ኋላ ነው የሚበትነው፡፡ የፋንድያው የእርጥበት ይዘት በጣም አነስተኛ በመሆኑ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ለማገዶነት ማዋል ይቻላል፡፡ የግመል ወተት በማዕድናት እና በብረት ይዘቱ ከሌላው ወተት ይበልጣል፡፡ ቆለኞችና የበረሃ ሰዎች ወተቱን እንደ ምግብም እንደ ውሃም ይጠቀሙበታል፡፡ ስጋው ደግሞ ቅባት የሌለው በመሆኑ ለጤና ተስማሚ ነው፡፡ ከዚህም በላይ እንስሳው ልዩ ልዩ ተክሎችን የሚበላ በመሆኑ ስጋው መድኃኒትነት ያለው መሆኑ ተረጋግጧል (የሀገራችን አርብቶ አደሮች ግመል “ሀሞት” የለውም በማለት ያምናሉ፤ በመሆኑም ስጋው ከበሽታ የጠራ ነው ይላሉ)፡፡
ግመል ሲታረድስ አይታችኋልን!! … ግመሉ ሰታረድ ይንበረከካል እንጂ እንደ ከብትና ፍየል እግሮቹ በገመድ ተጠልፈው መሬት ላይ አይጣሉም፡፡ ግመሉ በእንብርክኩ ከተቀመጠ በኋላ አንገቱ በገመድ ወደ ኋላ ይታሰራል፡፡ ከዚያም ቢላዋው በታችኛው የአንገቱ ክፍል ይገዘገዝበታል፡፡ ታዲያ ግመል በሚታረድበት ወቅት ቢላዋውን እንዲያይ አይደረግም፡፡ እንስሳው ቢላዋ ካየ እንባውን እየዘራ ያለቅሳል ይባላል፡፡ ስለዚህ ቆለኞች ምንም ጊዜም ቢሆን ለግመል ቢላዋ አያሳዩም፡፡
*****
ግመል ከወተትና ከስጋው በላይ በመጓጓዣነቱ በሚሰጠው አገልግሎት ነው የሚታወቀው፡፡ ለብዙ ሺህ ዘመናት በረሃውን እያቆራረጠ ሰዎችን አገልግሏል፡፡ የጥንቱ ሲራራ ነጋዴዎች (Caravan Traders) ንግድን ሊያስፋፉ የቻሉት በግመል ታግዘው ነው፡፡ ይህ እንስሳ በአንድ ጊዜ እስከ አምስት መቶ ኩንታል መሸከም ይችላል፡፡ ዕቃው ተጭኖበት ምንም ዐይነት የድካም ስሜት ሳይታይበት ለብዙ ኪሎሜትሮች ይጓዛል (ግመል በአንድ ቀን እስከ 160 ኪሎሜትር ያህል መጓዝ ይችላል)፡፡
ታዲያ ግመል እንደ ሌሎች እንስሳት በቁሙ አይደለም ሸክሙን የሚሸከመው፡፡ ሰውም ሆነ ዕቃ ሲጫንበት በርከክ ብሎ መሬት ላይ ይቀመጣል፡፡ ዕቃው ከተጫነበት በኋላ ያለ ምንም ችግር ተነስቶ ይቆማል፡፡ ግመል በጉዞውም ይለያል፡፡ እቃ ተጭኖበትም ሆነ ባዶውን ሲጓዝ በአንድ ጎን ያሉትን እግሮቹን አንድ ላይ ያነሳል፡፡ በመሆኑም የበረሃውን ጉዞ በቀላሉ ይወጣዋል፡፡ ለግመል በአሸዋ ውስጥ መጓዝ በውሃ ውስጥ የመዋኘትን ያህል ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ሌሎች እንስሳት በጉዞ ወቅት በአንድ በኩል ያለውን የፊት እግርና በሌላው በኩል ያለውን የኋላ እግር ነው አንድ ላይ የሚያነሱት)፡፡ ግመል ከሁሉም በላይ የሚታወቅበት ባህሪው በገመድ አንድ ላይ ተቀጣጥሎ ለመጓዝ መቻሉ ነው፡፡ እስከ ሀምሳ የሚሆኑ ግመሎችን አንዱን በአንዱ ጭራ ላይ በገመድ አስሮ እንደ ኮንቮይ ማግተልተል ይቻላል፡፡
ግመል በአንዳንድ ቆላማ ስፍራዎች ከዚህም የተለየ አገልግሎትም ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ የሀገራችን ትልቁ በረሃ በሆነው የኦጋዴን ክልል የሚኖሩ የሶማሊ ቆለኛ ወገኖቻችን ግመሉን እንደ በሬ ያጠምዱትና እርሻቸውን ያርሱበታል፡፡ በትግራይ፣ በሱዳን እና በኤርትራ የሚኖሩ ቆለኞች ደግሞ በግመል እየተጠቀሙ ዘይት ይጨምቁበታል፡፡ እንዲሁም ግመሉን የወፍጮ ድንጋይ እንዲዘውር ያደርጉታል፡፡በሰሃራ እና በሌሎች በረሃዎች ደግሞ በረኸኞቹ በግመል ሀይል እየተጠቀሙ ከጥልቅ ጉድጓዶች ውሃ ይቀዳሉ፡፡
ግመል በሚዳራበት ሁኔታም ከሌሎች እንስሳት ይለያል፡፡ ኮርማውና ሴቷ ግመል ግንኙነት በሚፈጽሙት ወቅት ወደ ኋላ ዞረው ይተኛሉ፡፡ ሩካቤውን ለመፈጸም ግን የሰዎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ታዲያ በሀገራችን አርብቶ አደሮች ባህል መሰረት ግመሎች ሩካቤ በሚፈጽሙበት ወቅት በስፍራው የሚገኙት ሴቶች እንጂ ወንዶች አይደሉም፡፡ ግመሎቹን ወንድ ልጆች ካዩዋቸው በጣም ይቆጣሉ ይባላል፡፡
ግመል ከሰዎች ጋር በበጎ ሁኔታ እንደሚኖረው ሁሉ በመቆጣትና ቂም በመቋጠርም አንደኛ ነው፡፡ በተቆጣ ጊዜ ሰዎችን በጥርሱ ነካክሶ ሊገድል ይችላል፡፡ በእግሮቹም ደፍጥጦ አደጋ ያደርሳል፡፡ በጣም አደገኛ እርምጃው ደግሞ በፍርምባው የሚያስከትለው ጉዳት ነው፡፡ በተለይ ቂም የያዘበትን ሰው አዘናግቶ ይጥለውና በፍርምባው ተኝቶበት ይገድለዋል ሲባል ሰምቻለው፡፡ አንድ ሰው ግመሉ ከሚያደርሰው አደጋ ለመዳን ለፈለገ ልዩ ልዩ ዘዴዎችን መጠቀም አለበት፡፡ ለምሳሌ ሰውዬው ግመሉ መቆጣቱን ሲያይ የቁልቁለት አቅጣጫ ይፈልግና ለትንሽ ጊዜ ይሸሸዋል፡፡ ግመሉ ሰውዬውን በእልህ ማባረር ሲጀምር ሰውዬው ወደ ግራው ወይንም ወደ ቀኝ እጥፍ ብሎ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ ግመሉ ራሱን መቆጣጠር ስለማይችል ወደ ጎን ሳይታጠፍ የቁልቁለት ሩጫውን ያስነካዋል፡፡ በዚህ ዘዴም ሰውዬው ከአደጋው ተረፈ ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ግመል የተቆጣው ሰው ሸሚዙን አውልቆ ከፊቱ ቢጥልለት አደጋውን ሊቀለብስ ይችላል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ “ግመሉ ሰውዬውን ያገኘ መስሎት ሸሚዙን ባለ በሌላ ኃይሉ ይረጋግጠውና ንዴቱን በርሱ ላይ ይወጣል”-ይላሉ የቆላ ሰዎች፡፡
*****
ግመል ለብዙ ዘመናት ከሰዎች ጋር ከመኖሩ የተነሳ በስነ-ቃል ውስጥ በሰፊው ይጠቀሳል፡፡ ግመልን በመመርኮዝ የተፈጠሩ ብዙ ተረቶች፣ ምሳሌዎችና አፈታሪኮች አሉ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እየሱስ ክርስቶስ “ሃብታም መንግሥተ ሰማያትን ከሚወርስ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል” ማለቱ ተጠቅሷል፡፡ በቅዱስ ቁርአን ውስጥም “እነዚያ በአላህ አንቀጾች ያስተባበሉት ግመል በመርፌ ቀደዳ እስኪያልፍ ድረስ ገነትን አይገቧትም” የሚል “አያት” (አንቀጽ) አለ፡፡ ነቢያትና ሌሎች ታላላቅ ሰዎች በግመል ተጓጉዘዋል፡፡ አንዳንድ ዝነኛ ሰዎች ደግሞ ስማቸው ከግመል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለምሳሌ የነብዩ ሙሐመድ ባልደረባና የመጀመሪያው ኸሊፋ የሆኑት አቡበከር ትክክለኛ ስማቸው “አቢ ቁሃፋ” ነበር፡፡ “አቡ በከር” የሚለው ስም የተሰጣቸው “በከር” የምትባል ተወዳጅ ሴት ግመል ስለነበረቻቸው ነው፡፡
ግመል በፈሊጣዊ ንግግሮች ውስጥም ተደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡ ከነርሱም ውስጥ “እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ” የሚለው በጣም ታዋቂ ነው፡፡ ከተረትና ምሳሌዎች “ውሾቹ ይጮኻሉ፤ ግመሉ ግን ጉዞውን ይቀጥላል” የሚለው በጣም ዝነኛ ነው፡፡ “ግመሎች ያልፋሉ፤ ተራሮች ግን ለዘልዓለም ይኖራሉ” በሚል ርዕስ የሚጀምር የአርመን አጭር ልብወለድ በአማርኛ ተተርጉሞ በጣም ተወዳጅ ሆኖ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡
ግመልን በመንተራሰስ የሚነገሩ ቂሳዎችን (ጥኡም ትረካዎችን) እንጥቀስ ካልን ደግሞ አንድ ገጽ ቀርቶ ሙሉ መጽሐፍ አይበቃንም፡፡ ለማሳረጊያ እንዲሆነን ግን ከዐረቢያ የተገኘውን ይህንን ውብ ትረካ ላጋራችሁ፡፡
*****
ሶስት ልጆች የነበሩት አንድ የዐረቢያ ሰው ነበር። ይህ ሰው በህይወቱ መጨረሻ አካባቢ ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አላቸው።
“ልጆቼ ሆይ! በዚህ ምድር ላይ ስኖር የተገነዘብኩት ትልቁ ነገር የዕውቀት አስፈላጊነት ነው። ያለ ዕውቀት የሚሄድ ሰው በጭለማ እንደሚጓዝ በቅሎ ይደናበራል። ንግግሩም ሆነ ስራው አያምርለትም። ስለዚህ አዋቂና ታዋቂ እንድትሆኑልኝ እሻለሁ። ነገር ግን መምህራችሁን በጥንቃቄ መምረጥ አለባችሁ። ለዚህም ይረዳችሁ ዘንድ እነኝህን 17 ግመሎች ትቼላችኋለሁ። ታዲያ ግመሎቹን የምትከፋፈሉት በሚከተለው ቀመር መሰረት ይሁን።
“ልጆቼ ሆይ! በዚህ ምድር ላይ ስኖር የተገነዘብኩት ትልቁ ነገር የዕውቀት አስፈላጊነት ነው። ያለ ዕውቀት የሚሄድ ሰው በጭለማ እንደሚጓዝ በቅሎ ይደናበራል። ንግግሩም ሆነ ስራው አያምርለትም። ስለዚህ አዋቂና ታዋቂ እንድትሆኑልኝ እሻለሁ። ነገር ግን መምህራችሁን በጥንቃቄ መምረጥ አለባችሁ። ለዚህም ይረዳችሁ ዘንድ እነኝህን 17 ግመሎች ትቼላችኋለሁ። ታዲያ ግመሎቹን የምትከፋፈሉት በሚከተለው ቀመር መሰረት ይሁን።
• የመጀመሪያው ልጄ የግመሎቹን 1/2ኛ ይውሰድ።
• ሁለተኛው ልጄ 1/3ኛ ያህሉን ይውሰድ።
