“አንድነት የአዲሱ ትውልድ ፓርቲ ሆኗል” አቶ አስራት አብርሃም

አቶ አስራት አብርሃም በእስር ላይ የሚገኘው የአቶ ሃብታሙ አያሌው የስራ ኃላፊነት ተክቶ የአንድነት ፓርቲ ተጠባባቂ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ስለ ፓርቲው ወቅታዊ ሁኔታና የወደፊት አቅጣጫ በተመለከተ ከአቶ አስራት ጋር ተወያይተናል፡፡

ፍቱን፡-በዚህ ወቅት መንግሥት በያዘው አቋም እና ተቃዋሚዎች ባላቸው ደካማ አደረጃጀት እና ምላሽ ምክንያት ፓርቲዎቹ እንኳን የህዝቡን መብት ከጥቃት ሊከላከሉ ለራሣቸው መሆን አቅቷቸዋል፣ የፓርቲዎች መኖር ጉዳት እንጂ ጥቅሙ አልገባንም የሚሉ ድምጾች በዝተዋል?

አስራት፡-ባለው ነባራዊ ሁኔታ ነው የሚወስነው ፣ በእርግጥ እዚህ አገር ችግር አለ:: ተቃዋሚዎች በውጪያዊ ተጽዕኖና በውስጣዊ ችግር እንደተፈለገው ተጠናክረው ሊወጡ አልቻሉም:: እየተከፋፈሉ፣ እየፈረሱ፣ እየተገነቡ ነው ያሉት:: በዚህ ምክንያት የአቅመቢስ ሆነዋል:: ይህ ሂደት መቀየር አለበት ብለን ነው የምናስበው:: ከዚህ ጋር ተያይዞ በአንድነት ውስጥ ፖለቲካውን በተሻለ አቅምና ራዕይ መምራት ያስፈልጋል፣ አዲስ አመራር መምጣት አለበት የሚል አቋም አምጥተዋል:: ያንን የለውጥ ፍላጐት ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ ስልጣናቸውን ለቀው ለውጡ መጥቷል:: በዚህም ምክንያት ፓርቲውን ለሚያጠናክር አንዳንድ ሥራዎች እየሠራን ነው:: ፓርቲው የህዝብ ፓርቲ የሚሆንበትን መንገድ እየፈለግን ነው::በእርግጥም ፓርቲዎች ካልተጠናከሩ በስተቀር ብቅ የሚሉትን የፖለቲካ አመራሮች ለእስር እየዳረጉ፣ ፓርቲ እየተጐዳ፣ የህዝብ ሞራል እየተዳከመ የሚሄድበት ሁኔታ ሊቀጥል ይችላል::

ፍቱን፡-በምርጫ ለመሳተፍ ወይም ላለመሳተፍ ምክኒያት የሚሆናችሁ ምንድን ነው?

አስራት፡- ምርጫን ሥርዓቱ ስለፈለገው ብቻ መሣተፍ ትርጉም አለው ብዬ አላስብም:: ምርጫ እንደ ዋነኛ የሰላማዊ ትግል ስልት አድርጎ መውሰድ ይቻላል:: ነገር ግን በምርጫ ለመሳተፍና ከምርጫው ውጤት ይዘን ለመውጣት መሠራት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡- መጀመሪያ ሜዳው ለሁሉም ተወዳዳሪ እኩል መሆን አለበት:: ዳኛው ገለልተኛ መሆን አለበት፣ የሚዲያና ፋይናንስ አጠቃቀም እንዲሁ እኩል መሆን አለት:: ልክ እንደ ኳስ ጨዋታ ብንወስደው ማንችስተርና አርሰናል ተጋጣሚዎች ቢሆኑ ሜዳው የማንችስተር ፣ዳኛው የማንችስተር፣ አጠቃላይ ህጉ የሚሠራው ለማንችስተር ብቻ ከሆነ አርሰናል ከማንችስተር ምን ሊያደርግ ይጫወታል? የሚጫወትበት ምክንያት የለውም::

ፍቱን፡-ተቃዋሚ ፓርቲዎች በገ ዢው ፓርቲም ሆነ በህዝብ የምር እንድትታዩ ምን ማድረግ አለብን ትላለህ?

አቶ አስራት፡- መጀመሪያ ፓርቲዎችን ማሰብ ያለባቸው በተለይ የኢትዮጵያ ትግል ከዚህ በኋላ ማሰብ ያለበት ከፓርቲ ትግል አቀፍ ወጣ ያለ ህዝባዊ ትግልና ህዝባዊ ንቅናቄ እየፈጠረ በስርዓቱ ላይ ተጽእኖ አሳድሮ ስርዓቱ ወደ ድርድር እና ወደ ትክክለኛ ምርጫ የሚመጣበት አቅም መፍጠር ያስፈልጋል::

ፍቱን፡-ከአሁን በኋላ ኢህአዴግ ምን ሊፈጥር ይችላል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ?

አቶ አስራት፡-ኢህአዴግ በመከፋፈል ጀምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን ሊጠቀም ይችላል::መቋቋም ካልቻልክ አልቻ ልክም ማለት ነው:: አሁን በኋላ ኢህአዴግ ልብ ገዝቶ ጥሩ መንግሥት ሆኖ ተቀይሮ ተጸጽቶ የሆነ ነገር ያደርጋል ብለን መጠበቅ የለብንም:: ለ23 ዓመታት ያህል ኢህአዴግ የሆነ ነገር እንዲያደርግልን የብሔራዊ እርቅ እንዲያወርድ ተለምኗል:: ይሄ የተደረገው የኢህአዴግን እውነተኛ ባህሪ ባለማወቅ ነው:: ኢህአዴግ በልመና የሚሰማ መንግሥት አይደለም:: ስለዚህ በተገኘው መንገድ ኢህአዴግን በልጦ መገኘት ያስፈልጋል::በሃሣብም ይሁን በህዝብ አደረጃጀት ኢህአዴግን መብለጥ ያስፈልጋል:: ስለዚህ ተገዶ ወደ ድርድር እና ብሔራዊ እርቅ የሚገባበት፣ ተገዶ ወደ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የሚገባበት ሁኔታ መፍጠር ካልተቻለ ምንም በልመና የሚደረግ እንዳችም ነገር የለም:: ስለዚህ ትግሉ ገና ቅድመ ሁኔታ ይፈልጋል:: ሜዳውን የማስተ ካከልና እኩል የማድረግ ትግል ያስፈልጋል:: ይሄ ባልተሰራበት ሁኔታ ግን ታጋዮችን እንዲሁ እያስበሉ መኖር ሊያጋጥም ይችላል::

ፍቱን፡- ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጭራሽ ኢህአዴግን አልተረዱትም፣ ኢህአዴግን የሚመራን የፖለቲካ ስትራቴጂና ስልት የላቸውም:: ባለፉት 23 ዓመታት ሥራቸው ኢህአዴግን የማጀብ እንጂ የመፎካከር እና የመገዳደር ሊሆን አልቻለም የሚሉ አሉ?

