ሕዝቡ የሚደግፈው እንጂ ከውጭ ሆኖ የሚያዘው አይፈልግም – ግርማ ካሳ ( ለግንቦት ሰባቶች)
ግንቦት ሰባት የተሰኘው ፣ መሰረቱን አስመራ ያደረገው ድርጅት፣ በአገር ቤት ላሉ ተማሪዎች፣ መምህራን ጥሪ አቅርቧል። «የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የትምህርት ኃላፊዎችና ፕሬዚዳንቶች ሆይ! ለገዛ ራሳችሁ ክብር፣ ለአካዳሚ ነፃነት፣ ለትውልድ ስትሉ በዚህ መመሪያ ላይ አምጹ! “እንቢ፣ አሻፈረን፣ በዚህ መመሪያ አንገዛም” በሉ! የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናችሁ ይቆማል» ሲል ነው፣ ግንቦት ሰባት ጥሪ ያስተላለፈው።
ይህ የግንቦት ስባት መግለጫ ምን ያህል በኢትዮጵያ ያሉ ምሁራን እና ተማሪዎች ሊያነቡት እንደሚችሉ አላውቅም። ብዙ እንደማይሆን ግን አስባለሁ። ያነበቡትን ቦታ ይሰጡታል ብዬ አላስብም።
ግንቦት ሰባት አንድ ጊዜ መለዮ ለባሹን፣ አንድ ጊዜ ሌላው ቡድን፣ አሁን ደግሞ አስተማሪዎችን እና ተማሪዎችን ለአመጽ እንዲነሱ ጥሪ ሲያቀርብ፣ ጥሪዉን ተግባራዊ ለማድረግ ሕዝቡ ጋር በመሄድ ትልቅ ድርጅታዊ ሥራ አስቀድሞ መሰራት እንዳለበት ሳያውቅ የሚቀር አይመስለኝም። «ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ» እንደሚባለው ፣ ሕዝቡ ሳይደራጅ፣ ከዉጭ ሆኖ በሪሞት ኮንትሮል፣ መግለጫዎችና ጥሪዎች በማቅረብ፣ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ማምጣት እንደማይቻል ያጡታል ብዬ አላስብም።
መሰረታዊ ጥያቄዎቹ እንግዲህ ፣ «ግንቦት ሰባቶች፣ ጠዋትና ማታ ሕዝብ የሚያውቀዉን፣ የገዢውን ፓርቲ ሐጢያት እየደጋገሙ ከመተረክ፣ በየራዲዮኑና ቴሌቭዥኑ እየቀረቡ አስተያየቶችን ከመስጠት፣ በየስብሰባው ፖዲየሙን በእጆቻቸው ከመደብደብ፣ ለምን ሕዝቡን በማደረጀት ላይ ትኩረት አይሰጡም ? ለምን ሕዝቡን በአገር ቤት እያደራጁ ላሉ ኃይላት ሶሊዳሪቲ አያሳዩም ? ለምንስ ለትግሉ ቁልፍ የሆነ ሥራ ከሚሰሩ፣ ህዝቡን እያደራጁ ካሉ ድርጅቶች ጋር አብረው እንዳይሰሩ እንቅፋት ከሆነባቸው ከሻቢያ ጋር ያላቸውን ትሥሥር አያቋርጡም ? ለምን አመኔታቸው በሻእቢያ ላይ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሕዝብ ጉልበትና አቅም ላይ አያደርጉም ? » የሚሉት ናቸው።
አገር ቤት ያለው ወገናችን፣ ከዉጭ ሆኖ ፣ ሌክቸርና መመሪያ የሚሰጠው ቡድን አይደለም አሁን የሚፈለገው። አገር ቤት ያለው ወገናች ተደራጅቶ በአንድነት፣ በሰማያዊ፣ አረና ..ስም እየተንቀሳቀሰ ነው። አገር ቤት ያሉትን ድርጅቶች መደገፍ ማለት ሕዝቡን መደገፍ ማለት ነው። ግንቦት ሰባቶች፣ ሕዝቡ ለመብቱና ለነጻነቱ እንዲነሳ ፍላጎት ካላቸው፣ ህዝቡ እያደረገ ያለውን ትእግስት አስጨራሽ ሰላማዊዉን ትግሉን ሊደገፉ ይገባል። ግንቦት ሰባቶች እያራመዱት ያለውን የተሳሳተና ወጤት አልባ መንገድ ትተው፣ ለግንቦት ሰባትም ሆነ ለትግሉም ፣ ለአገርም የሚበጀዉን መንገድ ቢከተሉ ጥሩ ይሆናል እላለሁ።
ይሄን ቢያደርጉ በዉጭ ካሉ እንደ ሽግግር ምክር ቤቱ፣ ሸንጎ ካሉ ደርጅቶች ጋር ህብረት ሊፈጠሩ ይችላሉ። በጋራና በተቀናጀ መልኩ አገር ቤት ያለውን ወሳኝ ትግል በማድረግ፣ በተቀናጀና በሰለጠነ መልኩ ዳያስፖራዉን በማሰባሰብ ዉጤት ያለው ሥራ መስራት ይቻላል።
«አይ የሰላም ትግል አይሰራም። ወያኔን በጦር አፍንጫዉን ብለን እንጥለዋለን። ሻእቢያ ኢትዮጵያን ያድናል» የሚሉን ከሆነ እንግዲህ ያሉትን በሥራ ያሳዩን። እጆቻቸዉንና እግሮቻቸዉን አልያዝናቸውም። በአገር ቤት የሚደረገው ትልቅ ላይ አስተያየተ ከመስጠት ቢቆጠቡ፣ ያላደራጁትን እና እንዲደራጅ ቅንጣት ድጋፍ ያልሰጡትን ሕዝብ ፣ የማይተማመኑበትብ ህዝብ አስመራ ሆነው መመሪያ ባይሰጡት ጥሩ ነው እላለሁ። አገር ቤት ያሉ ደርጅቶች በሚያደርጉት ሥራ ጣልቃ ገበተው ፣ በሞኖፖል በሚቆጣጠሩት ሜዲያዎች፣ «ምርጫ ግቡ፣ አትግቡ ወዘተረፈ እያሉ ባያወሩና ባያስወሩ መልካም ነው። ያንን የማድረግ የሞራል ብቃትም ያላቸው አይመስለኝም።