የበረከትና የልደቱ ግንኙኝት
ተፈረደኝ አለሙ
ይቺ የፈረደባት ሃገር ይሄ የፈረደበት ሕዝብ ዘወትር በስሙ እንደተለመነ፤ በስሙ እንደተማለ፤ በስሙ እንደተገደለ በስሙ እንደ ተነገደ አለ ወደፊትም እንዲህ አይነት ሰዎች እስካሉ በዚሁ የሚቀጥል ነው፡፡
ውህደት ሲሏቸው ውህደቱን ወደ ክህደትነት ለመለወጥ በር ቢዘጋባቸው በስርቆሽ በር የሚገቡ፤ ትብብር ሲሏቸው ትብብሩን ወደ ድንብርብርነት ለመቀየር ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ በየወቅቱ ስማቸውንና ካባቸውን በመቀየር፤ ሎሌዎች ቀጥረው፤ አንጋቾች አሰልፈው የሚጓዙ ነበሩ፤ አሉ ወደፊትም በሌላ ልውጥ ካባ መኖራቸውን ለማረጋገጥ ድንጋይ ይፈነቅላሉ፡፡
በሃገራችን ባለው የቅርብ ሊባል በሚችለው ፖለቲካ ውስጥ በተቃዋሚነት ተሰልፈው አጀማመራቸው አሳማኝ ተልእኳቸው ግን ሚስጥራዊ ሆነው በተቃዋሚነት በሕዝብ ውስጥ ቦታ ይዘው ግን ተግባራቸው የሕዝብን ነጻነት አስረግጦ ለገዢ ለማስረከብ የታጠቁ ሕዝብ አውቆም የተፋቸውና አይንህ ላፈር ያላቸው አሁንም ሌላ፤ አስራ ስንተኛ መሆኑ ነው ካባ ለውጠው፤ አድራሻ ቀይረው ጅብ በማይታወቅበት ሃገር ሄዶ ቆዳ አንጥፉልኝ ያለው አይነት ሆነው ሸር ጉድ፤ አርቲ ቡርቲ ጀምረዋል፡፡
ሃገርና ሕዝብ እንባውን አፍሶ ረግሟቸዋልና እርግማን ተሸክመው የጥፋት መልዕክተኝነታቸውን እያከናወኑ ነው፡፡ ለተቃዋሚዎች መንገዱ ተዘግቷል፤ ምርጫው አስቀድሞ አልቋልና በጭራሽ አትግቡበት ሲባል አሻፈረኝ ብለው፤ በቀድሞ ወዳጆቻቸው ተማምነው፤ተስፋ ሰንቀው ወደ ምርጫው ገብተው ፎሪ ሲወጡ ለመሸነፋቸው ሰበብ ፈጥረው ሃገር ጥለው ወጡ፡፡ ምነው ቀደም ብለው በሆነ አወጣጣቸው ትንሽም ቢሆን ድጋፍ ያገኙ፤ ለማታለልም እድል ያገኙ ነበር፡፡ነገሩ ሌላ ነው ምርጫም እንዳያሸንፉ የተደረገው፡፡ በምርጫው መሸነፋቸው የጥላቻ አይደለም አስቀድሞ የተደረሰበት ስምምነት ነው፡፡ አቶ በረከት ያቀዱት ደባ ለአቶ መለስ ቀርቦ በሚገባ ታስቦበትና ተጠንቶ የተከናወነ ጉዳይ ለመሆኑ አሁንም ማስረጃው አካሄዳቸው ነው፡፡ በቅድሚያ እንዲህ አይነት ሰዎች ለተልእኮ ሲላኩ እቅድ ወጥቶ ተነድፎ ተጠንቶ ተመክሮበት ነው፡፡
አሁን ወደ ዋናው ጉዳይ ልገባ ነው፡፡ መነሻዬ ከመሰረቱ ነው፡፡ መሰረት ስል ደሞ የተቃዋሚው ጎራ አይሎ ከወጣ በኋላ እስከተገነጣጠለበት ለማለት ነው፡፡ ግን ለመነሻ እንዲሆን ጥቂት ወደኋላ መለስ ብሎም መጠቋቆም አስፈላጊ ይሆናል፡፡
