ቅዱስ ሲኖዶስ: የፓትርያርኩን የአጠቃላይ ጉባኤ የስብሰባ አመራር በመገምገም ለሥነ ሥርዐቱ መከበር ውሳኔና መመሪያ ሰጠ፤ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቅ ላይ መወያየት ጀመረ

  • ምልአተ ጉባኤው በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው የጋራ መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ ላይ መክሮ አጽድቋል፤ በሥራ ላይ እንዲውልም መመሪያ ሰጥቷል፡፡
  • ከአጠቃላይ ጉባኤው አጀንዳ ውጭ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ለማስወሰን ታቅዶ በፓትርያርኩ ግፊትና በአማሳኞች ውትወታ የተከፈተው መድረክ÷ ስብሰባው ‹‹ባለቤት የለውም ወይ?›› ያሰኘና የአጠቃላይ ጉባኤው ክብረ ሞገስ በርእሰ መንበሩ አመራርና የቀጥተኛ ተሳትፎ መብት በሌላቸው አማሳኞች ሥርዐት አልባነት የተጣሰበት እንደነበር ገምግሟል፡፡

the heavily corrupt Haile Abreha barking on the multitude of the participants of the 33rd gen assembly

  • በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ የማሻሻያ ረቂቅ÷ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ለቅዱስ ሲኖዶሱ ተጠሪ የሚያደርገውንና የቅዱስ ሲኖዶሱን የበላይ አካልነት የሚያሳየውን አንቀጽ፣ ለፓትርያርኩ ለማድረግና በፓትርያርኩ ዐምባገነናዊ አመራር ሰጪነት ለመተካት በልዩ ጸሐፊያቸው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በኩል ሙከራ እየተደረገ ነው፡፡
  • በረቂቁ ላይ ተጨማሪ ማስተካከያ አድርጎ እንዲያቀርብ በምልአተ ጉባኤው በተሠየመው ኮሚቴ ውስጥ አንዱ አባል የኾኑት ልዩ ጸሐፊው÷ በማኅበራት ዕውቅና አሰጣጥ፣ የመተዳደርያ ደንብን በማጽደቅ፣ በማሻሻል፣ በመሰረዝና በማገድ አሠራር ተጠሪነታቸውን ለፓትርያርኩ በማድረግ ‹‹ማኅበራት አያስፈልጉም›› የሚለውን አቋማቸውን ገቢራዊ ለማድረግ እየጣሩ ነው፡፡
  • በተለያዩ አህጉረ ስብከት በቀደሙት ብፁዓን አባቶች ብርቱ ጥረት የተቋቋሙት የሕፃናት መርጃ ማእከላት፣ የማእከላቱን አስተዳደርና የቤተ ክርስቲያንን ተቋማዊ አሠራር በሚቃረኑ ደንቦችና መመሪያዎች የግለሰብ ሓላፊዎች መጠቀሚያ የኾኑበት፤ ቤተ ክርስቲያን በማታውቃቸው ውሎች መዘዝ ነባር ይዞታነታቸው ጥያቄ ውስጥ የወደቀበት ውዝግብ ተጣርቶ እንዲቀርብ ምልአተ ጉባኤው ትእዛዝ ሰጥቷል፤ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
  • ለሕፃናት ማሳረፊያ እንዲኾኑ በተሠሩ ቪላ እና ሰርቪስ ቤቶች ውስጥ ጠቅልለው ገብተው እየኖሩ የግል መኖርያ ቤታቸውን በከፍተኛ ዋጋ እንዳከራዩ የሚነገርባቸው የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ዋና ሓላፊ በቅዱስ ሲኖዶሱ ተጠርተው ተጠይቀዋል፡፡
  • የዕጓለማውታ ሕፃናቱን ጤንነት ለመከባከብ በክሊኒክ ደረጃ ተጀምሮ ወደ ጠቅላላ ሆስፒታል ያደገው የምግባረ ሠናይ አጠቃላይ ሆስፒታል ከውጭ የምግባረ ሠናይ ድርጅቶች ድጋፍ ተላቅቆ ራሱን ወደ ልማት ማእከልነት በመለወጥ በራሱ ገቢ ከመተዳደር አልፎ ዓመታዊ ገቢውን ወደ ስምንት ሚልዮን ብር ማድረሱ በድርጅቱ ሓላፊዎች ተገልጧል፡፡ ይኹንና ‹‹ተጠሪነቱ ለማን ነው? አናውቀውም›› የሚል ጥያቄ በፓትርያርኩ እንደቀረበበት ተሰምቷል፤ የመሬት ይዞታውም እየተገፋ ለግለሰቦች ጥቅም መዳረጉ የተነገረ ሲኾን ‹‹ኦዲትም አያውቀውም›› ተብሏል፡፡