ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ
ኤድዋርዶ ባይሮኖ
የስነጽሁፍ ሰው እንዳይሉት ለአንባቢያን በትኖአቸው ያለፈው ድንቅ መጣጥፎቹ ከስነ-አይምሮ ፈጠራ አድማስ ባሻገር የላቁ፥ የዘንድሮን ደርሶ ብሄርተኛ ጦማሪዎችን ክፉ ባህሪ እና የሰይጣናትን ስነልቦና ያልተላበሰው፥ ከታላቁ የወሎ ርሀብ በኋላ በደራሲ ብርሀኑ ዘርይሁን ብሩህ ብዕር ተስሎ በመጽሀፍት አለም የኖረውን በጎ ሰው የአያ ሙሔን ገጸ-ባህሪ በእውን የያዘው በዚህ ምስል ላይ በሰተግራ በኩል የሚታየውን አይደገሜው አቶ ጳውሎስ ኞኞን እናስታውሰው።

በምዕራባውያን አቆጣጠር በ1990ወቹ ላይ ያለፈው አቶ ጳውሎስ በእለት ዕለፈቱ ዋዜማ ስድስት የተለያዩ እስካሁን ድረስ ለሕትመት ያልበቁ መጽሀፍት እና አንድ ግዙፍ የኢትዮጲያን ህብረተሰብ የዘመናት ታሪካዊ ጉዞ እና ትዕይንቶችን የሚያወሳ በተለያዩ ዕርዕሶች ስር በተለያዩ መረጃወች ተደግፎ የተጻፈ በፈረንጅ አፍ “Encyclopedia “ ተብሎ የሚታወቅ ታላቅ ስራውን ትቶልን አልፎአል። እነዚህ ስራዎቹ በታማኝ ሰዎች እጅ ስለሚገኙ ጊዜ ሲፈቅድ ታትመው ለትውልድ ይከፋፈላሉ።
የእዚህን ከእንግዲህ የዘመን አውድማ ክምር የማይመልሰው ውድ የኢትዮጲያ ልጅ የህይወት ታሪክ እናንተ ከዚህ ጦማር ግርጌ ካለው ሰንዱቅ ውስጥ ትዘክሩልኝ ዘንድ አልፌዋለሁ። በሶሻሊስት ደርግ ስርዕት አቶ ጳውሎስ በጊዜው ለነበሩት አንድ የመንግስት ሹም በጻፈው ልብ በሚነካው ደብዳቤ ላይ ለህትመት ያቀረባቸው ሁለት ትላልቅ የታሪክ መጽሀፍት በኩራዝ አሳትሜ ድርጅት እንደተሰረቁበት አሳውቆ ከዛም እንዲያስመልሱለት በእጅግ ተማጽኖ ሳይመለሱለት ቀርተዋል።
የመለኮታዊ ጥበብ ተክኖ አሮጌ ሱፍ፥ የተገነጠለ ጫማ ተላብሶ የደከመ ኑሮ እየኖረ፥ ህብረተሰብ ያስተማረው ያነቃው እና ትውልድ ያነጻው ታላቁ ጳውሎስ ኞኞ፥ ፈጣሪ መጥኖ በጠራው ዘመን ተወልዶ የአቅሙን አስተዋጾ አብርክቶአል። ታዲያ የዚህ አይነቱ እንቁ ሰው አለፈ እንጂ ሞተ አይባልም። ዛሬ ደግሞ ይህን ሰው እናስታውሰው። ከቶ ደንብ አይደለምና የሄደን በቃ ሄዶአል ብለህ ልቦናህን አትዝጋ።