ቅዱስ ሲኖዶስ 141 ሚልዮን ብር ዓመታዊ በጀት አጸደቀ፤ የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ነገ ይጠናቀቃል፤ ጋዜጣዊ መግለጫም ይሰጣል

Holy Synod Fathersውጥረት በተመላበት ኹኔታ ተጀምሮ ተጋግሎ የሰነበተውና በመጨረሻም ወደ መግባባትና አንድነት የመጣው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ÷ ለኹለት ሱባዔ ያኽል ሲያካሒድ የቆየውን የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን ነገ፣ ጥቅምት ፳፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከቀትር በፊት ያጠናቅቃል፡፡

Holy Synod endingበስብሰባው ማጠናቀቂያ÷ ቅዱስ ሲኖዶስ መሰንበቻውን ስለተነጋገረባቸው ጉዳዮች፣ ስላሳለፋቸው ውሳኔዎችና ስለወሰዳቸው አቋሞች የምልአተ ጉባኤው ርእሰ መንበር ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በንባብ የሚያሰሙት ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥ ሲኾን የቅዱስ ሲኖዶሱ ቃል አቀባይ በኾኑት በቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ የሚመራ ጋዜጣዊ ጉባኤም ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

001kklkkk 003ምልአተ ጉባኤው በትላንት ከቀትር በኋላና በዛሬው ውሎው፣ በሥራ ላይ በቆየባቸው ቀናት የመከረባቸውንና ውሳኔ ያሳለፈባቸው ቃለ ጉባኤዎች በመናበብ የአባላቱ ፊርማ እንዲያርፍባቸው አድርጓል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶሱ የተወሰኑ ውሳኔዎች፣ የወጡ ሕግጋት፣ ደንቦችና መመሪያዎች በቅዱስ ሲኖዶሱ ጽ/ቤት አማካይነት ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ለሚመለከታቸው አካላት የሚተላለፉ ሲኾን በተግባር ላይ ስለመዋላቸው በቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ክትትል ተደርጎ ስለአፈጻጸማቸው ለቅዱስ ሲኖዶሱ የሥራ አፈጻጸም ዘገባ የሚቀርብባቸው ይኾናል፡፡

ጥቅምት ፲፩ ቀን በመክፈቻ ሥርዐት ጸሎት በተጀመረው የምልአተ ጉባኤው ስብሰባው ለቀናት ሲመክር የሰነበተው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ፣ ተወያይቶ ካጸደቃቸው ዐበይት አጀንዳዎች አንዱ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ አስተዳደርና ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውለው ዓመታዊ በጀት ነው፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት÷ የቤተ ክርስቲያናችንን አጠቃላይ የምጣኔ ሀብትና የሙዓለ ንዋይ አስተዳደር መመሪያዎችን (ፖሊሲዎችን) የመወሰን፣ ዓመታዊ በጀቷን የማጽደቅና ተግባራዊነቱን የመቆጣጠር ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶስ ተግባርና ሓላፊነት ነው፡፡

ዓመታዊ የሥራ ዕቅዱንና በጀቱን በየደረጃው ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላትና የሥራ ዘርፎች ተሰብስቦ በሒሳብና በጀት መምሪያ አማካይነት እንዲዘጋጅ የማድረግ፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ ሲጸድቅም በበጀት የተመደበውን ከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊውና ከፋይናንስ መምሪያው ሓላፊ ጋራ በመኾን በፊርማው የሚያንቀሳቅሰው የቤተ ክህነቱ ዋና ባለሥልጣን ደግሞ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ነው፡፡

በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተጠንቶና ተዘጋጅቶ በቋሚ ሲኖዶሱ በቀረበለት የ፳፻፯ ዓ.ም. የሥራ ዕቅድና በጀት ላይ የመከረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ታዲያ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ አስተዳደርና ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውል ብር 141 ሚልዮን ማጽደቁ ነው የተገለጸው፡፡

በምልአተ ጉባኤው ላይ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሒሳብና በጀት መምሪያ ሓላፊዎች የተሰጠው ማብራሪያ፣ ከበጀቱ በአመዛኙ ከሐዋርያዊ ተልእኮ (ስብከተ ወንጌልን ከማስፋፋትና ከማጠናከር) ጋራ ለተያያዙ ተግባራት፤ ለአብነት ት/ቤቶች እና ለገዳማት ድጋፍ እንዲኹም ለአህጉረ ስብከት የሥራ ማስኬጃ ድጎማ መደልደሉ የተመለከተ ሲኾን በካፒታል በጀት አንጻር የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት በቸርችል ጎዳና የሚያስገነባው ሕንፃ ማስጨረሻና የአኵስም ጽዮን ቤተ መዘክር ዲዛይን ክፍያም ተጠቃሽ ወጪዎች እንደኾኑ ተጠቅሷል፡፡

