በቅርቡ የታሰሩት የአንድነት አባላት ሺሻይ አዘናው እና አንጋው ተገኝ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመበት ተረጋገጠ!
በመቀሌ ዞን የአንድነት አመራር አባል የነበረው ወጣት ሺሻይ አዘናው ጥቅምት 22 በደህንነት ኃይሎች ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ በመቀሌ በሚገኝ አንድ እስር ቤት ኮማንደር ሰዓረ በሚባል የፖሊስ አዛዥና እርሱ በሚመራቸው ፖሊሶች ከፍተኛ የሆነ ድብደባ ተፈፅሞበታል። ከዚያ በኋላ የት እንዳለ ሳይታወቅ ተሰውሮ ቢቆይም፤ በአሁኑ ሰዓት ማዕከላዊ እየተባለ በሚጠራው የማሰቃያ እስር ቤት እንደሚገኝና በዚህም ቦታ በተከታታይ ለአራት ቀናት ሌሊት ሌለት እጅግ ዘግናኘ የሆነ ድብደባ እንደተፈፅሞበት ጠበቃው አቶ ገበዮህ ይርዳው በአካል ታሳሪውን አግኝተው አረጋግጠዋል። ሺሻይ አዘናው በሞላ ሰውነቱ ላይ ህመም እንደሚሰማው ከመግለፁም ባሻገር በጆሮው፤ በእግሩ፣ ልቡና ጎኑ አከባቢ ከፍተኛ የሆነ የመቁሰል ሁኔታ በግልፅ እንደሚታይ አቶ ገበዮህ ገልፀዋል። በሁሉም የግርፊያ ወቅቶች ለደምህት (TPDM) ሚስጥር ታቀብላለህ፤ ሰው እየመለመልክ ትልካለህ ወዘተ ስለዚህ ጉዳይ የምታውቀውን ንገረን የሚል እንደሆነ ጨምሮ ገልፀዋል።
ጠበቃው አቶ ገበዮህ በዓይን ያዩት ነገር ከጠበቁትና ከገመቱት በላይ ስለሆነባቸው፤ ወደ ወንጀል ምርመራ ሀላፊው ኮማንደር ተክላይ ሄደው ያዩትን ሁሉ በዝርዝር አሳውቃል።
እንደዚሁም ከጎንደር ተይዞ የታሰረው አንጋው ተገኝ ጎንደር ውስጥ ወደ አልታወቀ ስውር ቦታ ወስደው የደህንነት ሰዎችና የአማራ ክልል ፖሊሶች ለቀናት ምግብ ከልክለው ሲደበድቡት እንደነበር ለጠበቃው ለአቶ ገበዮህ አስረድቷል።
