ኦሮሞነት ዘረኝነት አይደለም — ግርማ ካሳ

በኦሮሞዉና በአማርኛ ተናገሪው መካከል ጥላቻ እንዲሰርጽ ተብሎ አንድ የተጻፈ መርዛማ መጽሐፍ አለ። የቡርቃ ዝምታ የሚባል መጽሃፍ። የዚህ መጽሀፍ ደራሱ አቶ ተስፋዬ ገበረ አብ ይባላሉ። የሕወሃት/ኢሓአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩ ጊዜ የጻፉት መጽሀፍ ነው። በቅርቡ “በሞጋሳ ኦሮሞ ሆኛለሁ” ሲሉ አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል። ምን ያህል የሞጋሳ ሚስጠር እንደገባቸው ግን አላውቅም።

ከአራት መቶ አመታት በፊት፣ የኦሮሞ ጦረኞች አንድ አካባቢን በሚቆጣጠሩና በሚማርኩ ጊዜ፣ አንድ የሚያደርጉት ሥርዓት ነበር። የጎሳው ሽማግሌዎች ከተማዋ ሲገቡ ከዚያ ጊዜ ጀመሮ ያቺ ክከተማ ኦሮሞ ትሆናለች። በከተማዋም የሚኖረው ህዝብ፣ በሽማግሌዎቹ ፊት ያልፋል። በዘሩ ከሌላ ወገን ቢሆንም፣ በአለቃዉ ያለፈ ሰው ሁሉ ኦሮሞ ይሆናል። ይህ ስርአት ሞጋሳ ይባላል። ኦሮሞነት ከዘር ጋር ግንኙንት እንደሌለው የሚያስተምር የኦሮሞ ባህል !

ሞጋሳ የሚያሠባስብ ነው። አንድ የሚያደርግ ነው። በመሆኑም ኦሮሞነት አንድነት ነው። ኦሮሞነት ሌላውን እንደ እራስ አድርጎ ማቀፍ ነው። ኦሮሞነት ሌላውን ማሳነሳ፣ ሌላውን ማባረር፣ ሌላውን መጥላት አይደለም።

እርግጥ ነው አንዳንድ አክራሪ የኦሮሞ ብሄረተኞች፣ በኦሮሞነት ስም ሌሎችን የመጥላት ፖለቲካ ያራምዳሉ። ከሌሎች የመለየት፣ ሌሎችን የማግለል፣ የመከፋፈል፣ የጥላቻ ፖለቲካ ያራግባሉ። የኦሮሞ ባህል ግን ፣ የሞጋሳ ባህል ግን ፣ አንድ የሚያደርግ ባህል ነው። እነርሱ ከሚናገሩትና ከሚረጩት መርዝ ጋር ግንኙነት የለውም።

ሌላው በአማርኛም ሳይቀር የምንጠቀማት ቃል አለች። ጉዲፈቻ። ጉዲፈቻ ማለት የሌላውን ሰው ልጅ እንደ ራስ አድርጎ ማሳደግ ማለት ነው። ጉዲፋቻ የሚለውን ቃል በአማራኛ መጠቀማችን በራሱ የሚያሳየው፣ የሌላውን ልጅ እንደራስ አድርጎ የማቀፍ ባህል፣ በኦሮሞው ማህበረሰብ ዉስጥ ምንም ያህል ስር የሰደደ ባህል እንደሆነ ነው። የኦሮሞው ማህበረሰብ፣ ትግሬ ይሁኑ አማራ፣ ጉራጌ ይሁኑ ከፊቾ ፣ ከሌላ ዘር የሆኑትን እንደራሱ አድርጉ የሚያሳድግ ማህበረስብ ነው። ከሌላው ጋር የተዛመደ፣ የተዋለደ፣ የዘረኝነት ነገር የሌለበት ማሀብረሰብ ነው።

