ሰማያዊ ትልቅ የፖለቲካ ክስረት አጋጠመው። በርካታ አባላቱም የአመራሩን ግትርነት መጠየቅ ጀመሩ። በአንድ አመት ዉስጥ የሰማያዉ ድጋፍ ወደ ታች አሽቆለቆለ።
ትንሽ የግል አስተያየት በሰማያዊ ላይ
==================== Girma Kassa
ኃዳር ሰባት ቀን በቤልሄር ሜዳ ሰማያዊ ፓርቲ ብዙም ስማቸው ከማይታወቅ ድርጅቶች ጋር በመሆን የአደባባይ ሕዝባዊ ስብሰባ ጠርቷል። የአደባባይ ስብሰባ ማለት ብዙ ከሰልፍ ተለይቶ የሚታይ አይደለም።
የሰማያዊ ፓርቲ ሰኔ ወር 2005 ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰልፍ በማድረግ ታሪክ የሰራ ድርጅት ነው። ወደ ሰባ ሺህ የሚሆን ሕዝብ በሰልፉ ተገኝቶ ነበር። ሰማያዊ ባደረገው ሥራ አንድነቶች ከእንቅልፋቸው ነቅተው የሚሊዮኖች ድምጽ በሚል ተስፋ ሰጪና አገር እቀፍ እንቅሳሴም ለማድረግ ችለዋል። ለዚህ የሰማያዊ ፓርቲ ትልቅ ምስጋና ይገባዋል።
ትንሽ ድጋፍ ሲያገኙና በየቦታው ስማቸው ሲጠራ፣ የሰማያዊ መሪዎች ሌሎች ድርጅቶችን ማሳነስ ጀመሩ። ሊቀመንበሩ ይልቃል «ምን የሚረባ ድርጅት አለ ብለህ ነው?” ብሎ እንደተናገው። በዚህ ምክንያት ከብዙ ድርጅቶች ጋር ሰማያዊ መጋጨት ጀመረ።
የአንድነት ፓርቲ ሚያዚያ 5 2006 በአዲስ አበባ ሰልፍ ለማድረግ ጠየቀ። ገዢው ፓርቲ እውቅና አልሰጥም አለ። ሚያዚያ 12 ተጠየቀ። ያኔም አልተቻለም ወደ ሚያዚያ 26 ሰልፉ ዞር። በዚህ መሃል ሰማያዊዎች በመሃል ገብተው፣ ሚያዚያ 12 ሰልፍ ለማድረግ ጠየቁ። ለአንድነት ተከልክሎ ለነርሱ እውቅና ተሰጣቸው (ያው አገዛዙ ማጋጨት ይወድ የለም) አብዛኞቻችን የሰማያዊ ድርጊት አልተመቸንም። ባይሆን ሰልፉ ከአንድነት ጋር ለምን አይደረግም ብለን ተሟገትን። በይልቃል የሚመራው የሰማያዊ አመራር ግን የአብራችሁ ቁም ጥሪያችንን አጣጣለው። ግትር ሆኑ።
በሰልፉ ቀን፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ለሰማያዊች መልእክቱን አስተላለፈ። ከዘጠኝ ወራት በፊት ወደ ሰባት ሺህ የወጣ ሕዝብ፣ ሰማያዊዎች ግማሽ ሚሊዮን ጠብቀው፣ ከአራት መቶ የማይበልጥ ህዝብ ብቻ ተገኘ። ሰማያዊ ትልቅ የፖለቲካ ክስረት አጋጠመው። በርካታ አባላቱም የአመራሩን ግትርነት መጠየቅ ጀመሩ። በአንድ አመት ዉስጥ የሰማያዉ ድጋፍ ወደ ታች አሽቆለቆለ።
በህዳር ሰባቱ ሕዝባዊ ሰብሰብ ወይም ሰልፍ፣ ከዚህ በፊት ግማሽ ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ይገኛል ብለው የነበሩት ሰማያዊዎች፣ «ወደ ሶስት ሺህ ይገኛል» አሉ። ሶስት ሺህ ሰው ብቻ የሚጠበቁ ከሆነ ለምን በአንድ አዳራሽ ስብሰባዉን እንደማያደርጉት አልገባኝም። ይመስለኛል በወረቀት ሶስት ሺህ ይበሉ እንጂ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ይገኛል የሚል ግምት ዉስጥ ዉስጡን ሊኖራቸው ይችላል።
የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝባዊ ስብሰባዉን አዘጋጀሁ፣ የሚለው ከሌሎች ስምንት ድርጅቶች ጋር ነው። ከነዚህ ድርጅቶች ዉስጥ መኢአድን ስታስወጡት የሚቀሩት ሰባት ናቸው። (ለምን መኢአድ በአሁኑ ወቅት በዉስጥ ችግሮቹ የተጠመደ ስለሆነ)። ሰባቱ ድርጅቶች የኦሞ ህዝቦች፣ የከንባታ ሕዝቦች የመሳሰሉ፣ ጥቂት ግለሰቦችን ያካተቱ፣ የማይታወቁ ድርጅቶች ናቸው። እነዚህን ድርጅቶችን አሰባሰቦ ሰማያዊ ትልቅ ትብብር እንደተፈጠረ ለማስመሰል ተሞከረ እንጂ፣ በዋናነት ይሄንን ስብስበ የሚያንቀሳቅሰው የሰማያዊ ፓርቲ ነው።
ይህን ስጽፍ ከላይ ባየሁት ነው። ዉስጣዊ ድርጅታዊ ሥራ ተሰርቶ፣ በቂ ዝግጅት ተደርጎ ሊሆን ይችላል። በርግጥ ያኔ ብዙ ሳይታወቁ የመጀመሪያዉን ሰልፍ ባደረጉ ጊዜ የተገኘውን ያህል ወደ ሰባ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ከተገኘ፣ በርግጥ ትልቅ ነገር ነው። ለአገዛዙም ጠንካራ መልእክት ለማስተላለፍ ይቻላል።
ሆኖም አንድ ነገር በግልጽ መታወቅ አለበት። ሰልፍ መጥራትና በሰልፉ ዉጤት ማስመዝገብ የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን። ብዙ ተጠብቆ የመጣው ሰው ቁጥር ካነሰ የፖለቲክ ክስረትም ሊሆን ይችላል። ሰማያዊ ፓርቲ ከዚህ በፊት ሰባ ሺህ ሕዝብ ሰብስቦ፣ እንደገና በመቶ የሚቆጠር ሰው ብቻ ከመጣለት፣ ፓርቲው መንገዱን እና ስትራቴጂዉን መቀየር ይኖርበታል እላለሁ። ደርጅቱ እንደዚህ ወደ ታች እንዲያሽቆለቁል ያደረጉ ግትር የአመራር አባላቱን ተጠያቂ ማድረግና መቀየር ያስፈልጋል። እየተደረገ ያለው፣ ብዙዎችን ትልቅ ዋጋ የሚከፍሉበት አገርን ነጻ የማውጣት ትግል እንጂ የግለሰቦችን ወይንም ትናንሽ አማባገነኖችን ተክለ ሰዉነት መገንባት አይደለም።
ለማንኛውም ከእሁድ በኋላ ፣ የድርጅቱን ጥንካሬና የአስቀድሞ ዝግጅት አይተን በስፋት ትንተናዎች እናቀርባለን። የፌስ ቡክ ዘመቻው ግሩም እንደሆነ ታዝቢያለሁ። በሜዳ በየወረዳዉና በየቀበሌውስ ? የምናየው ይሆናል …