በደቡብ ጎንደር የፎገራ ወረዳ እንዲሁም በምዕ/ጎጃም ደጋ ዳሞተ የአንድነት አባላትን ማሰሩ ቀጥሏል
በደቡብ ጎንደር የፎገራ ወረዳ የአንድነት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አለበል ዘለቀ በዛሬው ዕለት ከሚሰሩበት የእርሻ ቦታቸው ላይ በፌዴራል በፖሊስ ተይዘው ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውን እንዲሁም በአማራ ክልል ምዕ/ጎጃም ደጋ ዳሞት ወረዳ የወረዳው አንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን አበበ በተጨማሪም በወረዳው ያሉ 3 የአንድነት አባላት ከቤታቸው በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸው ከስፍራው ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ የደረሰው ዜና አመለከተ፡፡
በሰሜን ጎንደር ምዕ/አርማጨሆ ብርሃጅራ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩት የአንድነት ፓርቲ የአመራር አባላት ከታሰሩበት ሰዓት አንስቶ የከተማው ነዋሪ ልጆቻችንን አሳልፈን አንሰጥም በማለት ፖሊስ ጣቢያውን ከቦ እንዳይወስዷቸው ዋናው መንገድ ላይ ሲጠባበቅ በሌላ መንገድ ወደ መተማ መስመር ወዳልታወቀ ስፍራ እንደወሰዷቸው የአብርሃጅራ ከተማ የዜና ምንጮቻችን ለፍኖተ ነፃነት ዝግጅት ክፍል ገለጹ፡፡ በተለይ በፓርቲው አባላት ላይ የሚደረገው ማሳደድ፣ ማንገላታትና እስር አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በተመሳሳይም የመተማ የአንድነት ሰብሳቢ አቶ በላይነህ ሲሳይ መታሰራቸውን ቀደም ሲል ፍኖተ ነፃነት መዘገቧ ይታወሳል፡፡