በበጀት ድልድሉ የሐዋርያዊ ተልእኮ እንቅስቃሴ ቀዳሚውን ድርሻ መያዙ÷ አዲስ አማንያንን በየጊዜው ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመጨመርና የምእመናንን ፍልሰት ለመግታት ዋናው መፍትሔ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋትና ምእመናን በእምነታቸው እንዲጸኑ ማድረግ ከመኾኑ አኳያ፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎታችን ተጠናክሮ የሚቀጥልበት አስፈላጊው ጥረት ኹሉ እንዲደረግ በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከተያዘው አቋም የሚነሣ ነው፡፡

የአህጉረ ስብከት የበጀት ድጎማን በተመለከተ፣ በ፳፻፮ ዓ.ም. ከእያንዳንዱ ሀገረ ስብከት በቀረበው የዘመኑ የገቢ ሪፖርት መሠረት÷ ከኃምሳው አህጉረ ስብከት ኻያ ኹለቱ ራሳቸውን በገቢ ችለው ትርፍ የሚያስገቡ ሲኾኑ ራሳቸውን ያልቻሉት ኻያ ሰባት አህጉረ ስብከት ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ድጎማ እንደሚደረግላቸው ተገልጧል፡፡

የአብነት ት/ቤቶቻችንን ለመጠበቅ፣ ለማሳደግና ለማስፋፋት በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነው አምስት ከመቶና ከመንበረ ፓትርያርክ የተመደበው በጀት ለአብነት ት/ቤቶች መምህራንና ተማሪዎች ብቻ እንዲደርስ ክትትሉና ቁጥጥሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት በአጠቃላይ ጉባኤ ደረጃ አቋም ተይዞበታል፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ደረጃ የቤተ ክርስቲያናችን ዓመታዊ በጀት መሠረት የኾኑት ገቢዎች አጠቃላይ ምንጮች፡-

በቃለ ዓዋዲው እንደተደነገገው፡-
አህገረ ስብከት ከሰበካ ጉባኤ ክፍያና ከማናቸውም ገቢያቸው የሚከፍሉት 35 በመቶ ፈሰስ፤
የአ/አበባ ሀ/ስብከት ከሰበካ ጉባኤ ክፍያና ከማናቸውም ገቢው የሚከፍለው 65 በመቶ ፈሰስ፤

የልማት ድርጅቶች/ተቋማት ገቢ፡-
የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የኪራይ ገቢ
የቁልቢ ደ/ኃ/ቅ/ገብርኤል ገዳም ንዋያተ ቅድሳት ማደራጃ መምሪያ
የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት የመጽሐፍ ሽያጭ
የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት
የአልባሳት ማደራጃ መምሪያ(ማምረቻና ማከፋፋያ)
የጎፋ ጥበበ እድ ካህናት ማሠልጠኛ፤

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የበጀት ድጎማ (እስከ አንድ ሚልዮን ብር)
የመንበረ ፓትርያርኩ ልዩ ልዩ የውስጥ ገቢዎች
ከመንግሥት የሚሰጥ ኹለት ሚልዮን ብር ድጎማ (ስላልተመለሱ ቤቶች) ናቸው፡፡

ይኹንና ከእኒኽ አጠቃላይ የገቢ ምንጮች ውስጥ÷ የአህጉረ ስብከትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ፈሰስ፣ የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የኪራይ ገቢ እንዲኹም የቁሉቢ ንዋያተ ቅድሳት ማደራጃ መምሪያ እንደ ቅደም ተከተላቸው በየዓመቱ ቀጣይ ዕድገት የሚመዘገብባቸውና ከፍተኛ ገቢ የሚገኝባቸው ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ጉባኤው የጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት እንደተደመጠው÷ ከኃምሳው አህጉረ ስብከት ከ95 ሚልዮን ብር በላይ የፐርሰንት ገቢ ተገኝቷል፤ ይህም ከአምናው ጋራ ሲነጻጸር ከ16 ሚልዮን ብር በላይ ብልጫ የተመዘገበበት ነው፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ገቢ በዚኽን ያኽል ካደገ የአህጉረ ስብከትና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ገቢም ከዚኽ በበለጠ እያደገ ለመኾኑ አያጠያይቅም፡፡

በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ አንቀጽ ፶ ንኡስ አንቀጽ (፬) እና (፭) መሠረት፣ በማናቸውም ደረጃ የሚገኘው የሰበካ አስተዳደር የበጀት ዓመት ሐምሌ ፩ ቀን ተጀምሮ ሰኔ ፴ ቀን ይዘጋል፡፡ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ በየደረጃው የተጠናቀረው የንብረት አያያዝና አጠባበቅ፣ የገንዘብ ገቢና ወጪ ሒሳብና የሥራ ክንውን ሪፖርት እስከ ሐምሌ ፴ ቀን ድረስ መንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት መድረስ አለበት፤ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትም የበኩሉን አጥንቶና አጣርቶ ዓመታዊው ሪፖርት እስከ ነሐሴ ፴ ቀን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እንዲደርስ ያደርጋል፡፡

