አሁን 2007 እንጂ 1997 አይደለም ያለነው – ግርማ ካሳ
የሺዋስ አሰፋ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባል ነው። ሰማያዊ ከመቋቋሙ በፊት ነው የማውቀው። ሰማያዊ እንደተመሰረተ የሰማሁት ከርሱ ነው። የድርጅቱን ድህረ ገጽ ልኮልኝ ከጅምሩ ስለሰማያዊ ፓርቲ አላማ ይነግረኝ ነበር። የሰማያዊ ፓርቲም ደጋፊ ነበርኩ። ሰማያዊ የመጀመሪያዉን ሰልፍ ሲጠራ በዉጭ ያለን አንድነትን የምንደግፍ ድጋፋችንን ለሰማያዊም እንድንሰጥ መጠየቄን አውቃለሁ። የአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ መዋቅርም በወቅቱ ሰማያዊ በጠራው ሰልፍ መተባበራቸውም አስደስቶኝ ነበር። የሰማያዊ እንቅስቃሴን በመደገፍ ጽሁፍችን አቅርቤያለሁ።
ከመጀመሪያው ሰልፍ በኋላ በአንድነት እና በሰማያዊ መካከል መቀራረቡ እንደሚጠበቀው ባልመሆኑ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ከአንድነት ጋር ቢቻል መዋሃድ ካልተቻለ አብሮ መስራት የሚቻልበትን ሁኔታ እንደ አንድ ዜጋ ፣ አንዳንድ ሐሳቦች በኢሜል ከየሺዋስ ጋር እንለዋወጥ ነበር። በአብሮ መስራት ዙሪያ ሰማያውዊዎችን የተቸሁበት ጊዜ አለ። ሁልጊዜ የምንጻጻፈው በአገር ቤት እንዴት አድርገን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ማድረግ እንደሚቻል ነው።
ታዲያ ይሄን ወዳጄን፣ ሽብርተኛ ብለው ክስ መስርተውበታል። ግንቦት ስባት ነህ ነው የሚሉት። ግንቦት ሰባት የሚባል ነገር ከወሬ በስትቀር የለም። ይሄንንም በሚገባ ያወቁታል። ግንቦቶችም አይነግሩንም እጂ እነርሱም ያወቁትታል። ግን ሕወሃቶች ሁሉንም ግንቦት ስባት ብለው ታፔላ እየለጠፉባቸው ነው። ደና መጠቀሚያ አገኙ።
በጣም የገረመኝ ነገር ደግሞ አለ። ግንቦት ሰባት ነህ ብለው የሺዋስን ቶርቸር አድርገው ሲመረምሩት፣ “እንደነ ግርማ ካሳ ካሉ ግንቦት ሰባቶች ጋር ትገናኛለህ “ እንዳሉት የሚጠቁም አንዳንድ መረጃ ማግኘቴ ነው። የፌስ ቡክ የአገዛዙ ካድሬዎችን እነ ከበደ ካሳ ቢጠይቋቸው ኖሮ “ ራሳችንንማ አናስገምት፤ አገር ይስቅብናል” ይሏቸው ነበር፣ የዚህን ጽሁፍ ጸሃፊ ከግንቦት ሰንባት ጋር ሲያያይዙ።
እንግዲህ የዛሬይቱ የሕውሃት ኢትዮጵያ ይችን ትመስላለች ፣ ዜጎች ያለ አንዳች ምክንያት ወህኒ የሚወረወሩብት ፣ ፍርድ የሚዛባባት ፣ ዳኝነትና የሕግ ስርዓት የሌለባት፣ ጉልበተኞች በእጃቸው ነፍጥ ስላለ ብቻ ያሻቸዉን የሚያደርጉባት፣ አመጽ የበዛባት አገር !!!!
