በርቱ ብለዋልና እንበርታ!!! ግርማ ሰይፉ ማሩ
ዛሬ ከስዓት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀብታሙ አያሌውን ቂሊንጦ ወደሚገኘው ወህኒ ቤት ሄጄ ለማየት ከባለቤቱ ቤቲ ጋር ቂሊንጡ ተገኝቼ ነበር፡፡ እግረ መንገዴንም ባለፈው ተመስገን ደሳለኝን ለመጠየቅ ሄጄ የጠፋብኝን ስዓት ካገኘሁት የሚል ተሰፋ ነበር፡፡ የሰዓቱ ነገር … ውሃ የበላው መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ አርድቻችሁ ልለፍ ብዬ ነው፡፡ ነገሩ ትልቅ ጉዳይ ሆኖ ሳይሆን የተረሳ ንብረትም ሆነ በፖሊስ እጅ ድንገት የገባ ዕቃ የት ይሄዳል? የሚለው ነገር አሳሰቦኝ ነው፡፡ ለማነኛውም ወደፊት መጠንቀቅ ብቻ ነው ለጊዜው ያለው አማራጭ፡፡
ዛሬ ከጠበቅሁት በላይ ብዙ ወዳጆች አግኝቻለሁ፡፡ የሺዋስ አሰፋን ሳገኘው በጣም ነው የተደሰትኩት ባለፈው አንድነት ሰላማዊ ስልፍ ጠርቶ በመኪና ለቅስቀሳ ስወጣ ፖሊሶች አስቁመውኝ ለምን ትይዙታላችሁ? ብሎ ስለጠየቃቸው ሁከት በመፍጠር ብለው በጣቢያ ታስሮ የነበረ ሲሆን አንድ ሴት ዳኛ ፍቱት ብላ በነፃ አሰናብታው ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ አንድ ቀን ብቻ ስለነበር የተገናኘነው ዛሬ ጥሩ ጊዜ አግኝተን የሆድ የሆዳችንን አውርተናል፡፡ የአዲስ ጉዳዩ ጋዜጠኛ አስማማው ከመታሰሩ በፊት ኢንተርቪው አድርጎኝ ነበር፡፡ ዛሬ ስንገናኝ ግን ከጋዜጠኝነት አውድ ወጥቶ ፖለቲከኛ የሆነ ይመስላል፣ የጋዜጠኝነቱ ነገር ስለ አልተወው ብሎ ጥያቄ መጠየቅ ያበዛ ነበር፡፡ በጣም ጠንካራ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ዛሬ የተገናኘነው እንደ በፊቱ የተከበሩ አቶ ግርማ በሚልበት አውድ ላይ አልነበርንም፡፡ ሸቁጥቁጥ ይል የነበረው አስማማው አሁን ቆርጠን ብሎ አይቼዋለሁ፡፡ ጦማሪው ናትናኤል ጋር ሰለ ወጣቶች የወላጆች ኃላፊነትና እጅግ ብዙ ወጣት ተኮር ጉደዮች ተጨዋውተናል፤ ናትናኤል ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘሁት ሀምሌ 3 ቀን በልደቴ ዕለት መፅሃፍ ሳስመርቅ በውሃ ልማት አዳራሽ ነበር፡፡ ከፕሮግራሙ በኋላ ጠብቆ ብቻዬን ሲሞግተኝ ነበር ከረዥም ቁመቱ ጋር አንጋጥጪ ብዙ አውግተናል፡፡ ዛሬ ግን በውህኒ ቤት አጥር ሽቦ ስር ጎንበስ ብሎ ብዙ ተጫወተን፡፡ የዚህ ዓይነት ብሩህ ወጣቶችን ውህኒ ማጎር ማንን እንደሚጠቅም ማሰብ ይቸግራል፡፡ ጫጥ እየቃመ አርሴና-ማንቼ እያለ ካፍቴሪያ ቢዞር ማንም አያየውም ነበር፡፡ የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል ሲል ግን ርዝመቱ ታያቸቸው፡፡ በሰላምታ እና በመጫባበጥ ብዙ የህሊና እስረኞችን ለመጎብኘት በመቻሌ፣ የዛሬ ቀን የተባረከ ነው ብዬ ወስጄዋለሁ፡፡ የሙስሊም ታሳሪዎችን ጥንካሬ ልነግችሁ ከምችለው በላይ ነው፡፡
በአጠቃላይ እነዚህ የህሊና እስረኞች ያሉበት ጥንካሬ ደረጃ “ዞን ዘጠኝ” ለምንገኝ እስረኞች ብርታት የሚሰጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በርቱ የሚሉት እነርሱ ናቸው፡፡ ወህኒ ቤት ስንሄድ ለማበረታት የሚመስለን ካለን ተሳሰተናል፡፡ የትግል ባትሪ የደከመበት ሄዶ ቻርጅ መደርግ ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ በርቱ ብለዋልና እንበርታ!!! የእነርሱ ብርታት እና የሞራል የበላይነት መንፈስን ያድሳል፡፡
በመጨረሻም ምስጋና ለካህሳይ፣ ዛሬ ካህሳይ ያለምንም ማጉላላት ቅድሚያ ሰጥቶኝ አስገብቶኛል፡፡ ስለዚህ በተመደበበት ቦታ ላይ ላደረገው ትብብር ምስጋናዬ ይድረሰው፡፡ ስዓቴ ባይገኝም ይፈለግልኝ ዘንድ መመሪያ ሰጥቶዋል፡፡ የጠፋ ነገር ተፈልጎ ስለማይገኝ ጠፍቶዋል፡፡ በቅርቡ ከሌላ ሰዓት ጋር እንደምንገናኝ ተሰፋ አደርጋለሁ፡፡
ቸር ይግጠመን