ሌ/ጄነራል አበባው ታደሰ ወደ ውጭ ሊወጡ ሲሉ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በደህንነቶች ተመለሱ (ከኢየሩሳሌም አርአያ)

ጄ/ል አበባው ታደሰ ወደ ውጭ ለመውጣት ሲሉ ከቦሌ አየር ማረፊያ በደህንነቶች እንዳይወጡ መደረጋቸውን ታማኝ ምንጮች ጠቁመዋል።
ከመከላከያ የጦር አዛዥነታቸው በጄ/ል ሳሞራ የኑስ እንዲነሱ የተደረጉት ጄ/ል አበባው ከአገር እንዳይወጡ የተደረገበት ምክንያት ግልፅ እንዳልሆነ ምንጮቹ አያይዘው ገልፀዋል። በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ የተለያዩ ጥያቄዎች እንዳሉ በመግለፅ ለኢታማጆር ሹሙ ጄ/ል ሳሞራ ከረር ያለ ሪፖርት ያቀረቡት ጄ/ል ሰዓረ፣ ጄ/ል ሞላና ጄ/ል አበባው መሆናቸውን የጠቆሙት ምንጮቹ በሳሞራ የተሰጠው መልስ « የትምህክተኞች ጥያቄ ነው፤ ችግር የለም..» የሚሉና ጥያቄዎቹን የሚያጣጥሉ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ሶስቱ ጄኔራሎች በሳሞራ ምላሽ በመበሳጨት ከስልጣናቸው ለማስነሳት በምስጢር ቢመክሩም መረጃው ባልታወቀ መንገድ አፈትልኰ ጄ/ል ሳሞራ ዘንድ በመድረሱ ጄ/ል ሰዓረ ከሰሜን ዕዝ አዛዥነታቸው፣ ጄ/ል ሞላ ከአየር ሃይል እንዲሁም ጄ/ል አበባው ከያዙት ስልጣን በሳሞራ በአስቸኳይ እንዲነሱ ሲደረግ በተለይ ጄ/ል አበባው ከ2 ወር በፊት ከመከላከያ እንዲባረሩ መደረጉን ምንጮቹ አስረድተዋል። በጄ/ል ሰዓረ ቦታ ጄ/ል ገብራት አየለ ሲተኩ በጄ/ል ሞላ ደግሞ የአግአዚ ክ/ሰራዊት አዛዥ ጄ/ል አደም መሐመድ መተከታቸውን አስታውቀዋል።
ሁለቱ ጄኔራሎች ዝቅ ባለ ደረጃ ተራ የመምሪያ ሃላፊ ተደርገው መሾማቸውን ምንጮቹ ገልፀዋል። ጄኔራል የመሾምና የመሻር ስልጣኑ የጠ/ሚ/ሩ እንደሆነ ህገመንግስቱ ቢደነግግም ነገር ግን የተጠቀሱት ጄኔራሎች የተነሱት በጄ/ል ሳሞራ ትእዛዝ፣ የተተኩትም በሳቸው ውሳኔ እንደሆነና ጠ/ሚ/ር ሃ/ማርያም ከወራቶች በኋላ እንዲያውቁ ተደርጐ ለተሾሙት ጄኔራሎች የማእረግ እድገት እንዲሰጡ መደረጉን ምንጮቹ አስረድተዋል። ጄ/ል አበባውና ጄ/ል ሰዓረ በሙስና ከተዘፈቁ የጦር አዛዦች እንደሚጠቀሱ አክለው ገልፀዋል። ..ይህ በእንዲህ እንዳለ በመከላከያ ከፍተኛ ግመገማ ከሰሞኑ እየተካሄደ ሲሆን ስር የሰደዱ ቀውሶች እየፈነዱ መሆኑ ታውቋል

ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህን ሰሞን በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ እየተደረገ ባለ ግምገማ ላይ የመከላከያ ሰራዊቱ የአሸባሪ ሃይሎችን መቆጣጠር ካልቻለ እጣው እንደ ደርግ ሰራዊት መበተን ነው ሲሉ የግምገማው መሪዎች መናገራቸው ታውቋል:: በምድር ጦር መምሪያ ስር ባሉ የሰራዊት ክፍሎች በተደረገ ግምገማ በሁሉም አደራሾች ይህ አይነት የመበታተን አደጋ እንዳለ በይፋ ተገልጿል::የአሸባሪ ሃይሎች የተባሉት በሃገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የዲያስፖራ ጽንፈኞች እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን የዲያስፖራ ጽንፈኞች በሃገር ቤት የሚገኙሃይሎችን በመርዳት አመጽ ሊቀሰቅሱ ሕገመንግስቱን ሊያፈርሱ ምናምን የሚል ዛቻ እና ሃይል የተቀላቀለበት መመሪያ ሲሰጥ የነበረ ሲሆን ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የብሄራቸው ስም እየተጠራ እና እየተለየ ሲተቹ እና ሲገመገሙ እንደነበር ታውቋል::