ሌላ ደግሞ ልንገራችሁ። የሺዋስ አሰፋ ግንቦት ስባት ነህ ብለው አስረዉት፣ ሲጠይቁት የነበረው ስለሰማያዊ ፓርቲ ነበር። ሃብታሙ አያለውን “ግንቦት ሰባት ነህ” ብለው በአንድ በኩል፣ “አንድነትን የምትለቅ ከሆነና ከፖለቲካው ከወጣህ እንለቅሃለን “ ነበር ያሉት።
አያችሁ ….ገዥዎችን ግንቦት ስባት አይደለም አያሳሰባቸው ያለው። ያሳሰባቸው አገር ቤት ያሉ በሰላም ሕዝቡን እያነቃነቁና እያደራጁ ያሉ ድርጅቶች ናቸው። ያሳሰባቸው የአንድነት ፓርቲ ነው። ያሳሰባቸው መኢአድ ነው። ያሳስባቸው ሰማያዊ ፓርቲ ነው። ያሳሰባቸው አረና ነው።
በመሆኑም የፈጠራ መረጃ እያቀረቡ፣ በገንዘብ የገዟቸው ወይም በማስፈራራት ያሰለጠኗቸውን ምስክሮች እያሰማሩ፣ እዉነትን አጣመው፣ ጠንካራ የሚሏቸውን የፖለቲካ መሪዎች እንዲሰደዱ ማድረግ (ብርቱካን ሚደቅሳን እንዳደረጉት) ፣ ካልተሰደዱ ደግሞ ማሰር ተግብራቸው ሆኗል።
ጠንካራ የሚባሉ ድርጅቶችን ደግሞ ባላቸው አቅም ሁሉ ለማዳከምና ከጨዋታ ዉጭ ለማድረግ፣ ገላባ የሆኑ እንደ አየለ ጫሚሶ ድርጅት አይነቶቹን ብቻ አሰልፈው፣ ዴሞክራሲ አለ ለማስመሰል፣ እየተሯሯጡ ነው።
ነገር ግን ጥሩ ያለሆነ ዜና አለኝ ለሕወሃት/ኢሕአዴግ። እንደ አንድነት ያሉ ፓርቲዎች የበለጠ ይጠናከራሉ እንጂ አይደክሙም። ብዙ የሺዋሶች፣ ሃብታሙዎች ፣ አብራሃዎች ፣ ዳንኤሎች ይፈጠራሉ እንጂ፣ ጥቂቶችን በማሰር የለውጥ የነጻነት ድምጽ ማፈን አይቻልም። የሚሻላቸው ዘመኑና የሕዝቡ ሁኔታ የተለወጠ መሆኑን ተረድተው፣ ራሳቸውን ለሕዝብ ጥያቄ አስገዝተው፣ ከግትርነት ወጥተው፣ የሕሊና እስረኞችን ሁሉ ፈተው፣ መጪው ምርጫ ፍትሃዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ማድረግ ነው። የሚሻላቸው ከጫካ አስተሳሰብ ወደ ሰለጠነው የ21 ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ መሸጋገር ነው።
እሺ ቢሉ ይጠቅማሉ። እምቢ ቢሉ ግን ያለምን ጥርጥር የሕዝብ ማእበል ይበላቸዋል። ህዝቡ አምሯል። አሁን 2007 እንጂ 1997 አይደለም ያለነው።
ለተቀረነው በዞን ዘጠኝ እስር ቤት ላለነው፣ በሚሊዮኖች ለምንቆጠር ፣ በሚሰራው ግፍ ለምንቆጭ፣ አንድ ነገር መደረግ አለበት ብለን የአጸፋ መልስ ለአምባገነኖች መስጠት የምንልግ ካለን ሕወህቶች ሊያዳክሙት የሚፈልጉትን እንደውም የበለጠ ለማጠናከር መነሳት ነው ያለብን። እርሱም አገር ቤት የሚደረገዉን ሰላማዊ ትግል !!!! እንነሳ። ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን