ስለ ታቦተ ጽዮን ያለው ታሪክና እውነታው ምንድን ነው?! በዲ/ን ተረፈ ወርቁ
ከሰሞኑን በአንዳንድ ድረ ገጾችና በሶሻል ሚዲያው የታቦተ ጽዮን መሰረቅ/መጥፋት አሳዛኝ ዜናን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን መሪ የሆኑት በፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በይፋ መግለጻቸውን እየተቀባበሉ ሲያስነብቡን ሰንብተዋል፡፡ የሶሻል ሚዲያው ተከታታይ በኾኑት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ዘንድም ይህ ዜና ምናልባትም መርዶ ብሎ መግለጹ የተሻለ ሣይሆን አይቀርም ለጊዜውም ቢሆን ብዙዎችን ያደናገጠና ያስቆጨ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
የዜናውን እውነተኝነት ለማረጋገጥም በጣት ለሚቆጠሩ ጥቂት ቀናትም ቢሆን ከኢትዮጵያ እስከ አፍሪካ፣ ከአውሮጳ እስከ አሜሪካ፣ አውስትራሊያና ካናዳ ያሉ ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳቸው አሳብ ሲለዋወጡ፣ እንዴት ሊሆን ይችላል በሚል ኀዘናቸውን ቁጭታቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡ የዚህ ጥንታዊ፣ ታላቅና ዕፁብ መንፈሳዊ ሀብት/ቅርስ ጠባቂ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ብቻ ናት ብለው የሚያምኑ ጥቂት የውጭ አገር ሰዎችም ደግሞ ይህን ነጭ ውሸት ዜና ከማስተባበል አንስቶ ይህ በጭራሽ እውነት ሊሆን እንደማይችል እስከ መግለጽ የደረሱበትን አጋጣሚ ከማኅበረሰብ ድረ ገጾች አንብበናል፡፡
ስለ መጥፋቷ ወይም ስለመሰረቋ የተነገረላት ታቦተ ጽዮን ዜና ውሸትነቱ ከተረጋገጠ በኋላ ብዙዎች ተመስገን በሚል ደስታቸውን ሲገልጹ፤ ይሄ መቼም ሊሆን እንደማይችል የሚያምኑና የሚያውቁ አንዳንዶች ደግሞ የዜናውን ሐሰተኝነት ከማስተባባልም በላይ ታቦተ ጽዮን ዘላለማዊ በሆነ በመለኮታዊ ጥበቃ ሥር ያለች በመሆኗ ትጠፋለች ወይም ትሰረቃለች የሚለው ነገር መቼም የማይታሰብ የቀን ቅዠት እንደሆነ በመጻፍና አስተያየት በመስጠት ሌሎችን በማረጋጋት አሰባቸውን ሲያካፍሉ ነበር፡፡
የሆነስ ሆነና ስለ መጥፋቷ ወይም ስለ መሰረቋ የተነገረላት ታቦተ ጽዮንን ወይም የቃል ኪዳኑን ታቦት በተመለከተ ያሉት ታሪካዊ እውነታዎች ምንድን ናቸው? እነዚህ በታሪክና በትውፊት ለዘመናት ስለ ታቦተ ጽዮን ሲነገሩ የነበሩ የቆዩ መላምቶችና እውነታዎች አንድምታቸውስ ምንድን ነው? ምንስ መልክና እይታ ይኖራቸዋል? የክርስቲያኑ ዓለምስ ስለዚህ የከበረ ንዋይ ቅዱስ የሚሰጠው ምላሽም ሆነ መላምቶች ፋይዳቸው ምንድን ነው? በሚል በሚል አጭር ቅኝት ለማድረግ ወደድኹ፡፡
