በማሸማቀቅ እና ጥላሸት በመቀባት ለነፃነት ከሚደረገው ትግል ማስቀረት አይቻልም!! ከዳንኤል ፈይሳ

የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ ንግግር ተከትሎ የቆርጦ ቀጥል የፍረጃ ፖለቲካ አራማጆች እና ከሩቅ ሆኖ ድጋይ ለማቀበል የሚፈልጉ ኃይሎች ቁንፅል ነገር ይዘው በየአቅጣጫው በዱምዱም ጥፍራቸው አንድነት ፓርቲንም ደምረው መቧጠጥ ጀምረዋል ፡፡ ሆኖም አቶ ግርማ አሉ የተባሉትንና የመለሱትን ምላሽ እንዲሁም ከተቃወሟቸው ሰዎች መሃል ጥቂቱን ሰምቼአለሁ አንብቤያለሁ ፡፡ አልገባንም ምን ለማለት ተፈልጎ ነው ይብራራልን ማለት የአባት ሆኖ ሳለ በልዋሉበት ቤት ውስጥ የግድ ማግኘት አለብን ብሎ መፈለግ ትርፉ ብክነት ነው ፡፡ ምክንያቱም ማናችንም ብንሆን ልንጋፈጠው በማንችለውና በማንፈቅደው በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ብቸኛ የተቃዋሚ አባል ሆነው የሚያሳልፉትን የመከራ ዘመን ሳስብ ሲያሳዝኑኝ አሉና፡፡በተለይም ብቸኝነቱ ሳይበግራቸው በሚያቀርቧቸው ወሳኝ ጥያቄዎችና ክርክሮች የህዝብን ድምጽ ለማሰማት ያደረጉትን ጥረት ሳስብ አድናቆቴ ከፍተኛ ነውና ፡፡ በ10 ክፍለ ከተማ በዟዟር በራሳቸው ወጪ ብቻቸውን የፓርላማ አባልነታቸውን ተጠቅመው የህዝብን ብሶት ይዞ በመቅረብ ከደንቆሮ ካድሬ ተብዬ ኃላፊዎች ጋር የሚያደርጉት ከፍተኛ እሰጣ ገባ ለህዝብ ያላቸውን ተቆርቋሪነት ያረጋገጠ ነው ይሄም ተነግሮ እንዲዘመርላቸው ያልጠየቁ ነፃ ነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ የገባቸው ታላቅ ልንኮራባቸው የሚገባ ዜጋችን ናቸው ፡፡ በአንድነት ም/ፕሬዝደንትነት ዘመናቸው የሚሊየኖች ድምጽ ለነፃነትን ከመሩት ዋነኛዎቹ አንዱ መሆናቸው ደግሞ ተስፋ የሚጣልባቸው ታጋይ መሆናቸውን ይመሰክርልኛል፡፡

አሁን የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ የሚወቅሱ ሰዎች እና ለመፈረጅ አሞራ ያልቀደማቸው ኃይሎች ራሳቸውን ዞር ብለው ቢመለከቱ የሳቸውን ያህል ቀርቶ ርቡንስ ያህል ምን ሰሩ ከዚህ በፊት የነበረውን ልምድ የቀየሩት እሳቸው ናቸው ፡በየአምስት አመቱ እየመጡ ምረጡን የሚሉንን እንጂ ከመረጥናቸው በኃላ በቴሌቪዥን ብቻ አይተናቸው ተመልሰው ምርጫ ሲመጣ ምረጡን ሲሉ ነው ምናቀው እሳቸው በተመረጡበት የምርጫ ክልል ቢሮ ከፍተው ለረዥም ጊዜ የህብረተሰቡን ጥያቄዎች እና ችግሮች ያዳምጡና በተወከሉበት ፓርላማ ያቀርቡ እንደነበር አውቃለሁ አከራያቸው ልቀቁልኝ ብሎ እስካስለቀቃቸው ድረስ ይህን ሁሉ ያደርጉ የነበረው ማንም አካል በመደበላቸው በጀት አይደለም ከራሳቸው ኪስ አውጥተው ነው ፡፡