ላለፉት 23 አመታት ግን በሽታ ገባ። የኦሮሞ ማህበረሰብን ከሌላው ለማጣላት ብዙ ተሞከረ። የባለስልጣናቱ ካድሬዎች ሆን ብለው በኦሮሞው እና ኦሮሞ ባልሆነው ማህብረሰብ መካከል ልዩነቶች እንዲፈጠሩ ቀን እና ሌሊት መስራት ጀመሩ።

ለአማርኛው ተናጋሪዎች “ ኦሮሞዎቹ ዘረኞች ናቸው። አማርኛን ይጠላሉ። ይጨርሷቹሃል። ያርዱዋቹኋል” የሚል እድምታ ያለው መልእክት በጎን ያስተላልፋሉ። ለኦሮሞ ደግሞ ” እነርሱ ነፍጠኞች ናቸው። በቋንቋህ እንዳትናገር ሊያደርጉህ ነው። ሊያጠፉህ ነው። የድሮው የአማራ የበላይነትን ሊያመጡብህ ነው። አሃዳዊ ስርዓት ሊጭኑብህ ነው” ይሉታል። አማርኛ ተናጋሪዎች በአፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች ላይ ፣ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች ደግሞ በአማርኛ ተናጋሪዎች ላይ ጥርጥሬ እንዲያድርባቸውና እና እንዳይግባቡ እያደርጓቸው ነው። ኦሮሞዎች አማርኛ እንዳይማሩ፣ አማርኛ ተናጋሪዎች ደግሞ አማርኛ ብቻ እንዲናገሩ ተደርጎ፣ የአንድ አገር ልጆች ሆነን እንዳንግባባ ተደርገናል። መነጋገር ስላልቻልን፣ አንዳንች ስለአንዳንች የሚነግሩን የአገዛዙ ካድሬውዎችና ዉጭ ያሉ አንዳንድ አክራሪዎች ናቸው። ነገሮችን እየጠመዘዙ ስለሚነግሩንም እርስ በርስ እየታመስን ነው።

መንቃት ይኖርብናል። እነዚህ የጥፋት ኃይሎች በኛ ላይ የሽረቡትን ወጥመድ ማፈራረስ አለብን። የኦሮሞ ባህል፣ የኦህደድ ካድሬዎች ወይንም ዉጭ ያሉ አንዳንድ ለኦሮሞ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ግን በጥላቻ የተሞሉ አክራሪዎች እንደሚነግሩን አይደለም። ኦሮሞነት ዘረኝነት አይደለም። ኦሮሞነት አንድነት ነው። ኦሮሞነት ሌሎች እንደ ራሱ አድርጎ መቆጠር ነው። ኦሮሞነት የሚለያይ ሳይሆን የሚያሰባስብ ነው። የኦሮሞነት ፖለቲካ የጉዲፈቻና የሞጋሳ ፖለቲካ ነው።

የኦሮሞ ማህበረሰብ ከምንም በላይ ፣ በበሃሉ የሚመቸውና የሚቀበለው የአንድነትን እና የፍቅርን ፖለቲክ ነው። “እገሌ ከዚህ ዘር ስለሆነ፣ ወይንም ይሄ ቋንቋ ስለሚናገር ከአገራችን ይዉጣ። ይሄ ምድር የኦሮሞ ብቻ ነው ….ወዘተረፈ” የሚባለው አክራሪዎችና ካድሬዎች የሚረጩት እንጂ, ከሕዝቡ የሚመጣ አይደለም። የኦሮሞ ማህበረሰብ በባህሉ ሌላውን የሚቀበል፣ እንደራሱ አድርጎ የሚያኖርና የሚያሳድግ ነው።

ለዚህም ነው ከጊዜ ወደ ጊዜ የአንድነት ፓርቲ በኦሮሞ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነቱ እየጨመረ የመጣው። ለምን የአንድነት ፖለቲካ የፍቅር፣ የማሰባሰብ፣ የማቀራረብና የአንድነት ፖለቲካ ነዉና !