አቶ አስራት፡- ፖለቲካው በስትራቴጂ አይደም እየተሰራ ያለው:: አንድ ፓርቲ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥት እስኪሆንበት ጊዜ ድረስ የተለያዩ ደረጃዎች ማለፍ አለበት:: እድገቱንም የሚታይና የሚዳሰስ መሆን አለበት:: የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኢህአዴግን ሰው ጠልቶታል፣ አንድ ሐሙስ ቀረው ብለው ይጀምራሉ:: ስለዚህ በሆነ አጋጣሚ ሲወድቅ ስልጣንም በአቋራጭ እንይዛለን ነው እንጂ ሰርተን ወደ ስልጣን እንወጣለን የሚል አላማ የለም:: ኢህአዴግ ትንሽ ነው የቀረው የሚባለው በምን ስሌት እንደደረሱበት አይታወቅም:: ሌላኛው ስህተት ህዝቡ ኢህአዴግን ስለጠላ ተቃዋሚውን ይወዳል ማለት አይደለም:: አንደኛ ከዚሁ ሁሉ ብዙ ተቃዋሚዎች ህዝቡ የሚወደው የጥኛው እንደሆነ መታወቅ አለበት:: አንድ ሰው አበራሽ የምትባል ሴት የሚጠላ ከሆነ፣ አበበች የምትባል ሴት ይወዳል ማለት አይደለም:: ስለዚህ ሰው ኢህአዴግን ስለጠላ ተቃዋሚውን ይደግፋል በሚለው አልስማማም:: በአንድ ወቅት ዶ/ር መራራ ጉዲና በምርጫ ወቅት ህዝቡን ለመቀስቀስ ሁለት ቀን ይበቃል ሲሉ ሰምቻለሁ:: በዚህም አባባል አልስማማም:: ህዝቡ የአንተን ማንነት ለማወቅ ወደታች ወርደህ ማንነትህን ማሳየት አለብህ፣ ህዝቡ አንዴ ስለነገርከው የሚሰለፍ አይደለም:: የፖለቲካ ሥራ ስትሰራ ህዝቡ የእኛ ነው ማደራጀት አያስፈልግንም፣ ህዝቡ ሁሉ የእኛ ደጋፊ ነው የሚባለው ነገር ተገቢ ነው ብሎ አላስብም:: ህዝቡ እንዲመርጥህ በተጨባጭ ስራ እንድትሰራለት ይፈልጋል:: አሁን ባለው ሁኔታ ትግሉ ብዙም የእስትራቴጂና የአቅጣጫ ጥልቀት ያለው አልመሰለኝም::

ፍቱን፡- አንድነትም ከዚህ ውስጥ ይመደባል?

አቶ አስራት፡-አንድነት የአምስት አመት ስትራቴጂ ፕላን ሞክሮ ነበር::ነገር ግን ፓርቲው በአራት አመት ውስጥ የተጓዘበትን ሲታይ ፓርቲውና ስትራቴጂክ ፕላኑ አይተዋወቁም ነበር ብል በጣም ጥግ የያዘ አገላለጽ አይመስለኝም:: ስትራቴጂክ ፕላኑ ጥሩ ነው::አንድነት ሲጓዝ የነበረው በዚያ ፕላን መሠረት ነበር ወይ ብትለኝ አይደለም ነው የምልህ:: ለዚህ ሙከራው ጥሩ ሆኖ ሳለ አተገባበር ላይ እና ወደ መሬት በማውረዱ ጉዳይ ላይ ችግር ነበር:: ስለዚህ ሁሉም ፓርቲዎች ማለት ይቻላል፣ አቅጣጫና ስትራቴጂ አስቀምጠው የመታገል ነገር የለም:: ሰላማዊ ትግል ስታስብ በተለይ አደረጃጀት ላይ በጣም ብለህ መሆን ያስፈልጋል:: የሰላማዊ ትግል ፓርቲ በአባላቱ ብዛት ሳይሆን ባለው ሃሣብ ጥንካሬ፣ በያዘው ፖሊሲ ተመራጭነት ነው መሆን ያለበት:: ከዚያ በኋላ ህዝቡና ደጋፊው እንጂ አባላት አይደለም የሚመርጥህ::

ፍቱን፡-አብዛኞቹ ፓርቲዎች የከተማ ፓርቲዎች ናቸው ይባላል?

አቶ አስራት፡-ትክክከል ነው::በአብዛኛው አገር አቀፍ የሚባሉት ፓርቲዎች የከተማ ፓርቲዎች ናቸው:: ከተማ ተኮር ናቸው:: ከመሐል አገርም ብዙ ያለፉ አይደሉም:: ስለዚህ ትግሉ የተሻለ ለውጥ እንዲያመጣ ከተፈለገ ሙሉ ለሙሉ አሁን ከነበረው ልማዳዊ አሠራር የወጣ አዲስና ቆራጥ የሆነ አመራር ሊኖረው ይገባል::

ፍቱን፡-አብዛኞቹ የፓርቲ መሪዎች የፓርቲው ፕሬዝዳንት ከመሆን የዘለለ ችሎታና አቅም የላቸውም በሚባለው ወቀሳ ትስማማለህ?