የተከበሩ አቶ ግርማ ይህን መሰል ንግግር እናን በተረጎማችሁበት መልኩ ከአንደበታቸው እንደማይወጣ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በትጥቅ ትግል ሥልጣን ለመያዝ የሚደረገውን ትግል ሁሉ በሽብርተኝነት ካባ ለመጠቅለል የሚጥረውን ኢሃዴግን በዚያው በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ይህ አዋጅ ሲፀድቅ እና ሶስቱ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች በሽብርተኝነት ሲፈረጁ ከተቃወሙ ኢትዮጵያውያን ብቸኛው አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ እንደሆኑ ማንም የማያጣው ጉዳይ ነው!….ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ነው ነገሩ፡፡ከዚያ አለፍ ሲል ደግሞ ኢንስትራክተሮቹ ባይነግሩንም አብዮቱ በሪሞት ኮንትሮል የሚያፈነዱት ይመስል የሰላማዊ ትግል አንዱ መንገድ የሆነውን በምርጫ ተወዳድረን ለማሸነፍ እንችላለን እና እንወዳደራለን ማለት ለምን እንዳንጫጫቸው አይገባንም የአብዮቱ ሪሞቱ እዚያ ማዶ አደል ይጫኑትና ይፈንዳኣ!?
በዚህ አንፃር አቶ ግርማ በአንድ ወቅት ሲናገሩ ‹‹አንዷለምን ሽብርተኛ ነህ ብሎ ከእነ ዶ/ር ብርሃኑ ጋር ትገናኛለህ ብሎ ከመጠርጠር እኔን መጠርጠር ይሻላል›› እንዳሉት ሁሉ (በ‹‹ያልተሄደበት መንገድ›› ምርቃት ዕለት) ፤በቅጡ መሪዎቹን የሚያውቋቸውን ሰዎች ሽብርተኛ ናቸው እንደማይሉ መጠራጠር አልነበረብንም፡፡ከነበረብንም እንዲሰናከሉበት የቀረበላቸውን ጥያቄ ማብራሪያ አግባብ የሆነ እድል መንፈግ ባልተገባ እና ያልተፈለገ ስዕል ባልተፈጠረ ፡፡ ደግነቱ ለዚህ ወርጂብኝ ለበዛበት ጣጣቸው የሰጡት ምላሽ አጭር ብሎም ግልጽ ነበር፡፡‹‹ወደ ትግሉ የገባሁት ነብሴን አስይዤ ነው፡፡››ነበር ያሉት-በግል ብሎጋቸው፡፡

የኢትዮጵያ አብዮት ሾተላይ ለካ እንደጽንስ ሁሉ ከወራት ቀደም ብሎ ነው ኡደቱን የሚጀምረው፡፡‹‹አብዮት ልጆቿን ትበላለች››ሲባልም ከበኩሩ መጀመሯን ልናይ ይሆን?ስለዚህ ወደ ኋላ መለስ ብለን ከአቶ ግርማ ጋር በተያያዘ ልንፈትሻቸው የሚገቡ ሁነቶች አሉ ፡፡ እንጂ ዛሬ ይህን አለ ብሎ አጠጋግቶ መፈረጁ አያዋጣም ፡፡ ኢሳትም ቢሆን ጉዳዩን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የማስተባበል እድሉን እንዲጠቀሙ መጎትጎት አለበት እንላለን ፡፡

‹‹አንቺን ክፉ አይንካሽ !›› ያለው ክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ ለካስ ይህን መሰል ደባ በሀገር ጉዳይ ላይ ሲገጥም ነው፡፡ይህ ለማንም አይበጅም!! ለህወሃት በእርግጥ እድሜ ማራዘሚያ ይሆነዋል፡፡ግን ለእሱም ቢሆን አይበጅም! ኢሃዴግን አትጥሉ ጥላቻ ባለቤቱን ራሱን ነው የሚጎዳው ሲል የነበረው የተቃዋሚ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በስተመጨረሻ ወደ ሁለገብ ትግል የገባው ለዚህ ይሆን!? በሰላማዊ ታጋይነታቸው የምንጮህላቸው እነ እስክንድርና አንዷለም ሙጥኝ ሰላማዊ ትግል ሲሉ አልሰማ ያላቸው ዲያስፖራ፤ ሲታሰሩለት፣‹‹ እልል በቅምጤ!›› ያለው ውስጡን ‹እንኳን ታሰሩ› እያለ ‹ትንቢቴ ሰመረ› እያለ ነው ማለት ነው?