ባለፉት ጥቂት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ የአርኪዮሎጂ ባለሙያዎችና የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንቶች ዘንድ የእስራኤላውያኑን ቃል ኪዳን ታቦት በተመለከተ ትልቅ ጥያቄ ተፈጥሯል፡፡ በእርግጥስ ኢትዮጵያውን እንደሚሉት ታቦቱ በእጃቸው አሊያም በአክሱም ጽዮን ቤ/ን ይገኛልን? ከሆነስ እንዴት ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ ቻለ? አመጣጡስ እንዴት ነበር? ጉዞውንስ ወደ ኢትዮጵያ ያደረገው መቼ ነበር? የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን መንፈሳዊ አባቶች ይህን የክርስቲያኑ ዓለም ኹሉ በጉጉት ለማየት የሚሻውን ቃል ኪዳኑን ታቦት በይፋ እንዳይታይ ለምን ይከለክላሉ… ወዘተ የሚሉት ከብዙ በጥቂቱ የሚነሡ ጥያቄዎችና እንቆቅልሾች ናቸው፡፡
በያዝነው ክፍለ ዘመን ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ ለሚነሡ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት ሙከራ ካደረጉ ውጭ አገር ተጓዦችና ምሁራን መካከል እንግሊዛዊው ጋዜጠኛና ጸሐፊ ግራሃም ሃንኩክ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ይህ ሰው የክርስቲያኑ ዓለም ስለ ታቦተ ጽዮን የሚያነሷቸውን ጥያቄዎችና እንቆቅልሾች ምላሽ ለመስጠት ሲል ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ በሚገኙ ታላላቅ ገዳማትና አድባራት፣ ታሪካዊና መንፈሳዊ ቦታዎች ተዘዋውሯል፡፡ በርካታ ጥናቶችንና ምርምሮችንም አድርጓል፡፡
ሃንኩክ በግብፅ፣ በእስራኤል፣ እንግሊዝ፣ በፈረንሳይ አገራት በመጓዝ ስለ ታቦተ ጽዮን ያገኛቸውን አፈ ታሪኮች፣ ትውፊቶችና መረጃዎች በማጠናቀር በክብረ ነገሥት ውስጥ ከሚገኘው ከኢትዮጵያውያን ታሪክ በመነሳት በእርግጥ የእስራኤል የቃል ኪዳኑ ታቦት በንግሥት ሳባ ዘመን በልጇ በቀዳማዊ ምኒልክ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ እንደነበር ለመመርመር ከፍተኛ የሆነ ጥረት አድርጓል፡፡
ግራሃም ሃንኩክ ይህን ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ ለበርካታ ዓመት ያደረገውን ጉዞውን፣ የምርምርና የጥናት ውጤቱንም እ.ኤ.አ በ1992 ‹‹The Sign and the Seal›› በሚል አሳትሞ ለንባብ አብቅቶት ነበር፡፡ ይህ መጽሐፍ በታተመበት ወቅት ከፍተኛ ተነባቢነት ያተረፈና በመጽሐፍ ሽያጭም ረገድም በጊዜው የአንደኛ ደረጃን ጣራ ይዞ የነበረ መጽሐፍ እንደነበር በወቅቱ የወጡት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ይህ የግራሃም ሃንኩክ መጽሐፍ ታትሞ በገበያ ላይ ከዋለም ወዲህም የቃል ኪዳኑን ታቦት ትክክለኛ አድራሻ በማፈላለግ ረገድ ትኩረቱ እጅግ እየጠነከረ መጥቷል፡፡ ከዚህ መጽሐፍ ህትመት በኋላም በእንግሊዝ አገር ሮደሪክ ግሪሰንና ስቱአርት ሞኑሮ የተባሉ ምሁራን በጋራ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ‹‹The Ark of the Covenant›› የቃል ኪዳኑ ታቦት በሚል ርእስ ዳጎስ ያለ መጽሐፍን አሳትመዋል፡፡
