ምርጫ 2007 ለለዉጥ !!!!! – ግርማ ካሳ

በቅርቡ የሚከተለውን ጽፌ ነበር፡

“አገር ቤት ላሉ ተቃዋሚዎች ደግሞ የሚከተለዉን መልእክት አስተላልፋለሁ። የምርጫ ፓርቲ ናችሁ። ነገር ግን በባዶ እግራችሁ ብስክሌት ከያዘ ጋር እንወዳደራለን ብሎ መነሳት፣ ራሳችሁን ከማስገመት በተጨማሪም ለገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሚያ ብቻ ነው የምትሆኑት። ምርጫ የምትሳተፉ ከሆነ፣ የምርጫ ዘመቻ ማድረግ አለባችሁ። ምርጫው ሰባት ወራት ነው የቀሩት። በሚቀጥለው አንድ ወራት ዉስጥ አገዛዙ ነገሮችን ካላስተካከለ ፣ በምርጫ መወዳደራችሁ ፋይዳ አይኖረውም። እንዴት ብላችሁስ ነው የምርጫ ዘምቻ የምታደርጉት ? መልእክቶቻችሁን እንዴት ነው ለሕዝብ የምታቀርቡት ? ከሕዝብ ጋር በነጻነት ካልተገናኛችሁ፣ ጋዜጣ ካላተማችሁ ፣ ሽብርተኞች እየተባላችሁ ከታሰራችሁ እንዴት ምርጫ ልትሳተፉ ትችላለችሁ ? ምርጫው በአንጻራዊነት ሰላማዊና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ፣ በጋራ፣ ባሉ መስመሮች ሁሉ አገዛዙ ላይ ጫና ማድረግ መጀመር አለባችሁ። ሕወሃት/ኢሕአዴግ ዉስጥ ያሉ ሞደሬቶችን በማሳመን እና በማግባባት፣ ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ በማሳየት፣እነርሱ በፊናቸው በፓርቲያቸው ዉስጥ ለዉጥ እንዲመጣ ግፊት እንዲያደርጉ ማበረታታቱ አስፈላጊ ነው። በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ነገሮች ካልተስተካከሉ፣ የጠራ የአቋም በጋራ በመዉሰድ፣ በምርጫው እንደማትሳተፉም መግለጽ ይኖርባችሁል። ዋጋ ለሌለው ነገር ፣ ምርጫ ፣ ምርጫ እየተባለ ጉልበት፣ ጊዜና ገንዘብ ማጥፋት አያስፈልግም። ሕዝቡ አማራጮች ነጻ በሆነ መንገድ እንዲቀርቡለት ካልተደረገ ፣ ነጻነቱን እና መብቱን የሚያረጋግጥበት የራሱ የሆኑ ሌሎች መንገዶችን ይፈለጋል።”

አንድ አሜሪካን አገር የሚኖር ወዳጄ ሐሳቤን ተቃዉሞ መልስ ሰጠኝ። በስልክ ተነጋገርን። ያነሳኋቸው ነጥቦች በሙሉ ትክክል እንደሆኑ ገለጸልኝ። እንደውም ይህ ወዳጅ ገፍቶም ነው የሄደው። “ወያኔ በጭራሽ የፖለቲካ ምህዳሩን አይከፍትም። እንደውም ማሰሩን፣ ማፈኑን ይቀጥልበታል” አለኝ። በዚህ በአስቸጋሪ ሁኔታም ሕዝቡ ድምጹን እንዲሰጥና፣ ድምጹን እንዲያስከበር ማደራጀቱን መቀጠል እንጂ፣ ከምርጫው መዉጣት የሚያመጣው አንዳች ፋይዳ እንደሌለ በመገልጽ ተከራከረኝ።

“እሺ እንዳልከው፣ ተቃዋሚዎች ከምርጫው ወጡ። ከዚያስ ? ምንድን ነው የሚያደርጉት ? አርፈው፣ ጽ/ቤቶቻቸውን ዘግተው፣ ፓርቲያቸውን አፍርሰው መቀመጥ አይደለም ወይ እጣ ፋንታቸው የሚሆነው ? ከምርጫዉ መዉጣት ሙሉ ለሙሉ ሜዳዉን ለሕወሃት/ኢሕአዴግ መልቀቅ አይደለም ወይ ? “ የሚሉ ጥያቄዎች ጠየቀኝ። መልስ የለኝም።