በቅድሚያ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንን ጨምሮ ከፍተኛ ትችት የጣሉበትን የባህር ማዶ ትግል ወደ ሃገር ውስጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጥቂት ውጤታማነት እየታየበት ያለው ግና ገና ተጨባጭነት ያላሳየውን የውጪ ሃገር ተቀምጦ ትግል በቅጡ መመርመር ይኖርብናል፡፡ በእርግጠኝነት ለመናገር ምቹ ሁኔታዎች ቢኖሩ ለኢሳት ብቻ ከውጪው ዶላር በላይ ከሃገር ውስጥ የሚላከው ድርሻ በብዙ ዕጥፍ በበለጠ ነበር፡፡አሁንም ይመስለኛል፡፡ ሚዲያው ይሁን ውጪ ይቀመጥ! ሰው እንዴት ከጠላቱ ርቆ ድል ሊያደርግ ይችላል?ይህ መመለስ ያለበት ወሳኝ ጥያቄ ነው-ባስቸኳይ!
ደግሞስ በግሉ ለመስዋዕትነት የቆረጠ ሰው ከባህር ማዶ ሆኖ በስድብና በገንዘብ እርዳታ ብቻ ድልን ይመኛል፡፡ይህም ውጤቱ በሃገር ውስጡ ታጋይ ቁርጠኝነት የሚለካ ነውና እንዴት የራሱ ትግል አድርጎስ ሊያስበው ይችላል፡፡አንዳንዴ እዚህ ሆንን ስንታዘብ ውጪ ተወጥቶ ከሚሰራው የሚለፈለፈው ሲበዛ ለህወሃት ዱላ እንደማቀበል ያለ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ብትገነዘቡልን መልካም ይመስለኛል፡፡በእርግጥ በተፈለገው መስዋዕትነት ልክ፤ነፃነታችን እንዲገኝ እንደምትመኙ እናውቃለን! ይልቅ ኑና የድርሻችሁን ክፈሉ ያኔ በእርግጠኝት እናንተን ከማሰር እና ከመግደል ይልቅ ወንበሩን በጸጋ ቢሰት እንደሚመርጥ ብልጡን ወያኔን ታውቁታላችሁ! አንዳርጌማ ጀግና ነው! ከህዝቡ ጋር የመጨረሻ የሚባለውን ጽዋ እየተጎነጨ ያለ የቁርጥ ቀን መሪ ነው፡፡የዚህን ትንግርተኛ ሰው ጉዳይ አታንሱ እሱ ካንገት በላይ በሆነ ጩኸት ብቻ አይመለስምና፡፡

ከዚህ አነጋጋሪ ጉዳይ በስተጀርባ የድል ስምምነታችንን መፍረስ እንደዲያቢሎስ ቆሞ የሚጠብቅ እርኩስ ጭራቅና ከይሲ አንባገነን ገዢ እንዳለብን ታውቃላችሁ! ስለዚህ አፈሙዛችሁን ወይም ምላሳችሁን ወዲያ ብታዞሩት ይበጃችኋል! እናንተን እንደ ሙሴ ሲጠብቅ ኖረው ህዝባችን ከመከራው ውስጥ የራሱን ጀግኖች እየፈጠረ ነው፡፡ጀግኖቻችንም በፓርቲ ቢለያዩ ቃሊቲ አንድ አርጓቸዋል! የሙስሊሙ የፍትህ ጥያቄ የክርስቲያኑም ነው! የአንድነት አመራሮች ጥያቄ የሰማያዊም ነው! የኦብኮ ጥያቄ የሲአንም ነው!