አቶ አስራት፡-አዎን::አብዛኞቹ ከፖለቲካ ፓርቲ የሚመጡት ሰዎች የፖለቲካ ፓርቲ መሪ መሆን የመጨረሻ ግብ አድርገው የተቀመጡ ናቸው:: ከዚያ የዘለለ አገር የመምራት ግብ ያላቸው አይደሉም:: አቅማቸውም ያንን እንደማይፈቅድላቸው ፣ የአገር መሪ እንደማይሆኑ ያውቃሉ:: ስለዚህ የፓርቲ መሪ ሆኖ መቅረት ብቻ ነው ህልማቸው:: በደካማ ሰው የሚመራ ፓርቲ ምንም ጥርጥር የለውም ጠንካራ ሰው እንዲገባበት አይፈልግም:: በደካማ ሰው ስለሚመራ የተለየ ለውጥም አያመጣም::

ፍቱን፡-የአንድ ፓርቲ አባላት ግንኙነት እንዴት መሆን አለበት ታላለህ?

አቶ አስራት፡-አንተና እኔ የአንድ ፓርቲ አባላት ከሆንን ልንተሳሰብና የቤተሰባዊ ግንኙነት ሊኖረን ይገባል:: የራስህ ጉዳይ የእኔም ጉዳይ ነው የማልል ከሆነ ግንኙነቱ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል:: ሸክሙን በጋራ ነው ልንወጣ የሚገባው:: ለምሣሌ እነአንዱዓለም ታስረዋል:: እንደ አመራር ምን አደረግን? ቤተሰባቸውን ጠይቀናል? አግዘናል? እስር ቤት ሄደን ጠይቀናል? የሚለውን ነገር መጠየቅ አለብን:: እነዚህ ጥቃቅን የሚመስሉን ጉዳዮች ለታሳሪዎቹና ለቤተሰባቸው ለሌላውም ህብረተሰብ የሚያስተላልፈው መልዕክት ቀላል አይደለም:: ነገ እኔም ብታሰር ቤተሰቦቼ አይበተኑም:: ተስፋ አይቆርጡም፣ አያዝኑም ::የሚለውን ነገር ነው የሚያስተላልፈው:: ከዚህ ውጪ ሲሆን ትግሉን የውሸትና የታይታ ብቻ ያደርገዋል::

ፍቱን፡-ከነዚህ ነገሮች አንፃር አንድነት የወቅቱ ቁመና ምን ይመስላል?

አቶ አስራት፡- አሁን አንድነት ያለበት ሁኔታ ሳያው ያለምንም ጥርጥር ከሌሎች ፓርቲዎች የሚለይበት ሁኔታ አለ:: ሰፋ ያለ መዋቅር አለው:: በውጭም ሰፋ ያለ ደጋፊ አለው፣ የተሻለ ነገሮች አሉት:: ግን አሁን ባለው ቁመና የኢትዮጵያን ትግል ለመምራት የሚያስችል ቁመና አለው ብዬ አላስብም:: ገና ብዙ የሚቀረው ነገር አለ:: በእርግጥ አሁን የአመራር ለውጥ አድርገናል:: ይህ የአመራር ለውጥ አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት አንደኛ የትውልድም ሽግግር ማድረግ ያስፈልግ ነበር:: ፖለቲካው እነዚህ በ6ዐዎቹ የነበሩ የፖለቲካ ሰዎች ቅሪት የሚመሩት ነው:: በአጠቃላይ ከዚህ አይነት ኢሜጅ አንድነት መውጣት ነበረበት::አሁን አንድነት የአዲሱ ትውልድ ፓርቲ ሆኗል:: ከዚያ በኋላ የመጣው አዲሱ ትውልድ ወደ አመራር መጥቶ አሁን ዘመኑ የሚጠይቀውን አመራርና የትግል ስልት መከተል አለበት የሚለው ሃሣብ ነበር፣ በተሳካ ሁኔታ አካሄደናል ብዬ አስባለሁ::