ገና ወያኔ ኢህአዴግ ወደ ንግሥናው እንደመጣ የመጀመርያውን የበትን-አፍርስ ስራውን የጀመረው ልደቱ የማንኛውም ድርጅት አባል ሳይሆን በሸዋ ሆቴል ከቤተሰቡ አባላት ጋር በመሆን በተክራዬው ክፍል ውስጥ የንግድ ትርኢት አዘጋጅ በሚል መጠርያ ቢሮ ከፍቶ ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ እንግዲህ ተቃዋሚ የሚባል ፓርቲ ገና ያልተበራከተ በመሆኑና የፕሮፌሰር አስራት መአሐድ ብቻ ለአማራው ውክልና የቆመ ሆኖ በመንቀሳቀስ ላይ ስለነበርና አካሄዱ ተቀባይነትን እያገኘና ወያኔን የሚያስፈራው ተቀናቃኝ መሆኑ በይፋ ስለታወቀ በነ በረከት ስምኦንና በነአባይ ጸሃዬ መመርያ መሰረት የተጣለውን እቅድ ተግባራዊ እንዲያደርግ የተሰየመ ሆነ፡፡ በሆቴሉ ውስጥ ወንደሙንና ሌሎች የቤተሰብ አባላትን በማሰባሰብ አብረውት እንዴት ወደ መአሐድ እንደሚገቡና እቅዱን እንደሚተገብሩት የራሳቸውን ስልት ማውጠንጠን ያዙ፡፡ ለዚህም ዓላማቸው መሳካት ሌላ ድጋፍና መንገድ ጠራጊ በር ከፋች ስለአስፈለጋቸው በአካባቢ የትውልድ ሰፈር ቀረቤታ ያለው ሰው በማስፈለጉ ሻለቃ አድማሴ ወደ ድርጅቱ የመግቢያ ካርዳቸው ሆኖ በሱ አማካኝነትና ድጋፍ የድርጅት አባል ለመሆን ፎርም ሞልተው ወደ መቀላቀል ተጠጉ፡፡
አፍ ያለው ጤፍ ይቆላል ነውና ገና ወደ ድርጅቱ ከመግባቱ ከሁሉም የአመራር አባላት ጋር ቁርኝቱን አሳምሮ በለሰለሰና በተባ አፉ ከማንም በበለጠ ቀድመውት ወደ ድርጅት ከገቡትም በመፍጠን ሁሉንም አሳምኖ ሚስጥረኛ፤ አማካሪ በመሆን ተወዳጅነትን አተረፈ፡፡ አንዳንድ አካሄዱ የፈጠነባቸውና የሚስጥረኘቱ አደገኛነት የገባቸው ከፍተኛ የአመራር አባላትን ለማስጠንቀቅ ቢጥሩም የአመራር አባላቱ የዚህ ግለሰብ እባባዊ አካሄድ ተንኮል ያዘለ ነው ብለው ለመጠርጠር አልቻሉምና ማስጠንቀቂያውን ሁሉ አንሰማም፤ የሚባለውን ሁሉ ቅናት ነው በማለት ተረጎሙት፡፡
ሌው ቀርቶ ከጅምሩ የረዱትን ሻለቃ አድማሴን ሳይቀር በማሸሽና በላያቸው ላይ አጉል ወሬ በማስወራት ከከፍተኛ አመራር አባላት ጋር አራርቆ ተደማጭነታቸውንም አሸሸ፡፡ ሌሎች ጀሌዎችም ስለሱ ብልህነት፤ ከፍተኛ የፖለቲካ ዕውቀት፤ ሚስጥር አዋቂነትና ኢህአዴግ ምን ያህል እንደሚፈራው በሰፊው በማውራት ተቀባይነቱን በይበልጥ አጠናከሩለት፡፡ ይህ ደግሞ ለልደቱ የተውጠነጠነና ከነበረከትና አባይ ጸሃዬ የተሰጠውን አፍራሽ ተልእኮ አስፈጻሚነቱን የሰመረ አደረገለት፡፡ በዚህም በመኢሐድ ውስጥ የነበረውን ሁሉ እንደማይሆን እንደማይሆን አድርጎት በኢት ሬዲዮ በዚያን ወቅት ይሰራ ከነበረው ሳምሶን ከሚባል ጋዜጠኛ ጋር በመመሳጠር (ሳምሶን አሁን የኢትዮ ቻናል ጋዜጣ ባለቤት ነው) ፕሮፌሰር ታዬን ለማሳሰር በቃ፡፡
