ቅዱስ ሲኖዶስ ለኹለት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ምደባ ሰጠ
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬ፣ ጥቅምት ፳፬ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የቀትር በፊት ውሎው በተመለከተው የሊቃነ ጳጳሳት ዝውውርና ምደባ አጀንዳ፣ የሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ጉዳይ በመመልከት ለኹለት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ምደባ ሰጥቷል፡፡
በዚኽም መሠረት በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዳንኤል÷ የድሬዳዋ እና ምዕራብ ሐረርጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው እንዲሠሩ መድቧቸዋል፡፡
የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ አህጉረ ስብከታቸውን እንደያዙ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ ኾነው እንዲሠሩ መድቧቸዋል፡፡
ብፁዕነታቸው የተተኩት፣ የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ኾነው ሲሠሩ በቆዩትና ተደራራቢ ሓላፊነት በነበራቸው የሶማሌ/ጅግጅጋ/ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ በኾኑት ብፁዕ አቡነ ያሬድ ምትክ ነው፡፡

