በአገረ አሜሪካ የልጆቻችን ውጤት እንዴት ነው? (በወርቁ ለገሠ)
ዛሬ ይህን ለመጻፍ ያነሳሳኝ ብዙ አሜሪካውያን ስለትምህርት ጥራትና ስለልጆቻቸው መጻዔ ዕድል ሲጨነቁ ስሰማ ኢትዮጵያውያንም ይጨንቀቁ ይሆን? ለሚለው ጥያቄ እነሱ ሳይሰሙን በአማርኛ ሹክ እንድትሉኝ ነው። “እየበሉ እየጠጡ ዝም የጋን ወንድም እንዳይሆን” ወላጆች ያላችሁን ልምድ ማካፈል ይጠበቅባችኋል።
መቼም አገር ለቆ የተሰደደ ኢትዮጵያዊ አመጣጡ በፖሊቲካም ይሁን በዲቪ አሜሪካ ገብቶ ሊያገኘው የሚችለው ትሩፋት “ልጆቹን አስተምሮ ጥሩ ደረጃ ላይ ማድረስ ነው። ትክክል ነው። አንድ ልጅ እንደ አሜሪካ በቴክኖሎጅ የመጠቀ ኢኮኖሚ ውስጥ የሥራ ዕድል እንድያገኝ ለማድረግ የሚወጣው የትምህርት ወጭ 400000 እንደሚደርስ ይገመታል። የታይፕ ስህተት አይደለም. አራት መቶ ሽህ ዶላር! ታዲያ 4 ልጅ አሜሪካ ያስተማረ ሰው ያገኘውን ጥቅም በልጆቹ ቁጥር አባዝቶ፣ ወደብር መንዝሮ ካሰላው ግንባሩን ሰማይ እስኪመታው ድረስ መጓዙ ተገቢ ነው።
ነገር ግን ልጆቻችን አሜሪካ እያገኙ ያሉት ትምህርት በርግጥ ለመጭው ህይወታቸው የተሻለ ዕውቀት የሚያስጨብጥ ነዎይ? የሚለውን አንስቶ መነጋገር ተገቢ ነው።በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ተማሪዎች ከአውሮፓ ጋር ሲነጻጸሩ በሳይንስም ሆነ በሂሳብ ችሎታቸው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
Trends in International Mathematics and Science Study ዘገባ እንደሚያስረዳው አሜሪካ የሚማሩ የ4ኛ ክፍል ተማሪዎች የሂሳብ ውጤታቸው ከሆንግኮንግ፣ ሲንጋፖር፣ ቻይና፣ ቴይፒ፣ ጃፓን ካዛኪስታን ሩሲያን ፌደሬሽን፣ ኢንግላንድ፣ ላቲቪያ፣ ኔዘርላንድስና ሊይቲያኒያ በታች ሆኗል። በተመሳሳይ የሳይንስ ፈተና ውጤታቸው ከሲንጋፖር፣ ቻይና፣ ቴይፒ፣ሆንግኮንግ፣ ጃፓን ካዛኪስታን ሩሲያን ፌደሬሽን፣ ላቲቪያ፣ኢንግላንድ በታች ሆኖ ተገኝቷል። ላለፉት 12 ዓመታት ከጃፓን በስተቀር ከላይ በተጠቀሱት አገሮች የተማሪዎች የሳይንስ ውጤት ከፍተኛ መሻሻል ሲታይ የአሜሪካ ተማሪዎች ውጤት ደግሞ እንዳሽቆለቆለ መሆኑን ስንገነዘብ ወላጅ የሚያስደነግጥ ዜና ነው። እፎይ! የኢትዮጵያ ውጤት እዚህ ለንፅፅር አልቀረበም።
አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በኢንተርኔት (በተለይ ፌስቡክ)፣ አይፖድ፣ በቴሌቭዥንና በጌም ሱስ ስለተጠመዱ ነው በማለት እነዚህን ነገሮች እስከመከልከል ደርሰዋል። በአንድ ቴሌቭዥን ፕሮግራም እንደሰማሁት ደግሞ ወላጆች ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሁለት ሥራ ሲሰሩ ዱርዬዎች በወላጆች ቦታ ቤት ይገቡና ታዳጊ ወጣቶችን ለተለያዬ ሱሳና መዘናጋት እንደሚዳርጓቸው መረጃዎች አሉ ይላሉ። ከናትና አባት ያጡትን ፍቅርና እንክብካቤ ከዱር ቤቴዎች ለማግኘት ይሞክራሉ ማለት ነው።
ለነገሩ የአበሻ ልጆች አሜሪካ ከተወለዱት የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ የሚልም ተባራሪ ወሬ እሰማለሁ። ዕውነት ከሆነ ያድርግልን ነው የምለው። የአሜሪካ ልጆች ስፔሊንግ በትክክል የማይጽፉ ከሆነ ምናልባት ደህና ሲታጣ ይመለመላል ጎባጣ እንድሉ የኛን ልጆች “A” እየተሰጠ እንደሁ መጠርጠር ተገቢ ነው። በዚያ ላይ ደግሞ ብዙዎቹ የአሜሪካ ተማሪዎች በግል ት/ቤት ስለሚማሩ የኔ ቢጤው ልጆቹን የሚልክበት ት/ቤት ያን ያክል ተወዳዳሪ ሊኖረው እንደማችልም ግምት ውስጥ ይግባ።
ለማጠቃለለ ልጆቻችን በፍጥነት እየተለወጠ በመሄድ ላይ ባለው የአሜሪካ ህይወት ውስጥ ሠርቶ የመኖር ዕድላቸው ከፍ እንድል ከፈለግን ት/ቤት በሚያገኙት ዕውቀት ላይ ተስፋ መጣል የለብንም። እኛም ማስተማር፣ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንድጠቀሙ መርዳት፣ ከቴሌቭዝንና ኢንተርኔት ጋር ያላቸውን ግንኙነት መወሰን፣ የቅርብ ክትትልና እገዛ ማድረግ ለአሜሪካ ት/ቤቶች የሚተው ሳይሆን የወላጆች ሃላፊነት ነው።
የትምህርት ነገር ያሳስባችኋል? እስቲ እንወያይበት።
ወርቁ ለገሠ (11/14/10)