አፋን ኦሮሞ የማናውቅ ካለን፣ እንማር። አማርኛ የማናውቅ ካለን፣ አማርኛ እንማር፡ ብዙ ቋንቋ ማውቅ በረክት ነው። ሌላ ቋንቋ መማር አያሳንሰንም። እንደ ወንድማማቾች፣ ለመግባባት፣ ለመነጋገር፣ አብረን አገራችንን ለማሳደግ ቋንቋ አለማወቃችን እንቃፋት ሊሆንብን አይገባም።

1 Comment on “ኦሮሞነት ዘረኝነት አይደለም — ግርማ ካሳ”

  1. በባለቤት አልባዋ ድሬዳዋ – መሬት በገፍ እየተቸበቸበ ነው

    ድሬዳዋ ባለቤት የሌላት አሰተዳደር ሆና ከፌዴራል መንግስት በTPLF ስራ አስፈፃሚ በቀጥታ ትዕዛዝ የምትተዳደር ከተማ ናት:: ለምን በየአምስት ዓመታት ምርጫ በድሬዳዋ እንደሚካሄድ የሚታወቅ ነገር የለም:: ምክንያቱም አሸናፊ (ኢህአዴግ – 114 ወንበሮች) እና ተሸናፊ (ሶህዴፓ – 75 ወንበሮች) በየሁለት አመት ተኩል ከተማዋን በፈረቃ ያስተዳድራሉ:: በጣም የሚገርመው “ኢህአዴግን ምረጡ መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው!” ብሎ የምርጫ ቅስቀሳ አድርጎ ለአምስት ዓመታት ‘የተመረጠው’ ኢህአዴግ የማስተዳድራችሁ ለሁለት ዓመት ተኩል ብቻ ነው ማለቱ ከየት አገር ልምድ እንደወሰደ የሚያውቅ ካለ ለድሬዳዋ ህዝብ ቢያስረዳ መልካም ነው::

    እ.አ.አ. 2007 በተደረገው የህዝብ ቆጠራ የድሬዳዋ አስተዳደር ካላት 342,827 ህዝብ ውስጥ 46.08% (157,991) የኦሮሞ ብሄር ሲሆን 24.24% (83,114) ደግሞ የሶማሌ ብሄር ናቸው:: በአስተዳደሩ ካሉት የገጠር ነዋሪዎች የኦሮሞ ብሄር 73.61% (80,949) ሲሆን የሶማሌ ብሄር ደግሞ 25.94% (28,531) ነው:: ሰፊው የአስተዳደሩ ገጠራማ ቦታ (73.61%) በኦሮሞዎች የተሞላውን ከምስራቅ ሃረረጌ ዞን መሬት ቆርሶ በመውሰድ ነው የድሬዳዋ አስተዳደር የተዋቀረው:: ይህ ሰፊ የኦሮሞ መሬት ከከተማዋ በስተሰሜን እስከ 50 ኪሎሜትር (መልካ ቄሮ) በስተደቡብ እስከ 17 ኪሎሜትር (ደንገጎ) እና በስተምዕራብ 10 ኪሎሜትር (መልካ ጀብዱ) በከተማዋ ክልል ውስጥ ይገኛሉ::

    ምርጫ በመጣ ቁጥር አስተዳደሩ ካሉት 189 የከተማዋ ምክር ቤት ወንበሮች ውስጥ ኢህአዴግ ለ114 ወንበሮች እና ሶህዴፓ ደግሞ ለ75 ወንበሮች በመወዳደር እንዲያሸንፉ ይደረጋል:: ሆኖም 60% የአስተዳደሩ ህዝብ ኢህአዴግን ቢመርጥም ከአምስት አመቱ ውስጥ ኢህአዴግ የሚያስተዳድረው ሁለት ዓመት ተኩሉን ብቻ ሲሆን የተቀረውን ሁለት አመት ተኩል ደግሞ 40% ወንበር ያለው ሶህዴፓ ያስተዳድራል:: መንግስት ለምን ለምርጫ በሚሊዮን የሚገመት ብር በየአምስት ዓመታት እንደሚያወጣና ኢህአዴግን ምረጡ እያለ የከተማዋንና የገጠሩን ህዝብ ቁም ስቅሉን እንደሚያሳይ ግራ የሚያጋባ ነው:: የድሬዳዋ ህዝብ በመረጥነው ፓርቲ እንተዳደር ብሎ ኢህአዴግን ቢጠይቅ ምን መልስ ይሰጠው ይሆን? ጥያቄውንና መልሱን ለድሬዳዋ ነዋሪዎችና ለኢህአዴግ ሰዎች ትቼ ሰሞኑን በመቸብቸብ ላይ ስላለው የድሬዳዋ መሬት ጉዳይ ላምራ::