“ለምን ወደዚህ ድምዳሜ እንደመጣህ ይገባኛል። ግን የተሳሳተ ድምዳሜ ነው። እንደዉም ተቃዋሚዎች ከምርጫው ከወጡ የበለጠ የሚደሰቱት ሕወሃቶች ነው። አሁን እያደረጉት ያሉት ግፎች ሁሉ፣ ተቃዋሚዎች ምርጫዉን ቦይኮት እንዲያደርጉ ለመጫን ነው” ሲል ተቃዋሚዎች በምርጫው መሳተፍ እንዳለባቸው ገለጸልኝ። አሳመነኝ። ሐሳቤን በሐሳብ አሸነፈው። ልቤ አሁንም ቦይኮት ይደረግ ቢልም፣ የሚያስበው አይምሮዬ ግን አይሆንም ይላል። ልብን ሳይሆን አይምሮን ማዳመጡ እንደሚበጅ ተረድሁ። (በነገራችን ላይ አስተያየት ስንሰጥ ሐሳባችንን በሐሳብ የሚያሸነፉ፣ ተቃዉሞ አሰምተው የሚያሳምኑ የሰልጠኑ አስተያየት ሰጭዎች ሲኖሩ ያስደስታል ፤ ዝም ብሎ ፍሬ ከርስኪ ስድብ የሚወረዉሩ ናቸው የሰለቹኝ )

በሚሊዮኖች ንቅናቄ እንደ አንድነት ፓርቲ ያሉ ድርጅቶች ምን ያህል በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ትልቅ እንደሆነ አይተናል። በአገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ ያለው ሁሉ ዜጋ ከነአንድነት ጀርባ ተሰልፎ አቅማቸውን የበለጠ እንዲያጎለብቱ ማድረግ ከተቻለ፣ ህዝቡን በየምርጫ ጣቢያው ድምጹን እንዲያስከበር የሚችልበት ሁኔተ ከተመቻቸና ከተሰራበት፣ ትልቅ ዉጤት ሊገኝ እንደሚችል ተግባባን።

በመሆኑም የአንድነት ፓርቲና ሌሎች አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች ፣ ከወዲሁ በርግጠኝነት በምርጫው እንደሚሳተፉ ይፋ አድርገው፣ በዚያም ዙሪያ የምርጫ ዘመቻና ሕዝቡን የማስተባበር ስራ መጀመር ያስፈልጋቸዋል እላለሁ። ምርጫ እንደሚሳተፉ ይፋ ካደረጉ፣ ድርጅቶችን ወክለው እጩ ለመሆን ብዙ የተማሩ ሰዎች ፓርቲዎችን ይቀላቀላሉ። “ደክመን ደክመን፣ ወደ ምርጫ የማይገባ ከሆነ፣ ቁም ነገር የማይሰራ ከሆነ፣ ለምን ራሳችንን በባዶ እናደክማለን” ብለው ከዳር ሆነው ፓርቲዎቹ አቋም እንዲወስዱ የሚጠባበቁ ሁሉ ወደ ፓርቲዎቹ ይመጣሉ።

በዚህ ረገድ የአንድነት ፓርቲ የምርጫ ዘመቻና የሚሊዮኖች ንቅናቄ ኮሚቴ ማቋቋሙ ወቃታዊነቱ እንደተጠበቀ፣ ኮሚቴው በተቀላጠፈና ዘመናዊነት በተላበሰ መልኩ እንቅስቃሴዉ ወደፊት በቶሎ ያስኬዳል የሚል ተስፋ አለኝ። ሌሎች ድርጅቶችም፣ ከአገዛዙ ብዙ መጠበቃቸዉን አቁመው፣ ወደ ዉስጣቸው ተመልሰው፣ አቅማቸዉን እና ድርጅታዊ መዋቅራቸዉን በማሳደግ ላይ እንዲበረቱ፣ የምርጫ ዘመቻቸውን እንዲጀመሩ እመክራለሁ። ድርጅታዊ ጥንካሬና መዋቅር ከሌላቸው ደግሞ ድርጅታዊ መዋቅር ካላቸው ጋር አንድነት ቢፈጥሩ ትጉሉን ይረዳል ባይ ነኝ። ይሄን ስጽፍ ትእዛዝ እየሰጠሁ አይደለም። እንደ አንድ ተራ ዜጋ የግል አስተያየቴን ነው በአክብሮት የማቀርበው።

በምርጫ ለዉጥ አይመጣም የምንል ካለን ደግሞ፣ ብዙ ክርክር አልገጥምም። አስፈላጊም አይመስለኝም። ሆኖም፣ ከዚህ በፊትም ፣ አሁንም፣ ወደፊትም በሰላማዊ መንገድ፣ በምርጫ ለዉጥ ከማምጣት ዉጭ፣ የራሳችን ሌሎች አማራጭ መንገዶች የመዉሰድ መብታችንን የነፈገን ማንም እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል።

ምርጫ 2007 ለለዉጥ !!!!!