ግንቦት ሰባት በተባበሩት መንግስታት ራዳር ዉስጥ ገባ – – ግርማ ካሳ
በቅርቡ፣ ግንቦት ሰባት የተባለው ድርጅት ፣ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የሶማሊያና የኤርትራ ሞኒተሪንግ ግሩፕ በለቀቀዉ ሪፖርት ዙሪያ አንድ መግለጫ አዉጥቷል። አንዳንድ የተወሰኑ ድህረ ገጾች የግንቦት ሰባትን መግለጫ ለጥፈው፣የተባበሩት መንግስታ ሪፖርትን ግን ሳያያይዙ ቀርተዋል። ይሄን ሰነድ በሚከተለው ሊንክ ልታገኙት ትችላላሁ፡
http://www.un.org/ga/search/view_doc.as … S/2014/727
አስገራሚ መረጃዎችን ያካተተ ሰነድ ነው። ሰነዱ አልፎ አልፎ አንዳንድ ጥቃቅን ግድፈቶች አሉት። ለምሳሌ ግንቦት ሰባትን የአማራ ድርጅት እንደሆነ የገለጹበት ሁኔታ አለ። ከዚያ ዉጭ ከሞላ ጎደል በሰነዱ የተካተተው ዝርዝር፣ የሚታመን ነው ብዬ አስባለሁ። በዚህ ሪፖርት ላይ በስፋትና በቅርብ ጊዜ ትንታኔ እንሰጥበታለን። ግን ለአሁን በግርድፉ አንብቤ ከሰነዱ ያገኙኋቸውን ጥቂት አንኰ ነጥቦች እንዳስቀመጥ ይፈቀድልኝ፡
1) ኦ.ኤን.ኤል፣ኤፍ ከአልሻባብ ጋር እንደሚሰራና ማእከሉን ከኤርትራ ወደ ሶማሊያ እንደወሰደና አሁን ኤርትራ ከበስተጀርባ ሆና መደገፏን እንደቀጠለች
2) ኦነግ የሚባል ነገር እንደሌለ
3) የግንቦት ሰባት ጦር ከ50 እስከ 70 እንደሆነ
4) ደሚት የሚባለው ድርጅት ትልቁና ጠንካራው እንደሆነ፣ ከሕወሃት ተቃዋሚነት አልፎ የኢሳያስ ክብር ዘበኛና ቅልብ ጦር እንደሆነና ከባባድ መሳሪያዎች ከኤርትራ ጦር እየተወሰደ ወደ ደሚት እየተሰጠ እንደሆነ
5) ሻእቢያ ለግንቦት ሰባት ሆነ ለሌሎች ድርጅቶች የሚያደርገው እርዳታ የተባበሩት መንግስታትን ዉሳኔ የሚያፈርስ እንደሆነና ግንቦት ሰባት በተባበሩት መንግስታት ራዳር ዉስጥ እንደወደቀ
በቅርቡ ኢትዮጵያያ ሪቪው የተለያዩ ሪፖርቶች ሲያቀርብ እንደነበረ የሚታወቅ ነው። የዚህ ሞኒተሪንግ ቡድን ሪፖርት በአብዛኛው ኢትዮጵያ ሪቪው ካቀረበው ጋር የሚዛመድ ነው።
በተያያዘ ዜና ደግሞ በኤርትራ ዉስጥ ከፍተኛ ተቃዉሞ በኢሳያስ አፈርቂ አገዛዝ ላይ እየተነሳ እንደሆነ ነው። ሃርነር አርቢ የሚባለው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ድጋፍ እያገኘ ነው። በጦር ሰራዊቱ ዉስጥ ሁሉ ዘልቆ ስለገባ ፣ ኢሳያስ ፊቷን ወደ ደሚት ለማዞር እስኪገደድ ድረስ።
በ ኤርትራ ያለው ሁኔታ ይህ ሆኖ እያለ የተከበሩ ዶር ብርሃኑ ነጋ፣ ከአሜሪካን አገር ሳይወጡ ለምን የግፈኛው አቶ ኢሳያስ ተሟጋች እንደሆኑ አልገባኝም ? እርሳቸውስ እሺ ሌሎች የግንቦት አባላትና ደጋፊዎች፣ እንደ አበበ ገላው፣ መቼ ይሆን አንድ ግለሰብን ማምለክና መከተል አቁመው ለሕዝቡና ለትግሉ የሚጠቅም ነገር የማያደርጉት ?
የግንቢት ሰባት ንቅናቄ የተሳሳተ መንገዱን በአስቸኳይ መመርመር አለበት። ኢሳያስ ሊገነደስ ጥቂት ጊዜ የቀረው የበሰበሰ ዛፍ ነው። እስከመቼ ነው በበሰበሰ ዛፍ ላይ ተንጠልጥለው ትግሉን ብለው ወደነርሱ የመጡትን ለጋ ኢትዮጵያዉያን የሚያስበሉት ?