    ከላይ እንደተገለጠው በገጠሪቱ የድሬደዋ አስተዳደር የኦሮሞ ህዝብ (80,949 ህዝብ) በሚኖርበት ከከተማዋ እስከ 50 ኪሎሜትር ርቀት ድረስ የከተማዋ አካል ሲሆን ከድሬዳዋ ከተማ በ12 ኪሎሜትር ርቀት የምትገኘው የሺኒሌ ከተማ በሶማሌ ክልል ውስጥ በመካተት የሺኒሌ ወረዳ ተብሎ በሲቲ ዞን (በቀድሞው ሺኒሌ ዞን) ስር የተዋቀረ ነው:: በጣም የሚገርመው የሺኒሌ ወረዳ ዳር ድንበር ከድሬዳዋ ከተማ 50 ሜትር ርቀት መሆኑ ነው:: የሺኒሌ ወረዳ የመጨረሻ ድንበር የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አጥር ነው:: ይህ ቦታ መርማርሳ ይባላል (በኦሞምኛ የቀጥታ ትርጉሙ ዙሪያ እንደማለት ነው):: ይታያችሁ ድሬዳዋ የኦሮሞን መሬት እስከ 50 ኪሎሜትር (መልካ ቄሮ) በእቅፋ ይዛ ከከተማዋ በ50 ሜትር ርቀት ላይ ያለውን የኦሮሞ መሬት ለሶማሌ ክልል በማድረግ የኦሮሞን መሬት መቸብቸብ ተጀመረ::

    ባሳለፍነው ሳምንት መርማርሳ (ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ጎን) ሄጄ ያየሁት ሁኔታ ነው ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ:: በመርመርሳ 500 ካሬ ሜትር ለቤት መስሪያ የሚሆን ቦታ ከብር 100,000 እስከ ብር 130,000 እየተቸበቸበ ነው:: የሚገርመው ደግሞ የስም ማዛወሩ ሂደት በሁለትና ሶስት ሰዓታት ውስጥ በ12 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሺኒሌ ከተማ ለሶማሌ ክልል መንግስት ብር 4,000 በመክፈል ካርታና ፕላን መሬት ገዠዎች እየተረከቡ ነው:: መሬቱን የሚሸጡትና ገንዘቡን የሚረከቡት ሁሉም የሶማሌ ብሄር አባላት ሲሆኑ የሚገዙት ደግሞ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው:: በሺዎች የሚቆጠሩ የሶማሌ ብሄረሰብ አባላትን በኢኮኖሚ ለመጥቀም ታስቦ ለዚሁ ብሄር አባላት ተሸንሽኖ የታደለውን መሬት ለመግዛት የምትሹ በሞባይል ቁጥር +251 939600211 (አቶ ሃሰን) ብላችሁ ብትደውሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ባለ 500 ካሬ ሜትር የኦሮሞ መሬት ለቤት መስሪያ ቦታ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ጎን (መርማርሳ) ታገኛላችሁ::

    ጎበዝ የኢህአዴግ ህገ መንግስት መሬት አይሸጥም አይለወጥም ይላል:: መርማርሳ (ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ጎን) ያለውን መሬት ህገ መንግስቱ አያውቀውም ማለት ነው? ለማንኛውም ለአቶ ሃሰን (+251 939600211) ደውላችሁ የ500 ካሬ ሜትር ባለቤት መሆን ትችላላችሁ በባለቤት አልባዋ – ድሬዳዋ::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*