ይህ መጽሐፍ በታተመበት ሰሞንም ሄነሪ ሉዊስ ጌትስ (ጁኒየር) የተባሉ አፍሪካ አሜሪካዊ የሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰርን መሠረት በማድረግ የእንግሊዙ የቢቢሲ ቴሌቪዥን ጣቢያ ታቦተ ጽዮንን አስመልክቶ አንድ ልዩ ዝግጅትም አቅርቦ ነበር፡፡ እኚሁ ምሁር ከለንደኑ የቢቢሲ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታቸው የኢትዮጵያ ቤ/ን ታቦተ ጽዮንን አስመልክታ የምተርከውንና ጠብቃ ያቆየችውን ታሪክና ትውፊት በተመለከተ በሰጡት ምሁራዊ ትንታኔያቸውና አስተያየታቸውም፡-
‹‹ለዓለም ሕዝቦች ግዙፍ ታሪክና ገናና ሥልጣኔ አፍሪካ በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያና ‹‹የዓባይ ስጦታ›› የሆነችው ግብጽ የነበራቸውን ጉልህ ድርሻ በማንሳት፣ ኢትዮጵውያን ስለ ታቦተ ጽዮን ባለቤትነት ጠባቂነት የሚተርኩት ታሪክ ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ መሠረት፣ ትውፊትና ባህል ያለው በመሆኑ እንዲሁ ለማጣጣል እንደማይቻልና ሰፊና ጥልቅ የሆነ ጥናት እንደሚያስፈልገው፡፡›› ነበር የገለጹት፡፡
በሌላ በኩል የቅርብ መረጃ ደግሞ እንደሚያመለክተው ባለፈው ሰሞንም እስራኤልን ለመጎብኘት የመጡ የውጭ አገር ቱሪስቶች በልዩ ጥንቃቄ ጥንታዊ ታሪኩንና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ያሠሩትን የቃል ኪዳኑን ታቦት አምሳያ በጥንቱ ኢየሩሳሌም መቅደስ አንጻር ፍራሽ ፊት ለፊት ማቆማቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በአግራሞትና ሲዘገቡት እንደነበር ይታወሳል፡፡ የክርስትናው ዓለም ምሁራንም ይህ የኢየሩሳሌም ሦስተኛው መቅደስ መሠራትና የሐሰተኛው ክርስቶስ መገለጽ ትንቢታዊ ቃል ፍጻሜውን ሊያገኝ መቃረቡን የሚያመላክት ነው በማለት ነበር ይህን ክስተት በአግራሞት የገለጹት፡፡
በተመሳሳይም እ.ኤ.አ በ1981 በNews Week መጽሔት ላይ ራባይ ጎረን የተባሉ የአይሁድ መምህርና የታሪክ ሊቅም፣ ‹‹የቃል ኪዳን ታቦቱ ምስጢራዊ ስፍራ ሦስተኛው ቤተ መቅደስ ከመሠራቱ በፊት ይገለጻል፡፡›› ሲሉ መናገራቸውን ጽፏል፡፡ በኢትዮጵያ ቤ/ን ባለቤትነት፣ አደራና ጥበቃ ስር እንደምትገኝ ስለሚነግራላት የታቦተ ጽዮን ጉዳይ በጥንታ ታሪክ አጥኚዎችና ቅርስ ፈላጊዎች ዘንድ አሁንም ድረስ ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ በኢትዮጵያ ቤ/ን መጽሐፍ በሆነው በጥንታዊውና በታሪካዊው በክብረ ነገሥት መጽሐፍ ውስጥ በሰፊው የሚተረከውን ታሪክና የዚህ ትውፊት እውነታነት ለማረጋገጥ ብዙዎች የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ እናም ፍለጋው አሁንም ቀጥሏል ማለት ይቻላል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊትም ፕ/ር ግራንት ጄፈሪ የተሰኙ ካናዳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር፣ የታሪክ ተመራማሪና እንዲሁም ስለ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓትና የዓለም መጨረሻን በተመለከተ ባደረጓቸው በርካታ ጥናታቸው የሚታወቁ እኚህ ዕውቅ ምሁር፣ ‹‹Armageddon:- Appointment of Destiny›› በተሰኘው መጽሐፋቸውና እንደዚሁም ‹‹The Ark of the Covenant and the Red Heifer›› በሚል ባስቀረጹት ትምህርታዊ ቪዲዮቸው የቃል ኪዳኑ ታቦት ስለሚገኝበት ስፍራና ወደፊት ስለሚኖረው መለኮታዊ ሚና ሰፊ የሆነ ታሪካዊ ትንታኔና አስተያየታቸውን በሰፊው አቅርበዋል፡፡