ከዚያ በተረፈ የፖለቲካ ትግል ሁሉ መጋፈጥ የበዛበት ነው ብላችሁ አትስበኩን! ታላላቅ ወንድሞቻችንን ያጣንበትን ዘመንና ውጤት አልባ ስልቱን መቼም ቢሆን አንዘነጋውም! ለሃገራችን ባለን መልካም ምኞትም ሞታችን ስቃይዋን የሚቀንስ እንጂ የሚያበዛ እንዲሆን አንመኝም! የእያንዳንዱ ምስኪን ወጣት ህይወት ከኤሊቱ እኩል ያሳምምናል! ለእውነተኛ ዲሞክራሲና ነፃነት ከሁሉም ጠላቶቿ ጋር ሊጋፈጥ ብሎም ወድቆ ባለራዕይ ሕዝብ ለመፍጠር ህይወታችንን ቆጥረን እናስረክባችኋለን! በእኛ ዘመን ለወያኔ ባንዳነት ካልሆነ በቀር የሚያጓጓ አንዳችም ነገር እንደሌለብን ልንምልላችሁ እንችላለን! የስደቱን ምክነትና መሰለብማ አያድርስብን ባይ ነን! ደግሞ የእኛ ትውልድን ያህል የስደትን ገፈት ቀማሽ ኬየት ሊመጣ!
በትውልዳችን የእድሜ ዘመን ዲሞክራሲ ሊሰፍን ግዱ ነው አብረን ለመቋደስ ያብቃን!

ሰላማዊ ትግል በምን ዘዴ ውጤታማ እንደሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ እኛ ግን እየሞትን በሂደት እናመጣዋለን! ገዢ መሬታችን ሰላማዊ ትግላችን ነው! ይልቅ ታላቅ ታሪካዊ ድርሻ እንዲኖራችሁ ስደቱን ትታችሁ ተቀላቀሉን እዚህም ያደፈጣችሁ ኑ ራሳችሁን ግለጡና አብረን እንታገል! ለጨቋኞቻችን ዕድሜ ማራዘሚያ ከመሆን ይሰውረን ዘንድ ድል በትግል ነውና ኑ አብረን ኢትዮጵያን ትንሣኤ እናቅርብ! እኛ እየሞትን ለትውልድ መኖሪያ እናብጅ!

በጄ የማትሉ ከሆነ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይሻላታል እንደተባለው ባለፈረንካ እንዳትሆኑ እመክራችኋለሁ! ስለ ትውልዱ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት የሚጠብቅባችሁን ማስተላለፍ ብቻውን ዋጋ አለውና ታሪኳንና ገድሏን እንኳን አስተላልፉ፡፡ተውጣችሁ አታስውጧቸው! ሄይ አንተም ትውልድ ንቃ ! እዚህ በጎጥ ስያሜ ሰይሞ ከሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊለይህ ቢያልምም ፤ አርቆ ማንነቷን እስክትጠይቀው ድረስ ህያውነቷን ቢደብቅህም ! ምንጭህን መርምር! የዛሬው ማንነትህ ዋቢ የትላንቱ አሻራህ መሆኑን ስትደርስበት ሞግታቸው! ብትችል ኢትዮጵያን በስሜትህ በአካልህ በንፍስህ ውስጥ ቀርፀህ እደግ! ይህ እንዳይሆን ከፈረዱብህ መሞገትህን እንዳትተው! ሁሉም በአያቱ ንጉስ ነው ያለው ማን ነበር ባካችሁ? ባያት በቅድም አያቴ ንጉስ ነኝ በላቸው!
ወፍጮ ጉድ አለች እማማ ! ይሄ ሁሉ በዚያ ጥቁር ሰውዬ ነው የተጀመረው፡፡በሉ የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልንማ፡፡ቸር እንሰንብት፡፡

ማስገንዘቢያ
አንድነት ፓርቲ ከሁሉም የሃገሪቱ ፓርቲዎች በላይ ዋና ዋና የፓርቲው አመራሮች የታሰሩበትና የተገረፉበት በህገወጥ አያያዝ በእስር የማቀቁበት የቆሰለ ፓርቲ መሆኑን እንድትረዱልን እንሻለን፡፡ ዛሬም ቢሆን ፓርቲው ምርጫ እገባለሁ ስላለ የተቀየረ ነገር የለም፡፡በየክፍለሃገሩ ያሉ አደራጆችና አባላቱ እየታደኑ መሆኑን ስንገልጽ ለኢትዮጵያችን ዲሞክራሲያዊነት ሁሉም የፓርቲው ንቁ ተሳታፊ አባላት ለትውልድ የሚተርፍ ከእስርም በላይ የህይወት መስዋዕትነት ጭምር ለመክፈል የተዘጋጀን መሆኑን አበክረን እንገልፃለን፡፡

ነፃነት ከፍርሃት አይገኝም!
ድል የሕዝብ ነው!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!10500542_583639695069823_897748827157633310_nUDJ-SEAL