ወዲያውም የፕሮፌሰርን ቢሮ ቁልፍ አምጡ ብሎ አካኪ ዘራፍ አለ፡፡ ሰብሮ ሊገባና ሚስጥራዊ ዶኩሜንቶችንም ለማግኘት ጥረት አደረገ፡፡ ወዲያውም ከመኢሐድ ወጥቶ የራሱን ድርጅት መሰረትኩ አለ፡፡ መሰረተ፡፡
የመኢሐድ አባላትና በተለይም የወጣት ክፍል የነበሩትን ይዞ ወጣ፡፡ አንድ የማይረሳ ታሪኩ፤ አንድ ቀን ወጣቱን ሰብስቦ ይህን መንግስት ለመጣል በጣም አስፈላጊው ጉዳይ አንድ ሰው መስቀል አደባባይ በቤንዚን እራሱን ያቃጥል የሚል ሃሳብ አምጥቶ ሁሉም ተደናግጠው እንዴት ይሆናል ሲሉት መሆን እንዳለበት አምርሮ ይናገርና አንድ ፈቃደኛ ይጠይቃል፤ ይህን የሚያደርግ ግን ባለማግኘቱ እንግዲያው እኔ ለመቃጠል ዝግጁ ነኝ ይላል፡፡ አባላትም አይሆንም በሚል ልመና ይገባሉ ይህም ወሬ በከተማው ሁሉ ይሰማል በዚህም ቆራጥ አምበሳ ለመባል አቅዶ የሆነ ቢሆንም በሁዋላ ግን ያሰበው ሳይሳካለት ቀርቶ እሱም እኔ ልሰዋ ያለው ለወሬ ያህል መሆኑ ተረጋግጦበት እነሞሐመድ አሊ ጋር (በጣም የቅርብ ጓደኛውና የጥፋት ተልእኮው ዋና አስተባባሪ ነበር) ለመለያየት በቅቷል፡፡
ልደቱ ለጥፋት ሆን ብሎ የተፈጠረ በመሆኑ ሁል ጊዜ ከጥፋትና ከተንኮል ውጪ የሚያሰላው አንድችም ነገር የለም፡፡
ኢዴፓን ብቻውን ለማካሄድ እጅግ ብዙ ችግር እንደሚገጥመው በማወቁ ፕሮፌሰር መስፍንን በአማላጅነት ልኮ ዶ/ር አድማሱንና ዶ/ር ሃይሉ አርአያን በሊቀ መንበርነትና በምክትልነት ከያዘ በኋላ ለስሙ መጠሪያውን ሊቀ መንበር፤ምክትል ሚለውን ይስጣቸው እንጂ በውሳኔና እንዲሁም ድርጅቱን ወክሎ በመንቀሳቀስና በፋይናንስ ማዘዝ በኩል ልደቱ የማይነካ ግድብ አፍርጎት በባዶ ቼክ ላይ እያስፈረማቸው መንቀሳቀሱን ቀጠለ፡፡በተደጋጋሚ አብረውት የነበሩት ከመአሐድ መስሏቸውና አምነውት የተሰደዱት አባላት፤ የኦዲት ሪፖርት ይደረግ፤ ለአባላት የፋይናንስ ሪፖርት ይቅረብ ቢሉም አንድም ጊዜ ተቀባይነት ሳያገኙ እስካሁንም አንድም የኦዲት ምርመራ ሳይደረግ አለ፡፡
