ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾኑ

abune-qelemntos2

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፤ የከምባታ ሐዲያ ጉራጌና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ የበላይ ሓላፊ

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬ፣ ጥቅምት ፳፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ዐሥረኛ ቀን የቀትር በፊት ውሎው ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው እንዲሠሩ መደበ፡፡

ብፁዕነታቸው፣ ትላንት በተጠናቀቀው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ፣ የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ኾኖ በተደነገገው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው እንዲሠሩ በምልአተ ጉባኤው የተመደቡት በርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከተጠቆሙ በኋላ ነው፡፡

ምደባው አስመራጭ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሦስት ዕጩዎች ከተለዩ በኋላ በዕጣ እንዲከናወን ታስቦ እንደነበር ተገልጧል፡፡ ይኹንና በፓትርያርኩ ጥቆማ እንዲወሰን የተደረገው፣ የመንበረ ፓትርያርኩ መቀመጫ የኾነው አዲስ አበባ የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት በመኾኑ ጥቆማውም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንዲሰጥ ምልአተ ጉባኤው ከተስማማበት በኋላ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሀገሪቱ ርእሰ ከተማ ስለኾነና ከሌሎች አህጉረ ስብከት የሚለይባቸው ልዩ ኹኔታዎች በመኖራቸው እኒኽን ከግምት ያስገባ የተለየ አወቃቀርና የፐርሰንት አከፋፈል ሥርዐት እንደሚኖረው በተሻሻለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ሰፍሯል፡፡

በሀገረ ስብከቱ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች በቅዱስ ፓትርያርኩ የሚሾሙት በሕጉ÷ ስለ ትምህርት ዝግጅት፣ የአገልግሎት ልምድ፣ ግብረ ገብነት፣ የካህናትና ምእመናን አመኔታና ተቀባይነት የተዘረዘሩ የብቃት መስፈርቶች በሊቀ ጳጳሱ ሰብሳቢነት በሚመራው በሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ተመርጠው የምርጫው ውጤት ለቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ መኾኑ ተደንግጓል፡፡