• ሶስተኛው ልጄ 1/9ኛ ያህሉን ይውሰድ።
ይህንን ስሌት በትክክል መፍታት የቻለውን ሰው እስከ መጨረሻው ድረስ መምህራችሁ አድርጋችሁ ያዙት።”
አባታቸው ይህንን ተናዝዞ አረፈ። ልጆቹም አባታቸውን ከቀበሩ በኋላ ግመሎቻቸውን እየነዱ የተነገራቸውን ዓይነት መምህር መፈለግ ጀመሩ። በየከተማው ወዳሉ አዋቂዎች እየቀረቡ ከአባታቸው በተሰጣቸው ስሌት መሰረት ግመሎቻቸውን እንዲያካፍሉአቸው ጠየቁ። ነገር ግን አንድም ሰው ስሌቱን መፍታት አልቻለም። ሌሎች በርካታ አዋቂዎችንም አማከሩ። ይሁንና ሒሳቡን አውቃለሁ የሚል ሰው ጠፋ።
አባታቸው ይህንን ተናዝዞ አረፈ። ልጆቹም አባታቸውን ከቀበሩ በኋላ ግመሎቻቸውን እየነዱ የተነገራቸውን ዓይነት መምህር መፈለግ ጀመሩ። በየከተማው ወዳሉ አዋቂዎች እየቀረቡ ከአባታቸው በተሰጣቸው ስሌት መሰረት ግመሎቻቸውን እንዲያካፍሉአቸው ጠየቁ። ነገር ግን አንድም ሰው ስሌቱን መፍታት አልቻለም። ሌሎች በርካታ አዋቂዎችንም አማከሩ። ይሁንና ሒሳቡን አውቃለሁ የሚል ሰው ጠፋ።
በመጨረሻም አንደኛው ልጅ “ለምን ጥያቄውን ለኸሊፋ ዓሊ ቢን አቡ ጣሊብ አናቀርበውም? ኸሊፋው ከቻሉ ስሌቱን ለራሳቸው ይፈቱታል። ካልቻሉም አንድ መላ ይመቱልናል” የሚል ሀሳብ አቀረበ። ሌሎቹ ልጆችም በወንድማቸው ሃሳብ ተስማሙ። በዚሁ መሰረት ግመሎቻቸውን እየነዱ ወደ ዓሊ አቢ ጣሊብ (ረ.ዐ.) ዘንድ ሄዱና ጥያቄውን አቀረቡ። ዓሊ ኢብን አቡጣሊብ በነገሩ ትንሽ ካሰቡ በኋላ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጧቸው።
“አስራ ሰባቱን ግመሎች በአባታችሁ ቀመር መሰረት ባከፋፍላችሁ ውጤቱ በክፍልፋይ (fraction) የሚገለጽ ይሆናል። እንደዚያ ከሆነ ግመሎቹን መቆራረጥ ሊኖርብኝ ነው ማለት ነው። ስለዚህ እንዲያ እንዳይሆን የራሴን አንድ ግመል ልጨምርበትና የግመሎቹ ብዛት 18 ይሁን። ይህ ከሆነ ዘንዳ የአባታችሁ ቀመር የሚቀጥለውን ውጤት ያስገኛል።
· ታላቁ ልጅ ከጠቅላላው 1/2ኛ ያግኝ በተባለው መሰረት ዘጠኝ ግመሎች ይደርሱታል::
· ሁለተኛው ልጅ 1/3ኛ ያግኝ በተባለው መሰረት ስድስት ግመሎች ይደርሱታል::
· ሶስተኛው ልጅ 1/9ኛ ያግኝ በተባለው መሰረት ሁለት ግመሎች ይደርሱታል።
· ሶስታችሁ ያገኛችኋቸውን ግመሎች በአንድ ላይ ስንደምር (9+6+2) ውጤቱ አስራ ሰባት ይሆናል።
· ከአስራ ስምንቱ አንድ ግመል ብቻ ይቀራል አይደል? እርሱ ደግሞ የራሴ በመሆኑ ወደኔ ይመለሳል።”
ብልሁ ዓሊ ቢን አቢ ጣሊብ ሒሳቡን በዚህ አስገራሚ መንገድ ፈታው። ልጆቹም “አባታችን የጠቆመን መምህር ይህ ነው” በማለት እስከመጨረሻው ድረስ ተማሪዎቹ ሆነው ዘለቁ።
***** ***** *****
አፈንዲ ሙተቂ
***** ***** *****
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 24/2006