ወደ ቅንጅት መፈጠር ስንሄድም ልደቱ ከጅምሩ እንዳይሳካ ሰበብ አስባብ ሲፈጥርና መንገዱን ሁሉ በምክንያት ሊዘጋ ሲሞክር ቆይቶ በመጨረሻውም ለስሙም ቢሆን ሊቀ መንበርና ምክትል ተብለው የተሰየሙት ጉዳዩን ከግንዛቤ በማስገባት እግዱን ወደ ጎን ብለው ስብሰባዎቹን በመሳተፍ ወደ ቅንጅት ለመግባት የሚያስችላቸውና ይሁንታ ከስራ አስፈጻሚውና ከላእላይ መዋቅሩም በማግኘታቸው የልደቱና የዋነኛ ተባባሪው የሞሼ እምቢታ ፈርሶ የቅንጅት አካል ሀሆኑ፡፡በዚህም ጊዜ በቅንጅት አባል ድርጅቶች መሃል ተደርሶ ከነበረው ዋነኛ ውሳኔ አባል ድርጅቶች የኦዲት ምርመራ በማስደረግ የገንዘብና የቁሳቁስ ሪፖርት አቅርበው በአንድ አመራር ሥር እንዲሆን የሚለ፤ው ስለነበር እስከመጨረሸሻው ድረስ የፋይናንስ ሪፖርት ለማቅረብ ያልቻለው ኢዴፓ ነበር፡፡ ሊቀ መንበሩና ምክትላቸውም ተደጋጋሚ መመረርያና የጽሁፍ ትእዛዝም ቢሰጡ ዋና ጸሃፊው ሁሉንም ችላ በማለት ሳይተገበር ቀረ፡፡
ሌላው ቀርቶ ዶ/ር አድማሱ ለተለያየ ጉዳይ የሚሆን ወጪ ለማውጫ ተብሎ በባዶ ቼክ ላይ ስለፈረመበት ሂሳብ እንኳን ዝርዝር ሪፖርት ጠይቆ ሳያገኝ ነው ቅንጅት ሊፈራርስ የበቃው፡፡
ልደቱ በራሱ አንደበት የሕዝብ ግንኙነቱን ሥራ ለመስራት ወቅቱና የስራ ውጥረቱ አላስቻለኝምና ከኮሚቴው ልውጣ በማለት በጠየቀው መሰረት ስምምነት አግኝቶ ለቀቀ፤ በቦታውም የኢዴፓ ምክትል ሊቀ መንበር የነበሩት ዶ/ር ሃይሉ ተመደቡ፡፡ አሁንም ከሰብሳቢነቱ ቢለቅም በፕሮግራም ዝግጅቱ ላይ ግን አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግና ለመተባበር ፈቃደኛነቱን ገልጾ የነበረ ቢሆንም ሲያደርግ የነበረው ግን አዘጋጅቼ ጠዋት ስቱዲዮ ድረስ እመጣለሁ እያለ ሲጠበቅ የተለያየ ሰበብ በመስጠት መቅረትን ቢሆንም ፕሮግራሙን የሚያዘጋጁት ግን ባህሪውን ስለሚያውቁ ቢመጣም ባይመጣም ብለው አዘጋጅተው ይጠብቁትና ቀረሁ ሲል ያዘጋጁትን እያስተላለፉ ቆይተው በኋላ እንዲያውም መጠየቁንም ተዉት፡፡ የዚህ ሰበብ ምን እንደነበረ ሳይታወቅ ቢቆይም በኋላ ግን በኢቲቪ ይሰራ የነበረና ከበረከት ጋር የተቃዋሚ ፓርቲዎችን የቅስቀሳ ዝግጅት ይቆጠጣጠር የነበረ ኋላ ተባሮ ከሃገር የወጣ ውስጥ አዋቂ እነደተናገረው በረከት ለልደቱ ‹‹ከእንግዲህ አንተ አትግባበት በተቻለ እንዲያውም ፕሮግራማቸው የሚደናቀፍበትን መንገድ አፈላልግ›› የሚል ምክር ስለተሰጠው ከኮሚቴ ሰብሳቢነት የመልቀቂያ ጥያቄ ያነሳው ብሏል፡፡ይሀ ደሞ ሲያደርግ ከነበረው ተግባሩ ጋር በጣሙን ይገጣጠማል፡፡
በኋላስ?
