የአንድነት አባላት በመላ ኢትዮጵያ የማዋከቡ ህገወጥ ተግባር እንዲቆም እንጠይቃለን! አንድነት
በዚህ የምርጫ ወቅት እየተቃረበ ባለበት ወቅት ስርዓቱ የመንግስትን ተቋማት ተገን አድርጎ የአንድነት አባላትን በመላ ኢትዮጵያ በማሰርና በማዋገብ ላይ ይገኛል። ለጥቅምት 25/2007 ዓ.ም. አጥቢያ ላይ በምዕራብ አምርማጭሆ አብርሃ ጅራ ከተማ የሚገኙ የአንድነት አባላት አቶ አንጋው ተገኝ የአካባቢው የአንድነት ሰብሳቢ፣ አቶ አባይ ዘውዱ እና አቶ እንግዳው ዋኘው የተባሉ የአካባቢው የአንድነት አመራር አባላት የፌደራል ፖሊሶች የቤታቸውን በር ገንጥለው በመግባት እየደበደቡ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዷቸው፣ ከዚያም ወደ አልታወቀ ቦታ ወስደው እንደሰወሯቸው ለማወቅ ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪም በመተማ ከተማ የአንድነት ሰብሳቢ የሆኑት በላይነህ ሲሳይ እና በወረታ የአንድነት የአመራር አባል የሆኑት አቶ አለበል ዘለቀ በፖሊሶች በተመሳሳይ ዕለት ተወስዷል።
ባለፈው ሳምንት በወላይታ ዞን የአንድነት አመራች ከፍተኛ ድብደባና ወከባ እንደደረሰባቸው የሚታወቅ ነው። “አዲስ አማኝ ከጳጳሱ ይበልጣል” እንደሚባለው፤ በወላይታ ዞን የኢህአዴግ ካድሬዎች “የእኛ ልጅ መንግስት በሆነበት ሀገር ተቃዋሚዎች ልትንቀሳቀሱ አንፈቅድም” በማለት በዞኑ የአንድነት አመራሮች ላይ ድብደባ መፈፀማቸው እጅግ አሳፋሪ የሆነ ህገወጥ ተግባር ከመሆኑም ባሻገር የስርዓቱን ጋጥወጥነት የሚያሳይ የውንብድና ስራ በመሆኑ አንድነት ያውግዛል።
በወላይታ ዞን ድብደባ የተፈፀመባቸው የአንድነት አባላት አቶ ማሞ ጎሙ የዞኑ የአንድነት ሰብሳቢ፣ አቶ ወኖ በዳሳ የዞኑ የአንድነት የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ እና አቶ አልታዬ አቦታ የዞኑ የአንድነት የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ሲሆኑ ድብደባውን የፈፀሙት ደግሞ መስከረም ካሳ የሶዶ ከተማ ኮብልስቶን ስራ ሂደት ሀላፊና ሁለት የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሰራተኞች ይገኙበታል። ይህን ድብደባ በሚፈፀምበት ወቅት የከተማው ፖሊስ አዛዥ ሻለቃ ሌሊሳ ቆሞ ሲያይ የነበረ ከመሆኑም በላይ ደብደባውን ለማቆምም ሆነ ደብዳቢዎችን ወደ ህግ ለማቅረብ ምንም ዓይነት እርምጃ ሳይወስድ ቀርተዋል።
በመሰረቱ የህግ አካላት የዜጎችን ድህንነት የማስጠበቅና ህግ የማስከበር ሀላፊነት እንዳላቸው የሚታወቅ ነው። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ህገ ወጥ ወንጀል ሲፈፀም የፀጥታ አስከባሪ አካል ሆኖ ቆሞ ማየትና ምንም ዓይነት እርምጃ ያለመውሰድ ፍፁም ወገንተኝነት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ በህግም የሚያስጠይቅ ነው። አንድነት በሰላማዊ ትግል የሚታል ህጋዊ ፓርቲ ቢሆንም በገዥው ፓርቲ የተለያዩ ስሞች እየተሰጡት አመራቹና አባላቱ የማሰሩና የማንገላቱ ሁኔታ በስፋት እየቀጠለ ነው የሚገኘው። አንድነት ይሄ ጉዳይ ወደ ህግ እንደሚወስደውና ወንጀለኞች ደግሞ በፈፀሙት ወንጅል ልክ እንዲቀጡ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ ይፈልጋል።
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ
ጥቅምት 25/2007
አዲስ አበባ