ፕሮፌሰር ጄፌሪ በኢትዮጵያ ቤ/ን ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ በክብረ ነገሥት የተጻፈውን ወይም የሚተረከውን ታሪክ በዚህ መልኩ ነበር ያቀረቡት፡-
ወጣቱ ምኒልክ አባቱን ጎብኝቶና በእስራኤል የነበረውን ቆይታውን አጠናቆ ሊመለስ ሳለ አባቱ ንጉሥ ሰለሞን ልጁ ምኒልክ ከእናቱ አገር ከኢትዮጵያ እየመጣ በአይሁዳውያኑ ቤተ መቅደስ ውስጥ ለማምለክ ስለሚቸግረውና መንገዱም ሩቅ ስለሆነ ለአምልኮተ ሥርዓት ይዞት የሚሄደውን ታቦት ቅጂ ወይም ተመሳሳይ አሠርቶለት ነበር፤ ይሁን እንጂ ምኒልክ የአባቱን ከእግዚአብሔር መንገድ፣ ሕግና ሥርዓት መራቅ ስለተመለከተና ልቡም በአሕዝባውያን ሴቶችና ጣዖቶቻቸው ፍቅር በመነደፉ እጅጉን አዝኖ ትክክለኛውን ታቦት ከአይሁዳውያኑ ቤተ መቅደስ ሰርቆ ወደ አክሱም ይዞ እንደመጣ ያብራራሉ፡፡
ይህ የፕ/ር ጄፈሪ ትረካ ከክብረ ነገሥቱ ትረካ ብዙም ልዩነት ያለው አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ክብረ ነገሥቱ ስለ ታቦተ ጽዮን የሚተርከውን ትረካ በጥንቃቄ በመርመር እውነታውን ለማረጋገጥ የሚተጉ ብዙዎች እንዳሉ ሁሉ በአንጻሩም ደግሞ ይህን የክብረ ነገሥቱን ትረካ በጥርጣሬ ዓይን ከማየት ጀምሮ ጠቅላላ ታሪኩን የፈጠራ ድርሰት፣ አሊያም ይህ ሊታመን የማይችል ተረት ተረት ነው በሚል ሙሉ በሙሉ ውድቅ የሚያደርጉ ሰዎችና ሃይማኖት ምሁራንም ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አገር አልጠፉም፡፡
በተለይም ደግሞ ምዕራቡ ዓለም ክርስቲያኖች ምሁራን ለዚህ ክርክራቸው በአብዛኛው የሚያቀርቡት መረጃ ከታሪካዊ ፋይዳነቱ ይልቅ በይበልጥ በመንፈሳዊው ወይም በሐዲስ ኪዳን ዶክትሪን ወይም አስተምህሮ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ጽሑፍ ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ ወይም ደግሞ በአጠቃላይ ስለ ታቦት በክርስትናው ዓለም በተለይም ደግሞ በምዕራቡ የክርስቲያን ዓለም ያለውን ዶክትሪን/አስተምህሮ በማንሳት ወደዛ ሃይማኖታዊ ክርክር ለመግባት የጋዜጣው ገጽም ሆነ በዚህ ጽሑፌ ለማንሣት የወደድኩት ዐቢይ ርእስ ጉዳይም በእጅጉ ይወስነኛል፡፡
ስለሆነም በቀጣይ በታላቅ ድምቀትና መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት በሚከበርበት የአክሱም ጽዮን ክብረ በዓል ዋዜማ በቀጣይ ቅዳሜ ጽሑፌ ታቦተ ጽዮንን በተመለከተ ያላነሳኋቸውን ሌሎች ጥንታዊ የሆኑ ታሪካዊ ድርሳናትን፣ የታሪክና የሃይማኖት ምሁራን ምስክሮችንና ወቅታዊ መረጃዎችን በማካተት፣ በመፈተሽና በመመርመር ለመመለስ ቃል በመግባት ልሰናበት፡፡
ሰናይ ሰንበት!