የአህጉረ ስብከቱ ዓመታዊው የፈሰስ ሒሳብ መመዝገቢያ ቅጻቅጾችና ሪፖርቶች እስከ ነሐሴ ፴ ቀን ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ይድረሱ እንጂ አህጉረ ስብከቱ ፈሰሱን ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ገቢ የሚያደርጉት በጥቅምቱ የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ወቅት ነው፡፡ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤትም ከኹሉም አህጉረ ስብከት ባሰባሰበው ገቢ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዓመታዊ በጀት ከላይ እስከ ታች እንዲጠና አድርጎና ቀምሮ ለጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ በማቅረብ ሲወሰንለት ለልዩ ልዩ ሥራዎች ያውለዋል፡፡

እዚኽ ላይ የቤተ ክርስቲያናችንን የበጀት ዓመት (budget calendar) የተመለከተ ጥያቄ መነሣቱ አልቀረም፡፡ ይኸውም በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ መሠረት በማናቸውም ደረጃ የሚገኘው የሰበካ አስተዳደር የበጀት ዓመቱ ሐምሌ ፩ ቀን በሚጀምርበት ኹኔታ በጀቱ የሚጸድቀው ግን መደበኛውን የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ጠብቆና በሦስት ወራት ዘግይቶ መኾኑ ጥያቄ እየተነሣበት ይገኛል፡፡ የበጀት ዓመቱ በሐምሌ ቢጀመርም በጀቱ እስከሚጸድቅበት ጥቅምት ወር ድረስ በታሳቢና በማብቃቃት እየሠሩ እንደሚቆዩ በመግለጽ አስተያየት የሰጡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች ‹‹ባልገባና ባልጸደቀ በጀት እንዴት ሥራ ማስጀመር ይቻላል?›› በማለት ይጠይቃሉ፡፡

የአህጉረ ስብከት የፈሰስ አስተዋፅኦ እስከ ግንቦት ተሰብስቦ በርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ኹለተኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ተቀምሮ የሚጸድቅበት፣ ሰኔ የዝግጅት ወር ኾኖ በሐምሌ የበጀት ዓመቱ የሚጀምርበት አሠራር እንዲጤን ይጠይቃሉ፤ የዘመን አቆጣጠር ባለቤት የኾነች ቤተ ክርስቲያን የራስዋ የበጀት ዓመት ሊኖራት እንደሚችል በመጠቆም የበጀት ዓመቱ በጥቅምት የሚጀመርበትና መስከረም ፴ የሚዘጋበት አማራጭ ሊታይ እንደሚችልም ያመለክታሉ፡፡

በሌላ በኩል በጀመርነው በጀት ዓመት ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዘመናዊውንና ለቁጥጥር አመቺ የኾነውን የኹለትዮሽ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ ሥርዐት የሚጀምርበት ሲኾን ከዚኹ ጋራም የመምሪያዎች ገቢዎች በአንድ ቋት የሚሰበሰብበት (የገቢ ማእከላዊነት) አሠራርም በቋሚ ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት ተፈጻሚ ለማድረግ እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡

በዚኽም መሠረት ከኅዳር መጀመሪያ አንሥቶ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ፣ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ፣ የቅርሳ ቅርስ ቤተ መጻሕፍትና ወመዘክር መምሪያ እና የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ለየራሳቸው የነበራቸው የሒሳብ ቋት ታጥፎ ገቢያቸው ወደ ማእከላዊ ቋት ገብቶ በበጀት እየወጣ እንዲጠቀሙ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡

መምሪያዎቹ የገቢ ማእከላዊነቱን ቢደግፉትም የሥራ ማስኬጃ በጀታቸውን ግን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ አለመደረጉ ለቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድ እንደሚዳርጋቸው ይናገራሉ፡፡ የተተከለው የኹለትዮሽ የሒሳብ ሥርዐት ለቁጥጥርና ለተጠያቂነት አመቺ በመኾኑ የሥራ ማስኬጃ በጀቱን የሚጠቀሙበት አሠራር ከሒሳብ መመሪያው ጋራ እንዲጣጣም ይጠይቃሉ፡፡ የተሻሻለው የሒሳብ አሠራር ውጤታማነትና የበጀት ቀመሩም ለየመምሪያዎቹ ከተሰጣቸው ተልእኮ አንጻር በተገቢነት የሚታይበት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ሊዘጋጅ እንደሚገባው ያሳስባሉ፡፡

በአጠቃላይ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ እንዳወሱት፣ በኃምሳ ሳንቲም የጀመረው የሰበካ ጉባኤ አስተዋፅኦ ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የአቅም ማደግ፣ የራስን አገልግሎትና የልማት ዕቅዶች በራስ አቅም የመፈጸም ትልሟን የሚጠቁም ነው፡፡ ነገር ግን መሰብሰብ ብቻ ሳይኾን የተገኘውን የእግዚአብሔር ገንዘብ በተገቢው የሒሳብ አያያዝ ሥርዐት በጥንቃቄ በመያዝና ለሚገባው አገልግሎትና ልማት ለማዋል፤ የቤተ ክርስቲያንን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግና በራሷ ምእመናንና ልማት ላይ የተመሠረተ ሉዓላዊ ክብሯን ለመጠበቅም ተግተን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