ፕሮፌሰር መስፍን እቅጩን እንዳሉት፤
ለቅንጅት መዳከምና መፍረስ በመጀመርያ በሩን የከፈተው ልደቱ ስለሆነ ትንሽ ሰፋ አድርጎ መነጋገሩ ተገቢ ይሆናል፡፡የመጨረሻ የመገንጠያ መሳርያ ያደረገው ያደረገው የኢዴአፓን ማህተም ነው፡፡ዋና ጸሃፊ በመሆኑ ማህተሙ በቁጥጥሩ ነበርና በውህደቱ ሰነድ ላይ እንዳያርፍ አገደ፡፡የሱው ፓርቲ ፕሬዜዳንትና ምክትል ፕሬዜዳንት እንዲሁም ሌሎች የሥራ አስፈጻሚ አባላትን አሸንፎ ተለየ፡፡በስብሰባ ላይ አባላት ሁሉ በቅንጅትና በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ሲለምኑት አሻፈረኝ ብሎ ሄደ፤ከሁሉም በላይ ልደቱ የራሱን የመለየት አቋም ለማጠናከር ሲል ለምርጫ ቦርድና ለወያኔ ኢህአዴግ ቅንጅትን የመምቻ ሃሳቦችን እየደጋገመ በይፋ በጋዜጣ መግለጹ ነው፡፡( ስለዚህ ጉዳይ በሪፖርተርና በሌሎች ጋዜጦችም ላይ የሰጠውን ቃለ ምልልስ መመልከቱ ይበጃል)አቶ ልደቱ አቋሙ የተጠናከረለት እየመሰለው በንዴት ራሱን ከሚያስፈልገው በላይ አጋለጧል፡፡በጦቢያ ጥቅምት 17/1977 እንዲህ ይላል፡፡
‹‹እኔ ማንነቴን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሜ ደጋግሜ በተግባር ለማረጋገጥ ብዙ ዕድል አለኝ፡፡ እኔ እዚህ ፖለቲካ ውስጥ የገባሁት የጡረታ ጊዜየን ለማሳለፍ አይደለም፤ወይም ደግሞ በቀብሬ ላይ የሚነበብ አንድ ታሪክ ለመጨመር አይደለም፤ ራእይ ኖሮኝ ነው እዚህ ትግል ውስጥ የገባሁት፡፡››
አምላክነትን ለማወጅ ምንም ያህል አልቀረውም፤ ወይም እድሜውን በኮንትራት የያዘው ይመስላል፤በዕድሜ የገፉትን ተቀናቃኞቹን ለማዋረድ ሲል ራሱን አንጠለጠለ፤ ዛሬ ልደቱ በእድሜው ላይ 3 ዓመት ያህል ጨምሮ ወደ ሽማግሌዎቹ ጠጋ ብሏል፡፡ልደቱ በዚህ አያቆምም የሚከተለውንም ይጨምርበታል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ አለበት፤ለምንድን ነው ልደቱ ላይ ይህን ያህል ርብርብ የሚበዛው? ሰዎች እንዲህ አይነት ርብርብ እኔ ላይ ሲያዩ በጣም ያዝናሉ የምጨነቅ የምበሳጭ ይመስላቸዋል፡፡ እኔ ግን እውነቱን ልንገራችሁ በጣም እደሰታለሁ አልጨነቅም እኮራለሁ፡፡ ለምንድን ነው የምኮራው የምደሰተው፤ትኩረት የሳብኩ ፖለቲከኛ ባልሆን ኖሮ ይሀ ሁሉ ግምት አይሰጠኝም ነበር፡፡ይህን ሁሉ ርብርብ የሚያደርጉብኝ ትርጉም ያለኝ ፖለቲከኛ ሆኜ ስላዩኝ ነው፤ ባያዩኝ ኖሮ ይሄን አያደርጉም ነበር፡፡››