ፍቱን፡- አንድነት ውስጥ የነበሩ ሰዎች፣ በኢ/ር ግዛቸው እና በአቶ በላይ መካከል የተካሄደው የስልጣን ሽግግር ደንብ የጣሰ ነበር ብለው አቤቱታ አቅርበዋል:: ይሄ እንቅፋት አይሆንም?

አቶ አስራት፡-በእርግጥ እንቅፋቶች አሉት:: ሲጀመር ይሄ ለውጥ እንዳይመጣ በአለንበት እንሂድ የሚል አቋም ነበር:: ያ አቋም ተሸነፈ:: ለውጥ ያስፈልጋል፣አብዮት ያስፈልጋል፣ ስርዓቱን ከመታገልህ በፊት በመጀመሪያ የውስጥ ፓርቲ አብዮት ያስፈልጋል የሚለው ሃሣብ አሸንፎ አልፏል:: ይሄ አሳብ አሸንፎ ሲወጣ ደግሞ መለወጥ የለብንም ባለንበት መሄድ አለብን የሚለው ሃሣብ ቢሸነፍም የመንግሥት ድጋፍና የውጭ ተጽእኖ ተጨምሮበት አሁኑኑ ወደ ነበርንበት የእንቅልፍ ዘመን እንመለስ የሚሉ ጥቂት አባላት የነበሩ የሚያራምዱት አጀንዳ በተወሰነ መልክ እያራመዱ ያለበት ሁኔታ አለ:: ስለዚህ አዲሱ አመራር ከመጣ ሁለት ሳምንት ቢሆንም አሁን እየታገለ ያለው ፓርቲውን ሥራ ማስጀመር እና ይሄው ወደነበርንበት ተመልሰን እንተኛ የሚለው ሃሣብ በተቻለ መጠን የመከላከል ሥራ እየተሰራ ነው::

ፍቱን፡- በተፈጠረው ክፍፍል ምክንያት ፓርቲው እንዳይበታተን ስጋት ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ስልጣን የተረከቡበት መንገድ ድርጅቱን ለመከፋፈል ሊዳርገው የሚያስችል የተሰራ ስህተት አለ?

አስራት፡- ምንም የተሰራ ስህተት የለም ብዬ ልጀምር:: ኢ/ር ግዛቸው ከተመረጡ በኋላ በተለይ ከመኢአድ ውህደት ጋር ተያይዞ ፓርቲውን መምራት የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ለውጥ የመፈለግ ጉዳይ ስለነበር በውስም በውጭም ከፍተኛ የሆነ ተጽእኖ ስለተፈጠረባቸው በዚህ ተጽእኖ ውስጥ ሆነው ፓርቲውን ቢመሩት ፓርቲው የበለጠ የሚጐዳበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለው ስላሰቡ ራሣቸው ከአመራር ለመልቀቅ ነው የወሰኑት:: ከአመራር ኃላፊነት ከመልቀቃቸው በፊት ፣ ጥቅምት 1፣2007 ዓ.ም. የሥራ አስፈጻሚውን አባላት ሰብስበው፣ “ለአንድነት የተሻለ እድል ለመፍጠር ሲባል ነገ ከኃላፊነቴ ለቅቄ ስልጣኔን ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ላስረክብ ስለሆነ ካቤኔውን በትኛለሁ::” ብለዋል:: ምክንያቱም ካቢኔውን ያቋቋሙት እሣቸው ናቸው:: እሣቸው ያቋቋሙትን ካቢኔ ትተው መውረድ አልፈለጉም:: ስለዚህ ካቢኔውን በትነው በነጋታው ለብሔራዊ ምክር ቤቱ መጥተው፣‹‹ የሚያሰራ ሁኔታ ስለሌለ እኔ እንደመሪ ሆኔ መቀጠል አልፈልግምና ከህሊናዬ ጋር ተማክሬ ስልጣኔን አስርክባለሁ››፣ ብለው አመለከቱ:: ብሔራዊ ምክር ቤቱም ከትልቅ ምስጋናና አድናቆት ጋር የእሣቸውን ስልጣን መልቀቂያ ተቀብሏል:: ብሔራዊ ምክር ቤቱ ስልጣናቸውን ከተረከበ በኋላ ፓርቲውን ያለ ኃላፊ ባዶን ማሳደር ስላልነበረበት የፓርቲው ህገ ደንብ፣ በሚፈቅድለት መሠረት….

