የሰማያዊ መሪዎች ያስቡበት – ግርማ ካሳ
ዜጎች ሐሳባቸዉን በነጻነት የመገልጽ መብት፣ ዩኒቨርሳል መብት ነው። በተባበሩት መንግስት የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ላይ በግልጽ ተቀምጧል። በአገራችን ሕግ መንግስትም ሐሳብን በነጻነት የመገልጽና ሰላማዊ ሰልፎች የማድረግ መብት ባልተሸራረፈ መልኩ ተጠቅሷል። ህዝባዊ ስብሰባም ሆነ ሰላማዊ ሰልፍ ሲደረግ፣ ከአዘጋጆች የሚጠበቀው ሰልፉ ወይም ስብሰባው እንደሚደረግ ማሳወቅ ብቻ ነበር።
የሰማያዊ ፓርቲ ሕጉንና ደንቡን በመከተል መደረግ ያለበትን ሁሉ አድርጓል። ሆኖም አገዛዙ ሕግ መንግስቱን በመናድ እንደተለመደው የዜጎችን መብት እየረገጠ ነው።
አገዛዙ ይህ አይነት ሕገ ወጥ ተግባር ሲፈጽም የመጀመሪያው አይደለም። በሕወሃት ሃላፊዎች ዘንድ ሕግ ተንቋል። እነርሱ ከሕግ በላይ ሆነው፣ ለነርሱ ሲጠቅም፣ “ሕግ ፣ ሕግ” ይላሉ። እነርሱን የማይጠቅም ከሆነ ግን እንደ ቁሻሻ ወረቀት ሕጉን ቀዳደው ይጥላሉ።
ይሄ እንግዲህ ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚያዉቀው ነው። ስራአቱ የሕዝብን ጥያቄ የሚያከበር ሳይሆን አምባገነን ነው። ይሀ አምባገነን ስርአት እንዲለወጥ ነው ትግል የሚደረገው። አገዛዙ ምርጫን ይፈራል። አገዛዙ በሕዝብ እንደማይወደድ ያውቃል። አገዛዙ ካልተገደደ በቀር አፈናዉን አያቆምም።
አገዛዙንም ለማስገደድ ሕዝብ መነሳት አለበት። ሕዝብ እንዲነሳ ህዝብን ማደራጀት ያስፈልጋል። በሕዝብ ተቀባይነት ማግኘት ያስፈልጋል።
ለዚህም ነው የዛሬው ሰልፍ ያልተሳካው። በገዢው ፓርቲ አፈና ብቻ ሳይሆን በሰማያዊ ፓርቲ የአመራር ብቃት ማነስ መሆኑ መታወቅ ያለበት። አሥር በሚቆጠሩ ፖሊሶች በቀላሉ የሚበተን ሰልፍና ስብሰባ ከሆነ የተገኙት በጣም ጥቂቶች ነበሩ ማለት ነው።
እነ ኢንጂነር ይልቃል በደንብ ቅስቀሳ አድርገናል ብለዋል። ታዲያ ካደረጉ ህዝቡ ለምን አልወጣም ? እርግጠኛ ነኝ በሺሆች የሚቆጠሩ ቢመጡ ኖሮ ስብሰባው ይደረግ ነበር። ለምን የአገዛዙ ደህንነቶችና ፖሊሶች ስለሚፈሩ። በመሆኑም የሰማያዊ መሪዎች ለስብሰባው አለመሳካት ሃላፊነት መዉሰድ አለባቸው።እየወሰዱት ያለው አካሄድ መሰረታዊ ችግር ያለበት መሆኑን ተረድተው ቆም ብለው እንዲያስቡና ራሳቸውን እንዲመረምሩ እጠይቃለሁ። ሰልፍ ከመጥራት በፊት አስቀድሞ መዘጋጅትና የቤት ስራን መስራት ያስፈልጋል። ኅያልንና ጉልበትን ማስተባበር ያስፈልጋል።
ሰልፍ ስንጠራ በሕዝብ ያለንን ተቀባይነት ማሳደግ አለብን። ህዝብ ደግሞ ከሁሉም በላይ የሚፈልገው አንድ ሆኖ መታገልን ነው። በመሆኑ ሰማያዊዎች የሚከተሉትን እንዲያደርጉ በትህትና ምክሬን እለግሳለሁ፡
ከሌሎች ስምንት ድርጅቶች ጋር አብረው ለመስርት መሞከራቸው ጥሩ ነው። ሆኖም እነርሱና የመሰረቱት ትብብር ምልናባት ከአንድ፣ ሁለት አመታት በኋላ እንጂ፣ በመጪው ምርጫ ጠንካራ ሆኖ መወዳደር የሚችል አቅም ያላቸው አይመስለኝም። በመሆኑም ፣ በዋናነት ሰማያዊ እና በትብብሩ ያሉ ድርጅቶች አንድነት ፓርቲን እንዲቀላቀሉ ፣ በዚያ ረገድ ዉይይቶች እንዲጀመሩ እጠይቃለሁ።
ፓርቲዎች በሚዋሃዱበት ጊዜ ድርጅታቸውን አክስመው ነው አዲስ ዉህድ ፓርቲ የሚፈጥሩት። ያንን ለማድረግ የምርጫ ቦርድ ጣጣ አለ። ምርጫ ቦርድ ደግሞ በመኢአድ እና በአንድነት ዉህደት እንዳደርገው፣ ሕግ ወጥ በሆነ መንገድ ዉህደቱን ማቆም ይችላል።
ነገር ግን ፓርቲዎች ራሳቸውን አክስመው ፣ አንዱን ፓርቲ የሚቀላቀሉ ከሆነ (ዉህድ ፓርቲ ከመመስረት) ምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ጣልቃ የሚገባበት ምክንያት አይኖርም።
የሰማያዊ አመራሮች ከአንድነት ጋር ተዋህደው ትግሉን ካልቀጠሉ፣ ሕዝብን እና አገርን የሚጠቅም ምን የተሻለ አማራጭ እንዳላቸው አላውቅም። መቼም በፌስ ቡክ ዘመቻ፣ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ እየጠሩ በጥቂት ፖሊሶች መበተን፣ ወይንም ጠዋትና ማታ “አገዛዙ ይህን አደረገ” ብሎ መግለጫ ማዉጣት ብቻ መፍትሄ ይሆናል እንደማይሉን ነው።
ለኢንጂነር ይልቃል ይሄን እላለሁ
“ህዝቡ የአንድነት እና የሰማያዊን ዉህደት ይፈልጋል። የአንድነት አባላትና የሰማያዊ አባላት አንድ አለማ ነው ያላቸው። የሰማያዊ አመራር የሺዋስ አሰፋና የአንድነት አመራር ሃብታሙ አያሌው አንድ ላይ ነው የታሰሩት። ስንታሰር፣ ስንደበደብ፣ ስንገላታ በአንድ ላይ ሆኖ ስለምንስ ለዉጥ ለማምጣት በሚደረገው እንቅስቃሴ አንድ መሆን ያቅተናል ? እባክዎት ከስልጣንዎት በፊት የአገርን ጥቅም ያስቀድሙ”