ቦክሰኛው መሐመድ አሊን ያስታውሷል፡፡! የሚያሳዝነው እንደ ልደቱ ያለ ትሁትና ጨዋ ሰው በስልጣን ምኞት እንዲህ ያለ ሕመም ላይ መውደቁ ነው፡፡ሌሎች ተቀናቃኞች ደፍረው ያልገለጹትን ሕመም ልደቱ መጋረጃውን ሁሉ ቀድዶ ገልጦታል፡፡ በምርጫው ዘመቻ ሰሞን የሕዝብ ጭብጨባና ውዳሴ ላልመደው ሰው እንደ ክፉ መጠጥ የሚያሰክርና ጭንቅላትን የሚያሳብጥ ነበር ማስተዋል ለቻለ ሁሉ፡፡››
ፕሮፌሰር እንዳስቀመጡትና በተግባርም እንደተያው ልደቱ በረቀቀ ተንኮሉና ሰዋራ አካሄዱ በርካታ ኢሃዴግያዊ አስተዋጽኦ ለማድረጉ ጥርጥር የለውም፡፡ ሌላው ቀርቶ ፓርላማ አንግባ የሚለውን ውሳኔ አብሮ ከወሰነና ካስወሰነ በኋላ ቀድሞ ‹‹በድምጽ ብልጫ ተሸነፍኩ›› የሚል ዘገባ ለበረከት ካቀረበ በኋላ በማግስቱ ግን ወደ ፓርላማ ሄዶ እጁን ሰጠ ከእስርም ዳነ፤ እንጂ እንዳለውራ ተደርጓልረ ‹ትርጉም ያለው ፖለቲካኝ›› ሆኖ ቢሆን ኖር በምንም ሳቢያ ከእስር አያመልጥም ነበር፡፡ ያ ብቻም ሳይሆን የታሰሩትን በተመለከተ አንዳችም ቃል አለመተንፈሱና እንዲያውም የእስሩን ትክክለኛነት በመመስከር መቆሙ ሌላው ድክመቱና ሎሌነቱ ነው፡፡
እስቲ አሁን ልደቱ ይጠየቅ፡፡
1. ኢድአፓ ከቋቋመ ጀምሮ ምን ያህል ጊዜ የኦዲት ምርመታ ተካሂዷል
2. ለአባላትስ የፋይናንስ ሪፖርት ቀርቧል ወይ
3. የ2002 ምርጫ ዴሚክራሲያዊና ፍትሃዊ ነበር
4. ካልሆነስ ፓርቲው ለምን ግልጽ መግለጫ አላወጣም
5. የአንድነት መሪ ብርቱካን ሚዴቅሳ በታሰሩበት ወቅት ምን መግለጫ አወጣ
6. በቅንጅት አባላት ላይ የተላለፈው የሞት ፍርድ ትክክል ነው ብሎ ያምናል
እስቲ ለዚህ መልስ ያምጣና እንነጋገርበት፡፡ ጣትን ወደ ሚበልጡትና አምርረው ወያኔን ለመጣል ከተነሱት ጋር መጨበጫ የሌለው ውንጀላና ወሬ ከማውራት ይልቅስ ንስሃ ገብቶ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መታረቅ ነው የሚበጀው፡፡ ልደቱ እኮ እስከዛሬ በወያኔ ቅልቦች ስለተሰዉት ሰማእታት አንድም ቃል ተንፍሶ የማያውቅ ባለ ራዕይ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ነው፡፡ ከዚህ ወዲያ ሌላ ሊሰጠው የሚገባ ምንም የለም፡፡ ያሰበውና ያቀደው ዘውድ መድፋት ባለመሳካቱ እግዚአብሔር ያጥናህ ልበለው፡፡