ፍቱን፡- የፓርቲው ህገ ደንብ ምንድን ነው የሚለው?

አቶ አስራት፡- የፓርቲው ሕገ ደንብ የሚለው፣ ጠቅላላ ጉባዔው በማይኖርበት ጊዜ፣ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ፕሮግራምና ህገ ደንብ ከማሻሻል ውጭ፣ የጠቅላላ ጉባዔ ያለውን ኃላፊነት ሁሉ ማከናወን ይችላል ነው የሚለው:: ከጠቅላላ ጉባዔ ኃላፊነት አንዱ ደግሞ የፓርቲውን ፕሬዚዳንት መምረጥ ነው:: ስለዚህ በዚህ መንገድ ብሔራዊ ምክር ቤቱ የፓርቲውን ፕሬዚዳንት መርጧል::

ፍቱን፡- ህገ ደንብ ተጥሷል የሚሉት ሰዎች በምርጨው ሂደቱ ውስጥ ነበሩ?

አስራት፡- አዎን:: ተሳታፊዎች ነበሩ:: በወቅቱም የተቃወሙት ነገር አልነበረም:: ፕሬዚዳንትም ሲመረጥ አራት እጩዎች ነበሩ:: እነዚህ ሰዎችም ለፈለጉት እጩ ቀስቅሰው መርጠው ነበር የሄዱት:: እነዚህን ሰዎች ልናከብራቸው እንችል የነበረው ይህ ሂደት ህገወጥ ስለሆነ አንሣተፍም ቢሉ ነበር:: አላሉም:: ተሳትው እነሱ የፈለጉት እጩ ሳያሸንፍ ሲቀር ነው ኢቲቪ ሄደው ለስርዓቱ መጠቀሚያ ሆነው አንዳንድ ሃሜታ እየፈጠሩ ያሉት::

ፍቱን፡- ኢንጂነር ግዛቸው ስልጣናቸውን ካስረከቡ በኋላ ስልጣኔን የለቀቅኩት ከዲያስፓራው በደረሰብኝ ጫና ነው ብለዋል?

አቶ አስራት፡- በብሔራዊ ምክር ቤቱ ስብሰባ ላይም ፣‹‹በውስጥና በውጭ ከፍተኛ ተጽእኖ ስለበዛብኝ ፓርቲውን በአግባቱ መምራት አልቻልኩም››፣ ብለው ነው የለቀቁት:: በእርግጥ በውስጥም በውጭም ተጽእኖ ነበረ:: እኛው ራሣችን ኢንጂነሩ እንዲወርዱ ተጽእኖ አድርገናል:: ምንም ጥያቄ የለውም:: ያወረዳቸው ግን ተጽእኖ ብቻ አይደለም:: መጨረሻ ላይ እንዳሉት፡-“ከህሊናዬ ጋር ተማክሬ” ነው ያሉት:: ይሄንን ተጽእኖ እያለ መቀጠል ይችሉ ነበር እኮ:: ምንም ቢሆን ተጽእኖውን ተቋቁመው ፓርቲውን መምራት ይችሉ ነበር:: ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ላይ ፓርቲውን ብመራው አይጠቅምም:: ፓርቲውን እጐዳዋለሁ ብዬ በፈቃዴ ለቅቄያለሁ ብለው በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አልካዱም:: ተጽእኖ በተመለከተ በሁሉም አቅጣጫ ተጽእኖ ነበር:: ፓርቲው እንዲሻሻል፣ በአዲስ አመራር እንዲምራ የመፈለግ በጐ እና አዎንታዊ ተጽእኖ ነበር::

ፍቱን፡-ዲያስፖራው በፓርቲው ላይ ተጽእኖ የማሳረፍ ሚና ሊኖረው ይገባል?

አቶ አስራት፡- ኢትዮጵያዊያኑ ዲያስፖራዎች ተጽእኖ የማሳደር መብት አላቸው:: በእርግጥ በፓርቲው ውሣኔ ላይ አይሳተፉም ግን ኢትዮጵያውያን እንደመሆናቸው መጠን ገንዘባቸው፣ ጊዜያቸውንና ሃሣባቸውን የሚያዋጡበት ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን አዎንታዊ ተጽእኖ ቢያሳድሩ ችግር አለው ብዬ አላስብም:: ነገር ግን ፓርቲው ውሣኔ የሚወስንበት የራሱ የሆነ መንገዶች አሉ:: የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አለ፣ ብሔራዊ ምክር ቤቱ አለ፣ ከዚያ ሲያልፍ ደግሞ ጠቅላላ ጉባዔ አለ:: የፓርቲ ውሣኔዎች የሚወሰኑት በህገ ደንቡ መሠረትና በዚሁ ሁኔታ ነው:: አሁንም ከዚህ ሁኔታ የወጣ ነገር የለም:: ኢንጂነሩም በራሣቸው ፈቃድ ነው የለቀቁት:: ምናልባትም አንዳንድ ቅር የሚያሰኙዋቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ:: ያ ማለት ግን ያደረጉትን ትልቅ ሥራ የሚቀንሰው ነገር አይደለም:: ለአንድነት ፓርቲ ትልቅ ሥራ ሰርተዋል:: ፓርቲውን በአዲስ መንገድና በአዲስ አመራር እንዲመራ በሩን ከፍተዋል:: በተቃዋሚው ጐራም ይሁን በመንግሥት ጐራ እስካሁን በፈቃዴ ሥልጣኔን ለቅቄያለሁ ያለ መሪ የለም:: ይህንን እድልና ትልቅ ስም ኢንጂነር ግዛቸው ወስደዋል:: ይሄ መቼም ቢሆን ከሳቸው የሚወሰድ ነገር አይደለም:: አንድነትም ቢሆን ይሄንን ያደረጉት ትልቅ ነገር የሚዘነጋው አይደለም:: እንደ ጀግናም ነው የሚቆጥረው የሚያወድሳቸው::

ፍቱን፡- አንድነት በዚህ ዓመት ለሚኖረው አገራዊ ምርጫ ያለው አረዳድ ምንድን ነው?

አስራት፡- በእርግጥ ሰላማዊ ትግል ስትታገል ዋና የትግል አቅጣጫ የሚሆነው ምርጫ ነው:: ስለዚህ ምርጫን ዋንኛው የትግል ትልት እንደመሆኑ ለምርጫ ሁሌም ዝግጁ ነን፣ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫ ላይ እንሣተፍ አንሣተፍ የሚለው ውሣኔ የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት ነው:: ያ ማለት ፓርቲው ከምርጫ ዝግጅትና አጠቃላይ የሰላማዊ ትግል ሥራ አቁሟል ማለት አይደለም:: የተለመደውን ፓርቲውን የማጠናከር ፣ አላማና ፕሮግራሙን የማስተዋወቅ ሥራዎች አሁንም እየተሰሩ ነው ያሉት:: ምርጫ መሳተፍና አለመሳተፉን ብሔራዊ ምክር ቤቱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይወስናል ብዬ ነው የማስበው::index__Asrat-Abraham-Young-athour-and-plotician